Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሰብና ምፅዋ ወደቦችን ስናስብ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በባዕለ ሊመታቸው ላይ አፅዕኖት ሰጥተው ካስገነዘቡዋቸውና እንደሚተገብሩዋቸው ቃል ከገቡባቸው አበይት ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የቆየውን ቁርሾ ማከም፣ ብሎም መልክ ማስያዝና በሰላም ጎዳና መጓዝን ይመለከታል፡፡

ከዚህ አንፃር በወራት የሥልጣን ቆይታቸው ሊተገበሩ የማይችሉ የሚመስሉ፣ አንዳንዶቹም በፍፁም ያልተገመቱ ድንቅ የሚባሉ ክንዋኔዎችን ፈጽመዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ወደ ሁለት አሥርት ዓመታት የተቃረበን አስከፊ ታሪክ መለወጥ የቻሉበትን የአስመራ በረራ ማድረጋቸው፣ ከዚያም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን አዲስ አበባ መጋበዛቸውን በሁለቱ አገሮች ርዕሰ ከተሞቻቸው የታየው ትዕይንት በብዙዎች ዘንድ እንደ ተዓምር የታየ ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጎልበት የአየር ትራንስፖርት መጀመሩ፣ ለዓመታት የተቋረጠው የስልክ ግንኙነት መተግበሩ ሁሉ የታሪካዊ ክስተቱ አካላት ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠንከር ሌሎች ውሳኔዎችም መተላለፋቸውንም ልብ ይሏል፡፡

አዲሱን ዓመት በተቀበልንበት የመጀመሪያው ዕለት የተመለከትነው ሌላው ትዕይንት ደግሞ የሰውዬው ቃል የማይታጠፍ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የነገ ዕጣ ፋንታ በብርቱ እንድንናፍቅ ያደረገ ጭምር ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ለዚህ ደረጃ መድረስ ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ትስስሩንም ያጎለብተዋል፡፡ ለሁለቱም አገሮች እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታየው ይህ እውነት የበለጠ ትርጉም ሊሰጥ የሚችለው ግን በደረሱባቸው ስምምነት ልክ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን የሚመለከቱ ጉዳዮች በተግባር ወደ መሬት ሲወርዱ ነው፡፡

እንደ ሁለት አገር ግን እንደ አንድ ለመሥራት ስምምነት ሲያደርጉ በቀጣይ የሚጠበቁት ተግባራት ትኩረት የሚሹ ስለመሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ስምምነቱ በአሰብና በምፅዋ ወደብ መጠቀምን ያጠቃልላል፡፡ ከእነዚህ ወደቦች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በቀጣይ እንዴት ሊሠራ እንደታሰበ በግልጽ ለማወቅ ባይቻልም፣ የወደብ አጠቃቀሙን የተመለከቱ ቅድመ ዝግጅቶችና ለዚህ አገልግሎት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ድንጋጌዎች ይኖራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ከአሰብና ከምፅዋ ወደቦች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሁለቱ አገሮች በሚያደረጉት ስምምነት የወደብና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀረጸው ሕግ ነገ ውዝግብ ውስጥ የማይከተን መሆን አለበት፡፡

የሥራ ሒደቱን በአግባቡ የሚገዛ ሕግ ከተቀመጠ ነገ በአጋጣሚ ሊፈጠር የሚችል ክፍተት ቢፈጠር እንኳን በተቀመጠው ሕግ እንዲዳኝ የሚያስችል በመሆኑ፣ እንዴት ነው የምንሠራው ለሚለው ጥያቄ ጥርት ያለ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል፡፡

በተለይ ከወደቡ አገልግሎት፣ ከሎጂስቲክስና ትራንስፖርት፣ ከጉምሩክ፣ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተያዙ ሥራዎች ላይ ተመሥርተው የሚሠሩ ተቋማት እስከዛሬ የነበራቸው የአሠራር ሒደት አገርን ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ማስታወስም ይጠቅማል፡፡ አዲሱ የወደብ አጠቃቀምን አጠቃላይ የወደብ አገልግሎት ግልጽ የሆነ አሠራር እንዲኖረው በሠለጠነ መንገድ ለመምራት ከወደቡ አገልግሎት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካካቸውን አካላት ሁሉ በድጋሜ ማዋቀርና ወደ ሥራ ማሰናበትንም ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከወደቦቹ ዕቃዎችን አንስቶ ወደ መሃል አገር በማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሠማሩ የትራንስፖርት ድርጅቶች መብትና ግዴታን ጭምር በግልጽ የሚያስቀምጥ እንዲሆን ማድረግ ያሻል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በጅቡቲ ወደብና በደረቅ ወደቦቻችን የሚከማቹ ንብረቶችን በቶሎ ያለማንሳት ችግር እያስከፈለ ያለውን ዋጋ የሚቀይር አሠራር መዘርጋት ሊረሳ አይገባውም፡፡

አንዳንዴ ንብረቱን ያመጣው አካል ጠፋ እስከመባል የምንሰማበት ፌዝ የገቢና ወጪ ንግዱ ዕቃዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ ያለውን ደካማ አቅም የሚያሳይ በመሆኑ፣ የሚቀረፀው ሕግና በተያያዘ ሥራዎች መዘርጋት ያለበት አሠራር እንዲህ ያሉ ችግሮችንም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡

ነገም እንዲህ ዓይነቱ የሥራ ሒደት በምፅዋና በአሰብ ወደብ እንዳይደገም የሚያስችል አሠራር እስካለተዘረጋ ድረስ በሎጂስቲክስ፣ በትራንስፖርትና በወደብ አገልግሎት ዙሪያ የሚባክነውን የአገር ሀብት ማዳን አይቻልም፡፡ በዘርፉ የሚታየውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ከሚያስፈልጉን ሕጎች ባሻገር ቆራጥ ሠራተኞችና አስፈጻሚዎች ያሻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በጂቡቲ ወደብ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶች ምን እንደነበሩ በመለየት መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ብልኃት መፈለግ የግድ ይላል፡፡

በአሰብና በምፅዋ ወደብ መጠቀም ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ትርጉም እንዲኖረው ለማድረግ አሠራሩን ግልጽ መደረግ አለበት፡፡ እንዲህ ያለው ሥርዓት በትንሹ የሎጅስቲክስ ወጪዎችን በመቀነስ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ገቢ ዕቃዎችን ሸምተው እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል፡፡ ለወደቦቹ በቅርብ የሚገኙ የአገራችን ክፍሎች ከእስከዛሬው ባነሰ ዋጋ ምርቶችን መሸመት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራልና መልካም አጋጣሚው በአግባቡ ለመጠቀም የሎጂስቲክስና የወደብ አገልግሎት አሠራሮች ተፈትሸው የሚያሠራ ሕግ ይኖራቸው፡፡

ከፍተኛ የሚባለውን የሎጂስቲክስ ወጪ መቀነስ የሚችለው ደግሞ በሕግ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች ሲኖሩን ነውና ጉዳዩ ትኩረት ያሸዋል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት