Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4.43 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተያዘው አዲሱ የ2011 በጀት ዓመት የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ይሰፍናል ተብሎ በመታመኑ፣ የፌዴራል መንግሥት ከወጪ ንግድ ዘርፍ 4.43 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ አወጣ፡፡

በንግድ ሚኒስቴር ባለቤትነት የተዘጋጀው ይህ ግዙፍ ዕቅድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚመራው ብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ ቀርቧል፡፡

ብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ በ2010 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከተገኘው 2.81 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው ገቢ ለማግኘት በወጣው ዕቅድ ላይ ከመከረ በኋላ ያፀድቀዋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ ላለፉት ዓመታት በዕቅድ መሠረት እየተጓዘ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኤክስፖርት ዘርፍ ከነበረበት ችግር በተጨማሪ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የቆየው ቀውስ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል በማድረጉ በዕቅዱ መሠረት መሄድ አልቻለም፡፡

የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 ግማሽ ዓመት ከወጪ ንግድ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም፣ የተገኘው ግን 1.35 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በዋናነት የተመሠረተው በሦስት ዘርፎች ላይ ነው፡፡ እነዚህም የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ዘርፎች ናቸው፡፡

የወጪ ንግዱ በችግር የተተበተበም ቢሆንም የተወሰነ ዕድገት ያለው ሲሆን፣ ለአብነት ያህል በ2001 ዓ.ም. 1.45 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ በ2009 በጀት ዓመት የተገኘው 2.23 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

በተለይ ላለፉት ሦስት ዓመታት የጠፋውን ሰላምና መረጋጋት መልሶ በማስፈን የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰላም ጉዳይ በአገር ደረጃ ዋነኛ ሥራ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ዜጎች ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት ተገማች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ላለፉት አራት ወራት የተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ድርጅቱ [ኢሕአዴግ] በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባዔ ያካሂዳል፡፡ ጉባዔው ከዚህ በፊት የነበሩ የሥራ አፈጻጸሞችን ተመልክቶ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ይኖራሉ፤›› በማለት የገለጹት አቶ መላኩ፣ ‹‹ውሳኔዎቹ ተግባራዊ ሲሆኑ የበለጠ መረጋጋት ይመጣል፡፡ ተቋማዊ አቅም እያደገ ይሄዳል፡፡ ተቋማዊ አቅሙ አሁን ካለበት ወደ ላቀ ደረጃ ይሸጋገራል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መላኩ ጨምረው እንደገለጹት፣ በ2011 በጀት ዓመት የተሻለ ሰላም የሚሠፍን በመሆኑ የታሰበው የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች