Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅቼያለሁ አለ

ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅቼያለሁ አለ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል እንዲያደርጉ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በኢትዮጵያ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም.  የድርጅቱ ሊቀመንበርን ጨምሮ አራት አመራሮች የገቡ ሲሆን፣ ከአርባ ስድስት ዓመታት የህቡዕ ትግል በኋላ በይፋ ለመታገል መመለሱን ገልጿል፡፡

በድርጅቱ መሪ በአቶ በላይነህ ዘለቀ ንጋቱ (መርሻ ዮሴፍ) የተመራ አራት አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን በመገንዘብና በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ምላሽ በመስጠት፣ ኢሕአፓ አገር ውስጥ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በይፋ ለመታገል ወስኗል፤›› ያለው የፓርቲው መግለጫ፣ የፓርቲው አመራሮች አገር ቤት ሲገቡ ከተለያዩ የብዙኃን መገናኛ ብዙኃን ጋር አባላቱን የማስተዋወቅ፣ በቀይ ሽብር የህሊናና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን የመጎብኘትና የማስተዋወቅ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስብሰባዎችን የማድረግ፣ ከአባላቱ አመለካከታቸውን ከሚጋሩ ግለሰቦች ጋር በቀጣይ ዕርምጃዎች ላይ ውይይት የሚደረግና ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት የማድረግ መርሐ ግብሮችን መያዙን አስታውቋል፡፡

      በ1964 ዓ.ም. ተቋቁሞ ራሱን ይፋ ያወጣው ከ1966 ዓ.ም. አብዮት አንድ ዓመት በኋላ እንደሆነ የገለጸው ፓርቲው፣ በኢትዮጵያ በይፋ እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱ ምክንያት ለ46 ዓመታት ህቡዕ ለመግባት መገደዱን አስታውቋል፡፡

 ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተስፋ ጭላንጭሎች ስለሚታዩ፣ ኢሕአፓ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊነትና በይፋ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ተዘጋጅቷል፤›› ሲል በመግለጫው ያስታወቀው ፓርቲው፣ ‹‹የማኅበራዊ ፍትሕን አጀንዳ በማንገብ በአገራችን ውስጥ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለ ፍራቻና አድልዎ እንዲኖሩ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለድህነት ቅነሳ፣ ለፆታ እኩልነት፣ ለአካባቢ አየር፣ አፈርና ውኃ ጥራትና ተጠቃሚነት፣ ለሥራ አጦች ሥራ በመፍጠርና በአገራችን ውስጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የአገራችን ዕድገት እንዲጠበቅ ወዘተ ለመታገል ቆርጦ ተነስቷል፤›› ብሏል፡፡

ኢሕአፓ ከ1963 እስከ 1973 ዓ.ም. ድረስ ከፍተኛ ጭፍጨፋና የአባላት ሞት፣ ስደትና እስራት እንደደረሰበት አስታውቋል፡፡ ፓርቲው ራሱን ለመከላከል የወሰደው ዕርምጃ ከአቅሙ በላይ ከሆነ የመንግሥት ኃይል ጋር እንደነበርም አስታውቋል፡፡ በከተማ ውስጥ በተደረገ ግብግብም በኢሕአፓና በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ትልቅ ጉዳት መከሰቱን ገልጿል፡፡ ከተማ ግብግብ ይልቅ መዋቅሮቹን ወደ ገጠር በጊዜ አለማሸሹ ጥፋት እንደሆነ ራሱን መውቀሱን፣ በዚህም ምክንያት በደረሱ ጥፋቶች በፅኑ ማዘኑንና መፀፀቱን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ለሪፖርተር በላከው ሌላ መግለጫ ደግሞ፣ በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማንና ሌሎች ጉዳዮችን ምክንያት እያደረጉ የሚነሱ ግርግሮችንና ጥቃቶችን አውግዞ፣ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ችግር ፊጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይገባ ነበር ብሏል፡፡

‹‹መንግሥት ይኼንን እኩይ ተግባር በሚጠነስሱ ኃይሎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ካልወሰደ በስተቀር፣ በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን ሕዝባችን የሚሰማውን የመረጋጋት ስሜትና የሰላም አየር መተንፈስ ተስፋ ሳይውል ሳያድር ደብዛው ሊጠፋ እንደሚችል መገመት ይችላል፤›› ሲልም አሳስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...