በውብሸት ሙላት
ባሳለፍነው ሳምንት ለመንግሥትም ለሕዝብም ራስ ምታት ሆኖ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ የባንዲራ ጉዳይ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ባንዲራዎችን በአንድነት ይዞ ወይም የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ባንዲራዎችን በአንድ ዝግጅት ላይ በመያዝ ምንም ዓይነት ግጭት ሲከናወኑ አስተውለናል፡፡
እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት 7 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ዓርማ የሌለውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ባንዲራ በየአደባባዩ ተሰቀለ፡፡ በርካታ የከተማውም ሕዝብም የባንዲራውን ቀለም በተለያዩ አልባሳትና መዋቢያ በማድረግ ፍላጎቱንና ሐሳቡን ገልጿል፡፡ በመቀጠል ደግሞ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) ለመቀበል የኦሮሞ የነፃነት ባንዲራን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች በሰፊው ተሰቀሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ አደባባዮችና መንገድም ጭምር በባንዲራው ቀለም ተቀቡ፡፡ ይህንን ድርጊት ተከትሎም ግጭት እንደተፈጠረ የታወቀ ነው፡፡ ባንዲራ የሚወክለው ሐሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለም አለው፡፡
ለግጭት መነሻ የሆነውም ባንዲራዎቹ የሚወክሉት ሐሳብን ከመቀበል ካለመቀበል፣ ከመታገስ ካለመታገስ፣ ልዩነትን ከማስተናገድ አለመስተናገድ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች ንብረትን የባንዲራውን ቀለም በመቀባት ምክንያት የተነሱ ካሉ ከባለንብረቱ ምርጫና ፍላጎት ጋር ሊገናኝም ስለሚችል ይህንን እንተወው፡፡ እዚህ ላይ የንብረቱ ባለቤት መንግሥትም ያካትታል፡፡ በተጨማሪም ባንዲራውን ተገን አድርጎ ግጭት ለመፍጠር አባባሽ ሰበቦች ወይም ተንኳሽ ሊኖሩ እንደሚችሉም የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን አይደሉም፡፡ ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ ባንዲራዎቹ የሚወክሉት ሐሳብ (ርዕዮተ ዓለም) አለ ብለናል፡፡ የሐሳቡ ወይም የርዕዮተ ዓለሙ ተከታዮች (ባለቤቶች) ስላሉ በእነዚሁ መካከል የተፈጠረ ቅራኔና ግጭት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ሁለቱን ሐሳቦች ብቻ እንውሰድ፡፡ በአንድ በኩል ዜግነትን መሠረት ያደረገ ማንነት ወይም ብሔርተኝነት (Civic Nationalism)፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔርን መሠረት ያደረገ ማንነት ወይም ብሔርተኝነት (Ethno-Nationalism) አሉ፡፡ ከሰሞኑ ሁኔታ ረገድ ሲታይ አርበኞች ግንቦት ሰባትና ደጋፊዎቹ ከመጀመርያው፣ ኦነግና ደጋፊዎቹ ከሁለተኛው ምድብ ይካተታሉ፡፡ በእርግጥ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይና የሶማሌ ወዘተ. ብሔርተኝነትም የሚካተቱት ያው በሁለተኛው ነው፡፡ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ዓርማ የሌለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ባንዲራ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን፣ የኦሮሞ የነፃነት (የኦነግ ባንዲራ በመባል በሰፊው የሚታወቀው) ባንዲራ ደግሞ ኦነግን ለመቀበል ሲባል ነው አጀንዳ የሆኑት፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ አንዱ ባንዲራ የዜግነት ማንነትን፣ ሌላው ባንዲራ የብሔር ማንነትን ይወክላል፡፡ ግጭቱም እነዚህን ሁለት ማንነቶች ማስተናገድ መቻል አለመቻል ጋር የተያየዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለጽ የተለያየ ሐሳብ (አመላከከት) ያላቸው ቡድኖች ግጭት ሳይነሳ ውጥረት ሳይኖር እንደምን አድርገው ተቻችለው፣ ሕግና ሥርዓትን አክብረው፣ የሌላውን ወገን መብት ሳይጥሱ ሐሳባቸውን ያራምዳሉ የሚለው ነው፡፡
እንደሚታወቀው ብሔርተኝነት ከምክንያታዊነት ይልቅ ለስሜታዊነት፣ ከግላዊ ይልቅ ለጅምላዊ ውሳኔና ድርጊት የተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም ጭንቁ ስሜታዊነቱን ወደ ምክንያታዊነት (ሕጋዊነት)፣ ጅምላዊነቱን ወደ ግላዊነት ማምጣቱ ላይ ነው፡፡ የሰሞኑም ባንዲራን ሰበብ አድርጎ የተፈጠረው ግጭት የሚያረጋግጠውም ይኼንኑ ነው፡፡ እውነት ነው ማንኛውም ዓይነት ብሔርተኝነት ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ሥጋቶች አሉት፡፡ ለብሔርተኝነቱ መምጣት መነሻ የሆኑትን ችግሮች፣ በደሎች መቅረፍና ድጋሚ እንዳይከሰቱ ተቋማዊ ዋስትና መስጠት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር አበክሮ በመሥራትና የሕግ የበላይነትን በማስፈን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማረጋገጥ ብሔርተኝነት መግራት ይቻል ይሆናል፡፡ እንደ ቡድን ምንም ዓይነት ሥጋት እንዳይኖር ማድረግ የብሔርተኝነትን አመል ማረቅና ማላመድ ይቻላል፡፡ እነዚህን ማድረግ አለመቻል ደግሞ ብሔርተኝነት ሌሎች ሥጋቶችንና አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት በማድረግ መጽሐፍም መጣጥፍም ያላቸውን የማርጋሬት ኮኖቫንን ጽሑፎች ምርኩዝ በማድረግ ይህንን ሁኔታ ዘርዘር አድርገን እንመልከተው፡፡
እንደ ኮኖቫን ጥናት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የምዕራቡ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ ውስጥ የብሔር ጉዳይ መጮህ እየተገባው እንቅልፉን እንደሚለጥጥ ውሻ በመሆን አልፏል፡፡ የሚገባውን ትኩረት አልተሰጠውም አላገኘምም፡፡ ሌሎች ሀተታቸውን ሲጀምሩ እንዳለ ሳያብላሉና ሳይፈትቱ ይቀበሉት ነበር፡፡ ነገሩ ሲብስም ህልውናውንም ጭራሽኑም የካዱትም እንደነበሩ ትከራከራለች፡፡ የፖለቲካ ፈላስፋዎች የውሻውን መተኛት ምክንያት በማድረግ ኮሽታ ሳያሰሙ ማለፍን መርጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ውሻው እንቅልፉን ሲጨርስ ወይም ኮሽታ ሲሰማ ሊነሳ እንደሚችል የዘነጉት ይመስላል፡፡ አንዱን ቢያሳልፍ ከነቃ ሌላውን ላያሳልፍ እንደሚችል አልተገነዘቡትም ነበር ነው ነገሩ፡፡ ስለሆነም እንደተፈራው ነቃና መጮህ ጀመረ መናከስም ቀጠለ ብዙ ብሔሮች አገር መሆንን፣ ራስን ማስተዳደርን ናፈቁ፤ የተወሰኑትም ተሳካላቸው፡፡ የሶቭየት ኅብረት መፈራረስ የብሔርተኝነት ጥናት ላይ ታላቅ የመነቃቃት ሒደት አሳየ፡፡ በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ውሻው ሲነቃ ብዙዎች የሊብራሊዝም ሐሳብን ምርኩዝ በማድረግ ስለብሔርተኝነትና ስለብሔራዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መጻፋቸውን አጧጧፉት፡፡ ይሁን እንጂ ለአብዝኛዎቹ የብሔርተኝነት ማዳወሪያና ማጠንጠኛው ብሔሮች ሳይሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ነገሩ የጫካው ደኅንነት የሚጠበቀው እያንዳንዷን ዛፍና ችግኝ ስንንከባከብ እንጂ ጫካውን በጥቅል መንከባከብ አንዳንድ ችግኞችንና ዛፎችን መዘንጋት ይሆናል የሚል ነው፡፡ የሁሉም ዛፍና ችግኝ ፍላጎትና አመል ይለያያል፡፡ ለሁሉም እንደ ፍላጎትና አመሉ እንጂ ለሁሉም እኩል መጠን ያለው ፍግና ውኃ አያስፈልግም ብቻ ሳሆይን አላግባብ መጋት ይሆናል፡፡ ማዳበሪያው አንዳንዱን ያጋሽባል ሌላውን ያቀጭጫል ውኃውም እንዲያው ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ችግኝና ዛፎች እንክብካቤ ግለሰቦችን/ዜጎችን መንከባከብ ለጫካው ደኅንነት መሠረት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አተረጓጎምና ንጽጽሮሽ በኢትዮጵያም ውስጥ ይስተዋላል የሊብራል ዝንባሌ ባላቸው ላይ፡፡ ከዚህ አንፃር የአርበኞች ግንቦት 7ን ርዕዮተ ዓለም ያጤናል፡፡
ሌሎች ደግሞ ለዚህ ክርክር የሰላ ትችት አላቸው፡፡ የግለሰብ ማንነት መነሻው የባህሉ ውጤትነት የሚመጣው የግለሰቡ ከቡድኑ (ከብሔሩ) ጋር ከሚኖረው ትስስርና መስተጋብር ስለሆነ ግለሰቡን ብቻ ነጥሎ ማዕከል በማድረግ ቡድኑን መዘንጋት ውጤቱ ተመልሶ የግለሰቡ ማንነት ላይ አደጋ/ቀውስ መፍጠር ነው፡፡ በመሆኑም ስለቡድን ማንነት ዕውቅና አለመስጠት ስለግለሰቡ ቋንቋና ባህል ወዘተ. አለመጨነቅ ነው፡፡ ከቡድን አባልነቱ የሚቀዳውን ማንነቱን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው፡፡ ከፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ ውጭ በመሆን ዱር ለዱር ስትንከራተት የነበረችውን አነር ድመቷን፣ ብሔርተኝነትን፣ ለማዳ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ አንዳንዶች በአግባቡ ሊያላምዷት ባለመቻላቸው፣ ትክክለኛ መኖሪያዋን ስላላመቻቹላት ሌሎችን ወደ ጠላትነት በመቀየርና እያነቀች መብላት በመጀመሯ ወደ ዘር ጠረጋ አመራች፡፡ ሩዋንዳ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቦስኒያና ኮሶቮ ዓብይ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ የወቀሳው አተላ ተሸካሚዎች የፖለቲካ ፈላስፋዎች ሳይሆኑ የብሔሮቹ ፊታውራሪዎች ወይም የጦር አበጋዞች ናቸው፡፡
ብሔርተኝነትን እንደ አነር ድመቷ የማላመድና ቤተኛ የማድረግ ንጽጽሮሽ ሲነሳ ኮኖቫን የኤዞጵ ተረቶች ውስጥ ያለው የአይጦችና የድመቶችን ታሪክ ታነሳለች፡፡ አይጦች ከዋና ጠላታቸው ከድመት ለማምለጥ አንድ ሥልት መዘየድ ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም የአይጦች ጠቅላላ ጉባዔ ተጠራና ምክክር ተጀመረ፡፡ በጉባዔው ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ተነሱ፡፡ አንድ የአይጥ ጎረምሳ በአስደማሚ የንግግር ጥበቡ የመፍትሔ ሐሳብ አቀረበ፡፡ መፍትሔ ብሎ ያቀረበውም ማንኛውም አይጥ ከድመቶች ጥቃት ለመዳን እያንዳንዱ ድመት አንገት ላይ ከሩቅ የሚሰማ ቃጭል በማሰር ድመቶች ቃጭላቸውን እያቅጨለጨሉ ሲመጡ በመስማት ወደ ጉድጓድ ጥልቅ በማለት ማምለጥ እንደሆነ አስረዳ፡፡ አዳራሹን በአይጥኛ ጭብጨባ አናጉት፤ ለጎረምሳው አይጥም አድናቆት ጎረፈለት፡፡ ወደ ውይይታቸው መጨረሻ ላይ ከጥግ አካባቢ ተቀምጦ የነበረ የአይጥ ሽማግሌ የቀረበውን መፍትሔ አድንቆ፣ ነገር ግን የድመቶቹ አንገት ላይ ቃጭል አሳሪው ማን ነው? ለማሰር መሰማራት ውጤቱ ለድመት ቀለብ መሆን ስለሆነ ጭብጨባ እንደማያስፈልግ ተናገረ፡፡
ብሔርተኝነትን በአንድ አገር የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ምሰሶ ለማድረግ መሞከር አይጦች ከጠላቶቻቸው ከድመቶች ለመከላከል የድመቶች አንገት ላይ ቃጭል ለማሰር እንደ መሞከር ይመስላል፡፡ ብሔርተኝነትን ለማላመድ መሞከር አገርን ቀረጣጥፋ ልትበላ ትችላለች፡፡ ብሔርተኝነት ላይ ቃጭል በማሰር ሊመጣ የሚችል መጥፎ አደጋን ከርቀት መስማት ከተቻለ ቀድሞ ጉድጓድ ውስጥ በመግባት (መፍትሔ በመዘየድ) ሥጋትን መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህ ሳይሳካ ቢቀር ደግሞ ዘር ጠራጊ ዴሞክራሲን ልታሰፍን ትችላለች፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የብሔርን ጣጣ ፈጽሞ በመርሳት የግለሰብ መብት ላይ ብቻ ጥብቅ ማለትም ችግር የለውም ባይባልም ግለሰባዊ መሠረት ላይ ሙጭጭ የሚሉ መኖራቸውን መዘንጋት የለበትም፡፡ ኮኖቫን ሁኔታውን ተምሳሌታዊ በሆነ አገላለጽ ማስረዳቷን ትቀጥልና በተለይም ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንድ ብሔር አንድ አገር ከሆነባቸውና የፖለቲካ ፍልስፍናቸውም ሊብራሊዝም፣ ማኅበራዊ መሠረታቸው ግለሰብ የሆኑ አገሮች ዜጎቻቸውን በተለያዩ ተቋማት አማካይነት ወደተለያዩ አገሮች እንደ እርግብ በመልቀቅ የራሳቸውን የፖለቲካ ጃኬት ለማልበስ ትልቅ ትግል እንደሚካሄድ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በምዕራባውያን ቁመትና ውፍረት የተሠራው ጫማና ጃኬት ረሃብና ድርቅ ላደቀቀው፣ ሀሩር ቁመቱን ላሳጠረው አፍሪካዊ ላይሆን ይችላል፡፡ ለሲዊዲናውያን ወይም ሩሲያውያን ብርዳማና ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ የሚሠራው ካፖርት ለአፍሪካ ሀሩር ወበቅ ከመጨመር ያለፈ ጥቅም የሚያበረክተውም ፋይዳ የለውም፡፡ እንደ ሁኔታው ማስተካከል ግድ ይላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ እንደነአሜሪካ ባሉ በጣም ድብልቅልቅ ያለ ማኅበረሰብ ባለበትና የፖለቲካና የማኅበራዊ መሠረቱም ግለሰብ የሆኑባቸው አገሮችን ብሔር፣ ነገድና ጎሳ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጥባቸው እንደ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያና ሶማሊያ ወዘተ. ባሉት ዘንድ ያለምንም ለውጥ እንዳለ እንዲተገበር መጣር አበሳ መጥራት ነው፡፡
አንድ ብሔር የራሱን ብሔርነት ከሌሎች ጋር ማጣጣም ካልቻለ፣ አስታርቆ መኖር አዳጋች ከሆነበት፣ የልዩነት ማማው ቁመቱ መጨመሩን ከቀጠለ ተለይቶ መኖር ተመራጭ ሊሆን ስለሚችል መገንጠል አይቀሬ ይሆናል፡፡ የብሔር መሪዎች ከዚህ ሒደት ለመጠቀም ሲሉ ጥርጣሬ ማንገሥንና ራሳቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችሉ መፈክሮችን ያዘጋጃሉ ይነዛሉም፡፡ በመቀጠልም ሌላውን የብሔሬ ልጅ አይደለም የሚሉትን ማግለል፣ መለየትና ማስወጣት ይጀምራሉ፡፡ እንደ ዩጎዝላቪያና ሩዋንድ በጭፍጨፋ ወይም አካባቢውን ለሌሎች ሠርቶ መኖሪያ እንዳይሆን በእሾሀማ ሕጎችና ተግባራት ማጠር የዘወትር ሥራቸው ማድረጋቸውን ይተጉበታል፡፡ ብሔር ላይ ብቻ የተመሠረቱ የክልልና የአካባቢ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋምና ሌሎችን እንዳያቅፍ በማድረግ፣ ከአስፈጻሚውምና ከዳኝነቱም በማግለል ሌሎች በባይታወርነት ስሜት እንዲሞሉ ማድረግ፣ የብሔሩን ቋንቋ የማይችሉትን ከመንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተቀጣሪ እንይዳሆኑ በሕግ መደንገግን የመሳሰሉትን በማከናወን ተሰበጣጥሮና በአንድነት ከመኖር ይልቅ አንድ ብሔር ብቻ የአካባቢውን ሁለመና የራስ ማድረግ ይቀጥላል፡፡ ከላይ የማርጋሬት ኮኖቫንን ሐሳብ መሠረት በማድረግ የቀረበው የብሔር ማንነት ሊያስከትላቸው የሚችሉ ሥጋቶች ቢኖሩም፣ እነሱን መግራትና ማረቅ እንደሚቻልም ያመላክታል፡፡ የብሔር ማንነትን ሙሉ በሙሉ በመካድ፣ በመተው ዜግነት ላይ ብቻ ለተመረኮዘ ማንነት ዕውቅናና ጥበቃ በማድረግ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችልም ጭምር ነው፡፡ ይልቁንም ትኩረት ሰጥቶ እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ቡድን የራሳቸው መብቶች አሏቸው፡፡ በራሳቸው ብቻ የሚወስኑባቸው፡፡ ይህም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው፡፡ እንግዲህ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አዲስ አይደለም አሮጌ ነው፡፡ ብዙ ተጽፎበታል፡፡ ብዙ ደም አፋስሷል፡፡ ሰላምም አምጥቷል፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ወሳኞቹም ይሁኑ መብቶቹ መቶ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተለዋውጠዋል ወይም እየጨመሩ ሄደዋል፡፡
የራስን ዕድል በራስ መወሰን ብቻውን ተገንጥሎ የሚቆም ጽንሰ ሐሳብም አይደለም፡፡ ሥራ ላይ ሲውልም ብዙ ነገሮች ጋር ተፅዕኖ አለው፡፡ በመሆኑም ከፌዴራሊዝም፣ ከክልልና ሌሎች ዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች (ራስን ማስተዳደር)፣ ከቡድን መብት፣ በቁጥር አናሳ ከሆኑ ብሔረሰቦች፣ ከመገንጠል፣ ከእኩልነት፣ ከውክልናና ተሳትፎ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠቀም ወዘተ. ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ለእነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች የሚሰጡ መልሶችና መፍትሔዎች ናቸው እንደ ቡድን የብሔር መብቶችም ፍላጎቶችም፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለእነዚህ ጉዳዮች የሚሰጠው መልስ ነው በተናጠል ከዜጎች መብት ጋር የማጣጣምም የማቀናጀትም ፈተና የሚኖርበት፡፡ ዜጎችም በቡድን መብት ሳይጨፈለቁ፣ ቡድኖችም ለዜጎች መብት ሲባል መብታቸው እንዳይካድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሁለቱንም በአንድ ላይ ማጣጣም ይቻላል፡፡ ዜግነትን መሠረት ያደረገ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ፓርቲም ብሔርን መሠረት ያደረገውን ማጥላላትም ግጭት ውስጥም የሚያስገባ አካሄድ መከተል አይገባም፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረገው እንደዚሁ፡፡ እውነታው የሚገኘው ሁለቱም ላይ እንጂ አንዱ ላይ ብቻ አይደለምና፡፡ የግለሰብም የቡድንም መብትም በአንድነት ማስከበር ይቻላልና፡፡ ከ1960ቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ወይ ‹‹ጥቁር›› ወይ ‹‹ነጭ›› ነው በማለት በሁለቱ መካከል ‹‹ግራጫ›› የሌለ ይመስል ጽንፍ ይዞ መሟገት ለምዶብናል፡፡ ዕድሜ ለማርክሲዝምና ሌኒኒዝማዊ ርዕዮተ ዓለምና እሱን ተከትሎ ለመጣው ጭነት የበዛባቸው ቃላት የመጠቀም አባዜ! በዚያ ላይ ብሔርተኝነት በባህሪው ወደ ጽንፍ የሚያንደረድር ነው፡፡ ብሔርተኝነት ላይ ማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ሲደመርበት ለጽንፉ ለከት የሚያጣ ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ይህ የ1960ቹ ትውልድ ማለትም አሁን በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉት ‹‹የፖለቲካ አባቶቻችን›› በማወቅም ይሁን ባለማወቅ (ባለማወቅ አይመስለኝም!) የእነሱን ግራጫ የሚባል ቀለም የማያውቅ የፖለቲካ ልማዳቸውን እያለማመዱን ነው፡፡ አንድ ነገር ወደ ልማድ ደረጃ ከተሸጋገረና በተለይ ልማዱ የሚጠቅም ካልሆነ የክፋቱ መጠን ወደር የለውም፡፡ ይህንን የልማድን ክፋትና መጥፎነት ከበደ ሚካኤል ‹‹የቅጣት ማዕበል›› በሚለው ተውኔታቸው ላይ በገጸ ባህሪያቱ በበላይና በከልሌ ምይይጥ እንዲህ ገልጸውታል፡፡
ከልሌ፡ የተማረ ሲሆን የሰው ልጅ ህሊና፣
የሚሻሻል መስሎህ አትውደቅ ከስህተት፣
መማር አለመማር ዋጋቢስ ነው ዕውቀት፣
በላይ፡ ልዩ ነው ማለት ነው የትምህርት ፈንታው፣
ከልሌ፡ ልማድ ያሰረውን ዕውቀትም አይፈታው፣
በላይ፡ ምን ያህል ብርቱ ነው ኃይለኛ ጠንካራ፣
ከልሌ፡ ልማድ የሁሉ ምንጭ ያሳር የመከራ፡፡
በላይ፡ ታዲያ ሰው መቼ ነው ከልማድ የሚድን?
ከልሌ፡ በልማድ ወፍሮ ሰብቶ ሲደነድን፣
ሥር እየሰደደ የያዘው በሽታ፣
ተገዥ ይሆናል በመታገል ፈንታ፡፡
ቂሙ አይነቀል መርዙ የማይጠፋ፣
ምን ነገር ይገኛል ከልማድ የከፋ፡፡
ፖለቲካዊ ቅን ልቦና ማጣት፣ ገዥዎች ስለሕዝቡ ከሕዝቡ የበለጠ አውቅልሃለሁ የማለት አባዜ፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ሁልጊዜም አጥፊና አውዳሚ አድርጎ ማየት፣ ገዥዎች ስለአገራችን ከሁሉም የበለጠ ተቆርቋሪ መምሰል ብዙ ብዙ፡፡ ልማድ እየሆኑ የመጡት በዝተዋል፡፡ ከእነሱ መላቀቅ ደግሞ በእጅጉ አቅቶናል፡፡ ከዚህ አንፃር ያቃተው ትውልድ ሆነናል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ዘመን ትውልድ የስድድብና የመወጋገዝ ውርስ (ሌጋሲ) እንድንላቀቅና የሠለጠነና ጨዋነት የተሞላበት ትችትና አቃቂር በማውጣት አንዱ ሌላውን እየተገነዘበና እየተረዳ ሙግታችንና ውይይታችንን መቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትም ወግና ቅርፅ የሚኖረው፣ መብትና ግዴታንም እንደ ዝቅተኛ የመግባቢያ መሥፈርት በመውሰድ እነሱን በማክበር ነው ሰላምና ሕጋዊ ሥርዓት የሚሰፍነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት የግለሰብና የቡድን መብቶችም የሚተገበሩትም በቅድሚያ ሕግን ማክበር ሲቻል ነው፡፡ ዜግነትንም ይሁን ብሔርን መሠረት ያደረገ ማንነት በመከተል አንዱ ሌላውን ማጥፋት የለበትም፡፡ አስፈሪ አድርጎ ማቅረብም ውጤቱ ግጭት ነው የሚሆነው፡፡ በባንዲራው መነሻነት እንደተፈረው ግጭት የቡድንና የግለሰብ መብቶች፣ ብሔርና ዜግነትን መሠረት ያደረጉ ማንነቶችም አይጋጩም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚገነባው ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎች ላይ ላሉት ድንጋጌዎች ተዓማኒ በመሆን ነው፡፡ ካልሆነ ተመልሶ ከእንደገና ‹ሀ› ብሎ መጀመር ይሆናል፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡