Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአስመጪነት ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓት ሊኖረን አይገባም››

አቶ መላኩ አለበል፣ የንግድ ሚኒስትር

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት፣ በተለይ ንግድና ኢንቨስትመንት ማካሄድና ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሒደት በተወሰኑ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረት፣ ኮንትሮባንድ ደግሞ የመስፋፋት አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአምስት ወራት በፊት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግን ያለመረጋጋቱ ጭጋግ በተወሰነ ደረጃ ገፎ አንፃራዊ መነቃቃት ታይቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ንግድ ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት የተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ዕቅዶችን አውጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በገጠሙና በተያዘው በጀት ዓመት ይከናወናሉ ተብለው በታቀዱ ሥራዎች ላይ ውድነህ ዘነበ የንግድ ሚኒስትሩን አቶ መላኩ አለበል አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መነገድም ሆነ መሥራት አልተቻለም ነበር፡፡ ባለሀብቶች በሕገወጦች ንብረታቸውን ያጣሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ከዚያ ባለፈም ያፈሩት ሀብት ይወድምባቸዋል፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ለነጋዴዎች መተማመኛ ለመስጠት የታሰበ ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ መላኩ፡- ይህ እንደ አገር ዋና ሥራ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ‹‹እንደመር›› የሚለው መርህ ዓላማ በአገሪቱ ውስጥ የተመቸና የተሻለ ከባቢ ለመፍጠር ነው፡፡ ሰዎች በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት፣ ተገማች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበት ከባቢ ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡

ባለፉት አራት ወራት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አሉ፡፡ የበለጠ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚያካሂደው ጉባዔ አለ፡፡ ጉባዔው ባለፉት ዓመታት በነበሩ የሥራ አፈጻጸሞች ላይ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ውሳኔዎች ይሰጣል፡፡ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በኋላ የበለጠ መረጋጋት ይፈጠራል፡፡ ተቋማዊ አቅምም እንዲሁ ያድጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በሁለት መመርያዎች ላይ ማሻሻያ አድርጋችኋል፡፡ ማሻሻያው የመጣው በዓለም ባንክ ግፊት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ምክንያቱም ከዓለም ባንክ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በቀጥታ በጀት ድጋፍ ለማግኘት ድርድር እየተካሄደ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መመርያዎቹ የተሻሻሉት በዓለም ባንክ ግፊት ነው?

አቶ መላኩ፡- ከዓለም ባንክ ጋር ብዙ ሥራዎችን ነው የምንሠራው፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት እናነሳለን፣ የሴፍቲ ጉዳይ እናነሳለን፡፡ የዱኢንግ ቢዝነስ ከባቢ ጉዳይ እናንሳለን፡፡ ሲስተም የመዘርጋት ጉዳይ እናነሳለን፡፡ ከዓለም ባንክ ጋር ብዙ ሥራዎችን አብረን እንሠራለን፡፡ ደግፉን ብለን እየጠየቅናቸው አብረን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቀጥታ በጀት ድጋፍ እየተሠራ ያለው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ፕላን ባደረግነው መሠረት ነው እነዚህን መመርያዎች ያሻሻልነው፡፡ ይህ ሥራ በአጭር ጊዜ የሚሠራ አይደለም፡፡ ብዙ ጥናት ተጠንቶ ነው መመርያዎቹ የተሻሻሉት፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምትመድብባቸው ዘርፎች አንዱ ብረት ነው፡፡ በብረት ማምረት ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ምን ያህል ጥበቃ ታደርጉላቸዋላችሁ? ምክንያቱም በግልጽ እንደሚሰማው አስመጪዎች በአምራቾች ላይ ጫና ያደርጉባቸዋልና፡፡

አቶ መላኩ፡- የእኛ ኢኮኖሚ ጤነኛ መሆኑን ከምታወቅባቸው መንገዶች አንዱ ላለፉት ዓመታት ለየትኞቹ ዘርፎች ትኩረት ተሰጠ በሚለው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ላለፉት ዓመታት ብዙ ገንዘብ ያወጣነው ለብረት ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ያወጣነው ለማሽኖች፣ ለኢንዱስትሪና ለኬሚካል ነው፡፡ ይኼ ምንን ያሳያል ብትል ፍጆታ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ሌላ ኢኮኖሚ ሊፈጥሩ ለሚችሉ ባለሀብቶች ነው፡፡ ብረት በመኖሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያድጋል፡፡ ኬሚካል በመግባቱ ኢንዱስትሪዎች ያድጋሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ኢምፖርት ላይ ነበር ትኩረት እየተደረገ የነበረው፡፡ ፋብሪካዎች በቂ አቅም አልነበራቸውም፡፡ አሁን የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች የበለጠ አቅማቸውን እያጠናከሩ ነው፡፡ የእኛ ፍላጎት የአገር ውስጥ አምራቾችን በፖሊሲ በመደገፍ እንዲጠናከሩ ማድረግ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ አቅማቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ ፍጆታ በአገር ውስጥ አምራቾች መሸፈን ይኖርበታል፡፡

እንደ አገር ከብረት አፈር ጀምሮ እዚህ ለማምረት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ይህንን እዚሁ ማምረት ሲቻል የእኛን ፍላጎት እዚሁ ማሟላት ይቻላል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን አሁንም መስተካከል ያለበት ነገር አለ፡፡ እሱም የተወዳዳሪነት ጉዳይ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ምርት በመሆኑ ምክንያት በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን የለበትም ማለት አይደለም፡፡ እስካሁን አልፎ አልፎ ለብረት ግዥ የሚሰጥ የውጭ ምንዛሪ ቢኖርም፣ አሁን ግን መንግሥት ዝንባሌው የአገር ውስጥ አምራቾች ጥሬ ዕቃ የሚገዙበትን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ማሻሻል ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ የብረት ንግድ ሰንሰለት በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተይዟል የሚል ቅሬታ አለ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ ጥናት እያካሄደ ነው፡፡ የንግድ ሰንሰለቱን የሚረብሹና የተወሰኑ ሰዎች ተቆጣጥረውታል ወይስ ምንድነው የሚለውን ጉዳይ ጥናቱ ይመልሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀረጥ ነፃ መብትን ያላግባብ የመጠቀም ሁኔታ ይታያል፡፡ ከሚያስፈልግ ዕቃ በላይ ማምጣት፣ አገር ውስጥ የሚመረት ምርት ከውጭ ማምጣት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ መላኩ፡- አንዱ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ይኼ ነው፡፡ አገር ውስጥ መግዛት የቻልነውን ከውጭ ማምጣት መስተካከል አለበት፡፡ ጥራትና የዋጋ ተወዳዳሪነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ጥራትን በመጠበቅ በዋጋም ተወዳዳሪ መሆን ይገባል፡፡

ነገር ግን በኢንቨስትመንት ማበረታቻ አዋጅ ባለኮከብ ሆቴሎችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚሰማሩ የቀረጥ ነፃ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ በሪፎርም ሥራችን መታየት ይኖርበታል፡፡ ተፅዕኖውና አስተዋጽኦው በሪፎርም ሥራችን ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ከኤክስፖርት የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ አልተቻለም፡፡ በዚህ ላይ ብቸኛው ዘመናዊ የወርቅ ማውጫ የሆነው ሚድሮክ ጎልድ (ለገደንቢ) እንዲቆም ተደርጓል፡፡ የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ሥራ ለማስጀመር ምን እየተሠራ ነው? ሚድሮክ ጎልድ ሥራ በማቆሙ የወጪ ንግድ ተፅዕኖው እንዴት ይገለጻል?

አቶ መላኩ፡- ይህን ጉዳይ የሚከታተለው የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ነው፡፡ ነገር ግን ከማዕድን የምናገኘው ገቢ እየቀነሰ ስለሆነ ሰፊ የማሻሻያ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ባህላዊ የማዕድን አምራቾች ላይ የሚታዩ ምርት የመቀነስ ችግሮች ስላሉ መስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ሚኒስቴር የሪፎርም ሥራዎችን እያካሄደ ነው፡፡ የትኞቹን አሠራሮች ለማስተካከል ታስቧል?

አቶ መላኩ፡- በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና፣ ግልጽነት ለማምጣትና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለንግዱ ማኅበረሰብ ቀላል ለማድረግ ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ በቀጥታ በድረ ገጽ የንግድ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችል ይደረጋል፡፡ በወጪ ንግድ ሰንሰለት ላይ ያሉትን ችግሮች፣ በተለይም እሴት የማይጨምሩትን በመለየት ማሻሻያ በማድረግ የሚገኘውን ገቢ የመጨመር ዕቅድ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት አቅዳችኋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተገኘው አንፃር በዕጥፍ ብልጫ ያለው እንደመሆኑ መጠን የዕቅዳችሁ መነሻ ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- በ2011 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 4.43 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ነገር ግን ዕቅዳችን በብሔራዊ የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ አልፀደቀም፡፡ በተጠናቀቀው 2010 በጀት ዓመት 2.81 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ የተፈጠረው ሰላምና መነቃቃት በ2011 ዓ.ም. ኤክስፖርት ያሳድጋል ብለን ተስፋ እንዲኖረን አድርጎናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በ90 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የጠረፍ ንግድ ታካሂዳለች፡፡ ይህ ንግድ በሥርዓት እየተመራ ባለመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይነገራል፡፡ በዘላቂነት ይህን ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?

አቶ መላኩ፡- የጠረፍ ንግድ ላይ ብዙ መሥራት አለበት፡፡ በሁሉም የጠረፍ አካባቢዎች ላይ ችግር አለ፡፡ አንዳንዶቹ ፍራንኮ ቫሉታ አሠራርን፣ አንዳንዶቹ የጠረፍ ንግድ ብለን ያስቀመጥናቸውን ይቃረናሉ፡፡ የጠረፍ ንግድ ሕግ በሚወጣበትና ስምምነት በሚፈረምበት ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በዚያኛው ወገን ያለውን አገርን ሐሳብ ያካተተ ነው፡፡ በእኛ በኩል ለምንፈልጋቸው ነገሮች በሌላኛው ወገን እኩል ስሜት ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአገር ተጠቃሚነት አንፃር ሳይረዝም መስተካከል ያለበት በማለት ንግድ ሚኒስቴር እየሠራ ነው፡፡ ምናልባት እስከ 2011 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ድረስ የመጨረሻ ዕልባት እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፓልም ዘይት ንግድን ለተወሰኑ ባለሀብቶች ስትሰጡ የዘይት ፋብሪካ ለመገንባት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል በሚል እሳቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ግንባታ የጀመሩ እንዳሉ ሁሉ ያልጀመሩም አሉ፡፡ ሥራው ከተሰጣቸው ውጪ ያሉ ኩባንያዎች ፋብሪካ እየገነቡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሥራው ሊሰጣቸው እንደሚገባ እየጠየቁ ነው፡፡ የንግድ ሚኒስቴር አቋም ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- ወደ አገራችን በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ይገባል፡፡ ፍላጎት ከዚህ ትንሽ ከፍ ይላል፡፡ በውጭ ምንዛሪ 440 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት በዓመት ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ ይኼ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ባለው አገር፣ የግብርና ምርትን ከውጭ እያስመጡ መቀጠል በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ ስለዚህ በቂ ስትራቴጂ ተቀርፆ የዘይት ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን፣ አለፍ ሲልም ኤክስፖርት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በአስመጪነት ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓት ሊኖረን አይገባም፡፡ በተለይ ዘይት፣ ስንዴና ስኳር ከውጭ ማስገባት የለብንም፡፡ ለዚህ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ስትራቴጂው በውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ ባይገባም፣ ሐሳቡ ዘይት በማምረትና የቅባት እህሎችን በማምረት የተሰማሩ ባለሀብቶችን የሚደግፍ ነው፡፡ ስለዚህ በዘይት ንግድ ላይ ያለውን ከመደገፍ ይልቅ አምራቹን የመደገፍ ዕቅድ ነው ያለን፡፡

ቀደም ሲል ግንባታ የጀመሩ፣ ቦታ የወሰዱና ዘይት ወደ ማምረት የገቡ ባለሀብቶችን ከዚህ ጋር አስተሳስረን ብንደግፋቸው የበለጠ ውጤት ያመጣሉ የሚል ሐሳብ ስለነበር ላለፉት ዓመታት ሲሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ባለሀብቶች ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ ግን ፋብሪካ አቋቁመው ወደ ማምረት እየገቡ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ መሻሻል ስላለበት በትክክል አምራሮቹ ብቻ እንዲጠናከሩ የሚያደርግ መመርያ ተዘጋጅቶ ወደ ክልሎች ወርዷል፡፡ መመርያው ዘይት ፋብሪካ እየገነቡ ያሉትን ይደግፋል፡፡ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ በአስመጪነት እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡ በእርግጥ ይህ ሥራ በነፃ ኢኮኖሚ መርህ መመራት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ምርቱን ካላሳደግን በስተቀር በኢኮኖሚ ውስጥ እጥረት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ በሚቀጥለው አንድ ወር የማጣራት ሥራ ተካሂዶ፣ ተወዳዳሪዎችና አሸናፊዎች ተለይተው ወደ ሥራ ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ100 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ አብዛኛዎቹ የፍጆታ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ አስመጪዎች ደግሞ በሙሉ አዲስ አበባ ላይ የከተሙ ስለሆነ የአገሪቱ ሕዝብ ከአዲስ አበባ መርካቶ ለመገበያየት ይገደዳል፡፡ ክልሎች የራሳቸው አስመጪ ለምን አይኖራቸውም?

አቶ መላኩ፡- ከዚህ በፊት መከናወን የነበረበት ሥራ ነው፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት አገር ብቸኛው የምርት መገኛ መርካቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አስመጪዎችን በየክልሉ መፍጠር ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ምልመላና ሥልጠና ተጀምሯል፡፡ በየክልሉ ሊያስመጡ ይችላሉ የተባሉ ባለሀብቶችን መመልመልና ማሠልጠን ተጀምሯል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለአስመጪነት ፈቃድ ለመስጠት አሠራሩ ከፌዴራል ወደ ክልሎች እንዲወርድና ክልሎች እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ነገር ግን ሥራው ከባድና ልምድ የሚጠይቅ እንደመሆኑ የንግድ ሚኒስቴር ለክልል ንግድ ቢሮዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ድጋፍ  ይሰጣል፡፡ ይህ ሲሆን ኢኮኖሚው በራሱ ይነቃቃል፡፡ አላስፈላጊ ወጪዎችን ያስቀራል፡፡ በዚህ ዓመት የመጀመርያዎቹን የክልል አስመጪዎች ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኮንትሮባንድ እየሰፋ መጥቷል፡፡ ኮንትሮባንድ ንግድ አገሪቱ ከወጪ ልታገኝ የምትችለውን ገቢ ከማሳጣቱ በተጨማሪ፣ በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ያን ያህል ትኩረት እንዳልሰጠውም ይነገራል፡፡ የእርስዎ መሥሪያ ቤት ያለው አቋም ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- ኮንትሮባንድን ለመከላከል በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡ ነገር ግን ኮንትሮባንድ በንግድ አሠራሩ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ በጋራ እየሠራን ነው፡፡ በጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በቅንጀት እየሠራን እንገኛለን፡፡ የንግድ ሚኒስቴር አመራርና ባለሙያ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰፊ ድንበር ትዋሰናለች፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ቁጥጥር ሲደረግ በሌላ ቦታ ይሾልካል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የንግድ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው ተቋማት እስከ ታች ድረስ በመውረድ ያለውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ በሚገባው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ኤክስፖርት በምናደርጋቸው ምርቶችን በገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡

አንዳንድ አገሮች ኢትዮጵያ የምታመርታቸውን ሳያመርቱ እነዚያኑ ምርቶች ግን እየላኩ ያሉ አገሮች አሉ፡፡ ይኼ በቀጥታ ከኮንትሮባንድ ጋር ይያያዛል፡፡ ለንግድ ሥራችን ዘመናዊነት ኮንትሮባንድን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋጋ ንረት እየታየ ነው፡፡ ይህንን ለመፍታት ንግድ ሚኒስቴር ምን እየሠራ ነው?

አቶ መላኩ፡- መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በተለይም ዘይት፣ ስኳርና የስንዴ ዱቄት መንግሥት በድጎማ እያስገባ ዋጋ ለማረጋጋት እየሠራ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በስፋት የሚጠቀምባቸው ስለሆኑ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ እያስገባ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ባሻገር ከብረትና ከሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ጋር የተያያዙ ምርቶች ባለፉት ወራት ገበያው ላይ ተፅዕኖ አሳድረው ነበር፡፡ ዋጋ ለማረጋጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠራን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ብረት ፋብሪካዎች በአጠቃላይ ከ3.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ብረት የማምረት አቅም አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፋብሪካዎች ለሚያስፈልጋቸው ጥሬ ዕቃ ግዥ የሚሆን ካለን የውጭ ምንዛሪ ላይ በዛ የሚለውን መድበንላቸዋል፡፡

ይህ የመደብነው የውጭ ምንዛሪ በሙሉ አቅማቸው መንቀሳቀስ ባያስችላቸውም እንኳ፣ በተወሰነ ደረጃ እንዲያመርቱ የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት በገበያ ውስጥ ሲጨምር የነበረው የብረት ዋጋ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ አሁንም በዚህ ዘርፍ መሥራት ያለብን ጉዳይ ይኖራል፡፡ የምርቱን ዱካ ተከትለን የመጣበት ዋጋ ምን ያህል ነው? ለማን ነው እየተሸጠ ያለው? በንግድ ሥራ ውስጥ ያለው የዋጋ መጋነን ነው? ወይስ ሌላ? የሚለውን እንመለከታለን፡፡ በአገር ውስጥ ያሉት ምርቶች ላይ ያየነው የምርት ትስስር ደካማ መሆኑን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የምንናገረው ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ ስለሚወጡት ምርቶች ነው፡፡ በአገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን ክልሎች እንዴት እየወሰዱ ነው የሚለው አልተሠራበትም፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ ላይ ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ ከተማ ከክልል የገበሬ ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር በመተሳሰሩ በዋጋ ላይ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ዓይተናል፡፡ ተቋማት ከተቋማት ጋር ተቀናጅተው እንዲገበያዩ ይደረጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ በቂ ምርት እንዲኖር ማድረግ እንጂ በፖሊሲ ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ...