Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአቶ በረከት ስምኦን መልኮች

የአቶ በረከት ስምኦን መልኮች

ቀን:

በአበራ ሳህሌ

እኔ እኮ ነኝ ከመስከረም ጀምሮ ሙግት በሚዲያ እንዲካሄድ በር የከፈትኩት. . . ሚዲያውን እኔ ነበር የምመራው፤አቶ በረከት ስምኦን ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ሸገር ታይምስ

የዓረብ ሳተላይት አስገብቼ በየቀኑ ሰዎቹን እሰማቸው ነበር. . . በረከትም በሩን ብርግድ አድርጎ ሰጣቸው፤ሼክ መሐመድ አላሙዲ ታኅሳስ 2004 ዓ.ም. ሸራተን አዲስ

ጩኸቴን ብትሰሙ. . . ’

የአቶ በረከት ስምኦን ድምፅ በአገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙኃን ይሰማል። ምክንያቱ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የተባለው ድርጅት ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዳገዳቸው መግለጹ ነው።ፓርቲውን ከመሠረቱት አንዱ ሆኜ ክብሬን በሚነካ መልኩ እንዴት በመገናኛ ብዙኃን ይነገረኛልበሚል ሞገዱን አጨናንቀውታል። የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን፣ ሪፖርተር፣ ታዲያስ አዲስ፣ ቢቢሲ አማርኛ፣ የጀርመን ድምፅና አሶሼትድ ፕሬስ የራሳቸውንእውነታካስደመጡባቸው መካከል ይገኛሉ። በዚያውም አዲስ ያወጡትን መጽሐፍ ለማስተዋወቅ ሁኔታውን እየተጠቀሙ እንደሆነ በተለይም የጀርመን ድምፁ ቃለ ምልልስ ያሳያል።

መጽሐፉቸውን ለማንበብ ጊዜውን የቸረ የአዲስ አድማስ መልካም ሳምራዊ፣ ይዘቱ ዘመን ተሻጋሪውን የፍራንክ ሲናትራን “I did it my way”  ያስታውሳል ብሏል። ዜማውሩጫዬን ጨርሻለሁዓይነት ነው። አቶ በረከትየመሞቴ ዜናእጅጉ ተጋኗልካላሉ በስተቀር፣ ሰሞኑን በሚወረውሯቸው ቃላት የፖለቲካ ሩጫቸው እየተገባደደ ገፋ ሲል ደግሞ አጥፍቶ ጠፊነትም ይመስላል።መወሰን የማይችሉ ሰዎች ኃላፊነት የያዙበት” (ኃይለ ማርያም ደሳለኝ)አስነዋሪ ባህሪ” (ታምራት ላይኔ)እኔ እንዳልመረጥ አደረግከኝ ብሎ የሚወቅሰኝ” (ክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን)

ዋናው ተቆጣጣሪ

የአቶ በረከት መግለጫ ዋናው ምፀት ከሩብ ምዕተ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የግል ንብረታቸው በነበረበት ወቅት ከፓርቲያቸው የተለየ ሐሳብእርኩስ ከመአርዮስተብሎ የተዘጋበት ነበር። ቴክኖሎጂ ምሥጋና ይግባውና ሌሎች ሐሳባቸውን ባገኙት መንገድ መግለጽ በመቻላቸው በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ድርሻ አበርክተዋል። ምፀቱ የዚያ ለውጥ የመጀመርያ ተጠቃሚ ራሳቸው አቶ በረከት ስምኦን የቀድሞው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ይፋዊ ባልሆኑ ሹመቶቻቸው ለረዥም ጊዜ የአገሪቱ ሁለተኛ ሰው።

በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እንዲያብብየነበራቸውን ፍላጎት ሳይታክቱ ያስረዱት የቀድሞው ሚኒስትር የሚታወቁት በተገላቢጦሹ ነው። በጉብዝናቸው ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዳይኖር ጠንክረው ሠርተዋል። ቴሌቪዥኑ ላይ መቶ በመቶ ተሳክቶላቸዋል። የሬዲዮና ጋዜጣንም ዕድገት በማደናቀፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ለአንድም የግል መደበኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፈቃድ ሰጥቶ አያውቅም። ፈቃድ ያገኙት ድሮውንም መንግሥት ሊቆጣጠራቸው የማይችሉ በሳተላይት የሚሠራጩ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው።

የግል ሬዲዮዎች በተለይም ኤፍኤም ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር ምናልባትም ከአፍሪካ የመጨረሻው ሳይሆን አይቀርም። ኤፍኤም ሬዲዮ 1980ዎቹ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ተስፋፍቶ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ግፊት 1998 ዓ.ም. ሲጀመር በከፍተኛ ጥንቃቄ ለተመረጡ ሁለት ድርጅቶች ነው የተሰጠው። ያኔ ኬንያና ኡጋንዳ በየሠፈሩ ጣቢያ ነበራቸው። እኛ ኤፍኤም ላይ ስንድህ ዓለም ወደ ኢንተርኔት ሬዲዮ እየተሸጋገረ ነው።  የጋዜጣው ነገር ሌላ ሀተታ ይወጣዋል። የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ በቅርቡ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አቶ በረከትለሚዲያ አካላት ማስታወቂያ በመስጠት ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ እንደ አቶ ከተማ ከበደ፣ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩትንና ሌሎችንየታክስ ጉዳይ ፈልገህ እሰርብለውኝ፤ነበር ብለዋል። በነገራችን ላይ በምርጫ 97 ማግሥት በጅምላ መንግሥት የዘጋቸው ጋዜጦች ትልቁ ችግር ማስታወቂያ ነበር። አዳጋች ቢሆንም አብዛኞቹ ጋዜጦች በሽያጭ ብቻ ነበር የሚተዳደሩት። እርግጥ የፈጠረው ችግር ሙያውን በእጅጉ ተገዳድሯል።

በአገሪቱ የግል ዕለታዊ ጋዜጣ ሳይታይ የኅትመት ዘመን ቀስ ብሎ እያለፈ ነው። ሳምንት ጠብቀው በሚወጡት ጋዜጦች ላይ ያልተፈጸመ አፈና የለም። ሳንሱር የተለያየ መልክ ይዞ መጥቷል። ማተሚያ ቤቶች ለኅትመት ውጤቶቻችው ይዘት ኃላፊነት አለባቸው በሚል የሳንሱር አድራጊነት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ዘመኑን ለማሳየት አንድ ጉዳይ እናንሳ። አቶ መለስ ዜናዊ በነሐሴ 2004 ዓ.ም. በይፋ ማረፋቸው ከመገለጹ በፊት ከወር በላይ ያሉበት ሁኔታ ከሕዝቡ ተደብቆ ነበር። ማንኛውም የመረጃ ምንጭ ነኝ የሚል  ይህንን ጉዳይ ካላስተናገደ ከቁም ነገር የሚቆጥረው አይኖርም። ፍትሕ የተባለው ጋዜጣ ያደረገውም ይህንን ነው። ስለጠቅላይ ኒስት ሁኔታ ያጠናቀረውን ይዞ ኅትመቱን ጨርሶ ከማተሚያ ቤት ሊወጣ ሲልእንዴት ተደርጎ?’ ባዮች ወደ 80 ሺሕ ብር የተከፈለበትን ዕትም አግደውታል።ዛሬ ይገባልነገ ሥራ ይጀምራል’፣ ‘ቀላል የሆድ ሕመም ነውሲባል የነበረውን ጉዳይ የአፍሪካ ኅብረትን ስብሰባ ለመካፈል ከሴኔጋል ድረስ መጥተው ሳያስቡት ንግግር የማድረግ ሸክም የወደቀባቸው ማኪ ሳል የመለስን መታመም ለአገሬው ዜጎች በይፋ ገለጹ። ዱብ እውነታውን ከመጋፈጥ ውጪ የቀረ ነገር እንደሌለ አሳይቷል። አቶ በረከትም ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የአዋጁን በጆሮ ነግረዋል።

እነ አቶ በረከት ማሠራጫውን ሁሉ ተቆጣጥረው እነሱ የማያዙበት ተቋም እንዳይሰማ ባለ አቅም ጥረዋል። የአገሪቱን ፕሬስ ሁሉ ‹Gutter› (ጭር ሲል አልወድም) ሲሉ የቆዩት አለቃቸው፣ የአሜሪካ ድምፅ እንዲታፈን ትዕዛዝ መስጠታቸውን እንደ ትልቅ ስኬት ጋዜጠኛ ጠርተው ነው ያወጁት። አቶ በረከትም ከቪኦኤ ጋር መካረራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሬዲዮ ጣቢያው የአማርኛ አገልግሎት ጋዜጠኞች ከአዲስ አበባ ወጥተው ለመዘገብ ችግር ነበረባቸው። ከወኪሎቹ አንዱ አቶ መለስካቸው አመሐ ተደብድቧል። በሰበብ አስባቡም ወከባና እስር ደርሶበታል። እሳቸውን ከጥቃቱ ጋር ለማያያዝ ለጊዜው ማስረጃ ባይኖርም ዝምታቸው በአርምሞአበጃችሁይመስላል። ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኙትን የሬዲዮው ሠራተኞች በዘር ማጥፋት ወንጅለው አፍ ለማዘጋት ሞክረዋል። በግላቸው ለአሜሪካ ድምፅ ትግርኛ አገልግሎት ካልሆነ መግለጫ አይሰጡም።

አንጋፋው ፖለቲከኛ ፈቃድ ሰጪና ከልካይ ስለነበሩ በውጭ ዜና ድርጅቶች ይፈሩ ነበር። የጀርመን ድምፅ አማርኛ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ሉድገር ሻዶምስኪ በአንድ ወቅት፣አዲስ አበባ በሄድኩ ቁጥር በረከት የሚዘረግፍልኝ ስሞችራስ ምታት ስለሆኑብኝ ኢትዮ ሚዲያን በመሳሰሉ ድረ ገጾች በስማችሁ አትጻፉ፤ሲሉ ለሠራተኞቻቸው በኢሜይል ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል። ለውጭ ጋዜጠኞች የሚሰጥ ፈቃድ የአቶ በረከት ዋነኛ የመጫወቻ ካርታ ነበር። ዊሊያም ዴቪሰን (ጋርዲያንና ብሉምበርግ)፣ ፒተር ሃይንላይን (ቪኦኤ) ጄሰን ማክሉር (ብሉምበርግ) እና ኡማም ዲያክ (ቢቢሲ) በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሰለባ የሆኑ ናቸው። አንዳንዶቹ ፈቃድ አይታደስልንም በሚል ሥጋት ኢትዮጵያ ውስጥ እንግልት እንደደረሰባቸው እንዲታወቅ አልፈለጉም። መታሰራቸው የታወቁትም በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በአገሪቱ ውስጥ ኢሳትንና ኦኤምኤን መከታተል በአዋጅ ነበር የተከለከለው።  ቁጥጥሩ ከመጥበቁ የተነሳ ጣራ ላይ የተሰቀሉ የመቀበያ መሣሪያዎችን አቅጣጫ እያዩ ሰዎችን ማሰር የዕለት ከዕለት ተግባር ሆኖ ቆይቷል።

ምርጫ ቅርጫ

ምርጫ እንዲህ እንደ ዛሬ መቶ በመቶ ሳይሆንጠንካራ ተቃዋሚ ስጠኝየሚለውን የኢሕአዴግን የዘወትር ፀሎት ሰምቶ እግዜሩ ቅንጅትንና ኅብረትን አመጣለት። በረከትም የፓርላማ አባል ለመሆን ተወዳደሩ። ከተወለዱበት ጎንደር ይልቅ የፖለቲካ ውቃቤ ወደመራቸው ሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ ሄዱ፡፡ ሕዝቡ ግን እንዳይሆኑ አደረጋችው። ሽንፈታቸውም በሚቆጣጠሩት ሬዲዮ ሳይቀር የዕለቱ ዜና ነበር። አቶ በረከት ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል በቦርዱ ኃላፊ አቶ ከማል በድሪ የሌት ተቀን ድጋፍ በድጋሚ ብቻቸውን ተወዳድረው እንዲያሸንፉ ተደርጓል። በአፍሪካ የሚገኝ ገዥ ፓርቲ ሲጭበረበር የመጀመርያ የሆነበትእንከን የለሽምርጫ በዩኔስኮ ልዩ ቅርስነት አለመመዝገቡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ያስወቅሳል። የእሳቸው ዓይነት ዕጣ የደረሳቸው የቀድሞ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ጁነዲ ሳዶ ግንምርጫውን ተዘርረናል. . . ምንም የሚያከራክር አይደለም. . . እኛ ያሸነፈው ኦብኮ ነው. . .ሲሉ ከሁለት ዓመት በፊት  ኢሳት ላይ ቀርበው ንሰሐ ገብተዋል። አቶ በረከት ግን ቁስሉን ለማድረቅወግመጻፍ መርጠዋል።

ከምርጫው የተማሩት ትልቅ ነገር ቢኖር ሚዲያውን በካድሬዎች መሙላትና አገሩን በሙሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ፀበል ማጥመቅ ነበር። በግዴታ የተካሄደው ምልመላ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአባላቱን ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን አድርሶታል:: በቅናት ይጠብቁት የነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በአንድ ጀንበርሰላም አስከባሪየሚል ቅጥያ በተሰጣቸውልማታዊ ጋዜጠኞችእንዲጥለቀለቅ አድርገውታል።

በረከተ መርገም

1997 ዓ.ም. በአገራችን የተደረገውን ምርጫ ለመታዘብ የአውሮፓ ኅብረትን በመወከል በኢትዮጵያ መንግሥት ተጋብዘው የመጡት አና ጎሜዝ ባወጡት መግለጫ፣ ምርጫውፍትሐዊ ለመባል ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን አላሟላምየሚል ብያኔ ሰጥተዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወይዘሮዋ የአቶ በረከትና የቀድሞ አለቃቸው የጥቃት ዒላማ ሆነዋል። እንዲያውም ቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመርያ ጊዜ በስማቸው ኢትዮጵያን ሔራልድ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በአውሮፓዊቷ ወይዘሮና በቅንጅት አመራር አባል መካከል የፍቅር ግንኙነት እንዳለ በሚጠቁም መልኩ ”What is love got to do with it” የሚባለውን የቲና ተርነርን ዘፈን በመጥቀስ አሉባልታ ውስጥ ተነክረዋል።

ሰሞኑን አቶ በረከት ለቢቢሲ አማርኛ በሰጡት መግለጫ ፖርቹጋል የአውሮፓ ደሃ አገር በመሆኗ፣ አና ጎሜዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ አስረግጠው ተናግረዋል። የፖርቹጋልን ድህነት ያሰመሩበት ኢትዮጵያ በቅርቡ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደምትሠለፍ የፈጠሩትን ታሪክ እየኖሩበት ስለሆነ ነው። ከተካኑባቸው ማሸማቀቂያዎች አንዱን በመምዘዝ፣የድሮ የፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ ነው. . . እርስዎን አያገባዎትም። አርፈው ይቀመጡ በልልኝየሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቸገረ ነገር. . .

አቶ በረከት የምርጫውን ቁስል ለማሻር ያወጡት መጽሐፍ በሕዝብ ቴሌቪዥን ብዙ የአየር ስዓት ተሰጥቶት ስለተዋወቀ ለማሻሻጥ ብዙም አልተቸገሩም። ብዙ የተወራለት የአገሪቱ ዕድገት የእሳቸውን ሥራ የማተም ብቃቱ ስላጠያየቀ በባለፀጋው ወጪ ባህር ማዶ ታትሞ እንዲመጣ ሆኗል። ምረቃው በሸራተን ሆቴል ድል ባለ ድግስ ታጅቦ የአገሪቱ ታዋቂ አርቲስቶች ቅኔ ዘርፈውለታል። አንድ ሚኒስትር የአገሪቱን ቁጥር አንድ ባለፀጋመጽሐፌን አሳትምየሚልመመርያሲሰጥ ሙስና ካልሆነ ታዲያ ሙስና ምንድን ነው? ይህ አገር በታደመበት ሆቴል በኩራት ያወሱት ኢቴቪም ሽፋን የሰጠው ጉዳይ ነው። አቶ ታምራት ላይኔን ከሼኩአሥራ ምናምን ሚሊዮን ወስዶበሕግ የተፈረደበት ሲሉ፣ የባለፀጋው ኪስ ለእሳቸው ክፍት እንዲሆን ተፈቅዶ እንደነበር አልተገለጸልንም። የሚገርመው ባለሀብቱ ትዕዛዝ የተሰጣችው በነካ እጃቸው የአቶ በረከትን ዘመዶችንም እንዲተባበሩ ነበር።የእኔ ሥራ መጽሐፉን መጻፍ ብቻ ነበር። የእኔንና በቅርቡ አቶ መዝሙር ፈንቴ የተረጎሙትን መጽሐፍ አል አሙዲ እንዲያሳትመው መመርያ ብቻ ነው የሰጠሁትቃል በቃል። ዘፋኙየቸገረ ነገር የጠፋ ለመላያለው ወዶ አይደለም።

ለጠቅ ስንል ደግሞ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊን እናገኛለን። በሙስና ወንጀል ተከሰው አምስት ዓመት በእስር ያሳለፉት አቶ መላኩ ፈንታ ለቢቢሲ አማርኛ እንደገለጹት፣ ከእሳቸው ጋር ግጭት የተጀመረው ይኸው ጣጠኛ ዘመድ ውድ የፊልም ካሜራ አስመጥቶ ያለቀረጥ ሊያስገባ ሲል ነው። አቶ በረከትምንም ጫና አላደረግኩም፣ መክፈል ካቃተህ ይወረስ ብያለሁሲሉ ተደምጠዋል። አንድ ተሽከርከሪ የሚያስገባ ግለሰብ ከዕቃው በላይ የሚያሰላው ቀረጡን ነው። እጥፍና ከዚያ በላይ መክፈል በአገራችን እንግዳ አይደለም። በአሥር ሺሕ ዶላሮች የሚቆጠር ዋጋ ያለው ካሜራ የሚያስገባ የሚተማመንበት ሰው ከሌለ በስተቀር በሚሊየን ነው የሚያስበው።

በረከት ፍሬዎች

አቶ በረከት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን ቦሌ ኦሎምፒያ ይገኝ ከነበረውና በዋናነት የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት አስመልክቶ መግለጫ በመስጠት የታጠረውን ቢሮ፣ ባለ ሦስት ሚኒስትር ጉልበታም መሥሪያ ቤት አድርገውታል።  ጽሕፈት ቤቱ በአገሪቱ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅሩ ሰፍቶ እየተሠራበት ይገኛል። በማኅበራዊ ሚዲያም ጭምር ከቻይና የተቀዳውን የኢንተርኔት ሠራዊት አዘጋጅቶ ትምክህተኞች፣ ጠባቦች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጥገኛ፣ መርህ አልባና ኒዮ ሊበራሎች የሚላቸውን በተግባር ግን ከገዥው ፓርቲ የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሲፈርጅ ባጅቷል። ደኅንነቱ በየሰበቡ አጉሮ የሚያሰቃያቸውን ዜጎች ቴሌቪዥኑጂሃዳዊ ሃረካትአዲስ አበባን እንደ ባግዳድእያለ በተጠርጣሪዎች ላይ ሥነ ልቦናዊ ሽብር ሲነዛ ቆይቷል። ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በጻፈው ጽሑፍ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 55 በመቶ ደርሷል፣ ሚሊየነር ገበሬዎችና የመሳሰሉ ትርክቶችን መፍጠርም የቤቱ አንድ ተልዕኮ ነበር።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከአሜሪካ ድምፅ የተኮረጀ የሚመስል የመንግሥት አቋም መግለጫ ሲያቀርብ፣ በዋናነት ግን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ይቆጣጠራል። ለዚህም እንዲረዳ መሥሪያ ቤቱ ቸርችል ጎዳና ወደሚገኘው የቴሌቪዥን ሕንፃ ገብቷል። ሚኒስትሩ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ የቦርድ መንበር ሲሆን፣ ዴኤታዎቹ የፕሬስ ድርጅትንና ዜና አገልግሎትን ይከታተላሉ። በል ሲላቸው ደግሞ አቶ በረከት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን፣ ቀኝ እጃቸው አቶ ሽመልስ ከማል ደግሞ የፕሬስን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርቡ ነበር። እዚያም የሚሾሙት ለፓርቲው አንገታቸውን የሚሰጡ ታማኞች ናቸው። ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴንንናይዋጣልንየሚሉ የሚመስሉት ጌታቸው ረዳን ማስታወስ ይበቃል። በአንፃሩ ከዚያ በፊት የነበሩት የማስታወቂያ ሚኒስትሮች ገጽታ የራቃቸውና መውጫ በር ላይ የደረሱ ሹማምንት ነበሩ።አቶ በረከት የቀድሞው ቅላይ ሚኒስትር በሞት ሲለዩ ቅጥ ባጣ ሐዘን አገላለጽ አገሪቱን ለሳምንታት ሰሜን ኮሪያን ያስመስሏት እንጂ፣ ከቀብሩ ሥርዓት ጀምሮ አዲስ ቅላይ ሚኒስትር እስከ ማንገሥ ያለውን ሽግግር በብቃት አስፈጽመዋል።

የተደገመ ህልም

በአገራችን 1966 ዓ.ም. አጋማሽ እስከ 1968 ዓ.ም. መጀመርያ፣ ቀጥሎ ደግሞ 1984 እስከ 1986 ዓ.ም. አካባቢ የዘለቀ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ክፍት የነበሩበት ዘመን እንደገና እየታየ ይመስላል። በየክልሎቹ መሪዎችን ሳይሆን ኅብረተሰቡን ለማገልገል የተነሱ ሚዲያዎች ተፈጥረዋል። በማዕከልም ያሉት አማራጭ ድምፆችን እያሰሙ ነው። የሳተላይት ሥርጭቶችም ከመሸጉበት መዝናኛ በመውጣት አቅማቸውን እየፈተሹ ነው። ከፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች ነፃነታቸውን ለመጠበቅ ሲታትሩ ይታያል።  ድምፁ የሚሰማ ማኅበረሰብ ችግሩን ተወያይቶ ይፈታል። የሚነጋገር ኅብረተሰብ የአቶ በረከትንም እሮሮ ለመስማት ዕድል ይሰጣል። አሳዛኙ ነገር ይኼንን ለመረዳት የአንድ ትውልድ ዕድሜ መፍጀቱ ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው    [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...