Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅፉዞ! ፉዞ!

ፉዞ! ፉዞ!

ቀን:

በሀያ አምስት ዓመት

ዕድሜው ሽበት ወሮታል፡፡ ወጣት እንጂ አዛውንት አለመሆኑ ግን ከፊቱ ወዝ ይታወቃል፡፡

አይናገርም፤ አይጋገርም፡፡ ብቻውን መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ይውላል፡፡ ሲደክመው ካገኘው ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ ያዛል፡፡ እስመጣለት ድረስ ፊቱን በመዳፉ ያሻሸዋል፡፡ ዓይኖቹን በጣቶቹ ጫፍ ጫን ጫን ይላቸዋል፤ እንቅልፉ መጥቶ ለመንቃት እንደፈለገ ሁሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሁልጊዜም ቢሆን በእንቅልፍ መሰል ሰመመን ውስጥ የሚኖር ይመስላል፡፡ ዓይኖቹ ውጫዊ ነገር የሚያዩ ቢመስሉም ውጫዊ ነገር አያዩም፡፡ ዘወትር የሚመለከቱት ወደ ውስጥ ነው፤ ወደ አእምሮው ውስጥ፤ ወደ ሕሊናው ውስጥ፤ በአጠቃላይ ወደ ሕይወቱ ውስጥ፡፡

በሰው መሃል ቢሆንም እንኳ ዘወትር ብቸኛ ነው፡፡ ሻይ ቤት በሚገባበት ጊዜ አሳላፊው ወይም አሳላፊዋ ሲመጡ ‹‹ሻይ›› ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል አይተነፍስም፤ በውስጣዊ ሕይወቱ ሰምጦ ስለሚቀር፡፡

ሻይ ቤት ውስጥ ያገኙትና ከሱ ራቅ ብለው የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ስለሱ ያወሩ ጀመር፤ አንድ ቀን፤

‹‹ታውቀው የለም?››

‹‹ማንን?››

‹‹ያን ወጣት አዛውንት …. ወይንስ አዛውንቱ ወጣት ልበለው? ለወሬ የማያመች አሳዛኝ ሰው! አሁን ማን ይሙት በሀያ አምስት ዓመት ዕድሜው ሽበት ያበቀለ ሌላ ሰው ታውቃለህ?››

‹‹ኦ! እሱን ማለትህ ነው! ለመሆኑ ስለሱ የሚወራው እውነት ነው እንዴ?››

‹‹ስለሱኮ ብዙ ነገር ይወራል፡፡ የትኛውን ማለትህ ነው?››

‹‹ከዚህ ያደረሰው የሴት ፍቅር ነው የሚባለው፡፡››

‹‹እውነት ነው እንጂ! እኔኮ ደህና አድርጌ አውቀዋለሁ፡፡ መምህር ነበር፡፡ እንዴት ያለ ደስተኛ ሰው ነበር መሰለህ ሳቂታ … ተጫዋች! በዚያ ላይ ለሴት የማይንበረከክ ኩሩ ወጣት ነበር፡፡ በኋላ ጣለበትና አንዷን ተማሪ ወድዶ ቁጭ! እሷ ደሞ የሰይጣን ቁራጭ ነች…. ክልፍልፍ፡፡ አልፈልግህም አለችው፡፡ የወንድ ልጅ ኩራቱን ሰበረችበት፡፡ ከዚያ ወዲያ ሰው ለመሆን አልቻለም፡፡ እምቢ አልፈልግህም ስትለው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ መሰለው፡፡››

‹‹ደካማ ሰው መሆን አለበት!››

‹‹እንዴት?››

‹‹አንዲት ሴት ልጅ አልፈልግህም ብትለው ሌላ ሴት ልጅ አይፈልግም ኖሯል? እንዴት የዓለም ፍጻሜ የደረሰ ይመስለዋል? በጣም ደካማ ሰው መሆን አለበት፡፡››

‹‹ረ አይጣል በል! ከጣለኮ ይኸው ነው! ፉዞ ሆኖ መቅረት!››

‹‹ፉዞ! ፉዞ!››

  • ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ‹‹ሽኩቻ›› (1987)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...