Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሎሚናት ቤቨሬጅ ብሔራዊ አልኮልን እንዲረከብ ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ አልኮልን ለመግዛት ከሁለት ወር በፊት 3.62 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያቀረበው ሎሚናት ቤቨሬጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 35 በመቶ ክፍያ ፈጽሞ ፋብሪካውን እንዲረከብ ተጠየቀ፡፡

በዚህም መሠረት ሎሚናት ቤቨሬጅ አጠቃላይ ካቀረበው ዋጋ ውስጥ 1.26 ቢሊዮን ብር ከፍሎ ድርጅቱን የሚረከብ ሲሆን፣ ቀሪውን 65 በመቶ ክፍያ ደግሞ በአምስት ዓመት ውስጥ ከፍሎ እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል፡፡

በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከፈተው ጨረታ ሎሚናት ቤቨሬጅን ጨምሮ ሦስት ኩባንያዎች መወዳደራቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስቴሩ አውጥቶት በነበረው ዓለም አቀፍ ጨረታ 97 ተጫራቾች የመጫረቻ ሰነዱን ገዝተው የነበረ ቢሆንም፣ ለመጨረሻው ዙር ሦስት ኩባንያዎች ብቻ የመጫረቻ ዋጋቸውን ሊያቀርቡ ችለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሎሚናት ቤቨሬጅ ከሁሉም ተሽሎ 3.62 ቢሊዮን ብር ዋጋ ሲያቀርብ አብረው የተወዳደሩት ፒዩር አልኮልና ቤቨሬጅ ማኑፋክቸሪንግና መታደም ማኑፋክቸሪንግ የተባሉ ኩባንያዎች እንደቅደምተከላቸው 1.65 ቢሊዮን ብርና 1.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ አቅርበው ነበር፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች አቅርበውት የነበረው ዋጋ ከብሔራዊ አልኮል መነሻ ዋጋ ሆኖ ከተገመተው 1.2 ቢሊዮን ብር ተቀራራቢ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለወራት ሎሚናትና ሁለቱ ኩባንያዎች ያቀረቡትን የቴክኒክ፣ የፋይናንስና ሌሎች ተዛማጅ ሰነዶችን ሲመረምር የነበረው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በመጨረሻ ሎሚናት ቤቨሬጅን አሸናፊ አድርጎ መርጧል፡፡ አሸናፊው ኩባንያ 35 በመቶውን ክፍያ አጠናቆ ፋብሪካውን እንዲረከብ መጠየቁን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋመው ሎሚናት ቤቨሬጅ በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ የአልኮል ማምረቻ ፋብሪካ በሞጆ እየገነባ ሲሆን፣ ብሔራዊ አልኮልን ከተረከበ በኋላም ሁለቱ ፋብሪካዎች አብረው የሚሠሩ ይሆናል፡፡

ሎሚናት ቤቨሬጅ ከዚህ ቀደም ላለፉት 20 ዓመታት ዲያጆ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኃላፊነት የሠሩት አቶ ብሩክ ወርቁና የካንትሪ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወነ የግል ኩባንያ መሥራችና ኃላፊ አቶ ቢንያም ብርሃኔ በአጋርነት የተቋቋመ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች