Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የዕዳ መክፈያ ጊዜ የተራዘመላት ኢትዮጵያ ከቻይና ድጋፍ ቀዳሚዋ ሆናለች

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  60 ቢሊዮን ዶላሩ ምን ያህል ይደርሳት ይሆን?

  በየሦስት ዓመቱ በአፍሪካና በቻይና መካከል የሚካሄደው የቻይና አፍሪካ  የትብብር ፎረም፣ ዘንድሮ  በቤጂንግ ተስነናግዷል፡፡ በፎረሙ ከታዩና ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ለአፍሪካ የተዘረጋው 60 ቢሊዮን ዶላር የቻይና ድጋፍ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡

  ከዚህ ገንዘብ ጋር በቀጥታ ስለመገናኘቱ ተጨባጭ መረጃዎች ባይወጡም፣ መንግሥት አሥር ዓመታት ውስጥ እንደሚከፍለው ይጠበቅ ለነበረውና ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጠየቀው የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክት ለተበደረው ገንዘብ የክፍያ ጊዜው ወደ 30 ዓመታት ተራዝመውለታል፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የቻይና ጉዞ ከዚህ አኳያ ትልቅ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስኬት ስለመሆኑ ዘገባዎች እያመለከቱ ነው፡፡ እስካሁን በአፍሪካ ደረጃ ከወጡ የቻይና ስምምነቶች መካከል የኢትዮጵያ የብድር ማራዘሚያ ስምምነት ቢጠቀስም፣ ሌሎችም ዝርዝር ይዘታቸው ይፋ ያልተደረጉ ስምምነቶች በቻይናና በኢትዮጵያ  መንግሥታት  መካከል  መፈረማቸው  አይዘነጋም፡፡

  ከሦስት ዓመታት በፊት በደቡብ  አፍሪካ በተስናገደው የቻይና አፍሪካ ፎረም፣ ቻይና 60 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል መግባቷ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ እንደተለቀቀና ተግባር ላይ እንደዋለ በዝርዝር የሚያስረዱ መረጃዎች አልወጡም፡፡ በዘንድሮው ፎረም ወቅት ከስብሰባው ውጪ ትልቅ መነጋሪያ የነበረው ጉዳይ ቻይና አፍሪካን በዕዳ ተብትባ ይዛለች የሚለው ስሞታ ነው፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አገሮች ቻይና የአፍሪካ መንግሥታትን በዕዳ እግር ተወርች ጠፍራ ይዛለች፡፡ በዚህም የአፍሪካን አንጡራ የተፈጥሮ ሀብት እየቦጠቦጠችና ሉዓላዊነታቸውን እየተጋፋች ስለመሆኗ በብዙው ሲኮንኑ ከርመዋል፡፡

  አፍሪካን በጎበኙ ማግሥት ከሹመታቸው የተነሱት የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ቻይና አፍሪካን በዕዳ አፈ ሙዝ  ስለማስጎንበሷ ተችተውና አስጠንቅቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካን ትችት ከሚገባው በላይ ተጋኗል የሚሉም አልጠፉም፡፡ ቻይና ለአፍሪካ ያበደረችው የገንዘብ መጠን ከሌሎች አበዳሪዎች አኳያ ሲታይ፣ ከጠቅላላው የአኅጉሪቱ የውጭ ብድር ዕዳ ውስጥ ከሁለት በመቶ እንደማይበልጥ የሚጠቅሱ ጸሐፍት፣ ጣት ቀሳሪዎቹ ምዕራባውያን ቻይና ለአፍሪካ ያደረገችውን ያህል እንዳላደረጉ በመግለጽም ሲወርፉ ይታያሉ፡፡ ይህም ሆኖ ... 2003 ጀምሮ ቻይና ለአፍሪካ የሰጠችው ብድር 40 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ባለፉት 18 ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ መንግሥታት በጠቅላላው 140 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ከቻይና ስለማግኘታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ኢትዮጵያ 12 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቻይና ብድር ስለማግኘቷም ይጠቀሳል፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ብድር ዕዳ መጠን፣ በመንግሥት ከሚወጡ መረጃዎች አኳያ እስከ 25 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

  ይህ በመሆኑም የአገሪቱ የብድር ዕዳ ጫና ወደ ከፍተኛው ደረጃ በመድረሱ ምክንያት፣ መንግሥት በዋናነት ከቻይና ያገኘው የነበረውን የአጭር ጊዜ ብድር ለማቆም አስገድዶታል፡፡ በዚህ ዓመት 20 ቢሊዮን ብር በላይ ለብድር ዕዳ መክፈል የሚጠበቅበት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ባለፈው ዓመት ወደ 17 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለብድር ዕዳ ማቅለያነት ከፍሏል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎችም መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች እንደ መንግሥት የመበደር ሚና እንዳይኖራቸው ወይም ለሚወስዱት ብድር መንግሥት ዋስትና  እንደማይገባ  ካስታወቀ  ወራት ተቆጥረዋል፡፡

  የአጭር ጊዜ ብድር ወይም ‹‹ነን ኮንሴሽናል ሎን›› በዚህ ዓመት እንደማይኖር ተደጋግሞ ቢገለጸም፣ በተሸኘው በጀት ዓመት በጠቅላላው 152.75 ቢሊዮን ብር በብድርና ዕርዳታ መልክ ቃል የተገባበት ገንዘብ መገኘቱንና 111 ቢሊዮን ብር በላይም ወደ ቋቱ ማስገባቱን ሚኒስቴሩ አስታውቆ ነበር፡፡

  በቅርቡ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃን መሠረት በማድረግ ሪፖርተር ዘግቦ እንደነበረው፣ ከበይነ መንግሥታት ወይም መልቲ ላተራል የተሰኘው የሀብት ማግኛ ምንጭ ነው፡፡ በመልቲ ላተራል በኩል በዋና የሀብት ምንጭነት የሚጠቀሱት የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ኢንቨስትመንት ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው፡፡  ሁለተኛው የውጭ ሀብት ማሰባሰቢያ መንገድ ከሁለትዮሽ የመንግሥታት ትብብር (ባይላተራል) ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ስሟ ጎልቶ የሚነሳው ቻይና ነች፡፡ ይሁንና ለኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች ድጋፍ የሚሰጡ ሌሎችም አገሮች በዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ፡፡

  በመሆኑም 2010 .. ከተገኘው 152.7 ቢሊዮን ብር የብድርና ዕርዳታ ገንዘብ ውስጥ በመልቲ ላተራል በኩል የተገኘው የሀብት መጠን 96 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በብድር የተገኘው 47.6 ቢሊዮን ብር ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዕርዳታ የተገኘውም 48.2 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ በጠቅላላው 95.8 ቢሊዮን ብር በላይ የብድርና የዕርዳታ ገንዘብ ለአገሪቱ ቃል እንደተገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ከሁለትዮሽ የመንግሥታት ትብብር ወይም ባይላተራል ምንጮች የተገኘው የብድርና የዕርዳታ መጠንም 57 ቢሊዮን ብር ገደማ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ በብድር መልክ እንደሚሰጥ ቃል የተገባው ገንዘብ 31 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ በዕርዳታ መልክ እንደሚመጣ የሚጠበቀው መጠንም 26.6 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

  በአንፃሩ ወደ አገሪቱ በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ፈሰስ የተደረገው የብድርና የዕርዳታ ገንዘብ መጠን በጠቅላላው 111.86 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደነበር ያስታወቁት የገንዘብና ፋይናንስ ትብብር ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢቢሳ፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በባይላተራል መንገድ የተገኘው ብድርና ዕርዳታ 50.34 ቢሊዮን ብር እንደነበርና በመልቲ ላተራል መንገድ የተገኘውም 62 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ 2009 .. ከባይላተራል ምንጮች የተገኘው ብድርና ዕርዳታ 35 ቢሊዮን ብር እንደነበር፣ በዚህም 15.2 ቢሊዮን ብር ወይም 43.2 በመቶ ብልጫ 2010 .. እንደታየም አብራርተዋል፡፡ በመልቲ ላተራል በኩል ዓምና 44 ቢሊዮን ብር ገደማ ፈሰስ መደረጉን በማስታወስ 17.8 ወይም 40.7 በመቶ ብልጫ በዘንድሮው ፍሰት መመዝገቡ ተጠቅሶ ነበር፡፡

  እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በአብዛኛው ብድር ሲያገኝ የቆየው ከቻይና መንግሥት መሆኑን ተከትሎ፣ አዲስ አበባ የቻይና ከተማ ሆናለች የሚል ይዘት ያላቸው ዘገባዎች በሰፊው ሲደመጡ ከርመዋል፡፡ ሲኤንኤን በቅርቡ ከአዲስ አበባ ባሠራጨው ዘገባ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ የሁዋጂዬን ጫማ ፋብሪካ ግዛት፣ የፀሐይ ሪል ስቴት ፕሮጀክት፣ የቴክኖ ሞባይል ኩባንያና ሌሎችም መሠረተ ልማቶችን በመጠቃቀስ ቻይና በአፍሪካ የጎላ ተፅዕኖ እያሳደረች እንደምትገኝ  ለማመላከት ሞክሯል፡፡

  በቻይኖች ወገን የሚደመጠው መከራከሪያ ግን ቻይና የአፍሪካን ሀብት የዕዳ መያዣ እንዳላደረገች የሚሞግት ነው፡፡ ብዙም የማያስኬደው ይህ መከራከሪያ ባይሆን ለአኅጉሪቱ ከፍተኛውን ብድር በመስጠት ቀዳሚዋ አለመሆኗን ግን ከአሜሪካ ወገን የሚወጡ ገለልተኛ መሰል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ይባል እንጂ እየተደራረበ በመጣው የዕዳ ጫና ሳቢያ፣ ቻይና ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ማቅማማት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ እንደውም ለአንዳንዶቹ የብድር ዕዳዎች ክፍያ ይውል ዘንድ በመንግሥት ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ድርሻ እንዲሰጣት ስለመጠየቋ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሥር በሚተዳደረው የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ውስጥ 40 በመቶ በላይ ድርሻ እንዲወስዱ የውስጥ ድርድር ሲካሄድ እንደነበር የሪፖርተር ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

  በቅርቡ ከተደረገው የመንግሥት አስተዳደራዊ ለውጥ በኋላ የቻይና ዝምታ የሚደመጥ መልዕክት እንዳዘለ ታዛቢዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የቻይና የበታች ዲፕሎማቶች ከኢትዮጵያ የወትሮው ጥብቅ ግንኙነት እንደማይደናቀፍ ሲገልጹም ተደምጠዋል፡፡ በቻይና አፍሪካ ፎረምም ቻይና ይህንኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት ማረጋገጫው ሰጥታና ጊዜያዊ ዕፎይታን የሚያሰፍን ምላሽ መስጠቷ ነበር፡፡

  ቻይና በአፍሪካ ለምታፈሰው የብድር ገንዘብ በምላሹ ይጠቅመኛል በምትለው ሀብት ሁሉ ላይ እጇን እንደምታሳርፍ የአሜሪካ ምሁራን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ከአፍሪካ ቻይና ግንኙነት ውስጥ የተጣራ ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ያብራሩት አሜሪካዊው የቀድሞ የሐርቫርድ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር፣ ታይለር ኮዌን ናቸው፡፡ ምሁሩ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ አሜሪካ ኤምባሲ ተገኝተው ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዕዳ ፈተና ውስጥ የምትወድቀው የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከብድር ዕዳዋ በታች በመሆን መተፈታተን ከጀመራት ነው፡፡ ይህንን ሊያባብሱ የሚችሉት ደግሞ የግብርና ዘርፏ በሚገባው መጠን ምርታማ መሆን ካልቻለ፣ አገሪቱ ያላትን ወጣት የሕዝብ ሀብት ለቴክኖሎጂ ዘርፉ የሚመጥን ኃይል እንዲሆን ያላደረገች እንደሆነና ሌሎችም ምክንያቶችን በማንሳት አብራርተው ነበር፡፡

  እንዲህ ያሉትን እውነታዎች ያስተናገደው የአገሪቱ የቻይና ዕዳ ጫና ከፎረሙ መልስ ተስፋ የሰነቀ መስሏል፡፡ በዚያም ላይ አገሪቱ እያሳየች ያለችው ቀጣናዊ የጥምረት እንቅስቃሴም ከውጭ የምታገኛቸው የሀብት ምንጮች እንዳይነጥፉ ተስፋ የሚሰንቁ መስለዋል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች