ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር
የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበርና ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል፣ አገር ቤት የተመለሱት የታገሉለት ዓላማ ወደ መጨረሻ ግቡ እንዲደርስ ለማገዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የንቅናቄው አባላት እሑድ ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ፣ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ እስከ አዲስ አበባ ስቴዲየም በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስቴዲየም በተደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የተገኙ ሲሆን፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
በዕለቱ ሰፋ ያለ ንግግር ያደረጉት የንቅናቄው ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ አገራችን ስንመለስ ከሚገባን በላይ በማክበር ላከበራችሁን እናመሠግናለን፤›› ብለዋል፡፡
ወደ ሰላማዊ ትግል ለመምጣት ንቅናቄው ሲወስን ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ በሚል እምነት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
እኩይ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን ለውጡ በፍጥነት ውጤት እንዲያመጣላቸው የሚፈልጉ ‹‹ችኩሎች›› ወይም ለውጡ በሚፈልጉት መንገድ ባለመሄዱ፣ እንዲሁም ለውጡን ወደሚፈልጉት መንገድ ለመውሰድ በሚፈልጉ እንቅፋቶች ሊገጥሙትና ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል፡፡
‹‹የመጣነው አሁን የተፈጠረውን የለውጥ ሒደት ወደ ታገልንበት የመጨረሻ ዓላማ ለማድረስ ነው፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹መከፈል ያለበትን ከፍለን ይኼንን ለውጥ ሲናፍቅ ከነበረው ማኅበረሰባችን ጋር በጋራ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚካሄደውን አስቸጋሪ ትግል ለማገዝ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አሁን የተጀመረው ለውጥ መጨረሻው ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ መቆሚያ ሊኖረው እንደማይችልም አስታውቀዋል፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ከአሁን በኋላ አንባገነናዊ ሥርዓት ሥር አንደወድቅም፤›› ሲሉ አስረግጠዋል፡፡ የንቅናቄው ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዚሁ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ለተወለዱበት አዲስ አበባ ከተማ እስከ መጨረሻው እንደሚታገሉም ገልጸዋል፡፡