Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች የሰሞኑን ጥቃቶች አወገዙ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰሞኑን ጥቃቶች አወገዙ

ቀን:

መንግሥት የዜጎች በሕይወት የመኖር መብትን እንዲያስከብር መኢአድ ጠየቀ

ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰንበቻውን በአዲስ አበባና በተለያዩ ሥፍራዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን አወገዙ፡፡ ፓርቲዎቹ ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በአገሪቱ እያጋጣሙ ያሉ ግጭቶችና ጥቃቶች አሳሳቢና አሳዛኝ ናቸው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)፣ የኦሮሞ አንድነት ለነፃነት፣ የኦሮሞ አንድነትና ግንባርና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ በዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ማውገዛቸውን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በግጭቱ የሚሳተፉ ተዋንያንና ከጀርባ ሆነው የሚያስተባብሩ የውጭና የአገር ውስጥ ኃይሎች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል የዴሞክራሲ ባህል በጋራ ማዳበር ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ለማንም አይጠቅሙም ብለዋል፡፡ ወጣቶች በመስዋዕትነት ያመጡትን ለውጥ ለመቀልበስ ከሚሹ ኃይሎች ጋር እንዳይሠለፉም አሳስበዋል፡፡

‹‹ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን፤›› ያሉት ፓርቲዎቹ ለአባላቶቻቸው፣ ለደጋፊዎቻቸውና ለሕዝቡ ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የመጣውን ለውጥ የመምራት ኃላፊነት ያለበት መንግሥትና አካላቱ፣ የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲሉ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የመከላከል ዕርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው፣ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ደግሞ በአስቸኳይ ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ መንግሥት ለዜጎች የሚያደርገው ጥበቃ ጠንካራ ባለመሆኑ ዜጎች በሕይወት የመኖር መብታቸውን አጥተው አሰቃቂ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን፣ በአያሌ ዜጎች ላይ ዘረፋ፣ ድብደባና ሌሎች ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም በአስቸኳይ እንዲቆምና ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጠየቀ፡፡

መኢአድ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ፣ ‹‹አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ አልቻለም፤›› በሚል መሪ ቃል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብና በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚፈልጉ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ሰላም ለማደፍረስና አገር ለማፍረስ እየሠሩ ነው በማለት የገለጸው ፓርቲው፣ ‹‹ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆኑ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት ባሉበት በአገራችን ኢትዮጵያ በመሀል አገር አዲስ አበባና ዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ዘር ተኮር ጥቃት መፈጸሙ፣ በታሪክ አሳፋሪና ለኢትዮጵያ የማይመጥን የኃፍረት ካባ ያከናነበን ነው፤›› በማለት መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

አገሪቱ አሁን ከምትገኝበት ችግር ለማውጣት መንግሥት ብቻውን መፍትሔ ያመጣል ብሎ እንደማያምን መኢአድ አስታውቆ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው፣ ‹‹አገር ውስጥ ካሉትም ከውጭ ከመጡትም ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከመንግሥት አካል የተውጣጡ ጥምር ኃይል መቋቋም ይኖርበታል፤›› ሲሉ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ጥምር ኃይል ካልተቋቋመ ችግሩ ሊፈታ አይችልም፡፡ ችግሩ ከሕዝብ የተሰወረና የራቀ ባለመሆኑ፣ ጥምር ኃይል ተቋቋሞ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረግ መቻል አለብን፡፡ በዚህም የተደበቀ ሐሳብ ያለውም ካለ፣ ያልተመለሰ ጥያቄ ያለውም ካለ በጠረጴዛ ዙሪያ ሐሳቡን ሊገልጽ ይገባል፡፡ ይኼንንም ሊያወያይ የሚችል ጥምር ኃይል ማቋቋም ያስፈልጋል የሚል ፅኑ እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

መኢአድ በመግለጫው አሁን በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸመው ግድያና ማፈናቀል አገር ወደ ማፍረስ ደረጃ ሳይሸጋገር መንግሥት የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ፖሊስና የሕዝብ ደኅንነት ተቋማት አሁን የሚታየውን መዘናጋት በማስተካከል ሕግና ሕገ መንግሥት በሚሰጣቸው ሥልጣን መሠረት በዜጎች ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ችግር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የሕዝቡን ደኅንት እንዲጠብቁ ጠይቋል፡፡

መንግሥት ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አምኖ በዜጎች ላይ አደጋ ከመድረሱ በፊት ሕይወታቸውን ሊታደግ የሚችል ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ‹‹ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ የማይወጡ በእንዝህላልነት ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር መንስዔ የሆኑ የፀጥታና የደኅንነት አስከባሪ ኃላፊዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስድና ለተፈናቀሉ ዜጎችም አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ፤›› መኢአድ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...