Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት የውጭ ብድር መፍራት የለበትም›› አቶ ፀደቀ ይሁኔ፣ የፍሊንትስቶን ሆምስ ኩባንያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ

በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ቢዝነስ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙት አገር በቀል ኩባንያዎች ውስጥ ፍሊንትስቶን ሆምስ ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው በተለይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፕሮጀክቶችን በማንቀሳቀስም ይታወቃል፡፡ ፍሊንትስቶን ሆምስ በዚህ ዘርፍ ከአሥር ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን አስረክቧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን በመገንባት ላይ ነው፡፡ የኩባንያው እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን ከአዲስ አበባ ውጪ በተመሳሳይ ሥራ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ አስገንብቶ ከሚያስረክባቸው ቤቶች ጋር በተያያዘ ከደንበኞች ቅሬታዎች ይቀርቡበታል፡፡ በዚህና ሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዩን ተንተርሶ ዳዊት ታዬ የፍሊንትስቶን ሆምስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀደቀ ይሁኔን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የሪል ስቴት ዘርፍ አሁን ያለበትን ደረጃ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ፀደቀ፡- አሁን ያለበትን ሁኔታና አቻምና የነበረውን የሪል ስቴት ሥራ ስንመለከት፣ ለብዙዎች አስቂኝ የሆነ ሥዕል የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ፀደቀ፡- አለመረጋጋትና ግርግር ሲበዛ ሌሎች ሥራዎች ይቀንሳሉ፡፡ በአንፃሩ ግን የሪል ስቴት ገበያ በተለይ እኛ ዘንድ ትንሽ ከፍ ያለ ስለነበር ነው የተለየ ሥዕል የነበረው ያልኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች ቢዝነሶች በተለየ የሪል ስቴት ገበያው ከፍ ያለበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ፀደቀ፡- እኔ ወደ ኋላም መለስ ብዬ እንዳየሁት አንዱ ማስታወቂያ የምናሠራጭበት ሚዲያ ነው፡፡ እኛ ለማስታወቂያ ስንጠቀምበት የነበረው ሚዲያ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው፡፡ ስለዚህ ግርግር ባለበት ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ ሌሎች ሚዲያዎች አድማጭ ተመልካች የሚያገኙ ስለሆነ፣ እኛ ገበያ ላይ ያቀረብነውን ነገር ሰዎች ስለሚያስተውሉ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ብዙ ጊዜ ሰው የያዘውን ገንዘብ ገበያው ያልተረጋጋ ሲመስለው፣ ሊያምን በሚችለው በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ማዋል ስለሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ገበያው ከፍ ያለው በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነው የሚል አመለካከት አድሮብኛል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን ግርግሩ በጀመረ በሁለት ዓመታት ውስጥ ገበያችን በጣም ጨምሮ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ብዙ ፕሮጀክቶች ያሉዋችሁ እናንተ ናችሁ ይባላል፡፡ ምን ያህል ፕሮጀክቶች አሉዋችሁ? በዚህ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ የሚይዘውስ ማነው?

አቶ ፀደቀ፡- የሌሎቹን ብዙ አላየሁም፡፡ ግን በቤት ግንባታ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው መንግሥት ነው፡፡ ከመንግሥት ቀጥሎ በቤት ግንባታ ዘርፍ የሚጠቀሰው ደግሞ የግል ቤት ሠሪዎች ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በማኅበር ወይም በግል የራሱን ቤት የሚሠራው መንግሥት ከሚገነባው ቀጥሎ ያለውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ለረዥም ጊዜ እኔ የማውቀው አያትንና ሰንሻይንን ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁለቱን ተቋማት እኛ ሳንበልጣቸው አይቀርም ብዬ እጠራጠራለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የዳሰሳ ጥናቶችንና የፕሮጀክቶችን ቁጥር ስመለከት እኛ በርከት ያሉ ሥራዎችን እያከናወንን ነው፡፡ እኛ አሁን ወደ ሦስት ሺሕ ደንበኞች አሉን፡፡ ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት አስረክበናል፡፡ ተጨማሪ አሁን የጀመርናቸው ወደ 2,500 የሚሆኑ ቤቶች አሉን፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ አሁን በእጃችን ላይ ልናስረክብ የምኝችላቸው ወደ 4,000 የሚሆኑ ቤቶች አሉን፡፡ እነዚህ በሁለትና ሦስት ዓመታት የምናጠናቅቃቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሁሉም አልተሸጡም ግማሽ ያህሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሪል ስቴት እንደ ድርጅት ለእኛ በተለይ ሰላምና መረጋጋቱ እየሰፈነ በሄደ ቁጥር የሚያጓጓ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በእርግጥ ገበያው ቢኖርም የመሥራት አቅማችንን ግን ተፈታትኖት ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- ገበያው እያለ የመሥራት አቅማችሁ የተፈተነው ለምንድነው? በምን ምክንያት?

አቶ ፀደቀ፡- የመሥራት አቅማችን የተፈተነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ መሠረታዊ ግብዓቶች የምንላቸው ለመነሻ መጀመርያ ውቅሩን የምንሠራባቸው እንደ ብረት፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉት ግብዓቶች እጥረት ስለነበረ ነው፡፡ በተለይ ብረት በጣም ችግር ነበር፡፡ አሸዋም እንዲሁ ችግር ነበር፡፡ በኋላ ዋጋው በጣም ናረ፡፡ ቢኖርም እንኳን ኮንትራታችን የታሰረ በመሆኑ ዋጋ አንጨምርም፡፡ ኮንትራታችን ከዋጋ መናር ጋር አብሮ ስለማይቀየር የመሥራት አቅማችንን በመፈታተኑ ብዙ አልሠራንም፡፡ ልንሠራ ከሚገባን 20 በመቶውን እንኳን ለመሥራት አላስቻለንም፡፡ በተለይ በ2010 ዓ.ም. መሥራት የነበረብንን ያህል አልሠራንም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውቅር ጨርሰን ሊጠናቀቁና ልናስረክባቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ እነሱ ላይ ደግሞ የኤሌክትሪክ ሥራ ከውጭ የሚመጡ እንደ ሊፍት የኩሽና ዕቃዎችና የመሳሰሉት በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በዋጋ መወደድና በመሰል ምክንያቶች ለመሥራት አልቻልንም፡፡ ቀጥ ነው ያደረገን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ቀድመው አነሱት እንጂ ከደንበኞቻችሁ ቤቶችን ቶሎ ባለማስረከባችሁ ቅሬታ እየቀረበብዎት ነው፡፡ ደንበኞች ቅሬታቸውን አቤት ለማለት ፈልገው እርስዎን ለማነጋገር ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ይገልጻሉ፡፡ ልናገኛቸው አልቻልንም፣ አያነጋግሩንም የሚል አቤቱታ እየቀረበብዎት ነው፡፡

አቶ ፀደቀ፡- በእውነት የምናስደስተውና የማናስደስተውን ሰው በሚዛን አስቀምጠህ እይ ብትለኝ፣ በእጅጉ የምናስደስተው ሰው ይበልጣል፡፡ ግን በቁጥር እያንዳንዱ ሰው ራሱን ችሎ የራሱ ኮንትራት ያለው ስለሆነ፣ ከብዙ ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው እንኳን ብናስከፋ ድርጅቱና ያ የተከፋው ሰው እኩል ቦታ ነው ያላቸው፡፡ እኛ መቶ በመቶ ሰውን ማስደሰት ነው ግባችን መሆን ያለበት፡፡ ይህንን የምናደርግበት መንገድ ደግሞ ሦስት ነው፡፡ አንዱ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ነው፡፡ ሁለተኛው ከደንበኛ የምንሰበስበውን ዋጋና የምንሠራውን ሥራ ማመጣጠን ነው፡፡ የማንሠራ ከሆነ ገንዘብ አለመቀበል ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው በሚጠበቀው ልክ ጥራቱንና ደኅንነቱን አስጠብቀን ሕንፃውን ማስረከብ ነው፡፡ ሦስቱንም ካላሟላህ ደንበኛው አይደሰትም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የጠቀሱልኝ ዓይነት ችግሮች እንዳሉ የሚናገሩ ደንበኞች አሉ፡፡ በጥራት ሠርቶ በቶሎ አለማስረከብና የመሳሰሉት ችግሮች ይሰማሉ፡፡

አቶ ፀደቀ፡- ችግሩ በሦስቱም ውስጥ ነው ልልህ ነው፡፡ ስናስከፋቸው በሦስቱም ውስጥ ነው፡፡ ስናስረክባቸው በምናስረክባቸው ቤት ሙሉ አለመሆን የሚከፉ ሰዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ደንበኞቻችሁ መረከብ ያለባቸው የተሟላ ቤት መሆን ሲገባው የማይሟላበት  ምክንያት ምንድነው?

አቶ ፀደቀ፡- አንዱ የሚጠበቀውን ያህል በጥራት አለመሥራታችን ነው፡፡ አገራዊ አቅማችንን ተከትለን ነው የምንሄደው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ቃል የምንገባውና አቅማችን ይፈተሻል፡፡ የባለሙያውም ሆነ የእኛም የአስተዳደር ችግር ወቅቱን ባልጠበቁ ግዥዎች ያልተጠበቁ ነገሮች ሲፈጠሩ፣ በኢኮኖሚው ላይ ለሚመጡ ንዝረቶች የምንሰጣቸው ምላሾች ከምንጠብቀው ያነሰ እንድናደርግ ያደርጉናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሚጠበቀው በላይ የምንሠራው አይቆጠርም፡፡ ከሚጠበቀው በላይ የተሠራለት ወጥቶ እንዲህ  ተሠራልኝ ብሎ አይናገርልህም፡፡ ከሚጠበቀው በታች ያገኘው ስለሆነ  በጣም ጉልህ ነገር ባይኖርም መከፋት መኖሩ አይቀርም፡፡ የእኛ ሥራ ያንን የተከፋ ሰው በቅጡ ማስተናገድና መከታተል ነው፡፡ አሁን እንዳልከው በቀጥታ እኔን በተመለከተ ልናነጋግረው ፈልገን አይገኝም የሚል አቤቱታ ይመጣል፡፡ እውነት ለመናገር የበለጠ ፋይዳ ያለው የሚመስለኝ በተደራጀ መንገድ ማስተናገድ ነው፡፡ እኛ የቤት ባለቤቶቹን መጀመርያ እንዲደራጁ እናደርጋለን፡፡ መጀመርያ ባለቤቶቹን የማደራጀት ሥራውን እኔ  ነኝ የምመራው፡፡ ምክንያቱም በተናጠል ያሉ ደንበኞች በአካባቢው ያሉትን ደንበኞች በሚወክል ሁኔታ ተደራጅተው ከእኛ ጋር ካልገጠሙ፣ ለየብቻ ተመጣጣኝ መሆን ስለማይቻል ነው፡፡ እኛ ካለን ገንዘብና በሥራ ላይ ከሚኖረን ተፅዕኖ አንፃር ከእኛ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ጉልበት የሚኖራቸው ተደራጅተው መሆኑን ሲያምኑ እናደራጃቸዋለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ከመጀመርያው ነው፡፡ ስለዚህ እኔን በቀጥታ ከሚያገኙኝ የእነሱ ውክልና ያለውን አካልና ፈጻሚውን ማነጋገር ይቻላል፡፡ ዕድሜ ለደንበኞቻችንና ድርጅታችን ትልቅ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ጥንካሬያችን ደንበኞቻችን ከሆኑ እነሱን አጠናክረን ድርጅቱን ከሚመሩት ሰዎች ጋር የሚገናኙበትን አመቺ መድረክ መፍጠር ነው በሚል ይህንን አሠራር የተገበርነው፡፡ ይህንን ተስማምተን እንዲተገበር እያደረግን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እዚያ ውስጥ ገብቼ የማደርገው ተፅዕኖ አነስተኛ ነው፡፡ እርግጥ በኢሜይል እከታተላለሁ፡፡ ቴክስት ሲያደርጉ ስልኬ ክፍት ስለሆነ አያለሁ፡፡ የበለጠ ተፅዕኖ ማድረግ ያለብኝ የድርጅቱ አመራርና ኃላፊዎች ሊያደርጉ የሚገባውን ነገር ማስተማርና መግለጽ ነው፡፡ ለዚህ ቦዝኜ አላውቅም፡፡ እጽፋለሁ፡፡ ሪፖርቱን አነባለሁ፡፡ እንደገና ደግሞ ከፍተኛ አቤቱታ ሲኖር የእኛን ኃላፊዎችና በተናጠል አንዳንድ ሰዎችንና የተደራጁት ማኅበራት አመራሮችን እያገኘሁ፣ ደግሞ ራሴን እንደ ዳኛ በማድረግ ሁለቱ ሙግት ሲገጥሙ እኖራለሁ፡፡ በጣም የሰነፉ ኃላፊዎች ሲኖሩ ኃላፊዎቹን ማንሳት፣ የእነሱንም ኃላፊነት ራሴ ተሸክሜ እስከ መሥራት ድረስ እሄዳለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- ሌሎች ቅሬታዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ቤቶቹን የተረከቡ ደንበኞች ካርታ አይሰጠንም የሚሉት አንዱ ነው፡፡ ደንበኞች ቤታቸውን ከተረከቡ በኋላ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ከፍተኛ ቅሬታ ይቀርባል፡፡ መብራትና ውኃ የሌለው ቤት ውስጥ ለመኖር ተገደናል የሚል ቅሬታም እየቀረበባችሁ ነው፡፡

አቶ ፀደቀ፡- መሠረተ ልማት በ721/2004 (የሊዝ አዋጅ) መሠረት መጀመርያ መሠረተ ልማቱን አልምቶ ነው ማስረከብ ያለበት ይላል፡፡ መሠረተ ልማት የተሟላባቸው አካባቢዎች ላይ የምንገዛቸው የመሀል ከተማ ሳይቶች ችግሮች የሉባቸውም፡፡ ከመሀል ከተማ ራቅ ያሉት ቦታዎች ላይ ግን አሁንም ቢሆን የከተማው አስተዳደር መሬቱን አስረክቦ፣ መሠረተ ልማት ሳይኖራቸው የተረከብናቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ጭቅጭቅ እንዳይመጣ ቀድመን ነው ለመንግሥት የምንናገረው፡፡ ይኼ የእኛ ኃላፊነት ሳይሆን የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን ደንበኞቻችን የተካተቱትም ቢሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ራሳችን ጄኔሬተር አዘጋጅተን መብራት እስኪገባ ድረስ ኃይል እናከፋፍላለን፡፡ ነገር ግን ይህ ከአቅም በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ከተገኘችው ትርፍ ለመጠባበቂያ ከተያዘችው ላይ ነው ይህንን የምናደርገው፡፡ ግዴታችን ባልሆነበት ሁኔታም ይህንን እናደርጋለን፡፡ ስለተሸከምነው የገበያ ኃላፊነት ነው እየሠራንበት ያለነው፡፡ እዚህ ላይ ግን በአብዛኛው ቤቱን የያዙት ወይም ውስጡ የሚኖሩት ደግሞ ተከራዮች ናቸው፡፡ ተከራዮቹ ደግሞ በእኛና በቤቱ ባለቤቶች መካከል ያለውን ውል አያውቁም፡፡ ስለዚህ ብዙ ተከራዮች ናቸው ይህንን ቅሬታ የሚያቀርቡት፡፡ ነባሮቹም ቢሆኑ ያማርራሉ፡፡ ምሬታቸው ግን ከመንግሥት ፖሊሲና ሕግ ጋር የተዛነፈ እንደሆነ፣ በኃላፊነት የሚጠይቁት እኛን መሆን እንደሌለበት በተደጋጋሚ እናስረዳለን፡፡ ይህንንም ብለን ግን አልተውነውም፡፡ አስተካክለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ደንበኛ ቤት አገኘሁ ብሎ ሲገባ መብራትና ውኃ ከሌለው ይደነግጣል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያልተቻለው ለምንድነው? ከካርታ ጋር በተያያዘ የሚቀርበው አቤቱታም ቢሆን በተደጋጋሚ የሚነሳ  ጉዳይ ሆኗል፡፡ ብዙ ደንበኞች ለተረከብነው ቤት ካርታ ልናገኝ አልቻልንም እያሉ ነው፡፡ እነዚህን አቤቱታዎች እንዴት ነው የሚያዩዋቸው?

አቶ ፀደቀ፡- በካርታ አሰጣጥ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ለረዥም ጊዜ የቆዩ የቪላ ቤቶች ጉዳይ አለ፡፡ ካርታ ከተጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚያስረክብ ድረስ ያንን የሚፈጽመውን አካል ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት የለም፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የካርታ ፍላጎትና አቅርቦት ውስጥ ብዙ ሰው የሚያማርረው ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእኛን የተለየ የሚያደርገው በአንድ ጊዜ ብዙ ፋይል ስለሆነ ይዘን የምንሄደው፣ 200 ወይም 300 አንዳንድ ጊዜ 500 ካርታ ይዘን ስንሄድ የምናገኘው መስተንግዶ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሥልጠና ሲገቡ፣ ስብሰባ ሲቋረጥ፣ አንድ ሰው በሹመት ሲዛወር እሱ የጀመረውን ሥራ ሌላው ስለማይቀጥለውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ደንበኞቻችን ብዙ ተበድለዋል፡፡ ማኅበራት ሳይቀሩ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሄደው እየተማረሩ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ጥረዋል፡፡ እኔም አመራሩ ድረስ በመሄድ እየለመንኩም ጭምር ያስፈጸምኳቸው ነገሮች አሉ፡፡ በአንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች ምክንያት እንደናቀፋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ፀደቀ፡- ለምሳሌ የቪላ ቤቶችን ካርታ የሚመለከት ነው፡፡ ቪላ ቤቶች መጠናቸው ከ500 ካሬ ሜትር በላይ ስለሆኑና በመመርያው መሠረት በሊዝ ውስጥ ስለሚካተቱ እንዴት እንደሚስተናገዱ አይታወቅም ተብሎ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚጠብቁ  አሉ፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ከ500 ካሬ ሜትር በላይ ይዞታ ካለው በሊዝ ይካተታል ይላል ሕጉ፡፡ ይህ ቀድሞውኑ በሊዝ የተካተተ መሬት ውስጥ ከ500 ካሬ ሜትር በላይ ሲሆን ግን እንዴት አድርጎ እንደሚፈታው ፈጻሚው አያውቀውም፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ እንደገና መመርያ ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን አሁን ከግንዛቤ ተነስቶ መመለስ ይቻላል፡፡ መጀመርያውኑ የሊዝ ይዞታ ውስጥ ነው፡፡ የጋራ ይዞታው 500 ካሬ ሜትር የሚለው ነገር አመላካች የሆነ ነው እንጂ፣ በመሬት ላይ ሲሠራ ቅርፁ ከ520 ወደ 480 ሊያደርገው ይችላል፡፡ አካባቢው በሊዝ የተካተተ ስለነበር አሁን ካርታ በሚሸነሽንበት ጊዜ እንደ አዲስ ሊዝ አይወጣለትም፡፡ አሁንም ቢሆን ለሚቀጥለው የሊዝ በሙሉ ተከፍሎ ነው የሚያልቀው፡፡ እነዚህን ሰዎች እኛ አልሚዎቹ የሊዝ ከፍለን ነው የምናስረክባቸው፡፡ ስለዚህ አዲስ የሊዝ አዋጅና አዲስ የሊዝ ዘመን ሲመጣ የሚነሳ ጥያቄ እንጂ፣ አሁን የሚነሳ ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህንን እየተሟገትን ሁለት ዓመት ቆይተናል፡፡ አንዳንዱ ነገር ፈጻሚው ይህንን ካርታ ሠርቶ አጠናቅቆ ማስረከብ ያለበት አካል ለሕዝብ አቤቱታ ተገዥ፣ ወይም በሕዝብ አቤቱታ ብዛት የሚጠየቅ እንዲሆን፣ የሚያደርግ ሥርዓት ከሌለ በእኛና በደንበኞቻችን መስተጋብር ብቻ ይፈታል ብዬ አላስብም፡፡  በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ራሱ መስተካከል ያለባቸው ችግሮች አሉ፡፡ ግን ሰው የሚያየው እኛን ነው፡፡ እኛም በአንድ በኩል ሥርዓቱን ማስጠበቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ መረጋጋት ጠቃሚ ነው፡፡ የመንግሥት ተዓማኒነት እኛንም ተዓማኒ ስለሚያደርግ፣ እኛ መንግሥትን ያን ያህል አፋጠን አናጋልጠውም፡፡ ምክንያቱም የመንግሥትን ችግር እንረዳለን ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነቱን ስንሸከም የደንበኞቻችን ችግር የእኛ ችግር ነው ብለን እንጂ፣ በውላችን ወይም በሕግ ተደንግጎ የተቀመጠ ኃላፊነት አለብን ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እየገለጹልኝ ያሉት ችግሮች መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ የሪል ስቴት ደንበኞች ውኃና መብራት የሌለበት ቤት እንዳይገቡ፣ በአግባቡ የየራሳቸውን ካርታ እንዲያገኙ ምን መደረግ አለበት? ይህ ክፍተት የመንግሥት ነው? ወይስ የእናንተ የአልሚዎቹ ነው ብለን እንውሰድ?

አቶ ፀደቀ፡- መጀመርያ ዋናው ነገር አሁንም ቢሆን እኮ የምናስደስታቸው የሪል ስቴት ደንበኞች፣ መንግሥትም ቤት የሚያቀርብላቸውና በአጠቃላይ የቤት ፈላጊዎች ቁጥር ምንም አይገናኝም፡፡ አሁንም ላለው አቅርቦት በጣም የሚጓጉ ሌሎች አሉ፡፡ ምነው ይኼ ቢኖረኝ የሚሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው መሠረታዊ ነገር ያለውን አቅርቦትና ፍላጎት የሚያጣጥም የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት አለ ወይ ነው? ይህ መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡

 ሪፖርተር፡- ስለሪል ስቴት ልማት ሲታሰብ የመሬት አቅርቦት ጉዳይ ቀድሞ ይነሳል፡፡ ለሪል ስቴት የሚሆን የመሬት የለም እየተባለ የግለሰቦችን ቦታ እየገዙ እዚያ ላይ ያለማሉ፡፡ በመሬት አቅርቦትና በሪል ስቴት ወይም በሊዝና ሪል ስቴት ዙሪያ ያለው ክፍተት ምንድነው?

አቶ ፀደቀ፡- እኛ በብዛት በሊዝ አግኝተን አይደለም የምናለማው፡፡ በሊዝ ያሸነፍነውንም መሬት በሙስና ነጥቀውናል፡፡ ልደታ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ነጥቀውን ለነጋዴዎች ሰጥተዋል፡፡ በሆነ ግርግር ገፍተው አስወጥተውን 16 ሚሊዮን ብር የገዛነውን ነጥቀውናል፡፡ እስካሁን በሊዝ ያገኘናቸው ቦታዎች አራት ናቸው፡፡ ከአራቱ ውስጥ አንዱን ተነጥቀናል፡፡ በእርግጥ በሊዝ ቦታ ያገኙ ሰዎችን ሸሪክ አድርገን የሠራናቸው አሉ፡፡ ሁለት ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ግን ትልቁ ነገር ከመንግሥት ጠባቂነት የሚገኘው ነገር ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡ ያለውን ሀብት አሟጠን መጠቀም አለብን፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዴት ያለውን ሀብት ነው አማጦ መጠቀም የሚቻለው? ኅብረተሰቡ ምን አለው?

አቶ ፀደቀ፡- በተለያዩ ሥፍራዎች ባለፉት ሥርዓቶች በነበረው የመሬት ሥሪት ምክንያት ቀድመው ሰፋፊ ቦታዎችን የያዙ ቤተሰቦች አሉ (አንዱም እኔ ነኝ)፡፡ በእነዚህ ሥፍራዎች የተያዙት መሬቶች መጠንና አሁን የሚፈለገው የሕዝብ ምጣኔ  አይገናኝም፡፡ ስለዚህ መጠጋጋቱን እያስተካከልን መሄድ አለብን፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አነስተኛ መጠጋጋት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ይፈልጋል፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ትስስሩ እያየን የምናስተካክለው ነገር ነው፡፡ አሁን ማስተር ፕላኑ ሠርቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- የሪል ስቴት አልሚዎች በአብዛኛው ከሚወቀሱባቸውና ከሚተቹባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ ገንብተን እናስረክባለን ብለው በሚያስቀምጡት የጊዜ ገደብ አለማጠናቀቅ ነው፡፡ ይህ በሁሉም ላይ የሚታይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለግንባታዎች መዘግየት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው? ደንበኞች በዚህ ጉዳይ ይማረራሉ፡፡ ችግራችሁ ምንድነው? ይህንን ለመለወጥ ለምን አልተቻለም?

አቶ ፀደቀ፡- አሁን የምንነጋገረው እኮ ብዙ እጥረቶች ባሉበት ኢኮኖሚ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ለምሳሌ መንግሥት በፕሮግራሙ መሠረት በዓመት 30 እና 40 ሺሕ ቤቶች ነው ለመሥራት ያሰበው፡፡ ስንት ነው ያስረከበው ስትል 975 ቤቶች ነው፡፡ ይህ በአምስት ዓመት ነው፡፡ መንግሥትን ያህል ነገር ይህ ሀብት እያለው ነው 975 የ40/60 ቤቶችን በአምስት ዓመት ያስረከበው፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የግል አልሚ የተሻለ ነው እየተባለ፣ በዚህ ላይ መንግሥትን ማነፃፀሪያ ማድረግ እንዴት ይቻላል? የግሉ ዘርፍ ትርፍ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ቶሎ ሠርቶ የማስረከብ ዕድል ሊኖረው አይገባም ነበር?

አቶ ፀደቀ፡- በእነዚህ የ40/60 ፕሮጀክት ቤቶች መንግሥት ባለቤት እንጂ ሥራውን እያከናወኑ ያሉት የግል ኮንትራክተሮች ናቸው፡፡ እኛም እኮ የክራውንን የ40/60 ፕሮጀክት ሠርተናል፡፡ የክራውንን የ40/60 ፕሮጀክት ስንሠራ የሚያሠራን አካል ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ምንድን ነበር? ነው ጥያቄው፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ትንሽ ነች፡፡ ገበያ መር አይደለም፡፡ መንግሥት ወደ ኋላ የሚቀርበት ምክንያት እኛን ወደ ኋላ የሚያስቀረን እንደሆነ መጀመርያ ሁላችንም መረዳት አለብን፡፡ መንግሥት ከሌሎች አምራች ዘርፎች የሰበሰበውን ገንዘብ ተፎካካሪ ባልሆነበት ጉዳይ፣ ወይም በሪል ስቴት ልማት  ውስጥ ይገባና ያለ ፉክክር ገበያውን ያጨናንቃል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ፀደቀ፡- ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ዋዜማ በቢሊየን ብር የሚገመት ብረት ገዛ፡፡ ለምን እንደገዛው ዓላማውም አይታወቅም፡፡ የምጠረጥረው ግን ሙስና ነው፡፡ ብረቱን ገዝቶ ምንም አላደረገውም፡፡ ይህ በመሆኑ ግን ብረት ‹‹ሽው›› ብሎ ጠፋ፡፡ ብረቱን አልተጠቀመበትም፡፡ እኔ እንደሰማሁት 20/80 እና 40/60ን በቶሎ ጨርሱ ስለተባለ ነው፡፡ ነገር ግን ያልገባውን ብረት ሳይቀር ነው ገና በመረከብ ላይ እያለ አየር ላይ ነው የሸጡት፡፡

ሪፖርተር፡- ለማነው የሚሸጡት? ገዥውስ ማነው?

አቶ ፀደቀ፡- ገዥው የቤቶች ልማት ነው፡፡ ሻጩ ብረት ነጋዴው ነው፡፡ አንድ ወቅት ደግሞ ዶላር 30 በመቶ በጨመረበት ወይም የብር የመግዛት አቅም በ30 በመቶ በወደቀበት ወቅት (እ.ኤ.አ. 2010) በማኅበር ተሰብስበን የብረት ዋጋ እንዳይጨምር፣ ቢጨምር እንኳ በገባው ብረት ላይ እንዳንጨምር፣ አዲስ የሚገባውም ላይ 30 በመቶ ልዩነቱን እናውጣና እንስማማ፣ የዶላር ልዩነቱ 50 በመቶ ከሆነ የ50፣ ለ30 በመቶ 15 በመቶ ነው ብለን በዚህ ተስማምተን መግለጫ አወጣን፡፡ በጎን ሄደው የመንግሥት ዕቃ ገዥዎች ከተማ ውስጥ ያለውን ብረት በሙሉ ገዙና አስገቡ፡፡ የገዙትም በውድ ዋጋ ነው፡፡ ይህንን እንዴት ብለህ መታገል ትችላለህ፡፡ ልክ ነህ ግን [የግል ዘርፍ] ቀልጣፋ ልትሆን ትችላለህ፡፡  መንግሥት ቀልጣፋ ከሆነ ደግሞ በምን ዓይነት ቅልጥፍና ነው ላሸንፈው የምችለው? መጀመርያ እኮ ችግሩ ይህ ነው፡፡ የግል ዘርፍ ቅልጥፍና የሚሠራው መንግሥት የሚያገለግለው ሕዝብን ከሆነና በሕዝብ የተለያዩ አጀንዳዎች ሲጠመድ እኛ መጠቀም እንችላለን፡፡ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ መንግሥትን የተቆጣጠረ አንድ ኃይል አለ፡፡ እሱ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ይዘርፋል፡፡ እኛ የሕዝብን ፍላጎት ይዘን በገበያ መር እንንቀሳቀሳለን ነው የምንለው፡፡ በዚያ ውስጥ እኛ ምንም ማሸነፍ አንችልም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሪል ስቴት ልማት አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ ግለሰብም ሲታሰብ ሊኖር የሚገባው ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አቅማቸው ይፈቅዳል የተባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ስለሚያደርግ ጠቀሜታው ግልጽ ነው፡፡ ግን ከሪል ስቴት ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ችግር በማስታወስ ደንበኞች አሁንም ያማርራሉ፡፡ እንዲህ ከዘገየብን ዕጣ ፈንታችን እንደ ሌላው ይሆናል ይላሉና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች እንዳይፈጠሩ በስምምነታችሁ ውስጥ የሚካተት ነገር አለ?

አቶ ፀደቀ፡- ደረጃውን የጠበቀ የግብይት ሥርዓት ስለሌለ እያንዳንዳችን ለደንበኛው የምንሰጠውን ጥቅም፣ ወይም በጎ ነገር እያንዳንዱ ደንበኛ አውቆ ይመርጠናል፡፡ ስለዚህ የምንዳኘው በገበያ መጠናችን ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ሪል ስቴትን ለማጭበርበር የሚቻልበት የለም፡፡ በሪል ስቴት ማጭበርበር አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት? ማረጋገጫውስ?

አቶ ፀደቀ፡- ብዙ ሰው በመጎዳቱ ምክንያት የሚጠይቀውን ነገር ስለሚያውቅ ማለቴ ነው፡፡ መብቱን ያውቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደኛ የሠራ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ አባባልዎ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱልኝ ነገር አለ?

አቶ ፀደቀ፡- ለምሳሌ ድረ ገጻችን ላይ ዲዛይንንና ካርታን ማረጋገጥ፣ ቦታን ሄዶ ማየት፣ ውሉ ውስጥ ያሉትን ማወቅ፣ ወዘተ. ማስቀመጥ ድረስ እንሠራለን፡፡ ይህ እንደ መነሻ ሆኖ ሌሎችም ሰዎች ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቢሆን ይታለላሉ፡፡ የሚታለል ሰው አይጠፋም፡፡ ነገር ግን ብዙዎች የፍሊንትስቶን ኮንትራትና የግዥ ደኅንነት የምንላቸውን መሥፈርቶች በማወዳደር አይ ከነሱ ጋር ብንሠራ ይሻላል ብለው ይመርጣሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ይህንን መንግሥት ማድረግ አልቻለም፡፡ መንግሥት ቤቶች መገዛት ያለባቸው እንዲህ ነው ብሎ ሕግ አላወጣም፡፡ ግን ይህንን በተመለከተ በተሰናዳው ረቂቅ ላይ ተነጋግረን ጨርሰናል፡፡ አራት ዓመት ይሆነዋል፡፡ አንድ ዘርፍ እኮ አስተዳደር ይፈልጋል፡፡ አስተዳደሩ ደንበኞችን የሚጠብቅ መሆን አለበት፡፡ የቆርቆሮ ስታንዳርድ አለ አይደለም? ለምን የቤት ስታንዳርድ አይኖርም? ለነገሩ ቆርቆሮውም ቢሆን በተሰጠው የጥራት ደረጃና መሥፈርት መሠረት ተመርቶ መውጣቱን እኮ በቅጡ አይከታተሉም፡፡ ስንት የውሸት ቆርቆሮ ይሸጣል፡፡ አሁን ዋናው ነገር ገበያውን ከመቆጣጠር ይልቅ ገበያውን ለብዙ ተሳታፊዎች እንዲመች ማድረግ ነው፡፡ ለብዙ ቅሬታዎችና ደንበኞች እንዲመች ካደረግከው ዋጋ የማውረዱ ነገር ይቀጥላል፡፡ የሪል ስቴት ችግር ብዙ ተፎካካሪዎች አለመኖራችን ነው፡፡ ሌላ ቦታ ብንሄድ የመጀመርያው ችግር ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ እንዲህ ከሆነ ተፎካካሪዎቹ ላለመኖራቸው ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ፀደቀ፡- ተፎካካሪዎች እንዲበራከቱ ለምሳሌ መሬት እንዴት አድርጎ ማግኘት የሚቻልበትን ነገር ማቅለል፣ ሥራውን ለመጀመር የሚያስፈልገውን ካፒታል ቀላል ማድረግ፣ በየቦታው ያሉና በከተሞች በመሬት ሥሪትና ማኔጅመንት ምክንያት ማዕቀብ የተጣለባቸው ማነቆ የሆኑ ነገሮችን ነፃ ማውጣት፣ የመሬት ግብዓትን ማብዛት፣ እንዲሁም አልሚዎችን ማብዛት ነው፡፡  ዋናው ሥራ ማነቆ የሆነውን ነገር አላልቶ ብዙ ሰው እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ነገርማ ባለሙያው ይሠራዋል፡፡ እዚህ አገር ግን የንብረት ገበያ ታንቆ ያለ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት  ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሥራት አለበት፡፡ በተደጋጋሚ ዴሞክራሲ የምለው ብዙ ሰው ማስደሰት ስላለበት ነው፡፡ አለበለዚያ በየአምስት ዓመቱ የተከፋ ሌላ ሰው ይመርጣል፡፡ ተረጋግቶ እንኳን የሚቆይ ሰው የለም፡፡ ግን ለአምስት ዓመት ይመጣና ጠራርጎ በልቶ ይወጣል፡፡ ሌላው ይመጣል፡፡ ያኛውን ያባርራል፡፡ እንኳን ፓርቲ ሪል ስቴት ኩባንያዎች ሳይቀሩ ስማቸውን ቀይረው ይመጡ የለም?

ሪፖርተር፡- መቼም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎችን በስፋት የሚያነጋግር ነገር አለ፡፡ ይህም ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንደ ሪል ስቴት አልሚ፣ እንደ ቢዝነስ ሰውና እንደ ባለሙያ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የለውጥ ሒደት እንዴት ይመለከቱታል? ከተገነዘቡት አንፃርስ ሒደቱ እንዴት መሆን አለበት የሚል እምነት አለዎት?

አቶ ፀደቀ፡- እኔ ከዚህ ከሪል ስቴት ጋር በተገናኘ ብነግርህ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ የሰላምና መረጋጋት ዕጦት ነበር፡፡ ይህንን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከማስተካከል አልፎ ለሕዝብ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ድርጅትና መንግሥት፣ ብዙ ነገሮች መጀመርያ ላይ ከቅጡ የወጣ የሚመሳስል የሚያስደነግጥ ነገር ቢኖራቸውም፣ አዲሱን ዓመት በተረጋጋ ሁኔታ እየጀመርን ነው፡፡ ይኼ በራሱ እንደ ሕዝብ ልንኮራበት የሚገባ ድርጅትም ሊመሠገን የሚገባበት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም ሊደነቅበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እንዴት ይቀጥላል? የሚለውን ድርጅቱም መንግሥትም እየሠሩበት እንደሆነ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንሰማለን፡፡ የእኛ ድርሻ ባለንበት ሙያ የምናውቀውን ነገር ለኅብረተሰቡ ይበልጥ ይጠቅማል ብለን ለምናስባቸው አካላት ማጋራት፣ የማይጠቅሙ ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች ደግሞ መቃወም፣ በጉልህ ይኼ ነገር ተገቢ አይደለም ብሎ መናገር ነው፡፡ ይህ ነው የሚጠበቅብን፡፡ እኔ በበኩሌ እሱን ነው የማደርገው፡፡ በተለይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በተመለከተ ብዙ የተዘነጉ ጉዳዮች ስላሉ እሱ ላይ ማተኮር አለብን፡፡ 

ሪፖርተር፡- በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ብዙ ትኩረት ያልተሰጣቸው ወይም የተዘነጉ ጉዳዮች ብለው የሚያስቧቸው የትኞቹን ነው?

አቶ ፀደቀ፡- ለምሳሌ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የሎጂስቲክስ ጉዳይ ትልቅ ክፍተት የሚታይበት ነውና እሱን መቀነስ አለብን እየተባለ፣ አሁንም ክፍተቱ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ የበለጠ ውድ እየሆነብን ነው፡፡ እንደ ደረቅ ወደብና ጂቡቲ ወደብን እንደ ራሳችን እየተጠቀምንበት ነው፡፡ በሐርጌሳ በኩልም እንጠቀማለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ህብር መደረግ አለባቸው፡፡ ይኼ ዘርፍ በትልቅ አዕምሮ አንድ አሥር ኤክስፐርቶች ተሰብስበው የሚመሩት ነገር ነው፡፡ ይኼ ዘርፍ በወሬ የሚሳካ አይደለም፡፡ የተሻለ አዕምሮ ያላቸው ተሰባስበው ነው የሚሠሩት፡፡ ይኼ ከጥንት ጀምሮ ያለ ነገር ነው፡፡ ይኼ የሚያስብ፣ ወደ መሬት አውርዶ ለሕዝቡ የሚያስረዳ አዕምሮ ያስፈልጋል፡፡ መናኸሪያ ብቻ አይደለም መሠራት ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሎጂስቲክስና ተያያዥ ጉዳዮችን ካነሱ ዘንድ ከሰሞናዊ ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንድ ጥያቄ ላነሳ እፈልጋለሁ፡፡ ከወቅታዊው የአገሪቱ የለውጥ ሒደት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዕርቅ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የምፅዋና የአሰብ ወደቦችን መጠቀም የሚቻልበት ዕድል እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህንን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ለመጠቀም ግን ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ሕግ መኖር እንዳለበት ይታመናል፡፡ በኋላ ሊከሰቱ ከሚችሉ ችግሮች ለመከላከል ቀድሞ አጠቃቀሙን በተመለከተ ሕግ ሊኖር አይገባም ወይ?

አቶ ፀደቀ፡- ይህ ጉዳይ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመራ የሚገባው ነው፡፡  ምክንያቱም በወደብ ችግራችን ይጠቀሙ የነበሩ አካላት ቁጥራቸው ብዙ ስለሆኑ ሳይሆን፣ ጥቅማቸው ግዙፍ በመሆኑ ብቻ ልንፈራቸው ይገባል፡፡ ብዙ ተጠቃሚዎች ቢኖሩ ኖሮ በእነሱ መካከል የሚኖረው ሽኩቻ መልሶ እኛን ጠቃሚ ይሆን ነበር፡፡ ተጠቃሚዎቹ ጥቂት መሆናቸው አይቀርም የሚለውን ከዋጋው ንረት ብቻ ትገምታለህ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ ትራንዚተሮች አሥር ሺሕ ብር ከፍለው ፈቃድ ይከራያሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ግልጽ ያድርጉልኝ?

አቶ ፀደቀ፡- የትራንዚት ፈቃድ የሆነ አካል ያወጣል፡፡ አሥር ሺሕ ብር በወር የሚከፈል ከሆነ እንዲህ ዓይነት ፈቃድ ያላቸው አሥር ሺሕ ከሆኑ፣ ከፈቃዱ ኪራይ ብቻ በወር 100 ሚሊዮን ብር ቀጥታ ገቢ አለ ማለት ነው፡፡ አሁን እንግዲህ ማነው እየመጣ ያለው? እነ ማን ናቸው የሚካፈሉት? የሚለውን አታውቅም፡፡ ጠቅላላ የአገራችን የወጪ ንግድ ሲተመን 1.5 ሚሊዮን ቶን ጭነት አካባቢ ነው፡፡ ይህችን ምርት መርከቦቻችን አራቴ ቢመላለሱ ፀጥ ያደርጓታል ማለት ነው፡፡ ይህንን ያነሳሁት ያልተጠቀምንበት ሀብት አለን ለማለት ነው፡፡ ይህን ስናንቀሳቅሰው ለሁሉም አካላት ያለው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ትልቅ ነው፡፡ ለአዲሱም የሚሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ልበ ብርሃንና ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ሰዎችን ማሰባሰብ መጀመር አለባቸው፡፡ ለምንድነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የምታጠነጥነው ብትለኝ ሕዝቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እምነት ስላለው ነው፡፡ በፍጥነት ይተማመኑባቸዋል፡፡ በተጋፋጭነት ይተማመኑባቸዋል፡፡ በቅንነት ይተማመኑባቸዋል፡፡ የራሱን ጥቅም አያስቀድምም ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ስላሉ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለሌላ ሰው አሳልፈው የሚሰጡ አይደሉም፡፡ ይህ የአገሪቱ ነርቭ ማለት ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ባለው ሽግግር ወቅት ሁሉም የራሱን ጥቅም ለማጉላት ወይም ለማስከበር በሚያደርገው ሩጫ፣ ሌላ የሚወዳደር ወይም የሚመጠን የመዥገር ባህሪ ያለው ነገር ከመፈጠሩ በፊት በቶሎ ይህችን ነገር ወደ ሕዝቡ ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ደግሜ የምለው የአገሪቱን አቅጣጫ የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ፈጣን ውሳኔ መስጠት ይፈልጋል፡፡ አሁን በአጭር ጊዜ የፈጠሩትን ሰላማዊ ድባብ ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመቀየር መነሻው ሎጂስቲክስና ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህ ሲነካካ ሌሎች ፍላጎቶችም ይወጣሉና በዚህ ላይ በብርቱ መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሎጂስቲክስ ዘርፍ ብዙ ትኩረት የተሰጠው የማይመስል ግን ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል የሚሉት ዘርፍ የትኛው ነው?

አቶ ፀደቀ፡- የፋይናንስ ዘርፍ ነው፡፡ ሎጂስቲክሱንም፣ ከተማ ልማቱንም ሆነ መሠረተ ልማቱን የሚያንቀሳቅሰው ፋይናንስ ነው፡፡ የፋይናንስ ምንጭ ሲታሰብ በዋናነት አንድ ከሕዝብ ከሚገኝ አቅም ነው፡፡ ከታክስና ከመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ቁጠባን ወደ ብድር ማምጣት የአገር ውስጥ ምንጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ንግድና ገበያ መኖር አለበት፡፡ የምርት ገበያና ንግድ መኖር አለበት፡፡ እነዚህን በቶሎ እንዴት ነው የምናሳልጠው የሚለው በፍጥነት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ሁለተኛው የፋይናንስ ምንጭ ተደርጎ የሚወሰደው የውጭ ኢንቨስትመንትና ብድር ነው፡፡ እዚህ ላይ በዋናነት መንግሥት የውጭ ብድር መፍራት የለበትም፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ‹‹ብድር አናታችን ላይ ወጥቷል›› እየተባለ ባለበት ወቅት ብድር መፈራት የለበትም የሚሉት እንዴት ነው?

አቶ ፀደቀ፡- ብድር አልበዛም! እኔ ብድር በዛብን የሚባለውን ነገር አልሰማም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ አሁን ያለባት ብድር ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ  ብድር ለመክፈል ያስችላል ከሚባሉ የገቢ ምንጮች አንፃር ከፍተኛ ነው፡፡

አቶ ፀደቀ፡- 24 ቢሊዮን ዶላር ምንድነው? 24 ቢሊዮን ዶላር ለማን ኢኮኖሚ? መጀመርያ ነገር የተጠራቀመ ብድር ሳይሆንመ አንተ ልትከፍል የምትችለውን መጠን ነው እንጂ፣ 100 ቢሊዮን ዶላር፣ ሁለት መቶ ቢሊዮን ዶላር ብንበደር አበዳሪው ለመክፈል ትችላለህ ብሎ ካሰበ እሱ ነው የሚጠብቅልህ፡፡ አንድ የውቅያኖስ ውስጥ ጠብታ ነች፡፡ ይልቅስ እስኪ ሕዝቡን እየው፡፡ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ማለት ለእያንዳንዱ 240 ዶላር ማለት ነው፡፡ 240 ዶላር አንድ መጫወቻ ማለት ነው፡፡ አንድ ስልክ አንድ ሺሕ ዶላር ይሸጣል፡፡ አይፎን በቀን አንድ ሚሊዮን ስልክ ይሸጣል፡፡ እኛ  240 ዶላር ብድር በነፍስ ወከፍ በቀን የምንባባል ከሆነ እኛ ሕዝባችንን አናውቅም ማለት ነው፡፡ በቁጥር ደረጃ እናውራ ካልን መጀመርያ 80 ቢሊዮን ዶላር ራሱ በእኔ ግምት ከግምት በታች ኢኮኖሚ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሚስማሙበት ነገር ነው፡፡ ቢያንስ በ40 በመቶ፣ በእኔ ግምት ደግሞ በ50 በመቶ ወይም በግማሽ የቀነሰ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ስለዚህ የውጭ ብድራችን ከጂዲፒ ምጣኔው አሁንም 14 እና 15 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የዕድገት ምጣኔያችን ሲታይ ደግሞ አሥር እና 14 በመቶ እያልን ነው የምናወራው፡፡ አሥር በመቶ ከሆነ የብድር መክፈል አቅማችንን ምን ያህሉን ነው እየተጠቀምንበት ያለነው ስንል በጣም ኢምንት ነው፡፡ ይኼ ሁሉ እየሆነ ያለው በኮንትሮባንድ እየተዘረፍን ባለበት፣ ኤክስፖርት በአንደር ኢንቮይስና በኦቨር ኢንቮይስ እየተዛባ ጭምር ነው፡፡ ይኼን ሁሉ ነገር ሊበራላይዝ አድርገን ስናየው ይህንን ሁሉ ተሳስቻለሁ ማለት ይቻላል? አበዳሪዎቻችን ከተሳሳቱ እነሱ ይከልክሉን እንጂ እኛ ለምንድነው የምንከላከለው? አበዳሪ ነው እንጂ አትችልም ማለት ያለበት ተበዳሪ አልችልም ይላል እንዴ? አይሆንም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን አቅም አናሳንስ፡፡ እኛ ከግምት በታች እናደርጋታለን፡፡ ቻይና፣ አሜሪካና እዚህ ኢንቨስት የሚያደርጉ ዳያስፖራዎች ከፍ ያደርጓታል፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን መናገር የምፈልገው የሚመሩት አገር በጣም ሀብታም ነው፡፡ ውስጡን እንዳይታይ ያደረገውና የከለለው የኪራይ ሰብሳቢ ጃንጥላ ነው፡፡ በጣም ሀብታም አገር ነው ይዘን  የተቀመጥነው የሚለውን ነው የማስተላልፈው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ስካት ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...