Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በፖሊስ ድብደባ ተፈጽሞብኛል አሉ

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በፖሊስ ድብደባ ተፈጽሞብኛል አሉ

ቀን:

በክልሉ የ36 ሰዎች አስከሬን ሲገኝ የበርካቶች እየተፈለገ ነው

በሶማሌ ክልል በተፈጸመ የሰዎች ግድያ፣ የንብረት ውድመት፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎና ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት፣ በፖሊስ ድብደባ እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት፣ ዓርብ መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር የቀረቡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ያለባቸው የደም ግፊት ከፍ በማለቱ ምክንያት ከተኙበት መነሳት አይችሉም ነበር፡፡ ፖሊሶች ለምርመራ እንደሚፈለጉ ገልጸውላቸው እንዲነሱ ሲጠይቋቸው እንዳመማቸው ቢገልጹም፣ በግዳጅ እየጎተቱና እየደበደቡ እንደወሰዷቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ አብዲ ደረሰብኝ ያሉትን ድብደባ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ላለፉት 14 ቀናት በእሳቸውና በሌሎች ሦስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሠራቸውን የምርመራ ውጤቶች ለማስረዳት በቀረበበት ወቅት ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከ14 ቀናት በፊት በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ፣ የዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን (አራቱ በማዕከላዊ የሚገኙ ቢሆንም ስለአምስቱ ተጠርጣሪዎች ያለው ነገር የለም) በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 27(2) መሠረት ተቀብሏል፡፡ የተጠርጣሪዎቹን አሻራና ፎቶም መውሰዱን፣ በክልሉ በጅግጅጋ ከተማና የተለያዩ ወረዳዎች ተፈጥሮ በነበረው አመፅና ብጥብጥ የተሳተፉትን በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል፣ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱንና ቤታቸውን የመበርበርትዕዛዝ ማውጣቱን አስረድቷል፡፡ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን መያዙን፣ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን፣ የተዘረፉና በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶችን ግምት በባለሙያዎች እንዲገመት ማድረጉን፣ በአመፁ የተገደሉ 36 ሰዎች አስከሬን ምርመራ ውጤት ከካራማራ ሆስፒታል መጠየቁን፣ የሦስት ግለሰቦች የምስክርነት ቃል ከጅግጅጋ ሆስፒታል መጠየቃቸውንና 130 ምስክሮችን ቃል መቀበላቸውን አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከላይ የተጠቀሱትን የምርመራ ግኝቶች የሠራው በክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሐመድ፣ በሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ራሂማ መሐመድና በዳያስፖራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ አማን ላይ ነው፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፈረሃን ጣሂር ላይ የሠራውን ምርመራና ግኝት መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው፣ አብዛኛው በእነ አቶ አብዲ ላይ በምርመራ ያገኛቸው ውጤቶች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በእሳቸው ላይ የ117 ግለሰቦችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን አክሏል፡፡

በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ በቀጣይ የሚሠራው በተጠርጣሪዎቹ ትዕዛዝ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ በጨለማ በርካታ ሰዎች በመኪና ተጭነው ቦታው ያልተገለጸ ቦታ እንዲወሰዱ ያደረጉ በመሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች የት እንደደረሱ ስላልታወቀ አስከሬናቸውን ማፈላለግ፣  ሞተው የተገኙ የ36 ሰዎች አስከሬን ምርመራ ውጤት ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ማስተርጎም እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎችን ከመፈለግም በተጨማሪ፣ ‹‹ሂጎ›› በሚባል ስያሜ የተደራጀው የጥፋት ኃይል እንዴት እንደተደራጀና በተለያዩ ቦታዎች ያደረሳቸውን የወንጀል ድርጊቶች ማጣራት እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ የተደበቁ የጦር መሣሪያዎችን አፈላልጎ ማግኘትና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት ሰዎች የምርመራ ውጤት ማስተርጎም፣ ተጠርጣሪዎቹ ያደረጉትን የስልክ ንግግር ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የቴክኒክ ምርመራ ውጤት መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

በጠበቃ የተወከሉት አቶ አብዲና አቶ አብዱራዛቅ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ አብዛኛውን ሥራ ሠርቷል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ ያላቸው የሥልጣን ደረጃ የተለያየ በመሆኑና አንድ ላይ በጅምላ፣ ‹‹ይኼንን አድርገዋል›› ብሎ ማቅረቡ የመከላከል መብታቸውን ስለሚያጣብብ፣ የምርመራ መዝገባቸው ተለይቶ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪው ቀረኝ የሚለው የተደበቀ የጦር መሣሪያ፣ ትርጉም ማሠራትና የሞተና የቆሰለ ለመለየት 14 ቀናት ስለሚበዛ አጭር ቀን እንዲፈቀድ ጠይቀዋል፡፡

አቶ አብዲ በተደጋጋሚ ቅዱስ ቁርዓንና መጽሐፍ እንዲገባላቸው ቢጠይቁ መከልከላቸውን፣ ቤታቸው ይፈተሻል በሚል ምክንያት ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርጎ እየተንከራተቱ መሆኑን ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ አቶ አብዱራዛቅ የታሰሩት ጠባብና ጨለማ ክፍል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የመፀዳጃ ቤቱ ፍሳሽ የሚያልፍበት በመሆኑ ከፍተኛ ሽታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

አቶ አብዲ ራሳቸው ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ ተከልክለዋል፡፡ የመናገር መብታቸውንም ‹‹እንዳትናገር›› መባላቸውንና ፍርድ ቤት ለሚኖራቸው ክርክር ለመዘጋጀት መጻፊያ ወረቀት መከልከላቸውን አስረድተዋል፡፡ ለብቻቸው የታሰሩ ቢሆንም ቅዱስ ቁርዓን እንዳይገባላቸው መከልከላቸውንና ሦስት የፖሊስ መኮንኖች የታሰሩበት ክፍል ድረስ በመምጣት፣ ‹‹ልክህን እናሳይሃለን›› እያሉ እንደሚያስፈራሯቸው ተናግረዋል፡፡ የአምስትና የስድስት ዓመት ሕፃናት ልጆቻቸው በሆቴል ውስጥ ስለሆኑ ፍርድ ቤቱ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ለምርመራ በሚል ለ12 ሰዓታት እጃቸውን በካቴና አጥብቀው ስላሰሯቸው እጃቸውን መታጠብ እንኳን እንዳቃታቸውም አክለዋል፡፡

አቶ አብዱራዛቅም ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸውና ከሃይማኖት አባቶቻቸው መገናኘት እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅድ ቢሆንም፣ መከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ መስገድ እንደተከለከሉና መድኃኒትና ሐኪም ስለሌለ የኮሌስትሮል ሕመማቸው እንዳስቸገራቸው አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ማስረጃ ሳናሰባስብ ሰዎችን አናስርም፤›› ስላሉ፣ እነሱም ፀሐይ ተከልክለው ጨለማ ቤት በመታሰር የጨጓራና የአስም ሕመማቸው ስለሚብስባቸው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ምርመራው እንዲጣራ ጠይቀዋል፡፡

የደም፣ የስኳር፣ የኩላሊትና የአስም ሕመምተኛ መሆናቸውን ያስረዱት የክልሉ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ራሂማ ደግሞ ይጠቀሙ የነበረው መድኃኒት ቀርቶ እየተሰጣቸው ያለው መድኃኒት ሌላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሕመማቸው የሚስማማ ምግብ እንደማይሰጣቸው፣ የደም መለኪያ እንደተከለከሉ፣ በማንነታቸው ምክንያት እንደሚሰደቡና ሌሎችንም አቤቱታዎች ገልጸው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ፈረሃን ደግሞ በሰጡት አስተያየት፣ የፖሊስ 14 ቀናት መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን፣ እንደሚበዛና መርማሪ ቡድኑ የሚናገረው እሳቸው የሠሩትን አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡  

የታሰሩበት ክፍል ጠባብ መሆኑን፣ ከታሰሩ ጀምሮ ቤተሰብ እንዳላገኛቸውና የት እንዳሉ እንደማያውቁ፣ የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውንና መድኃኒት እንደማይሰጣቸው፣ ጨለማ ቤት መታሰራቸውን፣ በር እንደማይከፈትላቸውና የፀሐይ ብርሃን እንደማያገኙ፣ ቅዱስ ቁርዓን እንዳይገባላቸው መከልከላቸውንና በብሔራቸው እንደሚሰደቡ ለፍርድ ቤቱ አመልክተው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና መጠየቃቸውን ተቃውሟል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳም አመፁ የተፈጸመው በጅግጅጋና በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ከመሆኑ አንፃር፣ ውስብስብና ገና ብዙ ምርመራ ይቀረዋል፡፡ የበርካቶች ሕይወት ማለፉን፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙንና በርካታ የሃይማኖት ተቋማት መቃጠላቸውን አስረድቷል፡፡ ዘርና ሃይማኖትን መነሻ በማድረግ በርካታ ሰዎች በተጠርጣሪዎቹ ትዕዛዝ እንዲሠወሩ በመደረጋቸው የት እንደገቡ አልታወቀም ብሏል፡፡

አቶ አብዲ ቤተሰብ አይጠይቀኝም ያሉት በከተማው ውስጥ ችግር ስለነበረ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ካልሆነ በስተቀር፣ ሌላ ጊዜ እንደሚጠይቋቸው መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ብርበራ መጨረሱን ጠቁሞ፣ ቤተሰቦቻቸው ቤታቸው መግባት እንደሚችሉም አክሏል፡፡ ካቴና ጠብቆ እንደታሰሩ የተናገሩት ትክክል አለመሆኑንና ተጠርጣሪ በመሆናቸው ግን በካቴና መታሰራቸው ግድ መሆኑን መርማሪ ፖሊስ አስረድቷል፡፡ የመናገር መብታቸውን እንደተከለከሉ የተናገሩት ሐሰት መሆኑን፣ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከፖሊስ ጋር ሲያወሩ እንደሚውሉ፣ አስፈላጊ ከሆነ የጠያቂዎችን መመዝገቢያ ሰነድ ማየት እንደሚቻል መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ሕክምናም በተሟላ ላብራቶሪ፣ ነርሶችና ዶክተሮች የሚሰጥ በመሆኑ ችግር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ምግብን በሚመለከት ከመስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በስተቀር በየቀኑ ከቤተሰቦቻቸው እንደሚቀርብላቸው አስረድቷል፡፡

ንፅህናን በሚመለከት ችግር እንዳለ አቶ አብዱራዛቅ አመልክተው መርማሪዎች መጎብኘታቸውን ገልጾ፣ ካልተስተካከለ እስረኛ አስተዳደር ጋር ተነጋግረው እንዲስተካከል እንደሚያደርግም አስረድቷል፡፡ ስግደትን በሚመለከት በታሰሩበት ክፍል ውስጥ እየሰገዱ መሆኑን፣ ነገር ግን የተለየ የማምለኪያ ቦታ እንደሌለ አክሏል፡፡ ቅዱስ ቁርዓንና መጻሕፈት መግባት የሚችል ከሆነ በመነጋገር እንዲገባ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ የምርመራ መዝገብ እንዲለይ የተጠየቀውን በሚመለከት፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል አንድ ዓይነት ስለሆነ እንጂ መለየት እንደሚቻል፣ በቀጣይ ተለይቶ እንደሚቀርብ አስረድቷል፡፡ አቶ አብዱራዛቅ ቤተሰብ አይጠይቀኝም ቢሉም እየተጠየቁ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ የደም ግፊት መለኪያ መግባት የሚችል ከሆነ ተነጋግረው ለወ/ሮ ራሂማ እንደሚገባላቸው አክሏል፡፡ አቶ አብዲና ወ/ሮ ራሂማ ‹‹መከላከያ ገብቷል፣ ዝም ትላለህ ወይ?›› የሚል መግለጫ ለክልሉ ልዩ ፖሊስ በመስጠታቸው ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል አንድ ዓይነት መሆኑን ማሳያ እንደሆነ መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ኮሚሽነር ፈርሃን የሚሰጣቸው መድኃኒት በባለሙያ የታዘዘና የታየ መሆን እንዳለበት፣ ምግብም ለሁሉም እስረኛ የተዘጋጀውን ሳይሆን በሐኪም የታዘዘው እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የሃይማኖታቸውን ግዴታ ማካሄድ መብታቸው በመሆኑና በመመርያና ደንብ ሊታገድ ስለማይችል፣ ቅዱስ ቁርዓን እንዲገባላቸውም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በማንነታቸው የተነሳ የስድብ ጥቃት ደርሶብኛል ስላሉ መርማሪ ቡድኑ አጣርቶ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የታሰሩበት ቦታ ብርሃን የሚገባበትና የተሻለ እንዲሆንም አክሏል፡፡ አቶ አብዲ፣ አቶ አብዱራዛቅና ወ/ሮ ረሂማን በሚመለከትም በአግባቡ እንዲያዙ፣ ቅዱስ ቁርዓንና መጻሕፍት እንዲገቡላቸው፣ በባለሙያ የታዘዘ ምግብና መድኃኒት እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የጠየቁትን ዋስትና ውደቅ በማድረግ መርማሪ በቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለመስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...