Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፖለቲካችንን ምን ይበጀው ይሆን?!

ፖለቲካችንን ምን ይበጀው ይሆን?!

ቀን:

በትዕግሥት ጋረደው

አገር ማለት ምድር ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ነው፡፡ በእኛ ሰዎች (በተለይ በአዲሱ ትውልድና በጽንፈኛ አስተሳሳብ በታመመው ወገን) እሳቤ ግን አገርን ከቡድን የመነጠል ልክፍት እንደ በረታ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌን እንደ አጥር እያበጀን ብሔራዊውን ጥቅም ስንዘነጋ ይታያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለተራ ፖለቲካ ትርፍ ሲባል አገርን አሳልፎ ለመስጠት የሚያጋልጥ ድርጊት በግለሰቦች፣ በድርጅቶችም ሆነ በስብስቦች ደረጃ ሲፈጸም ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን ከማውገዝና ከመጠየፍ ይልቅ፣ የአስተሳሳቡ ሰለባ ሆነን በመንጋነት የምንነዳ ጥቂት አይደለንም፡፡

ይህን ድፍን ትችት ለመሰንዘር የምገደድባቸው አንዳንድ ጭብጦችን በቀጣይ በማንሳት ሐሳቤን ለማፍታት እሞክራለሁ፡፡ በእርግጥ የማነሳቸው ማኅበራዊ (ፖለቲካዊ) ሂሶች በግል ዕይታ ላይ የተመሠረቱ ቢሆንም፣ በተለያዩ መድረኮችና ማኅበራዊ ውይይቶች የተብላሉ ሐሳቦች መሆናቸውን ለአንባቢያን መግለጽ እወዳለሁ፡፡

የፖለቲከኞቻችን ግራ መጋባትና አብሮነት ማጣት

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተበላሸው ከመሠረቱ ነው የሚሉ ተቺዎችን ሐሳብ የምስማማበት ሙሉ በሙሉ ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው የ1960ዎቹ የአገራችን ሁኔታ የፊውዳሉ የጃጀ ሥርዓትና በዓለም አቀፍ አብዮቶች ሞዴልነት እየተመራ፣ በምሁራንና በወጣቶች እየተግበለበለበ የነደደው የለውጥ መንፈስ የተላተሙበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ያ ታሪካዊ ክስተት በሰከነና ለአገር በሚበጅ መንገድ ሳይቋጭ በወታደራዊው ጁንታ በመጠለፉ፣ ለአገራችን አንድ ትውልድ ማለቅ ብሎም ለሰላማዊው ፖለቲካዊ ትግል መደነቃቀፍ በር ከፍቷል፡፡ አሁን ድረስ በሽታው አለቅ ላለን የጥላቻ ፖለቲካ ማቆጥቆጥም መሠረቱ ያ ክፉ ጊዜ ነው ቢባል ብዙዎችን የሚያስማማ ነው፡፡

የያኔዎቹ  ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሕወሓት፣ ኦነግ በኋላም በደርግ በጎ ፈቃድ የተሰባሰቡት እነ ኢጭአት፣ ማሌሪድ፣ ሰደድ …. መሠረታቸው ኅብረ ብሔራዊም ሆነ ብሔራዊ መልክ ያለው ፖለቲካ ቢሆንም በጥሎ ማለፍ፣ በአሸናፊነትና በተሸናፊነት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጨዋታ ማተኮር ተጀመረ፡፡ እነዚያ የ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲከኞችና አንዳንድ ድርጅቶች አሁንም ድረስ በሕይወት ቢኖሩም፣ ካለፉበት የጥላቻና የከረረ ተገዳዳሪነት ፖለቲካ መውጣት አለመቻላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ከተበላሸው አዙሪታም አስተሳሳባችን ለመላቀቅ መቸገራችንን መረዳት ይቻላል፡፡

በቴክኖሎጂና በመረጃ ከዳበረችው ዓለማችን አንፃር ነገሮች በዓመታት ሳይሆን በቀናት፣ በሰዓታት ብሎም በደቂቃና በሰከንድ በሚቀያየሩበት ወቅት እኛ ግን በአምስት አሥርት ዓመታት እንኳን አንድ ዕርምጃ ወደፊት የተራመደ ሰላማዊ ፖለቲካ መገንባት አለመቻላችን መፈተሽ ያለበት ጉድለታችን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓለም አቀፉ የዴሞክራታይዜሽን ጉዞ በብዙ ፈርጁ እየተስፋፋ የመጣ ቢሆንም፣ የአገራችን ምሁራንና ፖለቲከኞች የሥነ መንግሥት ቀንዲል በለኮሱበት ዘመን የተነሱ የሥልጣኔና የሥልጣን ዳዴ ባዮች (እነ ጃፓን፣ ቻይና ኢንዶኔዥያ፣ ከአውሮፓም ብዙዎቹ) ዛሬ እኛ በቆምንበት የጥላቻና የመጠፋፋት ልክፍት ውስጥ  አይደሉም፡፡

በመሠረቱ አገራችን የሰው ልጅ መገኛ፣ የእነ አክሱም ድንበር ተሸጋሪ ሥልጣኔ ባለቤት፣ የእነ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የእነ አፄ ፋሲል ሥነ ሕንፃ፣ የእነ ሐረር ግንብና የእነ ሶፍ ዑመር የተፈጥሮ ዋሻ ባለቤቶች ነች፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም በሃይማኖተኝነትና በፈሪኃ ፈጣሪ ለሺሕ ዘመናት የተገነባ ማኅበረሰብ ያለን፣ መቼም ቢሆን ለአብሮነትና ለአንድነት ዋጋ የሚሰጥ ሕዝብ ባለቤቶችም መሆናችን በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ ዛሬ ዛሬ ዋጋ ስንሰጣቸው ባይታይም የራሳችን ቋንቋዎች፣ ቁጥርና ፊደል ባለቤቶችም ነን፡፡ ታዲያ ለምን የፖለቲካ ድንቁርና ውስጥ ወድቀን ቀረን? እንዴትስ የመደማማጥና የአንድነት መንፈስ (ኅብረ ብሔራዊነትን) ዕውን ለማድረግ የሚቆም የፖለቲካ ምኅዳርና ዑደት መፍጠር ተሳነን?  የሚሉ ጥያቄዎች ደጋግመው ሊኮረኩሩን ይገባል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ በጽንፈኛ ፖለቲካ ምክንያት ለሥርዓት ለውጥ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው የሚሠራ የተሰበሰበበት ነው፡፡ ለዚህም ሁሉንም ነገር ጥላሸት በመቀባት፣ ለአገር ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ሁሉ ትዝብት ላይ በሚጥል መንገድ የሚቃወም አለ፡፡ እሳትና ውኃን ባልለየ መንገድና ዘረኝነትን በተላበሰ አኳኋን፣ የወዳጅና የጠላት አሠላላፍ በመፍጠር የሚነጉዱም በገሀድ እየታዩ ነው፡፡

በመንግሥት በኩልም የአገሪቱ ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰፋ፣ መሠረታዊ የዴሞክራሲና የፖለቲካ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩ ከንግግር ያለፈ የተግባር ዕርምጃ ቢጀመርም፣ በእልህና በግትር የፖለቲካ መንቻካነት በመታጠር ተፎካካሪን በተገኘው አጋጣሚ የማዳከም፣ ከሆደ ሰፊነት ባፈነገጠ መንገድ የማውገዝ ድርጊት ውስጥ ሲገባ ይታያል፡፡ ቢያንስ በአንዳንድ ጽንፈኛ ሚዲያዎችና የፌስቡክ ሠራዊት ካድሬዎች (አክቲቪስቶች) የሚነዛው ከጽንፈኛ ፖለቲከኛ ያልተሻለ ንግግርና መዘላላፍ ይህንኑ ያንፀባርቃል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመፅ ምክንያት፣ መንግሥት አስተካክለዋለሁ ብሎ የፎከረበት ተግባር አንዱ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ለዚህም ተብሎ በአገሪቱ የሚገኙ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንና በውጭ ያሉት ሳይቀሩ እንዲገቡ ተደርጎ እንደራደር፣ በውይይትም የአገራችንን ፖለቲካ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንውሰድ በማለት የጀመረውን ጥረት ብዙዎች በተስፋ ዓይተውታል፡፡ ይሁንና በመሀል የሚፈጠሩ ችግሮች በአግባቡ ካልተፈቱ የሚመጣ ለውጥ ሊኖር እንደማይችል ዕሙን ነው፡፡

መንግሥት አሁን እየተቸገረበት ያለው የሕግ የበላይነት የማስፈን ጉዳይ ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ ግን ትዕግሥቱ ማለቅ አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለቀቅ ሲደረጉ ጣልቃ የገቡ ኃይሎች በመኖራቸው ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ አርዓያነት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ በአስተሳሰብ ልዕልናቸውና አገራዊ ፍቅራቸው የሚጠቀሱ ምሁራን፣ መካር የአገር ሽማግሌዎችና ገለልተኛ ተቋማት እየተመናመኑ መምጣታቸውንም አብሮ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወገባቸውን ጠበቅ ማድረግ አለባቸው፡፡

እንግዲህ ለዚች አገር ሕዝብ ጥቅምም ሆነ ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋ ሲባል ከተበላሸው የፖለቲካ አካሄዳችን መውጣት የግድ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ከቂም በቀል ፖለቲካ፣ ከጥላቻና ከፍረጃ በመውጣት መነጋጋርና የመግባባት መንፈስ የመፍጠር ተግባርን አሁኑኑ መጀመር ያስፈልገናል፡፡ መንግሥትም  ለእውነተኛ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በቁርጠኝነት ሊነሳ ይገባል፡፡ የሠለጠነ ግፊትም መደረግ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለይ ከምንም ነገር በላይ ለሕግ የበላይነት መስፈን ጠንክሮ መሥራት አለበት፡፡

መሪ ያላገኘው የሕዝብ ፖለቲካ

በየትኛውም አገር የመንግሥትን ፖሊሲና አካሄድ የሚደግፍና አጋር የሆነ ሕዝብ ብቻ አይደለም ያለው፡፡ በአንድም በሌላም ያለውን መንግሥት ፖሊሲ የሚቃወምና ይወክለኛል ብሎ የማያምን መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ልዩነት እስካለ ድረስ፡፡  የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ አንዱ ማሳያ በአብላጫ ድምፅ ቢሸነፍም ነፍስ የሌለውን ሙት ተቃዋሚ ፓርቲ ሳይቀር ከኢሕአዴግ ይሻለኛል ብሎ በምርጫ ካርድ የመረጠ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እንዳለ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ሌላው አሁን ያለውን መንግሥት መረጠም አልመረጠም አልጠቀመንም፣ መድልኦ ፈጽሞብናል፣ በቂ የሥራ ዕድል አልፈጠረልንም . . . ብሎ ለከፋ አመፅና ሁከት የተነሳ አብዛኛው አዲስ ትውልድ እንደ ነበር ከወራት በፊት ዓይተናል፡፡ በዚህ አሳዛኝ ክስተት በርካታ የሰው ሕይወት የጠፋበት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ሀብት የወደመበት ዕርምጃ ሲወስድ ለውጥ ከመፈለግ ነው፡፡ ይህንን መቼም መርሳት አይገባም፡፡ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነውና፡፡

ይሁንና ይህን የተለየ የለውጥ ፍላጎት ያለውን ኃይል በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ብሎም በተደራጀ መንገድ ሊመራው የተዘጋጀና በርትቶ እያታገለ ያለ ኃይል  እስካሁን አልተገኘም፡፡ በእርግጥ አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አለን ማለታቸው አልቀረም፡፡ ነገር ግን አሁንም አንድም ፓርቲ አማላይ ፖሊሲ ወይም ፕሮግራም ለሕዝብ አቅርቦ ሲሸጥ አልታየም፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ሕዝቡ ዘንድ ወርዶ መሥራት የወቅቱ ዓብይ ጥያቄ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ማስቀጠል የግድ ይላል፡፡

ከዚህ ቀደም ፓርቲዎቹ በመከፋፈልና አንጃ በመፍጠር የተጠመዱ መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት በግልጽ እንደ ተመለከትነው በቀዳሚነት አንድነት፣ በኋላም መኢአድ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝቡ ክፉኛ እስኪታዘባቸው ድረስ ተከፋፍለዋል፡፡ ማኅተም ተናጥቀዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የአመራር ስድድብና ድብድብ የታያባቸው አምቧጓሮዎችን ፈጽመዋል፡፡

በዚህም እነዚህ ሰዎች (አብዛኛዎቹ የተቀዋሚ ፓርቲ ወኪሎች) እንዴት አገር ሊመሩ ይችላሉ ብለን እርማችንን ያወጣን ቁጥራችን ትንሽ አልነበረም፡፡ ለነገሩ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅትም ቢሆን ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲም ቢሆን፣ በአሉባልታና በውዥንብር ሊፈርስ የቻለው በዚሁ ዓላማ የማጣትና የመሸርሸር ችግር ነው፡፡ እዚህ ላይ ለአንዳንዶቹ ፓርቲዎች መከፋፈል የኢሕአዴግ ሥውር እጅ እንዳለ መጠራጠር አይገባም፡፡ ቢሆንም ግን እንደ አንድ ተገዳዳሪ ፓርቲ ይህን ቢያደርግ የሚገርም አይሆንም፡፡ ሊገርም የሚችለው የዕድርና የዕቁብን ያህል እንኳን ተማምኖና ተባብሮ ለአንድ ዓላማ መሠለፍ የተሳነው ኃይል ከንቱ አካሄድ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡስ እንዴት አድርጎ ተገዳዳሪ ፖለቲከኞችን ተማምኖ አባል ይሁን? ድጋፉንስ እንዴት አድርጎ በፊት ለፊት ይስጥ? ለሞት፣ ለስደትና ለእስር ራሱን የሚያዘጋጀው አንሶ በተፈረካካሰ የፓርቲ ፖለቲካስ እንደምን በጀሌነት ይነዳ? ብሎ ውስጥን መፈተሸ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ከውጭ የገቡ ጠንካራ የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የአገራችን ልማትና ዕድገት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ባህላችን ግን በእጅጉ የሚያሳፍር ነው፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታችንም ከመጠላላፍ ያላላፈና በዚሁ ከቀጠለም ለትውልድ የማይፈይድ ጨምዳዳ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው እንደ አንድ ዜጋ በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ እየናወዘ ያለውን የአገራችንን ፖለቲካ ማንና መቼ ይታደገው ስል የምጠይቀው፡፡ ትውልዱን ከተስፋ መቁረጥ አውጥቶ ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች አገር ለመገንባት ከዚህ ቁጭት መነሳት ይገባናል እላላሁ፡፡ በተለይ በዚህ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ሆነን ከተለመደው አዙሪት ብንወጣ ይበጀናል፡፡ ለውጡን ለማደናቀፍና የተጀመረውን በጎ ፍላጎት ለማሽመድመድ የሚደረጉ አሻጥሮችን ማክሸፍና አሸናፊ ሆኖ መውጣት የግድ ነው፡፡ በመሰሪዎች ሴራ በመጠለፍ ተስፋን ማጨናገፍ አገርን ቀውስ ውስጥ ይከታልና እንጠንቀቅ፡፡ መሰሪዎች በሚፈጥሩት ግርግር አገርን ማተራመስና ወደ መቀመቅ ለመክተት የሚደረገውን ሴራ በፍጥነት መግታት ይገባል፡፡ አሁን አገርን ማዳን ይቅደም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...