Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንደገና የተጠየቀባቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንደገና የተጠየቀባቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

ቀን:

አድማ በመፍጠር፣ በሕገወጥ መንገድ በመደራጀትና የሌሎች ሠራተኞችን ፊርማ አስመስለው በመፈረም የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረው በታሰሩ ዘጠኝ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች ላይ እንደገና የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ የወንጀል ችሎት ባቀረባቸው፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ዘጠኝ ተጠርጣሪ ሠራተኞች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆ ነበር፡፡

መርማሪ ቡድኑ በመጀመርያ ቀን የፍርድ ቤት ውሎው በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ የሠራውን ምርመራ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በዚህ መሠረት የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን፣ አሻራ መውሰዱን፣ የሌሎች ሠራተኞችን ፊርማ በማመሳሰል ለሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ያስገቡትን የሰነድ ማስረጃ መጠየቁን፣ በክልል ከሚገኙ ተመሳሳይ ሥራ ካላቸው ሠራተኞች ጋር ያደረጉትን የስልክ ንግግር ለማስመርመር ስልካቸውን ለመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) መስጠቱን፣ በፌስቡክ አድራሻቸው የተለዋወጡዋቸውን መጣጥፎችም መርምሮ እንዲሰጣቸው ኤጀንሲው መጠየቁንና የሦስት ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉንም አስረድቷል፡፡

የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል ከተለያዩ ተቋማት የጠየቃቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ለመሰብሰብ፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን ለመያዝ፣ በክልል ከሚገኙ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ቃል ለመቀበል የተላከውን የመርማሪ ቡድን የምርመራ ውጤት ለመቀበል፣ አስመስለው ፈርመዋል የተባለውን ሰነድ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ለመቀበል፣ የሙያ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ በክልል የሚሠሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሠራተኞች እንደወከሏቸው ተጠርጣሪዎቹ በመናገራቸው የማስመጣትና ሌሎች የቴክኒክ ሥራዎች እንደሚቀረው በመጠቆም፣ የጠየቀው ተጨማሪ የ14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች በጠበቃቸው አቶ ሚሊዮን አበራ አማካይነት የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱትም፣ ተጠርጣሪዎቹ ቃላቸውንና የአሻራ ምርመራ ሰጥተዋል፡፡ ምስክር ከመስማት ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ የጠየቁት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪ እንዲደረግላቸውና ይኼም ደረጃውን ጠብቀው ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ የቀጠሉበት መሆኑን፣ አሁንም ቢሆን ሥራ ያቆሙት መቼ እንደሚያቆሙ ቀኑንና ጊዜውን አሳውቀው በመሆናቸው ተጨማሪ ምርመራ ሊጠየቅባቸው እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡

እያንዳንዳቸው በግላቸው ያነሱት የመብት ጥያቄ እንጂ የመቧደንም ሆነ የማነሳሳት ተግባር እንዳልፈጸሙ አክለዋል፡፡ የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ተጠርጣሪ ለመያዝና የሰነድ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ በማለት መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ሆን ብሎ እነሱን በእስር ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር፣ ከእነሱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለም ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ሰነዶች የሚገኙት በመንግሥት ተቋማት ስለሆነ ከተጠርጣሪዎች ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ አክለዋል፡፡

አየር መንገዱ ኪሳራ ደርሶበታል በማለት መርማሪ ቡድኑ የገለጸው ከተጠርጣሪዎች ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ጠበቃው ተናግረው፣ እነሱ ከአየር መንገዱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለና የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሠራተኞች መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡ ስለአየር መንገዱ ኪሳራ ቢመለከታቸው እንኳን፣ አየር መንገዱ ራሱ በመገናኛ ብዙኃን ሰሞኑንና አሁንም የተናገረው፣ ‹‹ምንም ዓይነት ኪሳራ የደረሰብኝ የለም›› ስለሆነ፣ ምንም የሚያስጠይቃቸው ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ያለውክልና አስመስለው ፈርመዋል የተባለውም ትክክል እንዳልሆነ ጠበቃው አስረድተው ጓደኞቻቸው በሰጧቸው ውክልና መሠረት ሰብስበው መፈረማቸውንና ይኼንንም እነሱም ስላልካዱ የፎረንሲክም ሆነ ሌላ የቴክኒክ ምርመራ እንደማያስፈልገው አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁት መብታቸውን በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አቶ ሚሊዮን ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን የሚያልፈውም ከሆነ የቀጠሮ ቀኑ አንሶ እንዲቀጠር አክለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ለሥራው እንደሚያስፈልጉ፣ ሥራቸውን እያከናወኑ መርማሪው ሥራውን መቀጠል እንደሚችል፣ የአዕምሮ ሥራ በመሆኑ ጓደኞቻቸው ስለነሱ መታሰር እያሰቡ በአግባቡ ሥራቸውን ሊያከናውኑ ስለማይችሉ ችግር ሊያጋጥም ስለሚችል ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንማይገባ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ፊርማ አስመስለው እንደፈረሙ መርማሪ ቡድኑ የሚናገረው ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለተቋማቸው ያስገቡትን ደብዳቤ መሆኑን ይህ ደብዳቤ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀርቦ ውድቅ የተደረገ ከመሆኑ ተጨማሪ ምርመራ እንደማያስፈልገውም አስረድተዋል፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ስላልሆኑ አየር መንገዱ ከስሯል በሚል ምክንያት ታስረው ሊቆዩ እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞ ምክንያቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አድማ ለማድረግ አስበው የነበሩት 118 ሠራተኞች እንደነበሩ አስረድቶ፣ ለእነዚህ ሠራተኞች መነሳሳት ዋና ምክንያቶቹ ግን ተጠርጣሪዎቹ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የመብት ጥያቄን ምክንያት በማድረግ በውስጡ አሻጥር ያለበት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ጠቁሞ፣ መንግሥት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እንዲገቡ ስምምነት ላይ የደረሰበትን ሰላማዊ መንገድ ለማደናቀፍ ሆን ብለው ጊዜውን መጠቀማቸውን ተናግሯል፡፡ አንድ ሺሕ ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ምክንያት መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ጠቁሞ፣ ከሌሎች አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር አውሮፕላን እንዳይነሳ፣ እንዳያርፍና በአየር ላይ እንዲቆይ በማድረግ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም ሰነዶችን አስመርምሮና ከጠየቃቸው ተቋማት ተቀብሎ እስከሚጨርስ ድረስ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ደጋግሞ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የዋስትና ጥያቄውን በማለፍ፣ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...