ለውጥ በሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አለው። የዛሬይቱ ዓለም ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መልክዐ ምድራዊ ወዘተ ሁናቴ መነሻ ሲኖረው፣ በጊዜ ሒደት ውስጥ ታሽቶ ዛሬነቱን ሊያገኝ የቻለው በለውጥ ጉልበት ነው።ለውጥ በፈጣሪ የተዋቀረ ሥርዓት እንጂ ከፈጣሪ ጋር በተቃርኖ የቆመ ሥርዓት አይደለም። የለውጥ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ጉልበቱ ደግሞ ጊዜ ነው። ዓለምና ሥርዓቷ ከተቆረቆሩ ጊዜ ጀምሮ ለውጥና የለውጥ እንቅስቃሴና እሳቤ አብሮዋት የዘመኑ ዕድሜ ጠገብ ክንውን እንጂ ለውጥ ጊዜ አመጣሽ እሳቤ አይደለም፡፡ በመሆኑም ለውጥና መለወጥ የዓለም ወግ ነው። አንዳንዱ የዓለም ለውጥ አዝጋሚ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ፈጣን ነው። ሁላችን እንደምንታዘበው ነገ የሚባለውን ማንነትና ምንነት ለመፈጠር ዓለምና ሞላዋ በጊዜ ውደት ውስጥ መናጧን ዛሬም ቀጥላለች፣ ነገም ትቀጥልበታለች። ነገን ማየት የሚወድ፣ በነገው ዓለም ላይ የተሻለ ሆኖ መገኘትን የሚመኝ ሁሉ ዛሬውን በጊዜ ውስጥ አኑሮ፣ ዛሬን ስለነገ ዋጋ ከፍሎ ሊኖር ይገደዳል።
አንዳንዱ የዓለም ክንውኖች በጎ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በጎ ያልሆኑ ክስተቶችንም ዓለም አስተናግዳለች፣ እያንዳንዱ ክንውን ጊዜ በሚባለው አዙሪት ሥር የተቃኘ በመሆኑ፣ ፍጥረት ሁሉ የለውጥ ተጠቂ ሆኖ የዕድሜውን ዙረቱ ይኖረዋል። ፍጥረት ሁሉ ጊዜው የሚያደርገውን ይሆን ዘንድ ግድ ሆኖበት ዘመኑን አንድ ብሎ መቁጠር ይጀምራል፡፡ ተወለድን ብለን ለመቁጠር ጀምረን ሳንጨርስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሞተን በማጠቃለያ ዜናነት እንሆናትም ዘንድ እንገደዳለን። ሰው ከፍጠረታቱ ሁሉ ልዮ የሚያደረገው ጊዜ የሚያመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከፍተኛ ግብ ግብ ውስጥ መግባቱ ነው። በእርግጥም ሰው ጊዜና ዘመን የሚያመጡትን ለውጦች ለማስቆም ባይችልም በተወሰኑ ሁናቴ ለመዘግየት መቻሉ ግን ትልቅ ቁምነገር ነው። ሕይወት የሚጀምርበትና የሚቆምበትን ጊዜ ለመለወጥ የሚካሄደው ሙከራ እጅግ አድካሚ ነው፡፡ ሰው ግን ይህንን ይለውጠው ዘንድ ከሙከራ ጥበብ ውስጥ ገብቶ ዘወትር ይታገላል። ይህ ግብ ግብ ጊዜን በመቆጣጠር ረገድ ምን ያህል ከፍታ ላይ ይደርስ ይሆንን? የትግሉን ውጤት ጊዜው ራሱ ይነግረናል። ለእኔ ጊዜ በዓለማችን የለውጥ ሒደት ውስጥ እምብርት እንደሆነ ይሰማኛል።
ይህ የለውጥ እውነታ እንዳለ ሁላችን ብናምንም ለውጥን ግን አናምናትም። ከዚህ የተነሳ ለውጥን በብዙ መንገድ ስንሞግታት፣ አንዴ ሽቅብ አንዴ ቁልቁል ስንገፋት እንስተዋላለን፡፡ ለውጥ ግን ታላቅ ኃይል ናትና ብርታቱዋን በጊዜ ውስጥ ትገለጣለች። ለውጥን ማዘግየት ይቻል ይሆናል፣ የለውጥን ፍላጎት አቅጣጫ ወደ አልተፈገ መስመር መቀልበስም ይቻልም ይሆናል ነገር ግን ለውጡን ማስቀረት ከቶውኑ የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመደብ ትግል፣ የነፃነት ጥያቄ፣ ሀብት ክፍፍልና ፍትሃዊነትና ሌሎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በማኅበረሰቡ ልብ ውስጥ ሲንከባለል የኖረ ጥያቄ ነው። ማኅበረሰብ ጥያቄን አዝሎ በዝምታ ሲጓዝ ከርሞ ጊዜ የወለዳቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ጥያቄ ጉዳያቸው አድርገው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙና ማኅበረሰቡም በውስጡ ላለ ብሶት ምላሹን ሲቸር ለውጡ በድንገት ብርቱና ጉልበታም መሆን ይጀመራል። ለውጡን ሊመሩ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙ ሰዎች ግን ከማኀበረሰቡ ድጋፍ ብቻ እንደሚያገኙ ብቻ አስበው የጀመሩ እንደሆነ ግን እሳቤያቸው ልክ አለመሆኑን የሚረዱት አፍታም ሳይቆዩ ነው። ለውጥን የጀመሩ አካላት ድጋፍም፣ ተቃውሞም ከማኅበረሰቡ ሊገጥማቸው እንዲችል ከወዲሁ መገንዘባቸው መልካም ነው። ከቀደም “ወርቅ ቢያነጥፉለት. . .” እንዳለው “ቆራጡ” መሪ ማኅበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ ካልደገፈን ብሎ ከሙግት ውስጥ ራስን መዶል ለወድቀት መጀመሪያ ይሆናል። ማኅበረሰብ የገዛ ራሱ ምርጫና ፍላጎት አለው፡፡ አንዱ ሲወድ ሌላውን ሊጠላም መብት አለው፡፡ አንዱ የማኅበረሰብ ክፍል የሚያፀድቀውን ሌላኛው ሊያረክሰውም ይችላል።
መሪነት እነዚህን የተለያዩ የማይገናኙ የሚመስሉ ጽንፎች ባሉበት ለውጥን መጫር ነው፡፡ መሪነት ስለለውጥ ነው። መሪ ግልጽ የሆነ ተቃውሞ ከብዙኃኑ ቢገጥመው ምን ሊያደርግ ይገባል? ተቃውሞ በብዙ መልክ ሊገለጽ ይችላል። በእኛ አገር ተቃውሞ ቤት በመቀመጥ፣ ባልስማማበትም “ንብረት በማውደም”፣ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ በመሳተፍ፣ የተቃውሞ ጽሑፎችን በማሰናዳት፣ በሕዝቡ በመደራጀትና ጥቃት በመፈጸም፣ ምርታማነትን ሆን ብሎ በመቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገሪቷን እንዲያዳክማት በማድረግ፣ ከገዢው መንግሥት ጋር ወገንተኛነት ያላቸውን ሰዎች በማኅበራዊ ተሳትፏቸው ሆነ ብሎ በማግለል፣ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን በማሳጣት፣ በአገር ውስጥ ማኅበረሰቡ መረጋጋት እንዲያቅተው በማስቻል፣ ማኅበረሰቡ ቁጣውን በገዥው ላይ እንዲያሳይ በማነሳሳት፣ የገዥውን አመራሮች ግለስባዊ ቅቡልነት በማጎደፍ ተቀባይነት በማሳጣት፣ መሪዎች እርስ በራስ እንዳይተማመኑ መረጃዎች ከመካከላቸው አፈትልከው የሚወጡበትን መስመሮች በመገንባትና በሌሎች በርካታ መንገዶች ተቃውሞን ማኅበረሰቡም በጋራም ሆነ በተናጠል ያካሄዳል፡፡ ወደፊትም ያካሄዳል። ይህንን ተቃውሞ የሚቋቋም አመራርና ሥርዓት መገንባት የመሪ ትልቁ ድርሻ ነው። አመራርና ሥርዓት ደግሞ የሚገነባው ችሎታንና ታማኝነትን ባማከለ አካሄድ እንጂ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስለትምህርት እንዳሉት ከችሎታ ይልቅ ታማኝነትን በማስቀደም መሆን ያለበት አይመስለኝም። ችሎታ የሌለው ታማኝ ሥራ መሥራት አይቻለውም። በመሆኑም በሥራቸው ሒደት ለሚገጥማቸው ችግሮች ሁሉ መፍትሔ ለመስጠት የማይችሉ ታማኞች ይሆናሉ። ብልህ መሪዎች ለሚፈለጉት ሥራና ውጤት የሚመጥን ችሎታ፣ ጥበብ፣ ተነሳሺነት ያላቸውን ግለሰብና ቡድኖች ከዙሪያቸው ያኖራሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚሠሩበትን ሕጋዊ፣ ፍትሐዊ፣ ግልጽ፣ አሳታፊ፣ ከአድሎ የፀዳ ሥርዓትን ደግሞ ይገነባሉ።
ታዲያ ሰዎች ለውጥን ስለምን ይፈሩዋታል?
ለውጥ ሲመጣ ከዚህ ቀደም በሥልጣን ላይ ያሉትን አካላት የውሳኔ አቅምና ጉልበት ከንቱ ስለሚያደርግ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ያሉ ሰዎች ለውጥንና የለውጥን እንቅስቃሴ አጥብቀው ይፈራሉ። ይህ ፍርኃት በፖለቲካው ሥርዓት ላይ ስላላቸው አቅምና ተሰሚነት ብቻ ሳይሆን በገዛ ሕይወታቸውና ኑሮዋቸው ላይ የሚኖራቸውን ግላዊ ውሳኔን ጭምር እንደሚቀይረውም ጭምር ከሕይወት ተሞኩሯቸው ስለታዘቡ በእጅጉ ይሠጋሉ። ከዚህም የተነሳ ለለውጥ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ግለሰቦችና ቡድኖችን በማጥፋት ሥራ ላይ ዘወትር ይጠመዳሉ። ጨቋኞችና ገዢዎች ሁሉ ሊገነዘቡት ያልቻሉት ትልቅ ቁምነገር የሚያሳድዳቸው የገዛ ሥርዓታቸው እንጂ የሚያሳድዳቸው ሌላ አካል የለም። ይህ እውነት ጨቋኞች ላልሆኑት ሁሉ የሚሠራ ሀቅ ነው።
ብልህ መሪዎች በለውጡ ሳቢያ ሥልጣናቸውንና ምቾታቸን ያጡ አካላት የገዛ ምርጫቸውን እንዲወስዱ ዕድል የሚሰጥ እንጂ ከዚህ ቀደም በገዛ ዘመናችን እንዲሁም በታሪካችን እንዳሰተዋልነው ከሥልጣን የወረዱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ወደ ማጎሪያ ጣቢያ መውሰድ ወይንም የመኖር መብታቸውን ማሳጣት መፍትሔ አይደለም። የለውጥ አቀንቃኞች እንዲህ ያለውን ዕርምጃ ለመውሰድ የሚገደዱት ከፍርኃት የተነሳ ነው። የመሪ ድርጊት መነሻው ፍርኃት ሳይሆን የለውጡን ሞተር ያንቀሳቀሰበት ዓላማው ነው። በመሆኑም ብዙኃኑን ሊጠቅም የሚችለውን ዓላማውን ለሰፊው ሕዝብ ማሳወቅና ደጋፊ ማበራከቱ መልካም ነው። ስለሆነም ሕዝብ ወደ ተሻለ የኑሮ ግንባታ እንዲገባ ሁሉን አሳታፊ፣ ግልጽና የሚለካ ዕቅዶችን በማውጣት ሰፊውን ሕዝብ የዕቅዱና የሒደቱ ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል።
የማይታውቀው ጉዞ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በጎዳናዎች ላይ በተንቀሳቃሽ ነጋዴዎች ከሚሸጡ ዕቃዎች መካከል በአንዲት ሥዕል ላይ ዓይኔ አረፈ፡፡ ሥዕሉ ላይ አንዲት የምታምር ትንሽ ልጅ የእናትዋን ጫማ ተጫምታ መንገድ ጀመራ ይታያል፡፡ ከሥዕሉ አናት ላይ “ወደ የት እንደምሄድ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ጉዞ ጀምሬያለሁኝ” ይላል። ሥዕሉ ከመልዕክቱ ጋር በመመሳሰሉና በመግጠሙ እየተገረምኩኝ እኔም ጉዞዬን ቀጠልኩኝ። ሕዝብ የሚመራው ግልጽ በሆነ ራዕይ እንጂ በሚያማልሉ ብዙ ቃላት አይደለም። ራዕይ የሌለው መሪም ሆነ ሕዝብ ወሎ አድሮ መስመሩን መሳቱ አይቀሬ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የውጤታማ መሪነት መሠረቱ ባለራዕይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለያዘው ራዕይ የሚመጥን ዕቅድ፣ ዝግጅት፣ ሥልት፣ አደረጃጀትን፣ ቁርጠኝነትንና ሌሎችን ግብዓቶች ያለ ምንም ችግር ሲያሳልጥ ነው። ራዕይ የሌለበት ቡድንተኝነት ሆነ የሥልጣን ዘመን ያለፍሬ መደምደሙ ሳያንስ አክሳሪም ጭምር ነው። ታሪካችን ይህንን ደጋግሞ ይዘክረዋልና ልብ ያለው ልብ ይበል።
በአገራችን “ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል” ይባላል። ማኅበረሰቡ ከመልዓክ ይልቅ ሰይጣንን ወዶና አስበልጦ ሳይሆን ማኅበረሰቡ በአባባሉ እንዲተላለፍ የፈለገው የሚሻለውን መልዓክ እናውቀው ዘንድ እንደሚገባ ለማሳሰብ፣ እርሱን ባናውቀው ግን ቢያንስ ሰይጣኑን አውቀነዋልና ከሰይጣናዊ ተግባሩ ልንገታው ይቻለናል፣ ከሰይጣናዊ ተግባሩ ልንገታው ካልተቻለን ደግሞ ክፋቱንና ሰይጣናዊነቱ እንዳይጎዳ እንጠነቀቀዋለን የሚል ይመስለኛል። ይህ ሁሉ ሐተታ አንድ ነገር ለማስቀመጥ ነው፡፡ ይኸውም መሪነት ያለ ራዕይ ከንቱ ድካም ነው። ይህ ራዕይ ደግሞ ግልጽ የሚለካ፣ ሒደቱ ተጭባጭ፣ የማያሻማ፣ በጊዜ መርሃ ግብር የተዋቀረ መሆን ይኖርበታል። ብሩህ መሪዎች የሚከተላቸውን ብዙ መሪዎች ለማፍራት ከራዕያቸው ባሻገር ሒደቱን ግልጽና ሁሉም ሊገነዘበው እንዲችል ያደርጋሉ።
የጉዱ ካሳ ዱብ ዕዳዎች ሕዝቦች ያልታሰበና ያልተጠበቀ ድንገታዊ ክስተትን የማስተናገድ ብዙ አቅም የላቸው። በአገራችን ለተከሰቱት ለውጦች ድንገታዊ ዱብ ዕዳ የሆኑብን ብዙ ታሪካዊ ክስተቶች አሉን። የአፄ ቴዎድሮስ፣ የግርማሜዎቹን እንቅስቃሴ እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል። ሁለቱ የግርማሜ ልጆች በወቅቱ ንጉሡን ለማውረድ የሚያስችል ማኅበረሰባዊ አደረጃጀት፣ እሳቤና እምነት ባልዳበረበት፣ በመሪው የሚምል ሰፊ ማኅበረሰባዊ ኃይል በተንሰራፋበት ሁናቴ ሳይደራጁና ነገሩን በጥልቀት ሳይመክሩ የተፈጸመ እንቅስቃሴ በመሆኑ ለተነሱለት ዓላማ ሕይወታቸውን ገብረው ዛሬ ድረስ የደማቅ ታሪክ ባለቤት ቢሆኑም፣ ሊሞቱለት የፈቀዱለትን ለውጥ ግን መጎናጸፍ ሳይችሉ ጎድለዋል። እነዚህ ብርቅዬ የግርማሜ ፈርጦች ከማኅበረሰቡ ቀድመው ነቅተው፣ ማኅበረሰቡን ሳያነቁና ሳያላምዱ ለውጡን ሊያበስሩ ከማደሪያቸው እንደወጡ ያስቀራቸው ለውጡን ሊደግፍ የሚችል የለውጡ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ በሰፊው ስላልተሰናዳ ነው። መሪዎች ለውጥን በሚስጥር ይዘው ከርመው በአንዲት ጀንበር ወደ ማኅበረሰቡ ሊያሰርፁት መሞከር የለባቸውም፡፡ ሚስጥሩ የለውጡ አቀንቃኞቹ ማንነት እንጂ ለውጡ መሆን የለበትም። የንጉሣዊው ሥርዓት ሲገረሰስ ለውጡን ሲያቀነቅኑ ያልነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማግኘት አይቻልም። ለውጡ በገጠር፣ በከተማ በሁሉም ሥፍራ እንደ ዓመት በዓል ድግስ በየቦታው ይሸት፣ ይናኝ እንደነበር በወቅቱ ባንወለድም ከታሪክ ተምረናል። ደርግ የዚህ ለውጥ አስጠባቂ መስሎ የለውጡን አቀንቃኞች የነበሩትን ወጣቶች በጠራራ ፀሐይ ፈጅቶ የለውጥ ቀማኛነቱን በታሪክ ድርሳን ላይ አስፍሮም አልፎዋል፡፡ መሪዎች ሊያመጡ የሚወዱትን ለውጥ ማኅበረሰቡ እንዲገነዘብ በተለያዩ መድረኮች መረጃዎቻቸውን በጥንቃቄ ያስተዋውቃሉ፡፡ ሒደቱም ወደማያስፈለግ አቅጣጫ እንዳይሄድባቸው ነቅተው ይከታተላሉ።
በእንቁጣጣሽ ሁሉ ነገር ልዩ ይመስላል፡፡ ለውጥ ማለት አንድን ነገር የተለየ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ልዩ ነው? አንድ መሪ የሚያመጣውን ለውጥ ሰዎችስ ምን ያህል ልዩነቱን ይረዱለት ዘንድ አድርጎዋል? ለተመዘገበው ለውጥስ ማኅበረሰቡ ምን ያክል ቀኝ እጃቸውን ይሰጣሉ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ሰው በተፈጥሮው ለማዳ ፍጡር ነው፡፡ የለመደውን ቀዬ ጥሎ ወደማያውቀው ሥፍራ ሊነጉድ ሲነሳ መላ ማንነቱ በጭንቀት ይተራመሳል፡፡ ቀዬውን ጥሎ ርቆ ተመችቶት እየኖረ እንኳን ያንን የጥንቱን ሕይወት እንደሚናፍቅ ሲያወራ ቢስተዋልም ድንገት ወደ ቀድሞ ቀዬው ተመለስ ቢባል አይ አሁንማ እዚሁ ተላምጄዋለሁኝና እንደገና ደግሞ ሀ ሁ ልል ነውን? ማለቱ አይቀርም። ሰው በብዙ መልኩ ለውጥ አይመቸውና የለውጥ አቀንቃኞች ለለውጥ ሲነሱ ለውጡ የማኅበረሰቡን መሠረታዊ መቀመጫ የማይንድ አለመሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጎረቤታቸውን እማሆይ ቤት ማደስ ከአንድ ግለሰብ ባለፈ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ነው። እኔ እንደምረዳው እየመጣ ያለው ለውጥ ከቀዬህ የሚያፈናቅልህ አይደለምና ከሥጋት ውስጥ አትግባ እንደማለትም ጭምር ነው። እየመጣ ያለው ለውጥ ቤትህን የሚያድስ፣ ተስፋህን የሚያለመልም ነው የሚለውን መልዕክት በጉልህ ለሰፊው ኅብረተሰብ በቀላል ተግባር ማስተላለፍ ተችሏል። መሪዎች ሁሉን ነገር በእኔ የሥልጣን ዘመን ካልለወጥኩኝ ሙግት ውስጥ መግባት ታላቅ ኪሳራ መሆኑን የቋራው ቋጥኞችን ለዘላለሙ ከተንተራሰው ጀግና መማር ይቻላል። መሪዎች በገዛ ዘመናቸው ሊለውጡ በተነሱት ጉዳዮች ብቻ ላይ አትኩሮቶቻቸውን ሊያውሉ ያስፈልጋል፣ ስለለውጥ ተብሎ የሚደረግ ለውጥ ሁሉ ውጤት አያመጣምና በዋና ጉዳዮች ላይ አትኩሮት ቢሰጥ ለውጡን እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ማስቀጠልም ያስችላል።
የጥንቱን ውብት መቼም ለውጥ ሲባል ወደ አዕምሮዋችን የሚመጣው ከቀድሞ የተለየ በመሆን የጥንቱን ጥሎስ፣ የትላንቱን ወደኋላ አሽቀንጥረን በመጣል ወደ ፊት ስለመገስገስ እንደሆነ የታሪክ መረጃችን ይነግረናል። ይህ ዓይነት ለውጥ ግን ለውጥ ብቻ ሳይሆን አፍራሽም ሊሆን እንደሚችል መገንዘቡ መልካም ነው። ድሮ ድሮ ልጅ እያለን ለበዓል አዲስ ልብስ ስንለብስ፣ አዲስ ጫማንም ስንጫማ ከዚህ ቀደም የለበስናቸውን፣ ለብሰንም ያጌጥንባቸውን ልብሶችና ጫማዎች ሁሉ ረስተን በአዲሶቹ ብቻ ተሽቀርቅረን በጓደኞቻችን ፊት ደምቀን መታየቱን እንወዳለን፡፡ ይህ ደስ የሚል ልጅነት ጊዜ ነው። አገር እንዲህ ባለ የልጀነት ልቡና መመራት ከጀመረ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ቀስ በቀስ እያየለ እንደሚሄድ ከእኛ ከሐበሾች የተሻለ የሚረዳው ላይኖር ይችል ይሆናል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የአገራችን ታሪክ ይኼና ከዚህም የከፋ ሁናቴን የያዙ መስተጋብሮችን በውስጡ ይዘዋል። በአገራችን ውስጥ የተከሰቱት ለውጦች የትላንትናውን ሥርዓት የማይቀበል ብቻ ሳይሆን የትላንትናውን ሥርዓትን የመሩ ኃይሎችን በሕይወት እንዳይኖሩ ሕይወታቸውን የቀጠፈ፣ የመንቀሳቀስ መብታቸውን ያገደ የትላንቱን ቂም በቀል በመመለስ ለአዲስ ቂም እርሾ የተወ ነበር። ብልህ መሪ ስለነገ ትላንቱን በአስተማሪነቱ የሰነቀ፣ የትላንቱን ከፍታ እንደ መነሻ የወሰድ፣ ጥፋቱን ላለመደገም የቆረጠ ካልሆነ በቀር እንደ ትላንቱ ከሾካማ ጭቃ ውስጥ ራሱን መዶሉ የግዱ ይሆንበታል።
የከረም ቁርሾና ቁጣ ዛሬ ላይ የታፈነ ቁርሾና መከፋት ተዳፍኖ ብናየውም አንድ ቀን አንዳች ንፋስ ሲያገኘው ረመጥ ሆኖ ሊፋጅ እንዲችል መረዳት መልካም ነው። ሁሉ ነገር ሲዳፈንና ሲሸፈን የተረሳ፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነ፣ የሥልጣንም እርካቡም የተደላደለ ይመስላል። ነገር ግን አንድ ቀን ልከኛ ንፋስ የምትመስል ሽውታ አመዱን የገለጠችው እንደሆነ፣ ሰዎችንም እንዲደራጁና ለውጥን እንዲሹ ያደረገች እንደሆነ የከሰመውና የተዳፈነው እሳት ትልቁን ጫካ የሚበላ ታላቅ ነበልባል ወደ መሆን ሊለወጥ እንዲችል መገነዘቡ መልካም ነው። ስለሆነም መሪዎች ነገን ለመገንባት ከመነሳታቸው አስቀድመው በሕዝቦች ዘንድ ያለን የትላንቱን ቁርሾ፣ ጥላቻ መፈወስ ይኖርባቸዋል። የከረመ ቁስል ሊከፈት ይችላል፡፡ የትላንትናው ታሪካዊ ስህተቶች በዛሬ ትውልድ እንደገና ሊታሰቡበት የሚቻላቸውን ሁናቴ ሊያገኙ ይችላል። ታዲያ መሪዎች ቆም ብለው የተዳፈነን ነገር ለመካድና እንዳልነበረ እንድንቆጥር ‹‹በቃ እርሳው›› አካሄድን ለማራመድ ቢወዱ፣ ከትልቅ ኪሳራ ውስጥ ራሳቸውን ሊዶሉ ጀምረው እንደሆን እንጂ በመንገዳቸው ትርፋማ አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ የትላንቱን ስህተት እንዳይደገም በብዙ ጥንቃቄ ሥርዓት ዘርግተው፣ በሕግ አግባብና ማዕቀፍ ነገሩን አስከበረው ማኅበረሰባዊ ፈውስ ፈጥረው ወደፊት ጉዞዋቸውን ሊቀጥሉ ያስፈልጋቸዋል።
ለውጥ አደጋም አለው፡፡ ብዙ ሰው ለውጥን የሚሸሽበት ምክንያት ለውጥ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ነው። አንዳች አዲስ ግኝት ሲፈጠር የቀድሞው ግኝት መንገዱንና ሥፍራውን ለአዲሱ መሰጠቱ ግልጽ ነው። በዚህም ሰዎች ራሳቸውን ከዘመኑ ግኝት ጋር ካላዘመኑ በቀር አዲሱ ግኝት ተግባራዊ ሲሆን ሥራቸውንና ጥቅማቸውን ሊነጥቃቸው እንዲችል ስለሚረዱ ለውጥን በእጅጉ ይፈሩታል፡፡ ለውጥን መፍራት ብቻ ሳይሆን የለውጡም ጽኑ ባላንጣዎች ይሆናሉ። ስለዚህ ለውጥን የሚያራመደው አካል ወይንም መሪ ለውጡን እውን ማድረግ በሚያደርግበት ጊዜ እያንዳንዱን የለውጥ ሒደት ግልጽ፣ ተአማኒነት ያለው፣ ፈጣንና ፍትሐዊ ሊያደርገው ይገባል።
ለውጥ ሲመጣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ስሜት የተተራመሰ ስሜት መፍጠሩ ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ መረዳት በማሳደግ ለውጡን እንዲረዱና እንዲገነዘብ ካልተደረገ በቀር ማኅበረሰቡ ሕግ አልባ ወደመሆን በቀላሉ ሊሸጋገር ይችላል። ከዚህ ውጪ በለውጡ ምክንያት ተንሳፋፊ እሆን ይሆንን? የሚል ፍርኃት ያደረባቸው ግለሰቦችና ቡድኖችም በተናጠልና በቡድን የለውጡን ሒደት ለማደናቀፍ መሞከራቸው አይቀርም። የተጀመረው ለውጥ እነርሱን ከምቾቶቻቸው እንደሚያፈናቅላቸው፣ ጥቅማቸውን እንደሚነካባቸው ከመሰላቸው ለውጡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ሰፊ የማጥላላት ዘመቻም ውስጥ ይገባሉ። ብልህ መሪዎች ይህንን ብዥታ ለማጥራት ብሎም የሰዎችን አቅም ለማደራጀት ሰፊና የተጠናከረ ሥልጠና፣ ለውጡን የማስተዋወቅ ተግባር ውስጥ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለሚያከናውኗቸው ዕቅዶችና ዓላማዎች ከባላንጣዎቻቸው ይልቅ ሥፍር ቁጥር መረጃዎችን ያሰራጫሉ፣ ከዚህም አልፈው ሁለቱ ሥርዓቶች ማለትም የቀድሞይቱና አዲስቱ በመካከላቸው ጠላትነት እንዳይፈጥሩ በሰላም እርስ በራሳቸው እንዲተካኩ ጊዜን ይሰጣሉ። በዚህም አዲሲቲቱ ሥርዓት በቀድሞይቱ ላይ ቀስ በቀስ እየበረታችና እየተተካች እንድትሄድ ያደርጋሉ። ይህንን መንገድ መከተል ለዘላቂ ዕድገትና መተማመን መሠረት ቢሆንም እስከ ሕይወት የሚያደርስ ትልቅ መስዋዕትነት ግን ሊያስከፍል እንዲችል አስቀድሞ ተረድቶ ሒደቱን በጥንቃቄ መመልከቱ መልካም ነው። በ1953 የግርማሜዎቹን ድንቆች ሕይወት ያስከፈለው እሳቤ ይኼኛው ነው።
ሌላ ተጨማሪ የራስ ምታት ሁላችንም እንደምንረዳው እንደ እኛ ባሉ አገር ላይ የሚከሰት ለውጥ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ለውጡን የሚመሩት መሪዎች ሳይቀር ስለለውጡ ፍርኃት እስኪያድርባቸው ድረስ የለውጡ ሒደት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፣ የባቡሩም ሐዲድ መንገዱን ቢስት የሚከሰተውን ዓይነት ፍርኃት የሚያስፈራን ጉዞ መሪዎች መጓዛቸው የግድ ይሆንባቸዋል። እንደ እኛ ለ27 ዓመት በገዛ ወንድሞቹ ያለ ፈቃዱ ታፍኖ ያለ ሕዝብ ድንገት ሲለቀቅ ግራ መጋባቱ አይቀርም፣ ይህንንም ጉዞ የሚመራውም መሪም ማኅበረሰቡ የሚያደርገውን ምላሽ በእርግጠኝነት ለማወቅ ይቸገራሉ። ማኅበረሰቡ ድንገት ለውጥ ሲፈነጥቅለት ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚጠይቀው፣ የሚፈለገው፣ የሚመኝው ሁሉ የበዛ አንዱ ከሌላው ጋር የተመታታም ሊሆን ይሆናል። ከዚህም ሌላ እኛ ለውጥን ከጥይት ጩኸት ጋር ስለለመድናት፣ ሳይጥሉና ሳይወድቁ የተደረገ ለውጥ እኛ ዘንድ አልተለመደም። ከዚህ የተነሳም ለውጡን ወደለመድነው ተራ ኪሳራ ሊነዱ የሚወዱም አይጠፉም፡፡ የግራው የቀኙ ፍላጎት፣ ሩጫ፣ ጫጫታ፣ ሁካታ ተደማምሮ ለውጡን አላስፈላጊ እንዲሆን፣ አይይይ ከዚህስ ይልቅ ሌላ ተጨማሪ 27 ዓመታትን ለመገዛት እንመርጣልን ብለን ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ እንድንል ሒደቱ ይሞግተናል። ስለዚህ ጉዳይ በሐርቫርድ የቢዝነስ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ሮዛቤት ሞስ ካንተር እንዳሉት፣ ሁሉ ነገር መሃል ላይ ውድቀት ይመስላል። ስለሆነም ሒደቱን ዓይተንና ፈርተን ከሩጫችን ልንቆም አያስፈልግም።
መሪዎች በሚገባ መንገዳቸውን የተረዱ ከሆነ በየመሃሉ የሚንገራገጨው የባቡር ፉርጎ አያስደነግጣቸውም። ስለሆነም መሪዎች መሥመራቸውን አጥብቀው በመረዳት እያንዳንዱን ሒደት አስቀድሞ በመረዳት፣ የተጠና መፍትሔ ለየችግሮቻቸው በአፋጣኝ በመስጠት፣ ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎን በማጠናከር፣ ችግር ፈቺና ኪሳራ አስተዳዳሪ ሥርዓትን በመዘረጋት ወደ ተነሱለት ትልማቸው ሊገሰግሱ ይገባል።
አንዲት አነስተኛ ጠጠር ከኩሬው ላይ ብትወረወር በኩሬው ላይ በሚፈጠረው ማዕበል የተነሳ የሚሠራው ክበባት እየሰፋ እየሰፋ ይሄዳል። እንዲት ትንሽ ጠጠር በመጠኗ ታይታ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳይደለች በመገመት ችላ ልትባል አይገባም፡፡ ጠጠሪቷ መረበሽ የቻለችውን ያህል ተፅዕኖ ትፈጥራለች። እንደ እዚህች ዓይነት አነስተኛ ጠጠሮች ሲደመሩና ሲሰባሰቡ ግን ታላቅ ማዕበልን የመፍጠር ጉልበት ላይ መድረሷ አይቀሬ ነው። ስለሆነም እንደ አገሬ ሰው ሳይቃጠል እንዲሉ ነው ነገሩን በወጉ መመለከት መልካም ነው።
መሪዎች አንድ ችግር ተከስቶ፣ የክስተቱን ቁስል ለማከም ከመድከም ይልቅ ክስተቱ ቀድሞውኑ እንዳይከሰት ማድረግ ቢመርጡ ዘመናቸው የተረጋጋና ቀጣይ ይሆንላቸዋል። በሕክምና ሰዎች ዘንድ በሰፊው እንደሚታወቀው “Prevention is better than cure” በመሆኑም አገር አቀፍ፣ ከተማ አቀፍ፣ መንደርና ጎጥ አቅድ ስልት፣ አደረጃጀት፣ የመረጃ ቅብብሎሽ በማጠናከር በትንሹም፣ በትልቁም ሊከሰቱ የሚችሉን ቀውሶች ከእንጭጩ ሙሉ በሙሉ ማድረቅ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል።
ተንጠልጣይ ተስፋዎች መሪዎች በሥልጣን የመጀመሪያ ዘመናቸው በድል ስካር ውስጥ በመደወቃቸው ሳቢያ ይሁን አልያም ሆን ብለው የሰውን ቀልብ ለመውሰድ ይሁን ብቻ በሆነ አንዳች ሰበብ በርካታ ተስፋዎችን፣ ዕቅዶችን፣ ቃል ኪዳንህን እየማሉ ከማኅበረሰቡ ጆሮ ያንቆረቁራሉ፣ ይኸው የመልካም ምኞታቸውና ሐሳባቸው ውሎ ሳያድር ግን በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታን ይፈጥርባቸዋል፡፡ ለመንገዳቸው ደንቃራ እንቅፋትም ሲሆን ይስተዋላል። ኅብረተሰቡ ምን ‘ፖለቲከ’ኞች ሲባሉ እኮ በመልክ ቢለያዩም እናታቸው አንድ ናት፤ ሁሉም ሥልጣናቸውን እስኪያደላድሉ ድረስ ሆዳችንን በተስፋ ነፈተው ነፍተው ሆዳችን እንደተቀበተተ እንተኛለን፤ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ባሮቻቸው አድርገውናል እንዳይል መታሰብ አለበት፡፡ ማኅበረሰባዊ መተማመንን ማግኘት ለለውጥ መሠረት ነው።
ልባም መሪዎች ተስፋ የሚሰጡትን ጉዳዮች ለይተው የተረዱ፣ ከራሳቸው መስመር ጋር ያስማሙና ያስተካከሉ ጠቢባን ናቸው። እኚህ መሪዎች ሊሠሩዋቸው የሚቻላቸውን ዋና ዋና ዕቅዶቻቸውን ለኅብረተሰቡ በመግለጽና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር በመግባት በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነታቸውን እየጨመሩ፣ ማኅበረሰባዊ መተማመናቸውን እየገነቡ ይሄዳሉ እንጂ የማይፈጽሙ በርካታ አማላይ ቃላት በመደርደር ራሳቸውን ከማኀበረሰቡ ጋር በገዛ ምላሳቸው አይነጥሉም።
በመጨረሻም ለውጥ ሁሉንም እንደማያስደስት እርግጥ ነው። ስለሆነም የለውጥ ሐዋሪያት ሁሉንም ካላሰደሰትኩኝ ዘመቻ ውስጥ ራሳቸውን ከነከሩ ፍጹም ባለድሎች ሊሆኑ አይችሉም። ይህ ማለት ግን አብዛኛውን ሰው ፍርኃት ውስጥ የሚከት፣ ከጥርጣሬና ከጭንቀት የሚዶል እንቅስቃሴ መሆን ግን የለበትም። መሪዎች ሁሉንም ባያስደስቱም አብዛኛው ሰው ግን ሊቃወማቸው አያስፈልግም። ምን አልባት አብዛኛው ማኅበረሰብ የሚቃወማቸው ጊዜ ሲገጥማቸው የነገሩን ምንጭ አንድ በአንድ በመመርመር፣ በመተንተንና በመረዳት ወደ ትክክለኛ መፍትሔና ውሳኔ በፍጥነት በመጓዝ ተቃዋሚዎቻቸውን ሳይቀር ደጋፊ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም የባላንጣዎችን ተቃውሞና ጥያቄ መፍትሔ በመስጠት መጓዙ፣ በተቃዋሚው ጎራ ያለውን በርካታ ሕዝብ እያመነመነ ዝም ማስባል ብቻ ሳይሆን ደጋፊና አጋዥ የማድረጉን ዕድል የመፍጠር አቅም አለውና ተቃውሞን በቸልተኝነት መመለከት አያስፈልግም። ስለሆነም የዛሬዎቹን ተቃዋሚዎችና ባላንጣዎች ደጋፊና ወዳጅ ማድረግ እንጂ የዛሬዎቹን ደጋፊዎች የነገ ተቃዋሚዎች ማድረግ ከብልህ መሪዎች መንደር የሚጠበቅ አይደለም።
(ኢዮብ ክፍሉ ገብረሩፋኤል፣
ከቨርጂኒያ፣ ሰሜን አሜሪካ)