Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓሹራ ክብረ በዓል

የዓሹራ ክብረ በዓል

ቀን:

‹‹የሙሀረም ወር 10ኛ ቀን የሚከበርባት ዓሹራ ብዙ ትርጉም አላት፡፡ ሰማይና ምድር የተሆለቁት (የተፈጠሩት) በዓሹራ ቀን ነው፡፡ አደምና ሐዋ የተሆለቁት በዓሹራ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሥራ የሚሠራበት ፍርድም የሚደረግበት በዓሹራ ነው፡፡ ሰው መካ መዲና እንደሚሄደው ሁሉ ብዙ ሰው ወደ ነጋሽ እንደሚመጣ ዱኣ የሚደርስበት፣ የሚዘየርበት፣ ሰደቃ የሚደረግበትም ነው፤›› የሚሉት ሐጂ መሐመድ አልኑር ናቸው፡፡

ይህ በየዓመቱ የሚከበረው የዓሹራ በዓል ሐሙስ ሙሀረም 10 ቀን 1440 ዓመተ ሒጅራ (መስከረም 10 ቀን 2011 ዓ.ም.) በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ተከብሯል፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር ዓመቱን 354 (355) ቀኖች ባደረገው እስላማዊ ካሌንደር መሠረት፣ አዲሱ ዓመት (ዓም) 1440 ዓመተ ሒጅራ (ዓ.ሒ.) የገባው ሙሀረም 1 ቀን (በፀሐይ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓም) ሲሆን የዓሹራ በዓልም ከአሥር ቀን በኋላ ተከብሯል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ በዓሉ በየዓመቱ ከሚከበርባቸው መስጊዶች መካከል አንዱ በሆነው በትግራይ ነጋሺ ከተማ በሚገኘው ጥንታዊ መስጊድ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡ የዘንድሮውን በዓል ለየት ያደረገው ከ300 በላይ ኤርትራውያን ሙስሊሞች በክብረ በዓሉ ላይ መገኘታቸው ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ነጋሺ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከመካ መዲና ተሰደው የመጡ ሰሃቦች የተስተናገዱበት ቦታ ነበር፡፡ ‹‹ዓሹራ በእስልምና ዓለም›› በሚለው መጣጥፋቸው አቶ አህመድ ዘካሪያ እንደጻፉት፣ በዓሹራ ዕለት ከነቢዩ አደም ጀምሮ የታወቁት ነቢያት በሙሉ ተአምራታቸው የታየበት ቀን ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የአደምና የሐዋ መፈጠር፣ የነቢዩ ኢብራሂም ከእሳት ቃጠሎ መዳን፣ ሙሳ ቀይ ባሕርን ከተከታዮቻቸው ጋር ማቋረጥ፣ ኑህ ከጥፋት ውኃ መዳንና የሌሎቹም ነቢያት ተአምራት የተመዘገበበት ቀን መሆኑም ይወሳል፡፡

አህመድ ነጋሽ የነቢዩ ሙሀመድ ቤተሰቦችን ተቀብለው ከማስተናገዳቸው፣ ከአደጋ ከመከላከላቸውና ታላቅ መሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ይከበራል፡፡ በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከሐጅ ሲመለሱ ነጋሺ መስጊድ ተገናኝተው  ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜም ይህ ልማድ ቀጥሎ ወደ ሐጅ ያልሄዱ የወሎ፣ የትግራይ፣ አልፎ አልፎ ይሁን እንጂ የጎንደር እስልምና እምነት ተከታዮች ወደዚያው በመሄድ የዓሹራን በዓል እንደሚያከብሩ በሐረሪም የተለየ አካባበር እንዳለውም ይታወቃል፡፡

ክፍለ ዘመናትን ያሳለፈው ታሪካዊው ነጋሽ መስጊድ ነባሩንና ታሪካዊ ይዞታው ሳይለወጥ የማደስና የመጠገን እንዲሁም በተንጣለለው ቅጥር ግቢ ውስጥ የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች ተሠርተውለታል፡፡ ከመስጊዱ እድሳት በተጨማሪ ከተከናወኑት አዳዲስ ግንባታዎች  የእንግዶች ማረፊያ፣ ምግብ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት ሲገኙበት፣ የቅጥር ግቢ አጥርና የመስጊዱን በረንዳ የማስፋት ሥራም ተከናውኖለታል፡፡

ከአዳዲስ ግንባታ መካከል ከዋናው በር እስከ ቀደምቱ ሱሃቦች መካነ መቃብር የሚወስደው መንገድ በዘመናዊ መልክ የተገነባና በመተላለፊያው የነጋሽና የ15ቱ ሱሃቦች ስም የሚጻፍበት የድንጋይ ምሰሶዎች 8 በግራ 8 በቀኝ ቆመዋል፡፡

የኢስላም ካሌንደር  

ከሁለት ሳምንት በፊት የእስላማዊ አዲስ ዓመት 1440 ዓመተ ሒጅራ ከመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. መባቻ ጋር የገጠመበት ነበር፡፡ ዕለቱም የሙሀረም ወር አንደኛ ቀን የእስላሚክ የጨረቃ ካሌንደር የመጀመርያ ወር ነው፡፡ የሙስሊም ዘመን የሚሰላው ከጨረቃ መውጣትና መግባት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ እስላማዊ የጨረቃ ካሌንደር (ሉናር ካሌንደር) የዓመቱ ቀኖች 354 (355) ሲሆን ከፀሐይ 365 ቀኖች በ11 ቀን ያንሳል፡፡ የ12 ወራት የእስላሚክ/ሒጅራ ካሌንደር የተጀመረው በሁለተኛው ከሊፋ ዑመር በ16 ዓ.ሒ. (637 ዓም) ነበር፡፡ የዓመቱ የመጀመርያ ወር፣ ሙሀረም የመታሰቢያ ወር በመባል የሚታወቅና በሙስሊም ካሌንደር ውስጥ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ወራት አንዱ ነው፡፡

በዴይሊ ትረስት እንደተጻፈው፣ ሙሀረም ‹‹የተከለከለ›› የሚል ፍች አለውና በርካታ ሙስሊሞች በፈቃዳቸው በዚህ ወቅት ይጾማሉ፡፡ የዓመቱ መባቻ የኢድ አልአድሃና ኢድአልፈጥር ዓይነት ከፍታ ባይኖረውም፣ ነቢዩ መሐመድ የመጀመርያውን ኢስላማዊ አስተዳደር በመዲና ከተማ (ባንድ ወቅት ያትሪብ ትባል ነበር) የመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ይወሳል፡፡ ነቢዩ መሐመድ በ622 ዓም ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት ስደት ሒጅራ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ይህም የሙስሊም ካሌንደር መጀመርያና መጠርያ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...