በተሾመ ብርሃኑ ከማል
መግቢያ
የኤርትራውያን ሙስሊሞች ከሃያ ዓመታት በኋላ የዓሹራ በዓልን መስከረም 10 ቀን 2011 ከኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻቸው ጋር አብረው ለማክበር በቅተዋል። በዓሉ ሁለቱ ወንድማማች ሕዝብ ዳግም የተገናኘበት ነው፡፡ ለመሆኑ የዓሹራ በዓል ለምን በትግራይ በአልነጃሺ መስጊድ ይከበራል? እነማንስ ያከብሩታል? እንደምንስ ይከበራል?
ከአዲስ አበባ 800 ኪሎ ሜትር ርቆ፣ ከአስመራ ደግሞ 160 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው አል ነጃሺ (ነጋሸ) ተብሎ በሚታወቀው ጥንታዊ ከተማ ከጥንት ጀምሮ ከመላው ኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከጂቡቲ፣ ከዓረብ አገሮች እየመጡ ዱዓ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። ለምሳሌ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢማም አህመድ ኢብራሂም ኤርትራን ለማስገበር በሐውዜን (ሐረማት) በኩል ሲያልፉ ቱርኮችና የመኖች አልነጃሺን አይተውና ጸሎት አድርገው እንዲያልፉ ጠይቀዋቸው እንደነበረና ኤርትራን ካስገበሩ በኋላ እንደጎበኙ ዓረብ ፈቂ የተባለ ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው አስፍሯል፡፡
ኤርትራውያን ከጥንት ጀምሮ በነጃሸ መስጊድ የዓሹራን በዓል ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር በጾምና በጸሎት ሲያከብሩ የነበረ ሲሆን የተቋረጠው ባለፉት 20 ዓመታት ነው። በቅርቡ በዘመናዊ መልክ የታደሰው መስጊድና 500 በላይ ሰው የሚያስተናግደው የቀድሞው አዳራሽ የተሠራው በኤርትራውያን ሲሆን በተለይም የሰሜናዊ ትራንስፖርት ባለቤት ሐጂ ዓብዱና ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል። እስከ አሁንም ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸው በሺ ለሚቆጠር ሰው መስተንግዶ ያደርጋሉ። ነጃሺ የሚከበረው ከሐጅ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ሓጃጆች ካልሄዱት ጋር ጭምር እየተገናኙ የልምድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር። በነጋሺ በዓል በርካታ ኢትዮጵያውያን መጥተው ዱዓ ስለሚያደርጉም ጠቀሜታው የላቀ ነው። በኔ እምነት ጥንት እንኳን ባይኖር ዛሬ የሙስሊሞችን አንድነት ለማጠናከር ሲባል እንደገና ተጠናክር መቀጠል ያለበት ነው። ለመሆኑ ይህን ታላቅ የኢትዮጵያና የዓለም ቅርስ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች እየተገናኘን ካላስከበርነው ማን ሊያስከብረው ይችላል?
እርግጥ ነው የዓሹራን በዓል የማይቀበሉ አሉ። ነገሩ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ጉንጭ አልፋ፣ አኞ፣ ማለቂያ የሌለው ክርክር የሚያመጣ ነው። ዱንያ ላይም አይመለስም። ሰው አይመልሰውም። መላሹ እርሱ ብቻ ነው። የኔ ዓላማ ግን የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በሰበበ ዓሹራ መገናኘታቸው ነው። በመሠረቱ፣ በነጋሺ የዓሹራ በዓል የሚከበረው በኢራቅ ወይም በኢራን እንደሚከበረው ዓይነት ፈጽሞ አይደለም። እንደማንኛውም የዱዓ ቀን ነው። ከመላው ኢትዮጵያ የሄዱ ሙስሊሞች ከሐጃጆች ጋር ተገናኝተው ዱዓ የሚያደርጉበት እንጂ ሌላ የተለየ አይደለም። ሽርክም፣ ሙሽሪክም፣ ተሸራኪም፣ አሻራኪም የለበት። ባለማወቅ የሚፈፀም ቢኖር ደግሞ ጨዋነት በተመላበት ሁኔታ ማስተማር ይገባል። በተረፈ ሙስሊሞች ባንድ ላይ ጸሎት ማድረጋቸውና አንድ ላይ መስገዳቸው ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ለመሆኑ መካ ላይ አንድነት እየተሰገደና ዱዓ እየተደረገ አይደለም? ስለዚህ የግል አመለካከታችን እንዳለ ሆኖ ይህን ግንኙነት ጠባብ ከሆነ አቅጣጫ አይተን ባናጣጥለው መልካም ይመስለኛል።
በመሠረቱ፣ አል ነጃሺ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሙስሊሞች ቅርስ ሲሆን፣ ነብዩ ሙሐመድ የመጀመሪያውን ሶላተል ቓኢብ ወደሰገዱበት፣ ፍትሕ የሚያውቅ ንጉሥ የነበረበት፣ ለመጀመሪያ በውክልና ሚስት ወዳገቡበት፣ ኢትዮጵያ አገራችን፣ እርሷን አምነው የሚመጡ የተጎዱ ዜጎች አሳልፋ የማትሰጥ መሆኗን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወዳረጋገጠችበት፣ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደሀገራቸው እስኪመለሱ የተመላለሱበት፣ የወጡበት፣ የወረዱበት፣ የሀገር ናፍቆታቸውን በተመስጦ ያሰቡበት፣ የተወጡበት ቦታ ነው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ረቂቅና ተጨባጭ ኢስላማዊ ቅርስም ነው።
የኢትዮጵያና የኤርትራ የኢስላማዊ ተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ ታሪክ ሲነሳም በአንድ ሕዝብ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አንዱን ከሌላው መለየት የሚያስቸግርበት ሁኔታ እንዳለ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በነብዩ መሐመድ ትእዛዝ ወደ ሐበሻ የመጡ ተከታዮቻቸውና የቅርብ ዘመዶቻቸው ታሪክ ማለትም የመጀመሪያው ሒጅራ ታሪክ ቀይ ባህርን አቋርጠው ከመምጣታውም በላይ የኖሩት በሐበሻ ምድር በመሆኑ ኤርትራንም ይጨምራል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቀይ ባህር የሚመጡ ሙስሊም ዓረቦችም ወደ መሀል አገር የገቡትም ሆነ በኤርትራ የኖሩት በዚች ምድር ነው፡፡ በመሃል አገር ወደ ሁሉም አራት ማዕዘናት ድንበሮች እየሄዱ ኢስላምን እንዳስተማሩ ሁሉ ከቀይ ባህርና ከኤደን ባህረ ሰላጤ ድንበሮች ወደ መሀል አገር እየገቡ ኢስላምን ማስፋፋታቸው ይታወቃል፡፡ በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል የመጡ የዓረበያ ሰዎችም ኢስላምን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ሕይወታቸውንም፣ ታሪካቸውንም፣ ባህላቸውንም፣ ሥነ ጥበባቸውንም፣ ንግዳቸውንም ቀስ በቀስ እንዳሰራጩ ሲታወቅ በተለይም በባህር ድንበሮች አካባቢ የነበረው ከመሃሉ የበለጠ ሥር እንደሰደደ ይታወቃል፡፡ የኢስላምን ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶች ታሪክ ስናወሳ በቅድሚያ ኢስላም እንደምን ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደገባ በአንድነት ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡
አሕመድ ሒፍኒይል አል–አዝሃሪ ‹‹ጀዋሂሩል ሑሳን፣ ፊ ታሪቒል ሐበሺን›› በሚል ርዕስ በጻፉትን እንደሚሉት ‹‹የሐበሻው ንጉሥ የነጋሺ አገር ከቀይ ባሕር ዳርቻ በምፅዋና በሱዳን የባህር ዳርቻ መካከል በሚገኝ በሳህል ውስጥ ገባ ብሎ በሚገኝ ቦታ ሱዋንኪን ነው፡፡ ስዋንኪን ከምፅዋ ከፍ ብሎ የሚገኝ የሱዳን ግዛት ሲሆን የጥንት ኢትዮጵያውያን ለሐጅ ወደ መካ የሚጓዙት በዚህ ወደብ ጭምር እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ያኔ የአክሱም መንግሥት መሪ የነበረው ሰው የዚያ አካባቢ ተወላጅ ሲሆን የንጉሡም ልጅ አንድ ነጋሺ ወይም አስሐማ ኢብን አብርሃ ነበር፡፡ እርሱ ሥልጣን ላይ እንደተቀመጠም ብዙ ጥሩ ሥራዎችን በማከናወንና ፍትሕን በማንገሥ ዝናው ከምድረ ሐበሻ አልፎ በዓረቢያ አገሮች የታወቀ ነበር፡፡ ንጉሥ አስሐማ በሥልጣን ላይ በነበሩት ዘመን ነቢዩ ሙሐመድ ከምድረ ዓረቢያ ተገኙ፡፡ እርሳቸውም የንጉሥ አስሐማን ዝናን ያውቁ ስለነበር ተከታዮቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ‹በሐበሻ መሬት ውስጥ ፍትሕ የማይጓደልበት ንጉሥ አለ›› ብለው ላኩ፡፡
ኢስማዒል ሙኽታር ከአሥር ዓመታት በፊት በዋሺንግተን ስድስተኛው ዓመታዊ የኤርትራ ሙስሊሞች ምክር ቤት ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳቀረቡት የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች ወደሐበሻ የመጡት በሦስት አቅጣጫዎች ሲሆን የመጀመሪያው የነብዩ ሙሐመድ ልጅ ሩቂያንና ባለቤቷ ዑስማን ኢብን ዓፋንን የሚጨምረው 11 ወንዶችና አራት ሴቶች የሚገኙበት ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የነብዩ ሙሐመድ የአጎት ልጅ የሆኑትን ጃዕፋር ኢብን አቢጣሊብ የሚመራውና 83 ወንዶችና 18 ሴቶች ነበሩ፡፡ ሦስተኛው ሃምሳ ስደተኞችን የሚያካትት ሲሆን እነሱም የመጡት በየመን በኩል ነበር፡፡ እነዚህ ስደተኞች ወደ ሐበሻ የመጡት ማዕበል አቅጣጫቸው አስቷቸው ሲሆን የሚጓዙትም ነብዩ ወደሚገኙበት ወደ መካ ነበር፡፡ ሦስተኛው ቡድን ሐበሻ መድረሱን ሲያውቅ ከሌሎቹ ስደተኞች ጋር ለስምንት ዓመታት ኖረ፡፡ የነብዩ ወዳጆች በምድረ ሐበሻ የኖሩት 13 ዓመታት ያህል ቁጥራቸውንም አንዳንድ ሰዎች እስከ 600 እንደሚደርስ ይገልጻሉ (Ibn Kathir, Albidaya wa Nihaya)፡፡ ኢስማዒል ሙኽታር ጨምረው እንደገለጹት፣ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች የመጡበት የባህር መስመርና የኖሩበት ቦታ የት እንደሆነ በትክክል መግለጽ ባይቻልም የኤርትራው ሙፍቲ ሸኽ ኢብራሂም ሙኽታር ዑስማን ኢብን ዓፋን ነገረኝ ብለው የተረኩትን ዓስከርን በመጥቀስ እንዳቀረቡት የገቡት በምፅዋ በኩል ሲሆን የመጡትም ከጂዳ እንደሆነ አስፍረዋል (Sabe Uthman, Tareekh Aritrea (Arabic), 1977.) ፋቲሕ ቐይዝ የታሪክ ተመራማሪውን ኢብን ሐሺምን መሠረት በማድረግ እንዳቀረቡት የነጃሺ ቤተ መንግሥት ዓባይ አጠገብ እንደነበረና ይህም ስፍራ ከተከዜ ብዙም በማይርቀው አክሱም ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሷል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከጂዛን (የመን) የዘመተው የኢማም አሕመድ ኢብራሂም መዋዕለ ዜና ጸሐፊ የነበረው ዓረብ ፈቂም የነጃሺ መቃም አሁን በሚገኝበት ስፍራ እንደነበረ ጠቅሷል (Pankhurst Richard, The Ethiopians, Blackwell Publishers, 1998.)፡፡
ምንም እንኳን ነብዩ ሙሐመድ ሐበሻን አስቀድመው ጦርነት ካልከተቱባችሁ እንዳትነኳቸው ብለው ቢያዙም ኸሊፋ ዑመር ኢብ አል–ኸጣብ በ20ኛው ዓመተል ሒጅራ ማለትም በ640 ከዳህላክ እየተነሱ ዓረብያን ይወሩ የነበሩትን ኃይሎች ለማስወገድ ሲሉ ዳህላክ ደሴትን ይዘው የነበረ ሲሆን የዐመያድ ኸሊፋዊ መንግሥትም በ84ኛው ዓመተል ሒጅራ ማለትም በ702 ላይ የባህር ወንበዴዎች መናሃሪያ ሆናለች በሚል ሰበብ ዳህላክን ቅኝ ግዛት አድርገዋል፡፡
ዑመያዶች ግብፅን በመያዝም በራሷ በግብፅ፣ በሱዳን፣ በቤጃ፣ በአሁኒቱ ኤርትራ ኢስላምን ማስፋፋት ጀመሩ፡፡ በሐሺማውያንና በዑማያዶች መካከል፣ በኋላም በዓባሲድና በዓለዋይት መካከል ጦርነት ሲነሳም በርካታ ስደተኞች ከሒጃዝ ወደ ምድረ ሐበሻ እንደመጡ ይታወቃል፡፡ ሣቤ ዑስማን እንደሚሉትም እነዚህ ከሒጃዝ የመጡ ስደተኞች በምፅዋ ምሽግ እንደሠሩና ከአካባቢው የቤጃና የኩሽ ሕዝቦች ጋር እየተጋቡ መኖራቸውን አስፍሯል (Sabe Uthman, Tareekh Aritrea (Arabic), 1977)፡፡ የምፅዋ በግብፆች መያዝ በኋላም የአጼ ልብነድንግል በኢማም አሕመድ ኢብራሂም መሸነፍ በዚያ አካባቢ ኢስልም እንዲስፋፋ አመቺ ሁኔታን ፈጠረለት (Sabe Uthman, Tareekh Aritrea (Arabic), 1977)፡፡
ምፅዋና ሐርቂቆ የኦቶማን ናኢቦች ተሹመው ሲገዙም በርካታ ኢስላም ምሁራን ከዓረብ ለመምጣት እንዲችሉ አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ምፅዋንም ኢስላማዊ ማዕከል አደረጓት፡፡ በርካታ ኢስላምን ለማወቅ የሚፈልጉ የመሃል አገር ሰዎችም ወደዚች ስፍራ መጉረፍ ጀመሩ፡፡ በርካታ ውብ መስጊዶችና መድረሳዎችም ተገነቡ፡፡
የኩነባ የሃይማኖትና አባቶችና ሊቃውንት እንደሚሉት ከሁሉ አስቀድሞ ከጥንት አያቶችና ቅድመ አያቶች ሲወርድ ሲዋረድ በነበረው ታሪክ መሠረት የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ነጋሺ ሲያልፉ ለተወሰነ ጊዜ የተቀመጡበት፣ የተቀበሩበት ቦታ የሚገኘው በዚህ ቦታ (ኩነባ) ብቻ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች ጋር የተያያዙ ኅብረተሰቡ በአንድነት የሚያምንባቸው መኖሪያዎች፣ ተምርን ጨምሮ ያሉ የአትክልት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተለያዩ የዓረብ የታሪክ ጸሐፊዎች የመጀመሪያው ሒጅራ ወደ ሐበሻ እንደሆነ፣ በቁጥር የሚታወቁ የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች እንደመጡ፣ የተወሰኑት እንደቀሩ፣ የተወሰኑት ደግሞ እንደሞቱ ጽፈዋል፡፡ በተለይም የታሪክ ጸሐፊዎቹ ከራሳቸው ከስደተኞቹ መረጃ በመሰብሰብ በጻፉት ታሪክ ውስጥ የተጠቀሱት ስፍራዎችም በኩነባ ወረዳ በተለይም በለሌገዲ፣ በዒሲ፣ በፊሾና በአጽቢ ደራ ላይ እንደሚገኙ መረዳት ይቻላል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ላለፉት 1400 በሕዝቡ ሲተላለፉ የነበሩ አፈ ታሪኮችና በዓረብ የታሪክ ጸሐፊዎች የተተረኩትን በዘመናዊ መንገድ መርምሮ መረዳት ይቻላል፡፡
ያም ሆኖ ግን በሐበሻ ምድር ስለነበሩት የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች በርካታ የታሪክ ምንጮችን በመጥቀስ ከጻፉ የታሪክ ሰዎች አንዱ ዓሊ ሸኽ አሕመድ ኢባብኩ (ዶ/ር) የተባለ ጸሐፊ ‹‹ሙሐዓሊም አል ሙሐደረተይን ኢላአርዱል ሐበሽ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፋቸው በዓፋር ውስጥ አስራ አምስት የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች በውሃ መመረዝ ምክንያት እንደሞቱ ገልጸዋል፡፡
እነሱም፡– አል ሙጠሊብ ኢብኑ አዝሃር፣ ቢን ዓብዱ ዓውፊ (አዝሃርይ–ጎሳ)፣ ዓብደላህ ኢብኑ ሙጠሊብ ኢብኑ አዝሃር፣ ሪጣታ ቢንት ሐሪስና አምስቱ ልጆቿ፣ ዘይነብ ቢንተል ሐሪስ ኢብኑል ኻሊድ ሙሳ ኢብኑ ሐሪስ ኢብኑል ኻሊድ ዓይሻ ቢንተል ሐሪስ ኢብኑል ኻሊድ፣ ፋጡማ ቢንል ሰፍዓን ቢን ኢመያ፣ ኸጣብ ኢብኑ ሐሪስ ኢብኑል ኻሊድ አሱክራን ቢን ዓምር ቢን ብዱሸምስ፣ ዓምር ቢን ዑመያ ኢብኑ ሪስ ኢብኑል ኻሊድ፣ ኢብን አሳድ፣ ሐጢብ ቢኑል ሐሪስ፣ ዓብደላ ቢኑል ሐሪስ፣ ዑርዋ ቢን ዑዛ፣ ቢን ሐርሳን፣ ጡለይ ቢን አዝሀር፣ ዑሙ ሐርመላ ቢንት ዓብዲል አሳድ፣ ናቸው፡፡
በታሪክ ጸሐፊው መረጃ መሠረት እነዚህ ሰዎች የሞቱት ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሲሆን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የሞቱትም የተመረዘ ውሃ ጠጥተው ነው፡፡ ነገር ግን ቦታው የት እንደሆነ አይጠቅስም፡፡ በኩነባ ደግሞ በተለይም ዒሲ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ‹‹የሱሐባዎች መቃብር›› ተብሎ የሚታወቅ ስፍራ አለ፡፡ በዚህም ስፍራ ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁ አምስት የመቃብር ስፍራዎች አሉ፡፡ በነዚህ ስፍራዎችም የዓፋር ሙስሊሞች የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች የተቀበሩባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን በመቀበል ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ ሰደቃ ያወጡ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚያ የመቃብር ስፍራ ውሃ የሚቋጥር ጎድጓዳ ስፍራ አለ፡፡ በዚህም ጎድጓዳ ስፍራ ውሃ የሚቋጠረው ውሃ አንድም እባብ ሊመርዘው ወይም በእባብ የተመረዘ እንስሳ ገብቶ ሊመርዘውና ሰዎቹም ያንን የተመረዘ ውሃ ጠጥተው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ለታሪክ ሽሚያ ሲባል የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች መጡት ‹‹በኛ በኩል አድርገው ነው›› ሲሉ ይሰማል፡፡ በዚህም መሠረት በዘይላ በኩል አድርገው መጡ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ በፑንት ላንድ በኩል እንጅ በዘይላዕ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ በታጁራ በኩል መጡ የሚሉ ቢኖሩ፣ በታጁራ ሳይሆን የመጡት ዳህላክ ደሴትን ተረማምደው በምፅዋ በኩል አድርገው በሰነዓፈና በዓጋመ መሬት አድርው በሰሜን በኩል መጡ ይላሉ፡፡
የኩነባ ሰዎች ደግሞ የመጡት ሚዕዲር ተብላ በምትጠራው ወደብ ሲሆን በዚህ ለማለፋቸውም ከወደብ ጀምሮ እስከነጋሺ የሚደርስ ተከታታይ መረጃዎች አሉ በማለት ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ በእርግጥም የተከታዮቹ አሻራ በተከታታይ የሚገኘው በኩነባ በኩል ነው፡፡ የሌሌገዱ፣ የዒሲ፣ የፊሾ፣ የአጽቢ ደራ መቃብሮች የሚመሰክሩትም ይህንኑ ነው፡፡ ይልቁንም እነዚህ ስፍራዎች ከወደብ ጀምሮ በእግር መንገድ ቢለኩ ከሁለት ቀን እስከ ሦስት ቀን የሚወስዱ ሲሆኑ በተለይም ከሌሌገዲ፣ ዒሲ፣ ፊሾና ዓጽቢ ደራ ያሉ መንገዶች ከአምስት እስከ አሥር ኪሎ ሜትሮች የሚራራቁ ናቸው፡፡ በተለይም ዐጽቢ ከሚገኘው የሱሐባዎች መቃብር እስከ ነጋሽ ድረስ ገረብ ሕዳርና ጓንጓ የሚባሉ ወንዞች ሁለቱንም ወንዞች ከሁለት ሰዓትና ሦስት ሰዓት የበለጠ የእግር ጉዞ በመሆኑ ንጉሡና የነቢዩ ተከታዮች በሁለት ተራሮች ትይዩ እንደነበሩ ወይም ተራርቀው እንዳልኖሩ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በጅቡቲና በሱማሊያ የሚታወቁና መሠረታቸው አንድ የሆኑ የሃይማኖት አባቶች ኤርትራና ሱማሊያ የኢትዮጵያ (የሐበሻ) አካላት እንደነበሩ አያጠያይቅም፡፡ የሐበሻ ታሪክ ሲወሳም የነሱ ታሪክ አብሮ መወሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ታሪካቸው ስለሆነ ነብዩ ሙሐመድ የቅርብ ተከታዮቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ወደ ሐበሻ ምድር ልከዋል ሲባልም በቀጥታ ይመለከታቸዋል፡፡ ከ1439 ዓመት ወዲህ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክም ታሪካቸው ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ዛሬ የሉሲ ታሪክ ሲነሳ የኢትዮጵያን ቀደምትነት እንጂ የዓፋርን ቀደምትነት ነጥሎ የሚያወሳ እንደሌለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚነገረው እንደዚህ ነው፡፡ የአክሱም ታሪክም ሆነ የአክሱም መንግሥት ቀጣይ አካል የሆነው የአልነጋሺ ታሪክም ታሪካቸው ስለሆነ የነብዩ ሙሐመድ የቅርብ ዘመዶችና ተከታዮች ወደ ሐበሻ መጥተው ነበር ሲባልም ያው ታሪካቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከነብዩ ሙሐመድ ማለፍ በኋላ በብዙ መቶዎች የሚቆጠር የእርስ በእርስ ውጊያና የሥልጣን ሹኩቻ ምክንያትም በርካታ የእስልምና ሃይማኖትና ተከታዮቹ መጥተዋል፡፡ የጦርነቱ ስፋት ሜዲተራንያን ባህርን፣ ቀይ ባህርን፣ የኤደን ባህረ ሰላጤና የፋርስን ባህረሰላጤ የሚያጠቃልል ስለነበር በዚህ ጊዜ ሕይወታቸውን ለማዳን ወደ ምድረ ሐበሻ ልዩ ልዩ ግዛቶች ወጥተው የተቀመጡት ዓረቦች፣ ፋርሶችና ቱርኮች በርካታ ናቸው፡፡ ስለሆነም በቀይ ባህርና በሜዲተራንያን አቋርጠው የመጡት በግብጽ፣ በሱዳን፣ በኤርትራና በጅቡቲ አካባቢ ሲቀመጡ፣ በኤደንና በፋርስ ባህረ ሰላጤ የመጡት ደግሞ በሶማሊያ፣ በጅቡቲና በዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ቦታዎች ተቀምጠዋል፡፡ ይልቁንም ስደተኞቹ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ትውልዳቸውን ከነብዩ ሙሐመድና ከተከታዮቻቸው አያይዘው ስለሚያቀርቡ በዚህ ረገድም ጥቅል የሆነ መረጃ እንጂ ዝርዝር መረጃ ባለመኖሩ ሁለቱም አገሮች ጥንታዊ መቃብሮችንና አፈ ታሪኮችን መሠረት በማድረግ የሱሐባዎች ቀብሮችና ታሪኮች ባለቤት እየሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ትልቁን የራሷን ታሪክ አካል በመደበቋና ደንታ ቢስነት በማሳየቷ አጎራባች አገሮች የታሪክ ባለቤት ለመሆን መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሁለቱን አገሮች እንቅስቃሴ ከልዩ ልዩ የኢንተርኔት ምንጮች ማግኘት የሚቻል ሲሆን በቅርቡም ጆናታን ሚራን የተባለ ጸሐፊ፣ ‹‹የቀይባህር ዜጎች›› (Red Sea Cities, Cosmopolitas Society and Cultural Change in Massawa በ2009) ባሳተመው መጽሐፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠቅልሎ ለኤርትራ ጀባ ማለቱን እንመለከታለን፡፡ ከዚህም መጽሐፍ በመነሳት የኤርትራ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እያቀባበለው ነው፡፡
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደሚለው የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ለስደት በመጡበት ጊዜ ባህረ ነጋሽ የተባለው ንጉሥ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አደረገላቸው፡፡ እንደደረሱም በባህር ዳርቻው ላይ ሰሓባ መስጊድ የተባለችውን አነስተኛ መስጊድ ከ1400 ዓመታት በፊት ሠሩ፡፡ ይህም በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው መስጊድ በኢስላማዊ ሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች እንደተሠራ እየመሰከረ ይኖራል፡፡ አል–ሻፊ መስጊድም ከአንድ ሺህ ዓመታት የተሠራ ሲሆን በዚህም መስጊድ ወደ ሐጅ የሚሄዱ ሰዎች ይጎበኙት ነበር፡፡ አል–ሸኽ ሐማልም ከ800 ዓመታት በፊት የተሠራ ነው፡፡ (እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 24 ቀን 2012 እንደተጻፈ)፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዓረብ ካልሆኑ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች ‹‹ሐበሾች›› ይሉና በቅንፍ ኢትዮጵያውያንና ሐበሾች በማለት ለጊዜው አስፍረዋል፡፡ ለማንኛውም ቢላል ኢብን ሪባህ፣ ዋሐሽይ ኢብን ሐርብ፣ ኡሙ አይመን (በረካ)፣ አል–ናህዲያህ፣ ሉባይናሀ፣ ኢም ዑበይስ፣ ሐሪጣ ቢነት ሙዐሚል፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሆነው ቀርበዋል፡፡ በመሠረቱ እስከ ኤርትራ ነፃነት ድረስ ሐበሻ በኤርትራና በኢትዮጵያ ተከፍሎ የሚያውቅበት ዘመን የለም፡፡ ለነገሩ ሶማሊኔት ፎረም ተብሎ የሚታወቅ ድረ ገጽ የሱሐባዎች መናሃሪያ ኤርትራ እንጅ ኢትዮጵያ አይደለችም ሲል አስፍሯል፡፡
ሰሎሞን አብርሃ የተባለ ኤርትራዊ ደግሞ ከረን ውስጥ በ650 ዓመተ ልደት የተሠራ የሰሐባ መስጊድ እንዳለ በትዊትር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ ይህም ሆኖ የበለው ሥርወ መንግሥት በኤርትራ ምድር (ከ12ተኛው -15ኛው ክፍለ ዘመን በነበረበት ጊዜ በኤርትራ የመጨረሻው ጥንታዊ መስጊድ ምጽዋ የሚገኘው የሸኸ ሐነፊ መስጊድ እንደሆነ አንዳንድ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኻቲምያው ጠሪቃ መስራች የሸኽ ሐሺም አል–ሚርቓኒ ዶሪሕ (መቃም) እዚያው ይገኛል፡፡
ከሦስቱም መረጃዎች እንደምንመለከተው በ10ኛው፣ ከ12-15ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ያለውን ጊዜ ስንወስደው ሰሐባዎች ያልነበሩበት ነገር ግን ከሊፋዎች በሥልጣን ሹኩቻ እርስ በእርስ ይዋጉ የነበሩበት ዘመን ነው፡፡ ከምፅዋ በፊት የምትታወቀው አዱሊስ እንደነበረች የሚታወቅ ሲሆን የዑማያድ ካሊፎች ከ702-750 በነበረው ጊዜ ምፅዋንና አካባቢውን ተቆጣጥረው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በዚህ መካከል ቤጃዎች በባህር ዳርቻዎች አካባቢ በ740ዎቹ ሥልጣን ይዘው የነበሩ ሲሆን በለዎች ከ12ኛው-15ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጣኑን ተቆጣጥረውት እንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ጊዜም የሸኽ ሐነፊን መስጊድ ጨምሮ በርካታ ኢስላማዊ ተቋማት መመሥረታቸው ይነገራል፡፡ ኡዝዶሙር ፓሻ የተባለው የኦቶማን ሥርወ መንግሥት የጦር አበጋዝ በ1557 ፖርቱጋላውያንን አባሮ ምፅዋንና አካባቢውን በተቆጣጠረበት ጊዜ ግን ዋና ከተማውን ወደ ጂዳ በማዛወሩ ሥልጣን ወደ በለዎች ተሸጋገረ፡፡
በኤርትራ ውስጥ የሱፊ ወንድማማችነት ሥርዓት የተዘረጋው ቀደም ሲል ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ቃዲርያ፣ አል–ኢድሪስያ፣ አል–ቲጃንያ፣ አል–አሕመድ ኢድሪስያ፣ አል–ሚርቓኒያ፣ አል–ካቲሚያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከሱፊ ወንድማማችነት ዓዲ ሸኽ፣ ዓዲ ሙዓሊም፣ ዓዲ ከቢረ፣ ዓዲ ሰይዲና ሙስጦፋ፣ ቤት አድ–ሸኽ ኢብራሂም ኸሊል፣ ፈቂ ሓረክ የሚጠቀሱ ናቸው (Nawood Mohamed Saeed, Al-Urobatu Wal-Islam Bil Qarn Al-Afriqi)፡፡ ከነዚህም ሱፊ ወንድማማችነት መንደጎች የሸኽ ሙሐመድ አልሚርቓኒ (1793) በምፅዋና በአካባቢው የላቀ ተከታይ ነበረው፡፡ ሸኽ ሙሐመድ ዑስማን አልሚርቓኒ፣ ሸኽ ሐሺም አል–ሚርቓኒ፣ የሻዚሊው አህመድ ቢን ኢድሪስ ተከታይ ነበሩ፡፡ አል ሚርቓኒ ወደ ሱዳን በመሄድ አስተምህሮታቸውን ያስፋፉ ሲሆን አል–ሐሰንን የተባለውን ልጃቸውንም በሱዳን በተለይም በከሰላና በኤርትራ ጠሪቃቸውን እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ የአልሚርቓኒ አስተምህሮትም በደጋማው የኤርትራ ግዛትና በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ትኩረት አግኝቶ ነበር (Trimingham J. Spencer, Islam in Ethiopia.)፡፡ ይህን አመለካከት ናውድ ሙሐመድ ሰዒድ የተባለው የታሪክ አጥኝም ይጋራዋል፡፡ Nawood Mohamed Saeed, Al-Urobatu Wal-Islam Bil Qarn Al-Afriqi የጣሊያን መንግሥት የሥልጣን ዘመትን ለማራዘም እንዲጠቅመው ኢስላምን አጥብቀው ከመያዛቸውም በላይ በእንደራሴዎች አማካይነት የታወቁ ሸኾች ወደ ተለያዩ ስፍራዎች እንዲዛወሩ በተለይም እንደምጽዋ፣ ዳህላክ፣ ሐርቂቆ፣ ኢምበረሚና ከመሳሰሉት ኢስላማዊ የትምህርት ማዕከላት ወደከረን፣ ሳህል፣ ባርካ፣ ከሰላ፣ ሐባብ፣ ቤንአሚር ስፍራዎች እንዲሄዱና አስተምህሮታቸውን እንዲያስፋፉ፣ እግረመንገዳቸውም ሕዝቡ የጣሊያን አገዛዝ እንዲቀበል እንዲያደርጉለት ይገፋፋ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ከ1897-1907 በኤርትራ የጣሊያን እንደራሴ ፈርዲናንዶ ማርቲኒ አንዱ ነው፡፡ ይህ ሰው እጅግ የታወቁት ሰይድ ሐሺም አልሚርቓኒ ከምፅዋ ወጥተው ወደ ተለያዩ የኤርትራ ግዛቶች እንዲያስተምሩ ጥረት አድርጓል፡፡ ፈርዲናንዶ ማርቲኒ ያሰበውን ያህል ባይሳካለትም ሰይድ ሐሺም አልሚርቓኒ በኤርትራ ምድር ሳይወሰኑ የኢትዮጵያን ሸኾችንም ስለደግ አገዛዙ እንዲመሰክሩለት ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ይልቁንም የሰይድ ሐሺም አልሚርቓኒ የሆኑት ሰይድ ዓሊ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው ከሰላ ውስጥ ከፍተኛ ታዋቂነት ስለነበራቸው ከሳቸው ጋር በመነጋገር የፖለቲካ ሚና እንዲኖራቸውም ጥረት ያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሰይድ ሐሺም አልሚርቓኒ በ1901 ሲያርፉም አስከሬናቸውን ወደከረን እንዲሄድ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም የሚሻለው መቃም ማሠራት መሆኑን በመረዳት ይህን አማራጭ ወሰደ፡፡ ሰይድ ሐሺም አልሚርቓኒ እንዳለፉም በምትካቸው ሰይድ ዓሊ ያሕያ አፈዲ ተተኩ፡፡ በሳቸውም ቢሆን ብዙም የተሳካ ውጤት አልተገኘም፡፡ ቀጥሎም በአጎታቸው ልጅ ማለትም የሰይድ አቡበከር አልምርቓኒ ልጅ የሆኑት በሰይድ ጃዕፈር ቢን ባሪክ፣ ቢን ጃዕፈር፣ ቢን ቢን ሙሐመድ ዑስማን አል–ሚርቓኒ በኩል ጥረቱን ቀጠለ፡፡ ሰይድ ጃዕፈር ቢን ባሪክ፣ ቢን ጃዕፈር፣ ቢን ቢን ሙሐመድ ዑስማን አል–ሚርቓኒ ከምፅዋ ወደከረን ሄደው ኢስላማዊ ትምህርት ለማስፋፋት ፈቃደኛ ሲሆኑም የሰይድ ሐሺምን መቃም በከረንና በሑጢሞሎ አሠራ፡፡ የከረኑን መስጊድም ዘመናዊ አደረገው፡፡ በሰይድ ጃዕፈር ቢን ባሪክ፣ ቢን ጃዕፈር፣ ቢን ቢን ሙሐመድ ዑስማን አል–ሚርቓኒ ወደ ከረንና ወደ ሳህል ኢስላማዊ ትምህርት መስጠት በመቻላቸውም ከሰላ በነበረው የኻቲሚያ ጠሪቃን አስተሳሰሩ፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያም ስማቸው መነሳት ጀመረ፡፡ እየመጡም ይጎበኟቸው ጀመር፡፡ ይሁንና የዓዲሸኽ ማለትም የምሥራቅ ኤርትራ የሃይማኖት አባቶች ፈርዲናንዶ ማርቲ ያደርገው የነበረውን ጥረት በበጎ ዓይን አልተመለከቱትም፡፡
ነገሩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው በኤርትራ የኢስላም መስፋፋትና ከኢትዮጵያ ሙስሊም ያላቸው ግንኙነት ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ Arnold Thomas Sir, The spread of Islam in the world, Goodword ጣሊያን ኤርትራን ቅኝ ግዛት ካደረገ በኋላ ግን ቅኝ ገዥነትና ዘረኝነት ባያይልበት ኖሮ በኢስላም ላይ እምብዛም ተፅዕኖ አላደረገም፡፡ ጣሊያኖች በተለይም የአል–ሚርቓኒ ተከታዮችን የበለጠ ያበረታቱ ነበር፡፡ ወደግብጽ በመሄድ በአልአዝሃር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የእስልምና ዕውቀት እንዲገበዩም አግዟቸዋል፡፡
በኤርትራ ውስጥ እንደመስጊድ፣ መቃብር፣ ዶሪሕ፣ ዛውያ፣ መኖሪያ ቤት የመሳሰሉ ጥንታዊ ተጨባጭ ቅርሶች ሲኖሩ በተለይም በምፅዋና በዳህላክ የሚገኙ ቅርሶች ድንቅ ናቸው፡፡ ከቤቶቹ በኦቶማን ሥርወ መንግሥት የተሠሩ የማሕሙድ መሐመድ ነሃሪና የአቡ ሐምዳን ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጥበብ የተቀረጹ የእንጨት በረንዳዎች፣ መስኮቶችና መዝጊያዎች ያሏቸው የቱርካውያንና የግብፃውያን መኖሪያ የነበሩ ቤቶች አሉ፡፡ አቡ ሐኒፍ የተባለው እጅግ ውብ መስጂድ በሐርቂቆው ሸኽ በሸኽ ሙዒድ 1203 የተገነባ ሲሆን፣ መስጅድ ሐማል ተብሎ የሚጠራው ደግሞ በሸኽ ዑመር ኢብን ሳዲቅ አል–አንሷሪ በ1543 የተሠራ ነው፡፡ መስጂድ ሻፊዒ በሸኽ አሕመድ ኢድሪስ አል–መሥሪ የተመሠረተ ነው፡፡ ከመስጊድም ከ500 ዓመት በፊት የተሠራው የሸኽ ሐነፊ ይገኛል፡፡ ከሱ በፊት እንዲያውም ኦቶማኖች ከመግባታቸው እንደተሠራ የሚነገርለት የሻፊዒ መስጊድ ከሐነፊ መስጊድ መቶ ሜትር በስተሰሜን ርቆ ይገኛል፡፡ በመሠረቱ የሚርቓኒ መስጊድም ሆነ የሸኽ ሐማል መስጊድ ከ2000 ካሬ ሜትር ባልሰፋ ቦታ የሚገኙ ሲሆኑ ለምን በቅርብ ርቀት ተሠሩ ብለን እንድንጠይቅ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
በዳህላክ ደሴትና ኢምበረሚ በተባለው ወደብ የተለያዩ ኢስላማዊ ተጨባጭ ቅርሶች ሲኖሩ በተለይም በኢንበረሚ የሚገኙት የዓዲ ሸኽ መስጅዶችና መቃሞች ጥንታዊ ባለ ቁባ መስጊዶቹና በጥንታዊ ዓረብኛ የተጻፉት መግለጫዎች ጥሩ የታሪክ ምንጮች ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ ከሚጠቀሱት መሻኢኾች አንዱ ሸኽ አል አሚን ቢን ሐሚድ ቢን ናፉዐታይ ሲሆኑ፣ እሳቸውም በመላው ኤርትራና በሰሜን ኢትዮጵያ ይታወቃሉ፡፡ ምጽዋ አካባቢ ሑቲሞሎ በሚባለው ስፍራም የሸኽ አል አሚን ቢን ሐሚድ ቢን ናፉዐታይ ቤተሰብ፣ የሸኽ ሙሐመድ ዑስማን ቢን ሙሐመድ ዓሊ የኢምበረሚው ሸኽ የልጅ ልጅ መስጅድና መቃም ይገኛል፡፡ በመሠረቱ በኤርትራ በርካታ መቃሞች ሲኖሩ የጃዐፈር አል–ጠያር፣ የሸኽ አቡበከር አል ሲዋሂ፣ የሸኽ ሐሚድ፣ የአል–ነጃሺ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የአብዱልቃድር አል–ጀይላኒ፣ የሸኽ አል አሚን ቢን ሐሚድ ቢን ናፉዐታይ፣ የልጅ ልጃቸው የሸኽ ሙሐመድ ቢን ዓሊ ቢን አል–አሚን በምጽዋ፣ በሐርቂቆ፣ በኢምበረሚ፣ በአሥመራና በሌሎችም ስፍራዎች እንደነበር ሲታወቅ የሸኽ አልአሚንም በገዛ ብርሃኑ መስጊድ አጠገብ ዛሬም በጉልህ ይታያል፡፡ ወደነዚህም መቃሞች ከኤርትራ ልዩ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች እየመጡ በየዓመቱ ዱዓ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህ ስፍራዎች፣ መስጊዶቹን የገነቧቸው መሻኢኾች ከመላው ኤርትራና ከሰሜን ኢትዮጵያ እስልምና ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ትኩረት የምንሰጣቸው ናቸው፡፡ በእርግጥም፣ ከምጽዋ፣ ከዳህላክ ከሐርቂቆ በተጨማሪ በከረን፣ በሰነዓፈ፣ በሐዘሞ ያሉ ጥንታዊ መስጊዶች፣ መቃብሮችና መቃሞች የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጥንታዊ ግንኙነት የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ የጅቡቲንና የሱማሊያን ተሰናሳይነት ደግሞ ወደፊት ተጨባጭ መረጃ እየሰጠን የምናቀርበው ይሆናል።
የሱፊ ወንድማማችነት ሥርዓት በአገራችን በኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጊዜ በሰፊው የገባ ቢሆንም ከዚያ በፊት የአብሩልቃድር ጀላኒ ተከታይ በነበሩት የሐረሩ አባድር በ12ኛው ክፍለ ዘመን ገብቶ ለ300 ዓመታት ያህል በአገሪቱ ሲስፋፋ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰይድ አብዱልቃድር ጀላኒ ተከታዮች በሐረር፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በኤርትራ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በኦሮሚያ በብዛት ይገኛሉ፡፡ በዓብይ ዓዲ ተቀራቂራ፣ በነበለት ዓዲር ጉድ፣ በራያ ሆጂራ ፎቂሳና ሆጂራ ወረባዬ፣ በዳዩ፣ በሐሸንጌ፣ በዳና፣ በገታ፣ በሐረር፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በስልጢ ታላላቅ የእስልምና የእምነት አባቶች ሱፊዎች ወይም የሶፊዎችን አመለካከት የሚያራምዱ ነበሩ ተብሎ ሲነገር ይሰማል፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸውም አንዳንድ አስደናቂ ተዓምራትን እንዳከናወኑ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ መረጃች ያመለክታሉ፡፡ የተዓምራቱ ታሪክ እንደ ሁኔታው ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል፡፡
ይህም ሆኖ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች ታሪኩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በግለሰቦች እጅ ታምቆ ቆይቷል፡፡ ግለሰቦችም በቃል፣ በእጅ ጽሑፍ፣ በእንጉርጎሮና በመንዙማቸው ከትውልድ ትውልድ ሲያስተላልፉት ቆይተዋል፡፡ የነዚህ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ በኅትመት ጽሑፍ፣ በድምፅና በፊልም መቀረፅ የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ከነዚህም ሥራዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክን በካሌት ያስቀረፁት ሸህ መሐመድ ወሌ፣ የአውሊያችንና ሙሻኢኮችን የሚያወድሱት ሸህ ሙሐመድ አወልና አብዱል ወሃብ ሸህ በድሪዲን አራት ዓይናቹ በሚል ርእስ ስለ አውሊያች መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ፣ በወለኔ ሸህ ዑመር ሸህ በሺር የተጻፈ የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማች ታሪክ (ጥሮነ) ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሸኽ ሁሴን ጅብሪልን ትንቢት ያሳተሙት አቶ ቦጋለ ተፈሪ ከነዚህም ሌላ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በዓረብኛ ወዘተ. የተጻፉትና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ ትልልቅ መጻሕፍትም አሉ፡፡ ከነዚህ ሁሉ መረጃዎች ውስጥ ለታሪክ ቀረቤታ ያለው ሸህ ሙሐመድ ወሌ በቴፕ ያስቀረፁት ትንታኔና በወለኔ ሸህ ዑመር ሸህ በሺር የተጻፈ የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ (ጥሮነ) እጅግ ጠቃሚ መረጃዎች ሲሆኑ ሸኽ ሙሐመድ አወል መንዙማዎችና እንጉርጉሮችም ለምርምር በር የሚከፍቱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወጣት ተመራማሪዎች ጠቃሚ መጻሕፍትን በመተርጎምም በማጥናትም ለንባብ እያበቁ ነው። ይህ ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ወደ ኢትዮጵያና ኤርትራ ኢስላማዊ ቅርሶች ቀረብ ብለን ስንመለከት ብዙ የሚያስገርሙና የሚያስደንቁ ነገሮችን እናገኛለንና የሚመለከታቸው ኢስላማዊ ተቋማት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።
በመጨረሻም
እነሆ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ አንድ ታሪክ የሚጋራና በባህልም በቋንቋም በእምነትም አንድ ነውና እስካሁን ድረስ ያከናወኗቸው አስደናቂ ተግባራት ሁሉ ከታሪካቸው፣ ከእምነታቸው፣ ከባህላቸው፣ ከኢኮኖሚያቸው ጋር ተያይዘው የተመዘገቡ ናቸው፡፡ እነዚህ አስደናቂ ድሎች እንደፖለቲካ ድባቡ ብቅ ጥልቅ እያሉ ቢኖሩ፣ አንዳንድ ጊዜም ብሩህ ሰማይ ውልብ ብሎ በሚያልፍ ደመና እንደሚሸፈነው ሁሉ የተደበቁ ቢሆንም ከምድረ ገጽ በማንኛውም ኃይል ተፍቀው አይጠፉም። አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚታየው በመንቃት ላይ የሚገኙ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚታየው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መነቃቃት ቀጣይነት የሚኖረውና ሁለንተናዊ ትስስሩ ወደ ዘላቂ አቅጣጫ የሚጓዝ ከሆነ ከሌላው የበለጠ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ የበለጠ የሚጠቅም በመሆኑ የሚሻለው በአንድ መሆኑ ነው፡፡ ይህች አገራችን ከጥንት ጀምሮ ብዙ ስደተኞች መጥተውባታል፡፡ ብዙ ማኅበራዊ ለውጦችም (የሰዎች እርስበርስ መዋሃድ) ተካሂደውባታል፡፡ በርካታ ሕዝቦች ተቀላቅለዋል፡፡ አንድ ሆነዋል። አዎን የሶማሊያው አውበርኸሌ፣ የሐረሩ አባድር፣ የድሬው ሸኽ ሑሴን፣ የወሎዎቹ በርካታ ማዕከላት፣ የመተከሉ፣ ጎንደሩ፣ የዓፋሩ፣ የቤንሻንጉልና የጉራጌው፣ የራያው ሆጂራ ፎቂሳ፣ የሐሸንጌው ዓብደኑር፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚች ምድር ላይ በዘር ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ማካሄድም ሆነ አስፈላጊ ያልሆነ በዘረኝነት የተመሠረተ አርበኝነት ታሪክ አንግቦ መንቀሳቀስ ፋይዳ የሌለው ነገር የሚሆነውም በዚህ ተጨባጭ ምክንያት ነው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ጂቡቲያውያን፣ ሱዳናውያንና ሶማሊያውያን በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት ከሚደረገው ጥረት ጋር ተደምረው የሚታዩ ናቸውና በአንድ ላይ ተባብረው ረቂቅና ተጨባጭ ኢስላማዊ ቅርሶቻቸውን በማጥናት የበለጠ ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡