Thursday, June 13, 2024

መንግሥት ይፋ ያላደረጋቸው የኤርትራና የኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ስምምነቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ባስቆጠሩዋቸው ስድስት ወራት ካከናወኑዋቸው ሥራዎች በዋናነት የሚጠቀሰው፣ ከኤርትራ ጋር የተደረገው ዕርቅ ነው፡፡ ይህ ዕርቅ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን የ20 ዓመታት የጦርነት ታሪክ በማብቃት የሰላም ምዕራፍ እንዲከፈት አድርጓል፡፡

በአገሮቹ መካከል ዕርቅ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ከመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ሲያስተጋቡ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ንግግራቸው ወደ ተግባራዊ ለውጥ ማምራቱን የሚጠቁም ክስተት ተፈጠረ፡፡ ይህም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኦስማን ሳልህና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ የማነ ገብረ አብ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ነው፡፡

የኤርትራ መንግሥት ልዑክ ጉብኝት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ በመሆኑ  አቀባበል ሊያደርጉላቸው ይገባ የነበሩት የኢትዮጵያ አቻቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ቢሆኑም፣ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በመገኘት አቀባበል ያደረጉላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ነበሩ፡፡ ይህን ክስተት በወቅቱ የተመለከቱ ምሁራን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ያደረጉት ለጉዳዩ ባላቸው ትኩረትና በሰጡት ክብደት እንደሆነ መስክረዋል፡፡

ይኼንን ተከትሎ ግን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሚገርም ፍጥነት የቀየሩ በርካታ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ የመጀመርያው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአስመራ ጉብኝት ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ መባቻ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ብዙም ሳይጠበቅ በጂቡቲ አየር ክልል አቋርጠው የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የልዑካን ቡድናቸው አባላት፣ አስመራ ሲደርሱ ከሕዝቡ የተደረገላቸው አቀባበል በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን የፈጠረ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታ ለመጀመርያ ጊዜ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ጦርነት በይፋ እንዳበቃ በማስታወቅ፣ የሁለቱን አገሮች ትብብርና ወንድማማችነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማምጣት ያለመ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ከዚህ ስምምነት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአስመራ ጉዞ ሳምንት በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በተጨማሪ፣ በሐዋሳ  ጉብኝት ሲያደርጉ ዕውን በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም ሰፈነ የሚያስብል ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በአዲስ አበባና በሐዋሳ በመንገዶች ዳርቻ በተሠለፉ ሰዎች፣ ብሎም በቤተ መንግሥት የምሳ ግብዣ ላይ የተደረገላቸው አቀባበል ከፍተኛ የነበረና የፕሬዚዳንቱን ስሜት የነካ እንደነበር ለማየት ተችሏል፡፡

የሰላሙን መውረድ ተከትሎ በድንበር አካባቢ በዛላምበሳና በቡሬ ታላቅ ደስታ ተፈጥሯል፡፡ በተለይ በሁለቱም አገሮች የሚከበረው መስከረም 1 ቀን (በኤርትራ ቅዱስ ዮሐንስ በመባል በኢትዮጵያ ደግሞ የዘመን መለወጫ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተገኙበት መከበሩ፣ የሁለቱ አገሮች ወንድማማችና እህትማማች ሕዝብ በአንድ ሥፍራ ተገናኝተው ተቃውፈው ሲያነቡ አሳይቷል፡፡

በይበልጥ በጦርነቱና ተከትሎ በተፈጠረው ጦርነትም ሆነ ሰላም አልባ ቆይታ የተጎዱት የሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ጉዳይ ቢሆንም፣ የሁለቱ አገሮች ዜጎች ምን ያህል ሰላም እንደናፈቁና አብሮነትን እንደተጠሙ ያሳየ ክስተት ነበር፡፡

ዘመድ ሲሞት ተራራ ላይ ወጥተው እርምህን አውጣ የሚባባሉ ወገኖች አሁን  ተቃቅፈው ለማንባት በቁ፡፡ የሁለቱ አገሮች አየር ክልል መከፈትም ዜጎች እንደ ልባቸው በመንቀሳቀስ ለ20 ዓመታት ያላዩዋቸውን ወገኖቻቸውን በዓይነ ሥጋ ለማግኘት በቅተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ በሁለቱ አገሮች መካከል ከ18 ዓመታት በፊት የነበሩትን ሳይጨምር በኤርትራና በሳዑዲ ዓረቢያ የሰላም ስምምነቶች ቢፈረሙም፣ የእነዚህ ስምምነቶች ይዘት ምን እንደሆነና ለምን ዝርዝር ዓላማዎች እንደተፈረሙ ብሎም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የመጨረሻ ምዕራፍ ምን ሊሆን እንደሚችል ያላቸው አመላካችነት ምን እንደሆነ በኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ አልተደረገም፡፡

ምንም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች በአስፈጻሚው የሚደረጉ ስምምነቶችን ለፓርላማ በማቅረብ ሕግ ሆነው እንዲፀድቁ የሚያደርጉ ቢሆንም፣ ከኤርትራ ጋር የተደረጉ ስምምነቶች እስካሁን ይህን መስመር ያልተከተሉና ይዘታቸውም በኢትዮጵያ ወገን በጠቅላይ ሚኒስትሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አማካይነት ከመነገር በዘለለ ይፋ ሳያደርጉ ቆይተዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያውና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ማንኛውም የአስፈጻሚ አካላት ስምምነቶች እነርሱ ያውቁልናል ብለን ልንተውላቸው እንደማይገባና ልንጠይቅ እንደሚገባ፣ በፓርላማ ቀርበው ፀድቀው አስፈጻሚው የፓርላማውን የሕግ አውጪነት ሚና እንዳይጋፋ ማድረግና ሕዝቡ ያለውን የመረጃ ነፃነት በአግባቡ እንዲጠቀም፣ እነዚህ ስምምነቶች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ይፋ መደረግ እንዳለባቸው አበክረው ያሳስባሉ፡፡

‹‹እኛ የዚህን ችግር ያየነው በሩቁ አይደለም፡፡ ከራሳችን ተሞክሮ ነው፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት በሁለቱ አገሮች መካከል ያልተፈረሙ ስምምነቶች አልነበሩም፡፡ ከመፈረሙ በፊት በፓርላማ የፀደቀውና ትልቅ ዋጋ ያስከፈለው የአልጀርሱ ስምምነት ልምድ አለን፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት አገራዊ ጉዳዮችን ለማንም አሳልፈን መስጠት የለብንም፣ መጠየቅ አለብን፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ኃላፊነት እንደሚወድቅበት ያሳሰቡት መምህሩ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ፕሮፓጋንዳ የሚመስሉ ፎቶዎችና ቅንጭብ ጽሑፎች እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ማግኘት ስለማይቻል ለማስተማር እንኳን የሚረዷቸውን ሰነዶች ለማግኘት ውጭ ካሉ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ድረ ገጾች እንደሚፈልጉና እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር ማረጋገጥ እንደቻለው፣ ከኤርትራ ጋር የተደረጉትም ሆኑ ከሌሎች የውጭ አገሮች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ይዘት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ አይገኝም፡፡ ነገር ግን የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በኤርትራ አስመራ የተደረገው የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን ጨምሮ፣ ተመሳሳይ የሆነ ይዘት ያለው የሳዑዲ ዓረቢያው የሰላም፣ የወዳጅነትና የአጠቃላይ ትብብር ስምምነት ሰነዶች ይዘቶች ሙሉ በሙሉ ተለጥፈው ይገኛሉ፡፡

በኤርትራ የኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴር ድረ ገጽ ሻባይት ዶት ኮም ላይ የወጣው በኤርትራ የተፈረመው የሁለቱ አገሮች የሰላምና ወዳጅነት ማብሰሪያ ስምምነት ሰነድ አምስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፣ ይዘቱ እንደሚያሳየው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ጦርነት ማብቃቱና አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ መከፈቱን፣ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት የሕዝቦቻቸውን ጥቅሞች በሚስጠብቅ መልኩ የተቀራረበ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህላዊና የደኅንነት ትብብሮችን እንደሚያደርጉ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የትራንስፖርት፣ የንግድና የኮሙዩኒኬሽን ግንኙነቶች እንደሚጀመሩና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች እንደሚቀጥሉ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ድንበር የተወሰነው ውሳኔ እንደሚፈጸምና ሁለቱም አገሮች ሰላም፣ ልማትና ትብብርን ለማምጣት በጋራ እንደሚሠሩ ያበስራል፡፡

ይህ ሰነድ አክሎም ሁለቱ መንግሥታት የኤርትራና የኢትዮጵያ ወዳጆችን እንኳን ደስ አላችሁ ያለ ሲሆን፣ አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን እጥፍ አድርገው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያቀርባል፡፡

በብዛት ተመሳሳይ ይዘት ያለው የሳዑዲ ዓረቢያው ስምምነት የያዘው ልዩ ነገር ቢኖር ሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ኃላፊዎችን የያዘ የጋራ ኮሚቴ እንደሚያቋቁሙና እንዳስፈላጊነቱ ንዑስ ኮሚቴዎች ኖረው የዚህን ስምምነት ተፈጻሚነት እንደሚያረጋግጡ ያትታል፡፡

ይህ የሳዑዲው ስምምነት በቅርፅ በኤርትራ ከተደረገው ስምምነት የተሻለ ሲሆን፣ ስምምነቱ የተፈረመው በጅዳ ሳዑዲ ዓረቢያ መሆኑን በማተት በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በዓረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ሁለት ሁለት ዋና ቅጅዎች መዘጋጀታቸውን፣ ልዩነት ሲፈጠርም የእንግሊዝኛው ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ያትታል፡፡ ይህ የመጨረሻ ይዘት የት እንደተፈረመ ከመግለጽ ውጪ በኤርትራ በተደረገው ስምምነት ላይ አልተጠቀሰም፡፡

በኤርትራ የነበረው ስምምነት አስገዳጅ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ተደርጎ የተፈረመ ቢሆንም፣ የሳዑዲው ስምምነት ተመሳሳይ ይዘት ኖሮት መዘጋጀቱ ለምን የሚል ጥያቄን አስነስቷል፡፡

‹‹እነዚህ ስምምነቶች አሁን ሰላም ስለሆንን መፈረማቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ችግሮችን በመደመር ተሻግረናቸዋል፣ ወዘተ. በሚሉ ምክንያቶች ሳይፈተሹ መታለፍ የለባቸውም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1993 ያልተፈረሙ የስምምነት ዓይነቶች  አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ከችግር ነፃ የሆኑ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀደሙትንና ዛሬም አስገዳጅ ተፈጻሚነት ያላቸውን ስምምነቶች አውጥቶ፣ አሁን እየተፈረሙ ካሉት ጋር እንዳይጣረሱና ለወደፊትም ችግር እንዳይፈጥሩ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሰነዶቹም ለሕዝብ ይፋ ሆነው ጥናቶች እንዲደረጉባቸውና ሙያዊ አስተያየቶች እንዲሰጡባቸው ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያውና መምህሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ያኔ በጫጉላ ስሜት የተደረጉ ስምምነቶች ሕጋዊ መሠረት ሳይኖራቸው ሥርዓት ያጣና የመንግሥት ባህርያትን ያልተላበሰ ስምምነት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ይኼንን ልማድ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻል አለብን፡፡ ብሔራዊ ጥቅማችንን እንዴት እያስጠበቁ እንደሆነ የማወቅ መብት አለን፤›› ብለዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል እ.ኤ.አ. በ1993 የተፈረሙ ስምምነቶች ዓላማ አድርገው የተነሱት ለሁለቱ አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት፣ የሁለቱ ኢኮኖሚዎችና ማኅበረሰቦች ወደ ላቀ ትብብርና ውኅደት አድገው ሁለቱ አገሮች በሚኖራቸው ቆራጥነት ወደ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርና የፖለቲካ ትብብር ማሳደግ ነው፡፡ የአሁኑ ስምምነትም ይኼንኑ ስሜት ይዞ እንደሚቀጥል የሚናገሩ ባለሙያዎች አልጠፉም፡፡

እነዚህን ስምምነቶች በማስመልከት ጽሑፍ የጻፉት ታዋቂው ኤርትራዊ ደራሲ ዓለምሰገድ ተስፋይ፣ በ1993 የተፈረመው ስምምነት በወቅቱ የነበረው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነትና ትብብር መንገሥ ምስክር ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ እንቅፋቶችን ማስወገድ፣ የጉምሩክ ፖሊሲዎችን ማጣጣም፣ ብሎም ኢትዮጵያ የአሰብንና የምፅዋ ወደቦችን በነፃ እንድትጠቀም የሚደነግግ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በላይ የሰዎች ነፃ ዝውውር ለመፍቀድና የኢሚግሬሽን ሕጎችን ለማጣጣም፣ በፋይናንስና በገንዘብ ፖሊሲ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ለመተባበርም ስምምነቶች ተደርገዋል ሲሉ ያክላሉ፡፡

ከዚህ ስምምነት በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚኒስቴሮች ኮሚቴዎች አማካይነት በርካታ ስምምነቶች ተፈርመው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ እምቢተኝነትና እብሪተኝነት የትኛዎቹም ስምምነቶች ተፈጻሚነት እንዳይኖራቸው ሆነዋል ይላሉ፡፡ ኤርትራ ለሰዎች ዝውውር እንዲያመች ጥምር ዜግነትን ፈቀደች፣ የተቀላጠፈ የንግድ ግንኙነት እንዲኖር ታክስ እንዳይጣል አደረገች፣ የገንዘብ ፖሊሲን በሚመለከት የኢትዮጵያን ብር ለመጠቀም ወሰነች (በኋላ የራሷን ገንዘብ ናቅፋ ብታትምም)፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በድንበሯ የኤርትራ ገንዘብ ለመገበያየት እንዳይውል አገደች፣ ጥምር ዜግነትን ከለከለች፣ ከኤርትራ ለሚገቡ ዕቃዎች ተደራራቢ ታክሶች እንዲጣሉ አደረገችና ስምምነቶቹን ሁሉ ጣሰች ሲሉ ያትታሉ፡፡

አሁንም ካሁን ቀደም የነበሩ ስምምነቶች ለምን ተፈጻሚ ሊሆኑ አልቻሉም የሚለው ተጠንቶና ተገምግሞ ለአዳዲሶቹ ስምምነቶች እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ተለይተው መቀመጥ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በሌላ ወገን ይህ ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት የሁለቱ አገሮች የተናጠል ተነሳሽነት ያመጣው ነው ቢባልም፣ ይህ ዕርቅ የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አገሮችን ቀልብ የሳበና አልፎ አልፎም የሁለቱ ጥረት ያመጣው ለውጥ እንደሆነ ይወሳል፡፡

ሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ ልዑል ከሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠልም መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በሳዑዲ ዓረቢያ ለስምምነት ያቀኑት ሁለቱ መሪዎች፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ሳልማን የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ተሸልመዋል፡፡

እንኳን እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሉ ደሃና ደካማ አገሮች ይቅርና ትልልቅ የዓለማችን አገሮችም ጭምር ከተፅዕኖ ነፃ ሆነው በራሳቸው እንዲህ ያሉ ትልልቅ ውሳኔዎችን ያደርጋሉ ለማለት እንደማይቻል የሚያስረዱት የሕግ መምህሩ ደረጀ (ዶ/ር)፣ ሁለቱ አገሮች የሚገኙበት ቀጣና ስትራቴጂካዊ በመሆኑና በርካቶች የሚረባረቡበት ስለሆነ፣ በዚህ አካባቢ በሚፈጠር ትልቅ ክስተት ዓይናቸውን ከዚህ  ለማይነቅሉት የምዕራብና የባህረ ሰላጤው አገሮች ብዙ ጉዳይ ሊለውጥ የሚችል ነበር ይላሉ፡፡

የትኛውም አገር ፖሊሲ ሲያወጣ ተለዋዋጭና ቋሚ ጉዳዮችን ለይቶ የሚያዘጋጅ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ግንኙነት ቋሚ ተደርጎ የሚወሰድ ጉዳይ እንደነበር፣ ይህ ተገልብጦ በቀጣናው ፍላጎት ያላቸው አገሮች የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲያቸውን የሚያስቀይር፣ የኃይል አሠላለፎችንም ሊለውጥ የሚችል፣ ብሎም በቀጣናው ትልቅ የኢኮኖሚ ውህደትን በማምጣት ጠንካራ ኃይል ለመፍጠር የሚችል ክስተት በመሆኑ የበርካቶችን፣ በተለይም የዓረብ አገሮች ቀልብ ሊስብ የቻለ ክስተት እንደሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ምንም እንኳን የውጭ ተፅዕኖ ቢኖርም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተፋጦ መቆየት አይበጀንም የሚለው አቋም ትልቅ ሚና የተጫወተና ነገሮች በፍጥነት እንዲጓዙ ያደረገ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ በሁለቱ አገሮችም ሆነ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር የምታደርጋቸው ስምምነቶች በግልጽነት ለሕዝብ ይፋ ሆነው መቅረብ እንዳለባቸው፣ አገሪቱ ወደፊት በዓለም አቀፍ ሕግ የምትዳኝበት ስለሆነ በጥንቃቄ ተመዝኖ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አስከፊ ውጤቶችን ከወዲሁ ማስወገድ ያስፈልጋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ይኼንን ሚናቸውን በጉልህ መጫወት እንዳለባቸውና መረጃን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ልምድ እንዲያዳብሩም ያሳስባሉ፡፡

ተመሳሳይ ስምምነቶችን በሁለት አገሮች የተፈራረሙት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት በሁለቱ አገሮች ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በተለይ ኤርትራና ጂቡቲ ብሎም ጂቡቲና ሶማሊያ ያሉበት ፍጥጫ አብቅቶ አገሮቹ ወደ ዕርቅ እንዲመጡም ያስቻለ ነው፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከ15 ዓመታት በኋላ የኤርትራን ምድር የረገጡ ሲሆን፣ በአገሮቹ መካከል የነበረው ቁርሾም እንዲቀር ተስማምተዋል፡፡ ራስ ዱሜራ በተባለች ተራራማ ሥፍራ ምክንያት የጦርነት አፋፍ ላይ የነበሩት የጂቡቲና የኤርትራ መንግሥታትም፣ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጂቡቲ ጉብኝት በኋላ ረገብ ብለዋል፡፡ በመሪ ደረጃም የሁለቱ አገሮች ፕሬዚዳንቶች ከዓመታት በኋላ በሳዑዲ ዓረቢያ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል፡፡

ይሁንና በደፈናው እየተደረጉ ያሉ ስምምነቶች ሕዝቡን ያገለሉና ታሪካዊ ተወቃሽነትን የሚያስከትሉ እንዳይሆኑ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -