Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት የኤርትራ መርከቦችን በሊዝ ለመውሰድ ተጫረተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የውጭ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች እንዲገቡ መፈቀዱ አያሳስብም ብሏል

ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ አዲስ ግንኙነት ከጀመሩ በኋላ የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን በአማራጭነት መጠቀም የጀመረው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የኤርትራን የወጪና የገቢ ዕቃዎች በራሱ መርከቦች ለማጓጓዝ መጫረቱ ታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የገቢና የወጪ ንግድ የጭነት አገልግሎት ለመስጠት ድርጅቱ ባሉት መርከቦች አገሪቱ ወደ ተለያዩ አገሮች የምትልከውን ማዕድናት ጨምሮ የወጪና የገቢ ዕቃዎችን በማጓጓዝ በባህር ትራንስፖርት ያለውን የገበያ ድርሻውን ለማስፋፋት እየተቀንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ለኤርትራ ካርጎ አገልግሎት ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸውና በጨረታው መሳተፋቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ በዋጋም ሆነ በመርከቦቹ አጠቃቀም አስተማማኝና የተሻለ ሰነድ ያስገባ በመሆኑ ጨረታውን እንደምናሸንፍ ጥርጥር የለኝም፤›› ሲሉ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ድርሻው በጣም ውስን መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ብቻ እንኳ ሲታይ በገቢ ንግድ ያለው ድርሻ ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ፣ በወጪ ንግድ ደግሞ ምንም እንደሌለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአብነት ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ በባህር ትራንስፖርት ዕቃ ከማጓጓዝ ይልቅ በአገር ውስጥ የየብስ ትራንስፖርት የተሻለ መሆኑን፣ ድርሻውም እስከ 66 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ አሁን ካለበት ደረጃ በተሻለ የወጪ ንግድ ዕቃዎችን የሚያጓጉዙና እንደ ነዳጅ ዓይነት የፈሳሽ ውጤቶችን የሚይዙ ኮንቴይነር ተሸካሚ መርከቦች አስፈላጊ ቢሆንም፣ ሌሎች መርከቦች በመከራየትም አገልግሎቱን ሊያሳድግ እንደሚችልም አቶ ሮባ አስታውቀዋል፡፡

‹‹እኛ ያሉን መርከቦች ለኤርትራ የገቢና ወጪ ዕቃዎች ለማጓጓዝ በሚገባ ተስማሚ ናቸው፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈሚው፣ ለአገልግሎቱም ሁለት መርከቦችን እንደሚመድብ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል የተጀመረው የንግድና ኢኮኖሚ ድርድር መጠናቀቅ እንዳለበትና ድርጅቱ ተጨማሪ ድርድር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

አሁን ባለው የዓለም ገበያ በመርከብ የትራንስፖርት አገልግሎት አዳዲስ ኩባንያዎች እየገቡ ስለሆነና ነባሮቹም በራሳቸው መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው፣ ከሌሎቹ ጋር በመዋሀድ ከገበያው ላለመውጣት ሲታገሉ ይታያል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከገበያው ውጪ ይሆናሉ፡፡

በተያያዘ ዜናም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤርትራ አስመጪዎች በኢትዮጵያ መርከቦች ለመስተናገድ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

‹‹በእነሱ በኩል ያለውን የገበያ ሁኔታ በደንብ ዓይተናል፡፡ ፍላጎታቸውን የገለጹልንን ያህል እኛም ፍላጎቱ አለን፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ነገር ግን ተጨማሪ የገበያ አዋጭነት ጥናት የሚያስፈል በመሆኑ ለተጨማሪ ስምምነት ድርድር ይጠይቃል፡፡ እኛም የዚያን ያህል እየተዘጋጀን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባለፈው ሳምንት ለአገር ውስጥ ብቻ ተከልሎ የቆየውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍና የመረከብ ውክልና አገልግሎቶችን ለውጭ ባለሀብቶች መፍቀዱ፣ የድርጅቱን አቅም እንደሚያሳድግለትና ከሥጋት ይልቅ መልካም አጋጣሚ እንዳለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከእኛ የተሻለ አቅም ስላላቸው፣ ይዘውት የሚመጡት ልምድ የእኛንም አቅም የሚያሳድግ ስለሚሆን ትክክለኛ ውሳኔ ነው፤›› ሲሉ ውሳኔውን መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ውሳኔው ወደፊት ወደ ግል ይዞታነት ለመዘዋወር የሚደረገውን ዝግጅት የሚያግዝ ነው፤›› ያሉት አቶ ሮባ፣ ድርጅታቸው ከሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ጋር በአጋርነት ወይም በሽርክና ለመሥራት መንገድ ይከፍትለታል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች