Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በአገራችን በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከመጠን በላይ እየሆኑ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በመጥረቢያ ተጨፍጭፋ ከተገደለችው የደቡብ ክልል አንዲት ወገናችን ጀምሮ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተፈጸሙ ዘግናኝ ወንጀሎችን ለምንሰማ ዜጎች ኧረ የመፍትሔ ያለህ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሴትን ልጅ በመጥረቢያ መፍለጥ፣ በኤሌክትሪክ ገመድ አስሮ በእሳት ማጋየት፣ ፊቷ ላይ አሲድ ደፍቶ ማቃጠል፣ በስለት ዓይኗን መጎልጎል፣ በጦር መሣሪያ መግደል፣ ወዘተ የአውሬነት መገለጫ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸም ከሰብዓዊ ክብር መውረድን ያሳያል፡፡ የእኔ ገጠመኞችም ይኼንን ያሳያሉ፡፡

ከዓመታት በፊት ደቡብ ክልል ውስጥ ሳስተምር ጎረቤቴ የነበሩ ባልና ሚስት በየጊዜው ይጣላሉ፡፡ መንደሩ ይረበሻል፡፡ ሽማግሌዎች በዚህም በዚያም ብለው ያስታርቃሉ፡፡ ችግሩ ከምንጩ ስለማይወገድ ነገም ሌላ ጠብ ይከሰታል፡፡ እንደገና በማለባበስ ይታረቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ምንም መሻሻል የለም፡፡ ሁሌም እንደታመስንና እንቅልፍ እንዳጣን እንኖራለን፡፡ አንድ ቀን ቢቸግረኝ አባወራውን ለብቻው ቀጥሬ የጠባቸውን ምክንያት እንዲያስረዳኝ ጠየቅኩት፡፡ ሰውየው ያለምንም ማንገራገር የነገረኝ መጠጥ ሲቀማምስ ቅናት እንደሚይዘው ነው፡፡ ይኼ ከሆነ ችግሩ መጠጡን ቢተው ለትዳሩ ሰላም እንደሚሆን ነገርኩት፡፡ ለጊዜው እሺ ቢለኝም መጠጡን ባለመተው የመረራት ሚስት ትታው ጠፋች፡፡ በኋላ ስሰማ አዲስ አበባ ውስጥ ሴተኛ አዳሪ ሆናለች፡፡ በመጠጥ ሱስ በናወዘ አባወራ ምክንያት አንዲት የቤት እመቤት ሴተኛ አዳሪ ስትሆን አያሳዝንም? ምን ገጥሟት ይሆን?

አዲስ አበባ ተዛውሬ ስድስት ኪሎ አካባቢ ስኖር ሚስቱን በወጣች በገባች ቁጥር የሚደበድብ አንድ አባወራ ነበር፡፡ የዚያች ሴት ጉዳይ ሁሌም ያንገበግበኝ ነበርና እንደተለመደው ይኼንንም ችግርህ ምንድነው አልኩት፡፡ ዓይኑን እያጉረጠረጠ በገዛ ባለቤቱ ምንም እንደማያገባኝ ከነገረኝ በኋላ፣ ‹‹ከእሷ ጋር አንድ ጉዳይ ቢኖርህ ነው እንጂ በማያገባህ ጣልቃ ገብተህ አትጠይቀኝም ነበር፤›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ በተቻለኝ መጠን በሥርዓት ላስረዳው ብሞክር አልሰማ አለኝ፡፡ ጭራሽ ዱርዬዎችን በገንዘብ ገዝቶ ሊያስገድለኝ መሆኑን ስሰማ አማላጅ ብልክም አልሰማ አለ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ጋር አብሮ መኖር የማይችል በመሆኑ ሠፈሩን ጥዬለት ተሰደድኩ፡፡ ከወራት በኋላ ሚስቱ ተሰቅላ መሞቷን ሰማሁ፡፡ እስከ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ስንገበገብ እኖራለሁ፡፡

መነን ትምህርት ቤት አካባቢ ስኖር ዘወትር ሚስቱን የሚቀጠቅጥ ሰው ነበር፡፡ ከአካባቢው ሰዎች አልፎ ለፖሊስ ጭምር አስቸጋሪ የነበረ በመሆኑ ሚስትየው ፊቷ የበለዘ፣ ጥርሶቿ የወለቁና የምታነክስ ነበረች፡፡ ይኼ ሁሉ የአካል ጉዳት የደረሰባት በሰውዬው ዱላ ምክንያት ነበር፡፡ ለራሴም የመጨረሻ ሙከራ ይሁን ብዬ ጎረቤቶቻችንን አሰባስቤ ከዚህ ድርጊቱ ይታቀብ ዘንድ ልመና መሰል ተማፅኖ አቀረብን፡፡ ግለሰቡ ዓለምን የናቀ ጥጋበኛ ስለነበር፣ ‹‹በገዛ ሚስቴ እንኳን እናንተ መንግሥትም አያገባውም፤›› ብሎ አንዳች የሚያህል የብረት ዘነዘና እየነቀነቀብን አባረረን፡፡ ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ለፖሊስ ብናመላክትም ሰሚ አጣን፡፡ ያቺ የመረራት ሴት ግን በዚያ የብረት ዘነዘና ተቀጥቅጣ ለዘለዓለሙ አሸለበች፡፡ አውሬዎች በነገሡበትና በገነኑበት ዘመን ደሟ ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ፡፡ አውሬው ባለቤቷ የተወሰነ ጊዜ ታስሮ ከተፈታ በኋላ ሲንጎማለል አየው ነበር፡፡ መጥኔ ከእንዲህ ዓይነቱ ጋር ለሚኖሩ፡፡

እነዚህ የነገርኳችሁ አሳዛኝ አጋጣሚዎች የተከናወኑት በደርግ ዘመን ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ሕፃናትን አስገድዶ ከመድፈር ጀምሮ እህቶቻችንን በጦር መሣሪያ ጭምር አሰቃይቶ መግደልን እያየን ነው፡፡ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ተመጣጣኝ ቅጣት አይቀጡም፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደ አገር በጋራ መቆምና ድርጊቶችን ማስቆም ሲገባን ዝም ያልን እንመስላለን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ወቅት የታዘብናቸው አፀያፊ ድርጊቶች ምን ያህል የአገራችንን ገጽታ እንደሚያበላሹ፣ ሕፃናትን ወላጅ አልባ እንደሚያደርጉ፣ አዛውንቶችን ጧሪ ቀባሪ እንደሚያሳጡ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለዴሞክራሲ የሚደረጉ ትግሎችን እንደሚያጨናግፉ እየታየን አይደለም፡፡ ለጊዜው ከሚደረጉ ወከባ የበዛባቸው ጫጫታዎች ውጪ ለዘለቄታው መፍትሔ የሚያሰጥ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ የሕጉ ክፍተት እንዳለ ሆኖ፡፡

በአንድ ወቅት እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈመውን ዘግናኝ ድርጊት በቅርብ ርቀት የተከታተለ አንድ የሥራ ባልደረባዬ እንዳጫወተኝ፣ አረመኔያዊው ተግባራችን ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ በፀጥታ አስከባሪዎች ፊት የተፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት በሕግ ፊት ቀርቦ እንዴት እንደሚዳኝ ለጊዜው ባላውቅም ለህሊና የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ የፈለገው ዓይነት ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዲት ራሷን መከላከል የማትችል ወገናችን ላይ ግን ያ ሁሉ ጥይት መርከፍከፍ አልነበረበትም፡፡ በጨዋነት ችግርን መፍታት ሲቻል እንዲህ ዓይነት ግፍ ምን ይባላል? ድርጊቱን በቅርብ ርቀት የተከታተለው ጓደኛዬ ግን፣ ‹‹በእንዲህ ዓይነቱ የአውሬነት ድርጊት እንደ አገር ሁላችንም ልናፍር ይገባናል፤›› ማለቱ አይረሳኝም፡፡ ሰሞኑን በቡራዩና በአካባቢው በተፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ደግሞ እናት ልጆችና ባልዋ ፊት ተደፍራ ተገደለች መባሉ ምን ይባል ይሆን? ከዚህ የበለጠ የሞራል ዝቅጠት ይኖራል ወይ? እኔም እንደ ጓደኛዬ ኃፍረቱ የሁላችንም ነው እላለሁ፡፡ ጣትን ሌላ ቦታ ቀስሮ ራስን ንፁህ ለማድረግ መፍጨርጨር ያስተዛዝባል፡፡  

(ቴዎድሮስ አመሐ፣ ከሣር ቤት) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...