Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ሚኒስቴር አወዛጋቢ የነበሩ ሁለት መመርያዎችን አሻሻለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድ ሚኒስቴር አወዛጋቢ ሆነው የቆዩትን የቅድመ ንግድ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫና የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመርያዎችን አሻሻለ፡፡

እነዚህ መመርያዎች በኢትዮጵያ በቀላሉ የንግድ ሥራዎችን ለማካሄድ እንቅፋት ናቸው ተብለው በንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡

በተሻሻለው የቅድመ ንግድ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫ ቁጥር 18/2010 ቀደም ሲል የብቃት ማረጋገጫ ሲጠየቅባቸው የነበሩ 1,352 የሚሆኑ መደቦች፣ ወደ 303 ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡

የቅድመ ንግድ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫ የሚጠየቅባቸው 303 መደቦች በአራት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆነው ተሻሽለዋል፡፡

የመጀመርያው በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ተፅዕኖ የሚኖራቸው የንግድ ሥራ ዘርፎች ለአብነት ምግብ፣ መድኃኒትና የጤና አገልግሎት ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው፣ ከአካባቢና ከአገር ደኅንነት አንፃር ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ለአብነትም የደን ውጤቶች፣ ማዳበሪያ፣ ተቀጣጣይ ይዘት ያላቸው ፈንጂዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጡት በአገር ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ የሚኖራቸው የንግድ ዘርፎች ሲሆኑ፣ በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ የተለየ የሙያ ፈቃድ የሚጠይቁ የሕክምናና የሒሳብ ሙያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በመጀመርያ ተግባራዊ የተደረገው አዋጅ ቁጥር 686/2002 ነበር፡፡ ይህ አዋጅ ነጋዴዎች ሁሉንም የንግድ ፈቃድ መስጫ መደቦች የቅድመ ብቃት ማረጋገጫ ይዘው ወደ ንግድ ሥራ እንዲገቡ ያስገድድ ነበር፡፡

ይህ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 980/2008 በወጣው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎለት ነበር፡፡ ማሻሻያ የተደረገባቸው ጉዳዮች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥባቸው መደቦች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ለመወሰን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በየዓመቱ የብቃት ማረጋገጫ የሚታደስበት ሥርዓት የሚቀርበትን ለመወሰን ነበር፡፡

ሁለቱም አዋጆች በአገሪቱ ያለውን የንግድ ሥራ ማቅለልና ማቀላጠፍ ባለመቻላቸው፣ ንግድ ሚኒስቴር አዋጁን መሠረት በማድረግ አውጥቶ የነበረውን መመርያ ማሻሻሉ ተመልክቷል፡፡

የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሐሙስ መስከረም 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ንግድ ከሌሎች አገሮች ጋር የተናበበ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

‹‹ከዓለም አቀፍ የንግድ አሠራር ቀላልነት መለኪያ አንፃር ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ዝቅ ያለ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትና የአገሪቱን የንግድ ማኅበረሰብ ፍላጎት ከግንዛቤ በመክተት ሁለቱን መመርያዎች በማሻሻል የንግድ ሥራን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ ማሻሻያ ተደርጓል፤›› ሲሉ አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛው ማሻሻያ የተደረገበት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦች መመርያ ቁጥር 17/2010 ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ከመውጣቱ በፊት የንግድ ፈቃድ የሚሰጠው አስመጪና ላኪ፣ ጅምላ ንግድ፣ ችርቻሮና አምራች ኢንዱስትሪ እየተባለ ነበር፡፡

‹‹ይህ አሰጣጥም ከዓለም አቀፍ ንግድ አንፃር የተቃኘ አልነበረም፣ ለክትትልም አያመችም ነበር፤›› በማለት የገለጹት አቶ መላኩ፣ ‹‹ይህ አዋጅ በወጣበት ወቅት 986 የንግድ ፈቃድ መስጫ መደቦች ነበሩ፡፡ አዋጁ በ2004 ዓ.ም. ሲሻሻል ወደ 1,352 አድገዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ መላኩ እንደሚሉት፣ የንግድ ሥራ ፈቃዶች በዚህ ደረጃ ቁጥራቸው ማደጉ ከንግዱ ማኅበረሰብ ቅሬታ አስነስቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት በተሻሻለው አዲሱ መመርያ ቁጥር ወደ 919 እንዲወርድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

‹‹አንድ ነጋዴ ከ20 በላይ ንግድ ፈቃድ ይይዝ ነበር፡፡ አሁን መመርያው በመሻሻሉ በአንድ በተጠቃለለ ንግድ ፈቃድ መሥራት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ምንጮች እንደሚጠቁሙት ለመመርያዎቹ መሻሻል ከመንግሥት ፍላጎት በተጨማሪ፣ የዓለም ባንክ ግፊት አለበት፡፡ የዓለም ባንክ በተለይ ከምርጫ 97 ጀምሮ ለመንግሥት ይሰጥ የነበረውን ቀጥታ የበጀት ድጋፍ አቋርጧል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ከዓለም ባንክ ጋር በመነጋገር በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የዓለም ባንክ ይህንን በጀት ለመልቀቅ ከሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶች መካከል የንግድ አሠራር ቀላልነት አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች