ኢንዲያን ዝሆን በእስያ ከሚገኙት የሱማርታን፣ የሲሪላንካና የቦርኒዮ ዝሆኖች ዝርያ የሚመደብ ነው፡፡ የኢንዲያን ዝሆን ህንድን ጨምሮ በእስያ ከሚገኙ የዝሆን ዓይነቶች በብዛቱ ይጠቀሳል፡፡
ይህ ዝሆን ባንግላዲሽን፣ ካምቦዲያን፣ ቻይናን፣ ላኦስንና ማሌዥያን ጨምሮ በሁሉም የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 20 ሺሕ የሚደርሱትም የዱር ናቸው፡፡
የኢንዲያንን ዝሆን በማላመድ ለቱሪስት መስህብነትና ለግልቢያ ይውላል፡፡ በጥንካሬያቸውና ለሰው ልጅ ባላቸው ቅርበት የሚታወቁት የኢንዲያን ዝሆኖች ከአፍሪካው ጋር ሲነፃፀሩ ጆሮዋቸው ያነሰ ሲሆን፣ የአከርካሪ አጥንታቸውም የጎበጠ ነው፡፡ ግዙፍም ናቸው፡፡
አንዲት ዝሆን አሥር ዓመት ሲሞላት መውለድ ትጀምራለች፡፡ የምትወልደውም አንድ ነው፡፡ የተወለደው ዝሆን ከእናቱ ጋር አምስት ዓመት ቆይቶ ከወንዶቹ ዝሆኖች ጋር ምግብ ለማደን መውጣት ይጀምራል፡፡
እነዚህ ዝሆኖች ለዝሆን ጥርስ ሲባል ስለሚታደኑና በየአካባቢው ባለው የደን ጭፍጨፋ ምክንያት ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱን ኤቱዜድ አኒማልስ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡