Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመስከረሟ አደይና ሆያ ሆዬ

የመስከረሟ አደይና ሆያ ሆዬ

ቀን:

የአዲስ ዘመን ብስራት በአንድ ጎኑ መሬት ከፀሓይ ጋር ካላት ግንኙነት የሚከሰት ነው፡፡ አንድ ዓመት፣ ሁለት ዓመት እየተባለ የሚጠራው መሬት በፀሓይ ዙሪያ ጉዞዋን ለማድረግ የሚፈጅባትን የ365 ከሩብ ቀናት የሚፈጅባት ጊዜ ነው፡፡ በነዚህ የዐውደ ዓመት ቀናት አራቱ ወቅቶች ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ይፈራረቃሉ፡፡ የፀሓይ ከጨረቃና ከከዋክብት ጋር መፈጠር ለዕለቶች፣ ለዓመቶች፣ ለዘመኖች (ወቅቶች) እና ለምልክቶች ለማገልገል እንደሆነ የዘፍጥረት ታሪክ ይነግረናል፡፡

ከሦስቱ ብርሃኖች በተጨማሪ በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ የተፈጠሩት ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልትም ከዘመን ብስራት ጋር ቁርኝት አላቸው፡፡ አንዱ ማሳያ በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን መባቻ በጠንካራው የክረምት ወቅት መገባደጃ አካባቢ ብቅ የምትለዋ አደይ አበባ ተጠቃሽ ናት፡፡ ሰኔ ግም ብሎ የሐምሌን ጨለማ የነሐሴን ጎርፍ አልፎ፣ እኝኝ ብላን (ከነሐሴ 28 ቀን እስከ 30 ባለማቋረጥ የሚዘንበው) ተሻግሮ በጳጉሜን በኩል ክረምቱ ሲያልፍ፣ መስከረምን የምታደምቀው አደይ አበባ ትከሰታለች፡፡ ዋዜማውን ጨምራ በመስከረም የምትፈነዳውና ለኢትዮጵያ ምድር ጌጧ፣ ሽልማቷም የሆነችው አደይ አበባ እንደ አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አደይ ሲፈታ የበጨጨ፣ ብጫ የሆነ አበባ ነው፡፡ ግሱ ‹‹ዐደየ›› በጨጨ፣ ብጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ሲሉም ይፈቱታል፡፡ በኦሮሚኛ ነጭን ‹‹ዐዲ››፣ ፀሐይን ‹‹ዐዱ›› የሚለው ከዚህ የወጣ ነው ሲሉም ያክሉበታል፡፡

ስለአደይ አበባ ተክል ምንነት ሳይንሳዊ መግለጫ ያዘጋጁት ከበደ ታደሰ (/ር)  ‹‹የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ አበቦች (Wild Flowers for Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ስለአደይ አበባ ከምትበቅልበት ከተለያዩ ከፍታዎች አንፃር በሁለት መልክ እንዲህ ጽፈዋል፡፡ የተከፋፈሉ ሰፊ ላይዶ ቅጠሎችና ስምንት የተበተኑ መልካበቦች ያሉት ዓመታዊ ሐመልማል፣ ከመንገድ ዳር ዳርና ከቃሊም፣ እንዲሁም በከፍተኛና ድንጋያማ ተዳፋት፣ 400 እስከ 2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ይበቅላል፡፡ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥም ያብባል፡፡ በሌላ በኩልም እስከ ኅዳር ድረስ የሚያብበው የሚገኘው 2,000 እስከ 3,600 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ ይህንንም / ከበደ ሲገልጹት፣ ዐደይ አበባ ረዣዥም ግንድና ሰፋ ያለ ላይዶ ቅርፅ ያላቸው ቅጠሎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚበቅል ከረምመልማል ነው ይሉታል፡፡ መሀላቸው ብርቱካንማ የሆነ ብጫ አበቦች በግንዱ ጫፍ ሰብሰብ ብለው ይታያል፡፡

‹‹አደይ አደይ የመስከረም

እንዳንቺ ያለ የለም

አደይ አበባ የመስከረሙ

እነ ጉብሌ ወዴት ከረሙ

አደይ አበባ የሶሪ ላባ

እፍ እፍ በዪ እንደ ገለባ››

በሌላ በኩል ከወፎች ወገን በክረምትና በበጋ በፀደይ መደበኛ መልኳን ይዛ የምትበረው ‹‹የመስቀል ወፍ›› በነባር ስሟ ‹‹የመስከረም ወፍ›› ክረምቱ ሲያልፍ ጥቢው መፀው (አበባው) ሲመጣ ደምቃና ተውባ ትመጣለች፡፡ በሔኖክ ሥዩም በተዘጋጀው ቱባ ድርሳን ላይ የአዕዋፋት ተመራማሪን አልዓዛር ዳቃን ጠቅሶ ስለመስቀል ወፍ ምንነት አውስቷል፡፡ በገለጻው መሠረት ዓይናቸው ቢጫና ሰውነታቸው ሰማያዊ የሆኑት ወፎች የትም የሚኖሩ ናቸው፡፡

ከዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የልጃገረዶች ‹‹አበባየሽ ወይ›› ነው፡፡ ወንዶችም ከዘመኑ መቀየር ጋር የሚጫወቱት በተለይ ‹‹ሆያ ሆዬ . . . ሆዬ›› ይጠቀሳል፡፡ በነሐሴ አጋማሽ አካባቢ ከደብረ ታቦር ጋር ተያይዞ ልጆች የሚጫወቱት ሆያ ሆዬ ከመስከረም ዋዜማ እስከ መስቀል በዓል ድረስም ይዘልቃል፡፡ ይህም በሰሜንም ሆነ በሰሜን ምሥራቅና በሰሜን ምዕራብ በትውፊትነቱ ይታወቃል፡፡ ከነዚህ አካባቢዎች መካከል ላስታ ላሊበላ ይጠቀሳል፡፡

ሆያ ሆዬ በማንኛውም ጊዜ የሚዘወተር ባህላዊ ጨዋታ ሳይሆን ወቅትን ጠብቆ የሚከወን ነው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች ከመስክ ጥናታቸው በመነሳት እንደሚገልጹት፣ የሆያ ሆዬ ባህላዊ ጨዋታ በአንዳንድ አካባቢ እየተረሳና እየቀዘቀዘ አንዳንድ ጊዜ በዜማውና ግጥሙ እየተዛባ ይምጣ እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በላስታ ላሊበላም ሆያ ሆዬ እንደ ሌሎቹ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ ይከወን እንጂ ዛሬ ድረስ እየተከናወነ የሚገኝ ጨዋታ ነው፡፡ ሆያ ሆዬ በአብዛኛው በቡሄ ሰሞን በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ ከቡሄ ጀምሮ እስከ መስቀል ድረስ ባሉት ይከናወናል፡፡ በላስታ ላሊበላም ከመስከረም 1 እስከ 17 ባሉት ቀናት ይከበራል፡፡

በኢታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ጥራዝ ውስጥ እንደተገለጸው፣ በመስከረም ላስታ ላሊበላ ዙሪያዋ ያምራል፣ አካባቢው ያብባል፣ እህሉ ያሸታል፣ አዝመራው ይደርሳል፣ ወንዙ ይጠራል፣ ፏፏቴው ይወርዳል፤ መሬቷ ታሸበርቃለች፤ ፍጥረት ትስቃለች፤ ምድር ትፈነድቃለች፤ የወጣቱ ልብም ይደሰታል፤ ፊቱ ያብባል፤ ገጹ ይፈካል፡፡ የላስታ ወጣት ይህን ስሜቱን ከሚገልጽበት ሕይወቱን ከሚያድስበትና ደስታውንም ከሚያካፍልበት አንዱና ዋናው ‹‹ሆያ ሆዬ›› ነው፡፡

የሆያ ሆዬ ጨዋታ በየዓመቱ በደስታ ተከብሮ ብቻ የሚያልፍ ሳይሆን ለጨዋታው የሚሰባሰቡ ወጣቶች የማኅበራዊ ሕይወት ትስስር መሠረት የሚጥሉት በተለይ በገጠር አካባቢ የስብስብ ሒደቱ ወደ ሚዜነት የሚያድግብት፣ የሚዜነት ተግባሩም ለጊዜው ሳይሆን ሁሉም እስኪያገቡ ድረስ በዘላቂነት የሚቀጥሉበት፤ አግብተው ሲጨርሱም ማኅበራዊ ቁርኝቱ የሚዳብርበት፣ የጽዋ ማኅበር የሚጠጡበት/የሚዘክሩበት፣ አብረው የሚበሉበት/የሚጠጡበት፣ በደቦና በወንፈል እየተረዳዱ የሚሠሩበት፣ ይህም በእነሱ ሕይወት ብቻ ሳይወሰን በልጆቻቸው የሚቀጥልበት እንደሆነ የአካባቢው የባህል አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹ሆያ ሆዬ የማኅበራዊ ትስስር መፍጠሪያነት ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ አገልግሎት ሚና በልጅነት ሙከራ የሚደረግበት ማለትም መሪ ለመሆን የሚችል አለቃ፣ ታማኝ ገንዘብ ያዥ፣ ድምፃዊና አቀንቃኝ ወዘተ. ሆኖ ወጣቶች ለቁም ነገር የሚታጩበትም ጭምር ነው፤›› የሚለው ሰነዱ፣ ከዚህ በተጨማሪ በጨዋታው  ግለሰቦች በመልካም ሥራቸውና ሙያቸው በግጥም የሚወደሱበት በተቃራኒ ደግሞ ፍርኃት፣ ስንፍና፣ ሙያ ቢስነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ጊዜውን አልባሌ ሥፍራና ቦታ ማሳለፍ የሚነቀፍበት እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

በላስታ ላሊበላ የሚከበረው የሆያ ሆዬ ጨዋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት የሚጀምረው ዕለተ በዓሉ ከመከበሩ አምስት ቀናት ቀድሞ (ከጳጉሜን አንድ) ጀምሮ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ወጣት ወንዶች ወንዝ እየወረዱ ገላቸውን ይታጠባሉ፣ ልብሳቸውን ያፀዳሉ፣ ለጭፈራው ዋና መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግለውን ዱላ ያዘጋጃሉ፡፡ ለጨዋታ የሚያስፈልጋቸውን ግጥምም ያጠናሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አለቃና ገንዘብ ያዥም ይመርጣሉ፡፡

የዘመን መለወጫ ዕለትም ሁሉም በየቤቱ የተገኘውን ሲበላና ሲጠጣ ይውልና ወደ ማታ ጅራፍ በማጮህ ይሰባሰባሉ፡፡ ያልወጣውን ለማስወጣት፣ ያልመጣውን ለማስመጣት ሲሉ በየአደባባዩ እየዞሩ ይጣራሉ፣ እየተቀባበሉም ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፡፡ የጭፈራ ሰዓቱ ማታ ማታ የሚከወን ሲሆን፣ ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ገበሬና ከብት ጠባቂ በመሆኑ ከየሥራ ሥምሪቱ ሲመለስ በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን የሚያሳርፍበት፣ የሚዝናናበትና ሕይወቱን ደስ የሚያሰኝበት በመሆኑ ነው፡፡

ጭፈራው የበዓሉን ድባብ ሞቅ ደመቅ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት በወጣቶች እየተዘፈነና እየተጨፈረ የሚተላለፈውን የግጥም መልዕክትና የአኳኋን ሥልት ከቅርፅና ይዘት አኳያ በአራት ከፍለው እንደሚመለከቱት መረጃ ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የሥነ ሰብ (አንትሮፖሎጂ) እና የነገረ ባህል (ፎክሎር) ተመራማሪዎቹ የቅርስ ባለሙያዎች እንደዘገቡት ግጥሞቹን የጉዞ/የመንገድ የቤት የምስጋናና የቅሬታ በማለት ይጠቀሳሉ፡፡ የመጀመርያው የጉዞ/የመንገድ ግጥም የሚባለው ወጣቶች ገና አባወራ ቤት ከመሄዳቸውና ‹‹ሆያ ሆዬ›› ከማለታቸው በፊት የሚጠራሩበትንና የሚገጥሙትን በየመንገዱም ‹‹እሆይ ሲራራ፣ እሆይ ሲራራ›› የሚሉትን የዜማ/ግጥም ዓይነት ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ወደሚሉበት ቤት ገና ሳይገቡ ከአጥሩ/ግቢው ትንሽ ራቅ ብለው የቤቱ ጌታ ወይም ጠባቂ በሩን ከፍቶ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቃቸው የሚያባብሉበት ዜማና ግጥም በዚሁ ይካተታል፡፡ የ‹‹ቤት›› የሚባለው የግጥም ዓይነት ደግሞ በጨዋታው ወቅት የሚጨፍሩበት ቤት በር እንዲከፈትላቸው ካስፈቀዱ በኋላ ወደ ቤት ገብተው የባለቤቱን ማንነት በግጥም እየተናገሩ ‹‹ምስጋናና ውዳሴ›› የሚያቀርቡበት ነው፡፡

የባህል ባለሙያው መምህር ዓለሙ ኃይሌ የእሆይ ሲራራ፣ አሆይ ሲራራን ግጥም እንዲህ ይገልጹታል፡፡

‹‹እሆይ ሲራራ

እከሌ ሲፈራ

ከምድጃው አራ

እናቱ ተነሺ

ያንን አብሺ››

ጎረምሳውም ዱላውን ይዞ ‹‹እኔ ወንዱ›› ብሎ ማታ ይመጣና

‹‹ክፈት በለው በሩን

የዚያን ወንዱን፣

ክፈት በለው ተነሳ

የወንዱን ጎረምሳ

ክፈት በለው በሩን

የጌታዬን››

እያለ ከነ አጀቡ ይገባል፡፡

በዚህ ሁኔታ ሆያ ሆዬ ተጨዋቾች ዓመቱን ጠብቀው እንኳን አደረሳችሁ ለማለትና የደንቡን ለመጠየቅ መምጣታቸውን የሰማ አባወራም ቤቱን በመክፈት ጭፈራውንና ሁኔታውን በሚገባ ይከታተላል፡፡ የሚገባውንም ስጦታ ያዘጋጃል፡፡ ስጦታውም የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ በገጠሩ እርጎ፣ ጋን ጠላ ከነመክደኛው/ዳቦ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ ሙክትም የሚሰጥ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን ገንዘብ ይሰጣል፡፡

ሦስተኛው የምስጋና ሲሆን፣ ይህም በዓይነትም ይሁን በገንዘብ ለሰጣቸው ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡

ምስጋናውም እንደ መምህር ዓለሙ አገላለጽ፣

‹‹ማር ይዘንባል ጠጅ

ከጌታዬ ደጅ

ከመቤቴ ደጅ

አሆሆ በል እረኛ

በጊዜ እንተኛ፤

ይኸ የማነው እንዝርት እመከታው ላይ

ይቺ የኔ እመቤት የቀጭን ፈታይ

እሷ ፈትላ ባሏ መልበስ ያውቃል

ይኼ የኔ ጌታ በሩቅ ያስታውቃል፡፡››

በሆያ ሆዬው ላይ የሚንፀባረቁት የቅሬታ ግጥሞች በአራተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡት ናቸው፡፡ እነዚህ የቅሬታ ግጥሞች አጠርና ደመቅ ባለ የዜማ ሥልት የምስጋናውን መልዕክት ካጠናቀቁና ከጨፈሩ በኋላ ስጦታው የሚዘገይ ወይም የሚያንስ ከሆነ ቅሬታቸውን በግጥም ማሰማት የተለመደ ነው፡፡  ይህንንም መምህር ዓለሙ እንዲህ ያብራሩታል፡፡ ቡሄውን ጨፍረው በጎ ምላሽ ካላገኙ፣ ካልተሸለሙ፣ በግጥማቸው በመጎሸም ብቻ አይወሰኑም፡፡ ‹‹ቀበራ›› የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ማዶ ለማዶ እየተጯጯሁ ባልሰጧቸው ሰዎች ላይ አደጋ እንደደረሰ አድርገው በቅብብሎሽ ያስተጋባሉ፡፡ ‹‹እከሌ ተጎድቷል – ድረሱ›› እያሉ መርዶ ይናገራሉ (ተጎዳ ማለት ሞተ ማለት ነው)፡፡ ይኼን መርዶ የሰማ በቅርብም በሩቅ ያለ ዘመድ ፀጉርን እየነጨ እያለቀሰ ሲመጣ ጉዳዩ ሌላ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ቡሄ፡፡ ሞተ ለተባለው ዘመዳቸውም ‹‹ምነው አንድ ብር አትሰጥም አፈር በበላህ›› ይሉታል፡፡ ይህም ሆኖ በቅሬታቸው ዜማውን ለውጠውና ከግጥሙ ጋር አዋህደው ሲያቀርቡ ቅሬታ ተሰማኝ ብሎ የሚያኮርፋቸው አይኖርም፡፡

በዚህ ሁኔታ ጨዋታቸውን ሲከውኑ የሰጧቸውን ተቀብለውና አመስግነው፣ ባገኙት ገንዘብም አሸንድዬ ከሚሉት ልጃገረዶች ጋር ደግሰው በልተውና አብልተው የከርሞ ሰው እንዲላቸው ተመራርቀው በጉጉት ዓመት ጠብቀው የሚያከብሩትን ባህላዊ ጨዋታ ያጠናቅቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...