የማኅበራዊ ፖለቲካ ይዘት ምንድነው?
በአንዳርጋቸው አሰግድ
2011 በተስፋ ተከፈተ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) “በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር” ጥሪ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ምንም ነገር ያለተቃርኖው እንደማይኖር ሁሉ ግን፣ በተስፋ የተከፈተው 2011 የሥጋት ወቅቶችም ይኖሩታል፡፡ በዓመቱ የመጀመርያ ሳምንት ገና፣ በርካታ አሳሳቢና አሥጊ ሁኔታዎች እየተመዘገቡ ናቸው፡፡ የ2011 የተስፋ ገጽታ እየጎለበተና የሥጋቱ ገጽታ እየተዳከመ የሚቀጭጭበት ዘመን ከሆነ፣ የኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል ብሩህ ይሆናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጥረት ለተስፋው ገጽታ መጎልበት አስተዋፅኦ የማድረግ ነው፡፡ በዘሁ መንፈስ ታስቦ ቢነበብ አመሠግናለሁ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጥሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን በይቅርታ ተሻግረውና በፍቅር ተደምረው ወደ አንዲት ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አዳራሽ እንዲገቡ የሚጋብዝ በጎ ጥሪ ነው፡፡ ይሁንና፣ ‹‹መሻገርና መደመር›› ክንዋኔዎች (Processes) እንጂ፣ በራሳቸው የመዳረሻ ግብ አይደሉም፡፡ ስለዚህም ከአዳራሹ በደስታና በተስፋ ከተገባ በኋላ፣ አንዲት ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትገነባውና የምትደረጀው በምን ዓይነት የጋራ ብሔራዊ ወይም አገራዊ የፖለቲካ ማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ ነው? የሚለው ጥያቄ የግዴታ ይነሳል፡፡ በግቡ ማኅበራዊ ፖለቲካ ምንነት ላይ ከወዲሁ ውይይት የተደረገውን ያህል፣ አቅጣጫው ግልጽ ይሆናል፡፡ የሽግግሩና የመደመሩ መዳረሻ ይታወቃል፡፡
የመሻገርና የመደመር ክንዋኔ የጫጉላ ሰሞን መስከረም አምስት ዕለት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል፡፡ በምን እንደሚቋጭ ወደፊት ይታያል፡፡ መንግሥት ከእንግዲህ ግን፣ በአንድ በኩል የሕግና ሥርዓት አስከባሪ ሚናውን አጉልቶ ወደ መያዝና ወደ መጫወት ማቅናት ይኖርበታል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና የዋለለ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የተባለው መሻገርና መደመር ፀር ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በአንድ ወገን የመዳረሻውን ምንነት ግልጽ አድርጎ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ የሽግግሩንና የመደመሩን ሒደት በቅጡ አስምሮ ወደ ተጨባጭ ሥራዎች መገባት ይኖርበታል፡፡ ለመስከረም የመጨረሻ ሳምንት የተቀጠረው የኢሕአዴግ ጉባዔ በእዚህ አኳያ የወሳኝነት ሥፍራ አለው፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ በዚሁ ወደ ርዕሱ ለመመለስ የ‹‹በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር›› ማኅበራዊ ፖለቲካ ይዘት ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ አርበኞች በ1930ዎቹ ፋሺስት ኢጣሊያንን የገጠሙት ‹‹እናት አገር ወይም ሞት›› እያሉ ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ የነፃነቱን ዘመን የከፈቱት ‹‹አዲስ ዘመንን›› በማወጅ ነበር፡፡ ደርግ በ1966 ዓ.ም. ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› እያለ የሥልጣን ማማዎችን ጨበጠ፡፡ አንደኛው በወቅቱ የቀረበለት ዓብይ ጥያቄ ምን ማለት ነው? የሚለው ነበር፡፡ ደርጉ የተዘበራረቁና የተምታቱ መልሶችን ሲሰጥ ከከረመ በኋላ፣ በኅዳር 1967 ዓ.ም. በፈጸመው ግድያ ኢትዮጵያ ትቅደሙን ከደም ባህር ውስጥ አስምጦ አሰናበተው፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊነት፣ ዴሞክራሲያዊ አብዮት፣ ሶሺያሊዝም እያለ የማታ ማታ የኢሠፓን አገዛዝ መሠረተ፡፡ ‹‹አንድ ሰውና አንድ ጠብመንጃ እስኪቀር ድረስ›› እስካለው የአጥፍቶ ጠፊ የዕብደት ‹‹ፖለቲካ›› ድረስ ዘለቀ፡፡ በ1983 ዓ.ም. ተወገደ፡፡ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የተባለውን የማኅበራዊ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ባነገበው ኢሕአዴግ ተተካ፡፡ ከ27 ዓመታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዚያው ከኢሕአዴግ ውስጥ ፈልቀው፣ በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር እያሉ መጡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር የሚሉትን ቃላት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ ካስተዋወቁ መንፈቅ ሊሞላው ነው፡፡ ይኼንን ጽሑፍ ለኅትመት እስከላኩበት ዕለት ድረስ ግን፣ የቃላቱን የማኅበራዊ ፖለቲካ ወይም የፖለቲካዊ ፍልስፍና መሠረትና ይዘት አላብራሩም፡፡ ስለሆነም ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት ለደርግ ይቀርብ የነበረውን ጥያቄ መልሰን እንድናቀርብ የተገደድን መስሏል፡፡ የጥሪው ማኅበራዊ ፖለቲካ ይዘት ምንድነው? ለማቆምና ለመገንባት የሚፈልገው ወይም የሚታሰበው ሥርዓተ አገዛዝ ምን የሚባልና ምን ዓይነት ነው? ዕቅዱ ምንድን ነው? ወደተግባር የሚተረጎመው እንዴት ነው?
በ1966/67 ዓ.ም. የደርጉን ኢትዮጵያ ትቅደም ምንነት የጠየቁትና የሞገቱ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ‹‹ፀረ ኢትዮጵያ ትቅደም›› እየተባሉ የተወገዙትና የተሳደዱትም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ከደርጉ ኢትዮጵያ ትቅደም እስከ የኢሠፓ አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ የነበሩትን ጥሪዎች አብዝተው ያዜሙት ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና የኪነት ሰዎች ግን ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም በርካታ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና የኪነት ሰዎች የኢሕአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲና ሌላ ሌላ ሳይሞግቱና ሳይጠይቁ ለ27 ዓመታት ሙሉ ሲዘምሩ ኖረዋል፡፡ የቀድሞው የቀጠለ ይመስል ዛሬ ደግሞ፣ አንዳንድ የመገናኛ አስተናጋጆች፣ ምሁራንና የኪነት ሰዎች የዶ/ር ዓብይን በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር ጥሪ በሰፊው ማስተጋባት ይዘዋል፡፡ ‹‹ነፃ ናችሁ›› እየተባሉ እንኳን ትርጉማቸው ምንድነው? ብለው ለመጠየቅና ለመሞገት ሲዳዱ አይሰሙም፡፡ ለምን?
ዋናው ምክንያት ያለ ጥርጥር ሰላምና አንድነት ከናፈቀው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ልብ ውስጥ የገባ ጥሪ በመሆኑ ነው፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ማቅኛው የጠፋ የመሰለ የሥጋት ዓመታት ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ዶ/ር ዓብይ በይቅርታ መሻገርና በፍቅር መደመር እያሉ ያቀረቡት ጥሪ፣ አብዛኛውን ሕዝብ ከሥጋቱ መውጫ እንዳገኘ ያህል አስተንፍሷል፡፡ አንዳንዶች ዶ/ር ዓብይን ‹‹ከፈጣሪ የተላኩ››፣ “ነብይ” እያሉ መግለጻቸው በራሱ፣ የጭንቀቱን ስፋትና መጠን ያመለክታል፡፡ ደግሞም ከግጭት በይቅርታ፣ ከጥላቻ በፍቅር መደመር የማይመረጡበት ምክንያት የለም፡፡ ይቅርታና ፍቅር ከሁሉ ነገር በፊት የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ሁሉ መሠረታዊ አስተምህሮ ናቸው፡፡ ተቃራኒያቸውን ቂምንና ቁርሾን፣ ጥላቻንና ግጭትን፣ መለያየትንና መበታተንን የሚፃረሩ ክቡር ሰዋዊ እሴቶችና ፀጋዎች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የዶ/ር ዓብይ ጥሪ በፈጣሪ ስምና ስለፈጣሪ የተደረገ የሃይማኖታዊ ይቅርታና ዕርቅ ጥሪ አይደለም፡፡ ‹‹ነው›› ቢባልም እንኳን፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚሠራ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩባት አገር ነች፡፡ ወይም እንደ ቫቲካን፣ ኢራንና ሳዑዲ የወንጌላዊና የቁራናዊ (Theocratic) አገዛዝ አገር አይደለችም፡፡ የፖለቲካ ማኅበራዊ ይቅርታና ዕርቋን በጳጳሳዊ፣ ሙላሂና ፓስቶራላዊ ሥርዓት ለማስተናግድ የሚሆን የታሪክና የማንነት መሠረትና ጀርባ ያላት አገር አይደለችም፡፡
ዶ/ር ዓብይ በድርጅታዊ ፖለቲካ ውስጥ ያደጉና የኖሩ ሰው ናቸው፡፡ ከፍተኛ የክልልና የመንግሥት ባለሥልጣንና ኮሎኔልም ጭምር የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ከአምስት ወራት ወዲህ ደግሞ ከፍተኛውን የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጡ ሰው ናቸው፡፡ ሥልጣኑን የጨበጡት ከሦስት ዓመታት የተካረሩ የማኅበራዊና የኢሕአዴግ ውስጥ የፖለቲካ ፍትጊያዎች በኋላና በመጋቢት 2010 ዓ.ም. በተከናወነበት ሁኔታ ተካሂዶ ከተገታ በኋላ ነው፡፡
ነገር ግን ከእሳቸው ምርጫ በኋላም በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በአንድ በኩል፣ በየአባልና በየአጋር ድርጅቶቹ ውስጥ በሌላ በኩል እየተካሄደ ያለው የፖለቲካ ትግልና ትንቅንቅ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ በምን እንደሚያከትም እንኳን ውጫዊው ታዛቢ ቀርቶ ራሳቸው የኢሕአዴግ መሪዎችና አባላትም የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ነገሮች በተቃራኒው የሚያመለክቱት እያንዳንዳቸው ያለፉትን የ27 ዓመታት የኢሕአዴግ ጉዞ ለየክልል ቡድናቸው በሚያመቹ መንገዶች በአዎንታዊና በአሉታዊ እያብጠለጠሉ እንደሚገኙ ነው፡፡ የየክልል ቡድኖቻቸውን ጡንቻዎች በዚያም በዚህ ብለው ለማደለብና ለማፈርጠም እየተሯሯጡና እየተጣደፉ እንደሚገኙ ነው፡፡ የየክልል ምሁራኖቻቸውንና የዳያስፖራ ወገኖቻቸውን እየጋበዙ ረድፍ ለማስያዝ በመጣር ላይ እንዳሉ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶችም፣ ኅብረት ወይም ውህደት… እያሉ ለመሸጋሸግ እንደሚጥሩ ነው፡፡
የቅርብና የሩቅ መንግሥታት አገሮችም ሠልፋቸውን ይዘው ሊጎትቱ የሚችሉትን ገመድ ሁሉ እየጎተቱ ናቸው፡፡ ‹‹እንዲያውም›› ይላሉ አንዳንድ ታዛቢዎችና የፖለቲካ ተንታኞች፣ ‹‹የውጭ እጆች ዘልቀው ገብተዋል››፡፡ ለዚህም በተለይ ከኅዳር 2010 ዓ.ም. ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የጎረፉትን የቅርብና የሩቅ መንግሥታትንና የፋይናንስ ድርጅቶችን መልዕክተኞች ይዘረዝራሉ፡፡ የዶ/ር ዓብይን የውጭ ጉዞዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የአንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን ሥፍራና ሚና ያመለከታሉ፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ወደ ኒዮ ሊበራላዊ መለወጥ እንደያዘ ያትታሉ፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ከሳዑዲ ሳሎን የገባበትን ምክንያት ይጠይቃሉ፡፡…
ከኤርትራ ጋራ የተጀመረው ግንኙነት በራሱ መልካም ቢሆንም፣ እየተጀመሩ ያሉት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ግንኙነቶቹ በምን ስምምነት ላይ እየተመሠረቱና እየተገነቡ እንደሆነ በይፋ አልተገለጸም፡፡ ዶ/ር ዓብይ በዚህ አኳይ እንዲያውም ግልጽነትና የመረጃ መብት የሚባሉትን ጉዳዮች ከቀድሞዎቹ ገዢዎች በተለየ በሥራ የሚያውሉ ሆነው እንዳልተገኙ ይተቻል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት በሕጋዊነት በሕግ የበላይነትና በሰብዓዊ መብቶች ጥያቄዎች ረገድ እስካሁን አንድም ዕርምጃ አለመውሰዱ ተገቢ ጥያቄዎችን መቀስቀሱ አልቀረም፡፡
የተመለከቱት ጉዳዮች የየራሳቸውን ሕይወት ማብቀላቸው የየራሳቸውን መንገድ መውሰዳቸውና የየራሳቸውን ጫና በአዎንታዊውም ሆነ በአሉታዊ ማሳረፋቸው አይቀርም፡፡ እያሳረፉም ናቸው፡፡ እንደዚሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሰፊ ድጋፍ እንዳላቸው አደባባዮች ቢመሰክሩም፣ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አመራሮች ውስጥና በአባላቶቻቸው ዘንድ ይሁን በቢሮክራሲው ውስጥ ያላቸው ተጨባጭ ተቀባይነትና ድጋፍ በግልጽ የሚታወቅ አለመሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ የቄሮ፣ ፋኖና የሌሎቹ ወጣቶች እንቅስቃሴዎች የወደፊት ጉዞም የሚታወቅ አይደለም፡፡ ‹‹ሰው ምን ይመስላል ቢሉት ኑሮውን አለ›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ወሳኙ ጉዳይ ዞሮ ዞሮ በተለይም የሕዝቡ ማቴሪያል ሕይወት መሻሻልና አለመሻሻል እንደሆነ ማስታወሱ የሚታወቀውን መድገም ይሆናል፡፡… በእነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያትና ከኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል አንፃር በጥሪያቸው ምንነት ላይ የፖለቲካ ውይይት ቢካሄድ፣ ጥሪያቸው ሥጋ የመልበስ ዕድል ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ይቅርታና ዕርቅ
የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ይቅርታና (Forgiveness) ዕርቅ (Reconciliation) የሚባሉትን የፖለቲካ ግብና አካሄዶች በየጊዜው አንስተዋል፡፡ በሥራ አውለዋል፡፡ የፖለቲካና የማኅበረሰባዊ ሳይንስ ተመራማሪዎችና ፈላስፎች በብዙ አትተውባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሓና አረንት፣ ሱዛን ዲዋየር፣ ጃክ ደሪዳ፣ ሃዋርድ ዜኸር፣ አሪ ኮኸን፣ አሊስ ማክላክላን… ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ የአገር ውስጥና የዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የይቅርታና የዕርቅ ጉበዔ እንዲጠራ ሲጠይቁ 27 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ይሁንና ተቃዋሚዎቹም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ስለጉዳዩ ያቀረቡት ጭብጥ አመለካከት ሐሳብና ፍኖተ ካርታ የለም፡፡
ከዶ/ር ዓብይ ወዲህ እንዲያውም የፖለቲካ ይቅርታና ዕርቅ፣ መንግሥት ለፖለቲካ እስረኞች የሚያደርገውን የክስ መቋረጥና ምሕረት ማለት መስለዋል፡፡ የዳያስፖራው ተቃዋሚዎችና የፌስቡክ ተዋናዮች ወደ አገራቸው መመለስና በመንግሥታዊ መስተንግዶዎች ጭምር በ‹‹ነፃነት›› መንቀሳቀሳቸውን ማለት መስሏል፡፡ አንዳንድ ሌሎችም ‹‹የጦር ትግል›› የሚሉትን ‹‹አቋርጠናል›› እያሉ የሚያወጡትን መግለጫ ማለት መስሏል፡፡ ይቅርታና ዕርቅ እነዚህን ጉዳዮች ማለት ከሆነ፣ የይቅርታና የዕርቁ ጥያቄ ከመሠረቱና ከድሮውም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና የፖለቲካ መድረኩ እንዲሰፋ ከመጠየቅ የማይዘል ነበር ያሰኛል፡፡ እንዲያም ሲል ከድሮውም ቢሆን ለፖለቲካ ሥፍራዎች ሲደረግ የነበረ ጥረት ነበር ያሰኛል፡፡
በይቅርታ መሻገር በሌላው በኩል ግን፣ አንዳንዴ ‹ዶ/ር ዓብይን ተቀብያለሁ፣ ከእሳቸው ጋር ተደምሬያለሁ› ማለትን ይመስላል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ሲጠብ በፀረ ሕወሓትነት፣ ሲሰፋ በፀረ ኢሕአዴግነት መሠለፍ ማለትን ይመስላል፡፡ ደግሞ በሌላ ጊዜ፣ ‹‹የቀን ጅቦች፣ ሌቦችና ፀጉረ ለውጦች›› ከሚባሉት ጋራ የመታገያ መሣሪያ የተደረገ ይመስላል፡፡ በእኔ አረዳድ ይህ የኋለኛው በተለይ፣ ያላግባብ በልፃጊዎችንና በሥልጣን ባላጊዎችን መታገል በሚለው ቢተካና የተባሉት ክፍሎች ጉዳይ ለሕጋዊ መንገዶች ቢተው፣ በይቅርታ መሻገር ከተባለው ጥሪና መንፈስ ጋራ ይበልጡን የሚጣጣም ይሆናል፡፡ በይቅርታ መሻገር ሲቃ ከሚያስገቡና ሲቃ ከሚያስይዙ ቃላት መታቀብንም ይጠይቃል፡፡
አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች በተገቢው የሚጠይቋቸው ተቋማዊ ለውጦችና የሕግ የበላይነት በተግባር ተገልጸው፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኃይሎችና የፌስቡክ ተዋናዮች ወደ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል የሚወስዷቸው ከሆነ፣ በራሱ መልካም ነው፡፡ አንዳንዶች የመጀመርያው ሥራ ሰላምንና መረጋጋትን ማስፈን ነው የሚል አቋም መያዛቸውም እንደዚሁ መልካም ነው፡፡ ይሁንና በፖለቲካ ኃይሎቹ መካከል የሚካሄድ ድርድር ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ ኃይሎቹ በየግላቸው በሚደፉት የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ልክ የሚፈጸም ስለሚሆን፣ የማኅበራዊ ፖለቲካ ይቅርታና ዕርቅ ተደርጎ ሊታይ አይችልም፡፡ ወደ ዘላቂ የማኅበራዊ ፖለቲካ ዕርቅ የሚያደርሰው ሁነኛ መንገድ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋራ በተገናዘቡ መንገዶች መልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ (Restorative Justice) የሚባለው የፍትሕ መንገድ በሥራ የዋለውንና ያልዋለውን ያህል ይሆናል፡፡
የፖለቲካ ይቅርታ ዣክ ደሪዳ እንደሚለው፣ ‹በይቅርታ ሊታለፍ ለማይገባው የግፍ ዕርምጃ (ድርጊት) ይቅርታ ሲጠየቅ ይቅርታን መለገስ ነው› (Is to Forgive the Unforgivable)፡፡ የፖለቲካ ይቅርታን መጠየቅ የበዳዩ ወገን ፈንታና ግዴታ ነው፡፡ እንደዚሁም በዳዩ ወገን፣ ‹‹የፈጸምኩትን ግፍና በደል መቼም አልደግመውም፣ ሌላም እንዲፈጽመው አልፈቅድም›› ብሎ ባደባባይ ቃል የሚገባበት ሥርዓት ነው፡፡ ይቅርታን መለገስ ወይንም አለመለገስ የዚያኑ ያህል ደግሞ ግን፣ የተበዳዩ ወገን ነፃነት ነው፡፡ ለምሳሌም የጀርመን ቻንስለር ዊሊ ብርንት፣ በሂትለር የተፈጸመውን ግፍ በማስታውስ በኅዳር 1963 (1970) አይሁዶች ታጉረው ከነበሩበት የዋርሶው ጌቶ ፊት ተንበርክከው እንደጠየቁት ይቅርታ፡፡ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬቪን ሩድ በየካቲት 2000 (2008) አቦሪጀኖችን እንደጠየቁት ይቅርታ፡፡ ወይም፣ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰቲን ትሩዶ በመስከረም 2010 (2017) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፊት ቁመው የካናዳ ህንዳዊያንን ይቅርታ እንደጠየቁት፡፡ ሁሉም ግን የጠየቁትን ይቅርታ መቀበል ወይም አለመቀበል የአይሁዶቹ፣ የካናዳ ህንዳዊያንና የአቦሪጀኖቹ የማይገሰስ ነፃ ውሳኔ እንደሆነ የተቀበሉ ነበሩ፡፡
በአጭሩ ለማመላከት መልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ እንደ ሌሎቹ የፍትሕ መንገዶች በሕግ መሠረት ብያኔ ለመስጠት የሚጥር የፍትሕ መንገድ አይደለም፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በጥሩ እንደገለጹት፣ ‹በግጭቶች ምክንያት በማኅበረሰቦች መካከል የተሰበጣጠሰውን መተማመን መልሶ ለማከም፣ ለመጠገንና ለመገንባት የሚጥር የፍትሕ መንገድ ነው› (Restorative Justice Seeks to Repair Broken Trust Between Hostile Groups in the Aftermath of … Conflict)፡፡
በሌላ አገላለጽ የአንድ አፍታና የአንድ ሰሞን ሁነትና ትርዒት አይደለም፡፡ በዳይና ተበዳይን በአደባባይ አቀራርቦ በማወያየት የሁለቱንም ወገኖች ስብራቶች ለማከም፣ ለመጠገንና ለመገንባት የሚጥር የፍትሕ መንገድ ነው፡፡ ይኼንን ማለት ሃይማኖታዊ/ምግባራዊ (Moral) ይቅርታና ዕርቅ፣ በማኅበራዊ ፖለቲካ ይቅርታና ዕርቅ ክንዋኔ ውስጥ ሥፍራ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ፖለቲካ ዕርቅ የበዳይንና የተበዳይን ስብራቶች አክሞ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ፍትሕን በአዲስ የመገንባት ግብ ስላለው፣ ከሃይማኖታዊ/ምግባራዊ ይቅርታና ዕርቅ አካሄድ ይለያል፡፡ የሚጠቀመው የመልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ ዘዴዎችንና መንገዶችን ነው፡፡
መልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ በዳይ/በዳዮችንና ተበዳይ/ተበዳዮችን ለየቅል የሚሞግቷቸው የቂም፣ የጥላጫና የቁርሾ ስብራቶች እንዳሉ ይቀበላል፡፡ በዳዩ ያንን የመሰለ ግፍና በደል የፈጸምኩት በእውነት እኔ ነኝ ወይ? በሚለው ጥያቄ ይታሻል፡፡ ምን ዓይነቱ ሰይጣን ቢጠናወተኝ ነው? እያለ ይብሰለሰላል፡፡ አረመኔያዊ ድርጊት ያስፈጸሙትን ሰዎች ማንነትና ምንነት ይጠይቃል፡፡ ግፍ የፈጸመባቸው የሕፃናት፣ የእናቶችና የሌሎች ሰዎች ምስሎች በውኑም በህልሙም ከፊቱ እየተደቀኑ ይጨነቃል፡፡ ወደቀድሞው ማንነቱ፣ ሰላሙና ሰዋዊነቱ ለመመለስ መልሶችን ይፈልጋል፡፡ ተበዳዩ የግፉ ምንጭ ምንድን ነው? ምን ባጠፋሁና ምን በበደልኩ በእኔ ላይ ደረሰ? ተፈጸመ? በሚሉት ጥያቄዎች ይብከነከናል፡፡ ለሰው ማንነትና ምንነት መልሶችን ይፈልጋል፡፡ የመልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ ሥራ፣ ሁለቱ ወገኖች በአደባባይ ተገናኝተውና ተወያይተው፣ ለረዥም ጊዜ ለሚያፍተለትሏቸው አስጨናቂ ጥያቄዎች የጋራ መልሶችን እንዲያገኙ ማገዝ ነው፡፡ በዳይና ተበዳይ የሚያስጨንቋቸውን ስሜቶቻቸውን ታግለውና አሸንፈው ጠባሳዎቻቸውን እንዲያደርቁ መርዳት ነው፡፡ የሁለቱንም ወገኖች ሰዋዊነት መልሶ ለማቆም መጣር ነው፡፡
መልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ በዳይ/ተበዳዮችን ወደ ቀድሞው ግንኙነቶቻቸው (Relationships) የመመለስ ግብ የለውም፡፡ ግቡ የበዳይ/ተበዳይን ሰዋዊ ግንኙነቶች በአዲስ መሠረትና መንፈስ ላይ መልሶ በማዋቀርና አፅንቶ በማቆም የማኅበራዊ ፖለቲካ ሰላማቸውን መልሶ ማቀዳጀት ነው፡፡ እንዳባባሉ አዎንታዊ ጥልቀት ያቀዳጀን ሰዋዊ ግንኙነት መገንባት ነው፡፡ ደሪዳ ቀጥሎ እንደሚለው ከዚህ ግብ ውጪ የሚደረግ የማኅበራዊ ፖለቲካ ይቅርታና ዕርቅ፣ ‹‹ንፁህ አይደለም››፡፡ ‘የፖለቲካ ይቅርታና ዕርቅ ጥያቄን እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ሸቀጥ ለፖለቲካ ገበያ ለማቅረብ የሚጥር ይሆናል፡፡ የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም የሚያቀንቅን ይሆናል’፡፡
ሁሉም የፖለቲካ በደሎች በመልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ መንገዶች የሚታዩ አይደሉም፡፡ ሙስና፣ ያላግባብ መበልፀግ፣ በሥልጣን መባለግ፣ ወይም አስተዳደራዊ በደልና የተዛባ ፍትሕ ጥያቄዎች ለምሳሌ፣ በሕግ መሠረት የሚታዩና በሕጉ መሠረት ብያኔ የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ መልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ ማንዴላ እንዳመለከቱት በዋናነት የሚያተኩረው፣ ኢሰብዓዊ (አረመኔያዊ) ማኅበራዊ ግጭቶች ጥለዋቸው ‹‹በሚያልፉት›› ስብራቶች ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔር ማንነት ላይ ተመሥርተው እየተፈጸሙ ያሉት ኢሰብዓዊ ጥቃቶች ጥለው ያለፉትን ጠባሳዎች ማለት ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ የኢትዮጵያ ብሔር ራሱን በብሔር ወገኑ ለይቶ፣ አደራጅቶና አስታጠቆ ወይም በግብታዊ ተነሳስቶ በሌላው ብሔር ላይ ግፍ ሲፈጽም የተሰማውና የታየው ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ይኼንን የመጀመርያ የመጀመርያውና የመጨረሻው አድርጎ ለማስቀረት የኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ጥረትና ትግል ይጠይቃል፡፡ የጥሪው አቅራቢዎች ጥሪያቸውን ከመልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ አንፃር ጭምር ቢያጤኑት የሚበጅና የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ለዚህም ከማንዴላ ቱቱ የሰላምና ዕርቅ ኮሚሽንና ፖል ካጋሜ በሥራ ካዋሉት የጋቻቻ ሥርዓት ድረስ ብዙ ትምህርቶችን መቅስም ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም የበርካታ ባህላዊ መንገዶች ባለቤት ናት፡፡ በመልሶ ገንቢ (አዳሽ) ፍትሕ የተመረቁና ከሴራሊዮን እስከ ሩዋንዳ ድረስ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን የቀሰሙ በርካታ ባለሙያዎችም አሏት፡፡
በፍቅር መደመር
ፍቅር የሚለው ቃል በፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ መወሳት የጀመረው ከ60ዎቹ ዓመት ጀምሮ ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ ምናልባት በ60ዎቹ የፀረ ቪየትናም ጦርነት ዘመን ‹‹ተፋቀሩ፣ ጦርነትን አቁሙ›› (Make Love, Not War) እያሉ ለአሜሪካን ወታደሮች አበባ ሲያድሉ የነበሩት ሂፒዎች ናቸው፡፡ ከዚያ ወዲህ ፍቅር በፖለቲካ ውስጥ ስላለው ሥፍራ አብዝተው የሚዘምሩት፣ በተለይ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና በተለይም በምርጫዎች ሰሞን ነው፡፡
ለዚህም ኮሪ ብሩክ የተባሉት ሰው በ2008 (2016) የአሜሪካ ብሔራዊ ዴሞክራቲክ ኮንቬንሽን ላይ፣ ‹‹የተጠራነው የፍቅር ብሔረ መንግሥት እንድንሆን ነው›› (We are Called to be a Nation of Love) በማለት የተናገሩት እንደ ምሳሌ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ በ2008 ምርጫ ወቅት የትራምፕ ተቃዋሚዎችም የትራምፕን ስም ባሹር አዙረው፣ ‘Love Trumps Hate’ የሚል መፈክር ያሰሙ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውጪና ሂፒዎች “የፍቅር በጋ” (Summer of Love) በሚሉት ዓመታዊ የአንድነት ውሏቸው ላይ ከሚያሰሙት የፍቅር ጥሪ ውጪ ፍቅር እንደ ማኅበራዊ ፖለቲካ ጥሪ በፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ አይወሳም፡፡
ዶ/ር ዓብይ በፍቅር መደመር ያሉት በአሜሪካ እንደሚሆነው የምርጫዎች ሰሞን የቅስቀሳ ጥሪ ማለት ከሆነ፣ በአሜሪካ እንደሚሆነው ዞሮ ዞሮ ፖለቲካዊ ነው፡፡ አሁን አሁን እንደ መፈክር ጭምር እየወረደ የፖለቲከ ሥነ ሥርዓቶች ማሳረጊያ መሆኑ ደግሞ፣ ወደ ፖለቲካ ቅስቀሳ (Agitation) ደረጃ የወረደ ጥሪ አስመስሎታል፡፡ ከፍተኛ የማኅበራዊ ፖለቲካ ለውጦች በሚካሄዱበት ወቅትና ሁኔታ ግን፣ ሁለቱን ቃላት በአንድ ማራመድና ከእነ ጭራሹም ወደ ፖለቲካ ቅስቀሳ ደረጃ ማውረድ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡
ፍቅር የስሜቶች መግለጫ ነው፡፡ ከግሪክ ፈላስፎች ጀምሮ ያሉት ፈላስፎች ከሚጠይቋቸው ከሦስቱ የፍልስፍና ጥያቄዎችም አንደኛው ነው፡፡ ሌሎቹ ሕይወት ምንድነው? ሞት ምንድነው? የሚሉዋቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ መደመር አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር የሒሳብ ክፍል ነው፡፡ ወደ ፖለቲካ ሲተረጎም ተቆጥረው የሚተባበሩትን፣ የሚዋሀዱትን፣ የሚጣመሩትንና የሚቀናጁትን… የፖለቲካ ኃይሎች ማለት ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር በእጅግ በተወሳሰበው የኢትዮጵያ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የማንነት ተፈጥሮ ውስጥ የሚስማሙበትን መለስተኛ የፖለቲካ ኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖለቲካ መድረክ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በከፍተኛ የፖለቲካ ማኅበራዊ ለውጥ እየተናጠች የምትገኝ አገር እንደሆነች ግልጽ ነው፡፡ ከብዙና ከባድ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የማንነት ጥያቄዎች ፊት የቆመች አገር እንደሆነችም ግልጽ ነው፡፡ የተለያዩት የፖለቲካ ኃይሎችም ረድፍ ረድፋቸውን እየያዙ የፖለቲካ ጡንቻቸውን ለማፈርጠምና ለማሳየት ያኮበከቡባት አገር ናት፡፡ … በዚህ ሁኔታ የሚሻለው ይልቁኑም ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን ለይቶና ተጨባጭ ቅደም ተከተሎችን አስቀምጦ ላፈጠጡትና ላገጠጡት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የማንነት ጥያቄዎች ሳይውሉ ሳያድሩና ዕለት በዕለት ተጨባጭ መልሶችን መሻትና መፈጸም ይመስለኛል፡፡ ወራት እየተደራረቡ ያለፉትን ያህል ጥያቄዎቹ እየተበራከቱ፣ እየተወሳሰቡና እየጠጠሩ ይደልባሉ፡፡ ማንኛውና መቋጠሪያው ሁሌም ከደጅ የሚገኝ አይደለም፡፡
መደመር የሚለው ቃል ወደ አንድነት መምጣት (Coming Together) በሚል ከተወሰደ የፖለቲካ ማኅበራዊ ይዘቱ ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌም በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ ተወያይቶና ተስማምቶ፣ ለአንድ የብሔራዊ አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች በአንድነት መቆምና መሠለፍ ማለትን ሊሆን ይችላል፡፡ ተነቅሰው የሚዘረዘሩት የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችም ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አምኖባቸውና ወዶ፣ ፈቅዶና የራሱ አድርጎ ዛሬ ለራሱና ነገ ለትውልዱ ሲል የሚቆምላቸው ብሔራዊ አገራዊ ንብረት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ብሔራዊ ስትራተጂካዊ ጥቅሞች በአጭሩ በአንድ በኩል የሚታወቁት የብሔራዊ ሉዓላዊነት የጋራ ውስጣዊ ሰላምንና የሳይበር ፀጥታን መጠበቅ፣ መከበርና መረጋገጥ ይመለከታሉ፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሌላው በኩል የሕገ መንግሥትና የሕግ የበላይነት መከበርን፣ የሰቪል መብቶች፣ ነፃነቶች፣ የዴሞክራሲና የብሔሮች እኩልነት መረጋገጥን፣ ከታሪክ ጠባሳዎች ቆጠራ የተላቀቀ የሕዝቦች ታሪኮች ትረካን፣ የብሩህ ብሔራዊ የጋራ ወደፊት ትረካን፣ የመልካም አስተዳደር መገንባትን፣ የጋራ ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግናን፣ ፈጣን የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕድገትን፣ የኢኮኖሚ ፍትሕና ተቋዳሽነትን፣ የስትራቴጂካዊ ተፈጥሮ ሀብቶች፣ ውኃ፣ ወንዞችና ሐይቆች እንክብካቤና የግድቦች አርበኝነትን፣ የአካባቢ ተፈጥሮ እንክብካቤ ጥበቃና ልማትን፣ የምግብ ሉዓላዊነትን መቀዳጀትንና ከዕርዳታ ጥገኝነት የመላቀቅን፣ የቤተሰብ ዕቅድና የሕዝብ ብዛት ቁጥጥርን፣ ያላሰለሰ ፀረ ዕፅና ፀረ ኤድስ ትግልን፣ የወደብ ባለቤት ለመሆን የመብቃትን፣ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ኅብረተሰብ መፍጠርን፣ ቀጣናዊና አኅጉራዊ ሐሳብ አመንጪነት፣ መሪነትንና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተከበረችና የኮራች አገርና ሕዝብ ባለቤት ለመሆን የመብቃት ጉዳዮችን ይመለከታሉ፡፡ በእኔ አረዳድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለተዘረዘሩትና እነሱን ለመሳሰሉት የዛሬና የነገ የጋራ ብሔራዊ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች በአንድ የማይሠለፉበት ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን እያንዳንዱ ዜጋ ዞሮ ዞሮ ‹‹የሚፋቀረውና የሚደመረው›› ከመሰሉ የማኅበራዊ–ፖለቲካ አመለካከት ቤተሰቡ ጋራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ወገን የብሔርና የሃይማኖታዊ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ማለታቸው እንደሆነ ባይታወቅም፣ ‹‹ንጉሣዊ››፣ ‹ወግ አጥባቂ›፣ ‹‹ሊበራል›፣ ‹ሠራተኛ›፣ ‹ሶሻል–ዴሞክራት› ነን ባዮች ናቸው፡፡ ነባራዊው ሁኔታ የሚያመለክተውም፣ ከኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አንስቶ እስከ ስንቶቹ ድረስ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ለዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚመጥን የፖለቲካ ፕሮግራም እንዳላቸው እንኳን አይታወቅም፡፡ በሌላው ወገን ነባር ኅብረቶች መለወጣቸው ወይም መሸጋሸጋቸውና አዳዲስ ኅብረቶች መወለዳቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ላይ ዶ/ር ዓብይን ጨምሮ አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ፣ ‹‹ሁለት ሦስት ፓርቲዎች ይበቃሉ›› እያሉ የሚያራምዱት አቋም አለ፡፡ ይህም የብሔርና የሃይማኖታዊ ድርጅቶች በሲቪክ ማኅበር ደረጃ አንዲደራጁ የሚጠራ ይመስለል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የተጣሩትንና መስመር የያዙትን ያህል የፖለቲካ ሥርዓቱ ውል ይይዛል፡፡
እዚህ ላይ ግን ዶ/ር ዓብይ ተቃዋሚዎችን ‹‹ተፎካካሪ›› ብለው መሰየማቸው፣ ከቅድመ ሁኔታዎቹ በእጅግ ቀድሞ የተዋወቀ ቃል እንደሆነም እንዲታወስ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፉክክር በፖለቲካ ተፎካካሪዎች መካከል እውነተኛ የፖለቲካ ፉክክር የሚሆነው፣ ተፎካሪዎቹ ራሳቸው ከሁሉ በፊት ሲቪክ ባህል በሚባለው የፖለቲከ ባህል የታነፁና በባህሉ የዳበሩ ሲሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛም የፖለቲካ ፉክክሩ ሜዳ ለሁሉም ተፎካካሪ እኩልና ፍትሐዊ (Level Play Field) መሆኑ የተረጋገጠና ከተፎካካሪዎቹ ባሻገር የመላ ሕዝቡን ተቀባይነትና አመኔታ ያገኘ ሲሆን ነው፡፡
ከፖለቲካ ፉክክርና ተቃውሞ በተጨማሪ ግን የየራሳቸው ጊዜና ወቅት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ለሥልጣን ይፎካከራሉ፡፡ በዚህም ወቅት፣ ገዢው ፓርቲ ራሱ ተፎካካሪ ነው፡፡ ተቃራኒው አመለካከት ገዢውን ፓርቲ ‹‹አፎካካሪ አድርጎ የመመደብ ያህል ይሆናል፡፡ በሁለት ምርጫዎች መካከል ባለው ወቅት ደግሞ፣ በምርጫ ያሸነፈው ይገዛል፡፡ በምርጫ የተሸነፈው እስከሚቀጥለው የምርጫ ፉክክር ድረስ የተቃዋሚነት ሥፍራውን ይይዛል፡፡ የተቃዋሚነት ሚናውን ይጫወታል፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ‹‹ተፎካካሪ›› የሚለው ስያሜ ሄዶ ሄዶ ወደ ‹‹ተፎካከሩ፣ አትቃወሙ›› ወደ ሚል የፖለቲካ ዓይነት እንዳይደፋ በእጅግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ምርጫ ተሸናፊና አሸናፊ የሚለዩበት ሒደት ቢሆንም፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ተፎካካሪዎቹ በጋራ በያዙት ብሔራዊ አገራዊ አቋም ላይ ተባብረውና አንድ ሆነው ሊቆሙና ሊሠሩ ይገባል ማለት ነው፡፡
ከዚህ ጋራ በተያያዘ ደግሞ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመዘኑት በፕሮግራማቸው ብቻ እንዳልሆነም እንዲመለከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰና በበለጠ እንዲያውም የገዢው ይሁን የተቃዋሚ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የፋይናንስ ምንጭ ጉዳይ መሠረታዊና በእጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፋይናንስ ምንጭ ግልጽ መሆን አለመሆኑ፣ ፓርቲዎቹ በእውነትና በሀቅ የዴሞክራሲያዊትና ሰላማዊት ኢትዮጰያ መሥራች መሐንዲሶች መሆን አለመሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ መመዘኛ ይሆናል፡፡ ፓርቲዎቹ የፋይናንስ ምንጫቸውን ግልጽ ማድረግ አለማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
ለፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ መኖር እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀም ሕግና ደንብ ጉዳይ በእጅግ እንዲታሰብበት የሚያስፈልግ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ነው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ገዢው ግንባር እንደ ግል ንብረቱ ሲጠቀምባቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህም አልፎ የመገናኛ ዘዴዎች ባለንብረቶች ናቸው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወዲህ ከእነ ጭራሹ ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተዋናዮች የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸውን እንዲተክሉ እየተፈቀደ ነው፡፡
ተደጋግሞ እንደሚባለው ‹‹መቼም ኢትዮጵያ ልዩና የተለየች አገር ናት›› ካልተባለ በስተቀር፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተዋናዮች በየትም አገር ከጋዜጣ በስተቀር የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ባለቤትነት አይፈቀድላቸውም፡፡ አንድ ብቸኛዋ አገር ዩክሬይን ናት፡፡ ሌላው የሚዲያ ማግኔት የነበረው የኢጣሊያኑ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ነበር፡፡ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገሮች ግን ፖለቲካ ድርጅቶችና ተዋናዮች እንኳን ባለቤት ሊሆኑ ቀርቶ የመገናኛ ዘዴዎች አክሲዮኖች ባለቤት እንዲሆኑ አይፈቀድም፡፡ የዴሞክራሲያዊ መድረኮች መስፋት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተዋናዮች የሚዲያ አጠቃቀም ሕግና ደንብ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ይህ መሠረታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ጉዳይ ሥርዓት ሳይዝ በፊት የሚወሰድ ማንኛውም ዕርምጃ፣ በዴሞክራሲ መድረኮች መስፋት ስም ዴሞክራሲን ራሱን መፃረር ይሆናል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚያስፈልገውን እኩልና ፍትሐዊ ሜዳ አጣሞ መገንባት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ አገራዊ የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ የተስማሙና የተዋዋሉ ቢሆኑ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ህልውናና የነገይቱ ኢትዮጵያ የጋራ ወደፊት መሐንዲሶች ይሆናሉ፡፡ ፍትሐዊና ሕዝባዊ ቅቡልነትን የተቀዳጀ ምርጫ ከተከናወነና ከተፈጸመ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለያዩት የፖለቲካ ቀለሞቻቸው ደምቀው ይደመራሉ፡፡ የዶ/ር ዓብይ በፍቅር መደመር ጥሪ የፖለቲካ ሥጋ ለብሶና የፖለቲካ ነፍስ ዘርቶ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ዕውን ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ወደፊት በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በእውነትና በሀቅ የኢትዮጵያ ከሆኑ 2011 ዓ.ም. ያቀረበውን የታሪክ አጋጣሚ ማባከን የለባቸውም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡