በዳዊት ታዬ
ባንኮች ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚው በጋራም ሆነ በተናጠል ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል አንዱ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ይገኝበታል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት አዋሽ ባንክ፣ ኅብረት ባንክና ንብ ባንክ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓትን ለመተግበር በጥምረት የሚያስተዳድሩትን ፕሪሚየም ስዊች ሶሉሽንስ (ፒኤስኤስ) በመባል የሚታወቀውን ኩባንያ በማቋቋም ሥራ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በሒደትም ብርሃን ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ጥምረቱን ተቀላቅለው የፕሪሚየም ስዊች አባል ተቋማት ብዛት ወደ ስድስት ከፍ ሊል ችሏል፡፡ በባንኮች መካከል እየተወዳደሩ የመተባበር ሥራ የሚገለጽበት ፕሪሚየም ስዊች፣ ከተመሠረተ ስድስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉና በፕሪሚየም ስዊች በኩል የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠንም በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፕሪሚየም ስዊች ሶሉሽንስ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ፀሐይ ሽፈራሁ የተቋሙን የ2010 ዓ.ም. አፈጻጸም በተመለከተ ሐሙስ፣ መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደገለጹት፣ በስድስት ባንኮች መካከል የሚከናወኑ የሒሳብ ልውውጦችን በማሳለጥ ለአባል ባንኮቹ ደንበኞችም የአገልግሎት እርካታንና ምቾትን እንዳተረፈና በአገር አቀፉ የባንክ ለባንክ የክፍያ ሥርዓት ውስጥም ወሳኝ ሚና በመጫወት በርካታ የክፍያ ልውውጦች እንዲስተናገዱ በማስቻል በኩል ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ. በተጠናቀቀው የ2017/18 የሒሳብ ዓመት፣ ከሲስተሙ ጋር በተገናኙ ከ600 በላይ የአውቶሜድ ክፍያ ማሽኖችን (ኤቲኤሞች) እና ከ1,200 በላይ የሽያጭ መዳረሻ የክፍያ ማሽኖችን (ፖይንት ኦፍ ሴልስ ተርሚናሎች ፖስ) በመጠቀም ፕሪሚየም ስዊች 7.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የ8.4 ሚሊዮን ልውውጦችን ለአባል ባንኮቹ እንዳስተላለፈና እንዳቀናበረ አቶ ፀሐይ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተፈጸመው ልውውጦች፣ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው ይልቅ ከፍተኛ ብልጫ የተመዘገበበት ነው፡፡ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮም ያስተላለፈውን የፋይናንስ የአገልግሎት ግብይት መልዕክቶች ብዛት ከ19 ሚሊዮን በላይ ማስመዝገብ አስችሎታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 58 በመቶ የአንዱ ባንክ ደንበኞች በሌሎች ባንኮች ክፍያ ማሽኖች አማካይነት ያካሄዷቸው ግብይቶች ሲሆኑ፣ ይህም ፕሪሚየም ሶሉሽንስ የተቋቋመለትን ዓላማ ማሳካት ስለመቻሉም ጠቋሚ ነው ተብሏል፡፡
ፕሪሚየም ሶሉሽንስ ሁሉን አቀፍ የሆነና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂ በመገንባትና ሥራ ላይ በማዋል፣ አባል ባንኮች ለደንበኞቻቸው ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ እያገዘ ይገኛል፡፡ ባንኮቹ በፕሪሚየም ሶሉሽንስ እየታገዙ ከሚሰጧቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከልም በኤቲኤም (የገንዘብ ወጪ መጠየቂያ) ካርድ አማካይነት ለደንበኞች አመቺ በሆኑ ቦታዎች በተተከሉ ማሽኖች አማካይነት አገልግሎት መስጠት አንደኛው ነው፡፡ በተጨማሪም ደንበኞች ክፍያቸውን በሽያጭ መዳረሻ የክፍያ ማስተናገጃ ማሽኖች እንዲጠቀሙ በማስቻል ሲስተሙ ሳምንቱን በሙሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት የፋይናንስ ግብይትን የሚያንቀሳቅሱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ማሽኖችን ትግበራ በንቃት በመከታተል የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓቱ የተቀላጠፈ እንዲሆን የድጋፍ አገልግሎት መስጠትና መሰል ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ፕሪሚየም ስዊች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት አባል ባንኮች የቪዛ፣ የማስተር ካርድና የዩኒየን ፔይ ካርዶችን በኤቲኤሞች አማካይነት እንዲስተናገዱ ከማስቻሉም በላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት፣ እነዚህ ካርዶች በፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናልም እንዲስተናገዱ ማስቻሉም የኩባንያው ሌላው ውጤታማ እንቅስቃሴ በመሆን ተጠቅሷል፡፡ ባንኮች እነዚህን ካርዶች በመቀበል ሊያገኙ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲጨምር አስተዋጽኦ ስለማድረጉም ተብራርቷል፡፡ አቶ ፀሐይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ የፕሪሚየም ስዊች አባል ባንኮች የቪዛ ካርድ፣ የማስተር ካርድና የዩኒየን ፔይ አባላት እንዲሆኑ የተደረገው በፕሪሚየም ስዊች ሥርዓት አማካይነት ነው፡፡ ‹‹ቪዛ ካርድ ያለው የውጭ ዜጋ ወይም ከአሜሪካ የመጣ ኢትዮጵያዊ፣ ወደዚህ መጥቶ ሆቴል ቢይዝ፣ በአዋሽ ባንክ ወይም በሌሎች ተጣማሪ ባንኮች የፖስ ማሽኞች አማካይነት ገንዘቡን ሲቀይር ባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ ያገኛሉ ማለት ነው፤›› ያሉት አቶ ፀሐይ፣ የባንኮቹ ጥምረት ለውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው ዕድገት ሚናውን እንዳበረከተ ገልጸዋል፡፡
ፕሪሚየም ስዊች እመርታ ያሳየበት ሌላው ጉዳይ፣ ተጣማሪ ባንኮች የሚጠቀሙባቸውን የክፍያ ካርዶች ቁጥር ማሳደጉ ነው፡፡ ኩባንያው በ2005 ዓ.ም. ሥራ ሲጀምር 37,122 ካርዶችን ወደ አገልግሎት በማስገባት እንደነበር ቀደምት መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ የካርዶቹን ቁጥር በሁለተኛው ዓመቱ ላይ ወደ 70,311 ከማሳደግ አልፎ በየዓመቱ አዳዲስ ካርዶች እየታተሙ ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ፕሪሚየም ስዊች ዓምና የነበረው አፈጻጸም፣ ካለፉት አምስት ዓመታት ይልቅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ካርዶችን ማሳተም የቻለበት ዓመት ነበር፡፡ ኩባንያው በ2010 ዓ.ም. ብቻ 382,000 ካርዶችን በማሳተም ለአባል ባንኮች አሠራጭቷል፡፡
እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ፕሪሚየም ስዊች በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ታትመው የተሠራጩት ካርዶችን ጨምሮ በገበያ ላይ የዋሉትና የኩባንያው መለያ ያላቸው ካርዶች ብዛት ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንዲሆን አስችለዋል፡፡ በመሆኑም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ካርዶች መታተማቸው ለውጡን አጉልቶታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው የዘረጋውን ሲስተም በመጠቀም የተወሰኑት ባንኮች ከወለድ ነፃ የካርድና የቅድሚያ ክፍያ ካርድ ለደንበኞቻቸው በአማራጭነት እንዲያቀርቡ ዕድል መስጠቱንም አቶ ፀሐይ ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው በዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ የተቀመጡትን የደኅንነት መመዘኛ መሥፈርቶችን በማሟላት የደንበኞችን መረጃ በጥንቃቄ ሲያስተላልፍና ሲያጠራቅም እንደቆየ አቶ ፀሐይ ይናገራሉ፡፡ ይህ ሒደትም ዓመታዊ የዕድሳትና የፍተሻ ሥርዓቶችን በማለፍና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘት ስለመቻሉም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ይህንኑ ሰርተፍኬት በእጁ እንዳስገባ ተጠቁሟል፡፡ የደንበኞችን መረጃ ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ሲያስተላልፍ፣ ሲያቀነባብርና ሲያከማች በማንኛውም መልኩ መረጃዎቹ ላልተፈቀደለት ሦስተኛ ወገን እንዳይደርሱ ማረጋገጫ የሚሰጥ ሥርዓት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኩባንያው ከታክስ በፊት 13 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት አኳያ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ትርፍ ማስመዝገቡም ታውቋል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉንም ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻለ የኩባንያው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ፕሪሚየም ስዊች እስካሁን ሲሰጥ የቆየው አገልግሎት የበለጠ እንዲያድግ ለማስቻል የታሰቡ ውጥኖች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን፣ ወደፊት ለሚተገበሩ አዳዲስ አሠራሮች የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርፆ መንቀሳቀስ እንደሚጀምር ተብራርቷል፡፡
እንዲህ ያሉ ዘመናዊ አገልግሎቶች ጠቀሜታቸው እየጨመረና እየጎላ ቢመጣም፣ ያለ ቴሌኮም መሠረተ ልማት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የማይታሰብ በመሆኑ፣ የቴሌኮም ኔትወርክ መቆራረጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጥሩ አልቀረም፡፡
በዚህ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት አቶ ፀሐይ፣ ‹‹ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ለባንኮች የደም ሥር ነው፡፡ የቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ጥራት ችግር የባንክ ኢንዱስትሪውን ጎድቶታል፡፡ ቅርንጫፎቻችን አብዛኛውን ጊዜ ከኔትወርክ ሲስተም ውጭ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ገንዘብ ለማውጣት ወደ አንዱ ቅርንጫፍ የሚሄድ ደንበኛ ቅርጫፎቹ ኔትወርክ ስለሌላቸው ገንዘብ ማውጣት አይቻልም ይባላል፡፡ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኔትወርክ መቆራረጥ ደንበኞች እንዲጉላሉ ምክንያት እየሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ውስጥ የአስተዳደር ለውጥ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ፀሐይ፣ አዲሱ ማኔጅመንት ይህንን ችግር በአግባቡ በመመልከት ይፈታዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
‹‹ኢትዮ ቴሌኮም የባንኮች ዓይን ከመሆኑ አንፃር አብረን እየሠራን ነው፡፡ ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ ግን የሲስተም ችግር አለ፡፡ ለወደፊቱ ይህ ጉዳይ ምን መሆን አለበት? የሚለውን በባንኮች ማኅበር በኩል ተነጋግረንበት ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮ ቴሌኮም ደብዳቤ ጽፏል፤›› በማለት አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡
ባንኮች የራሳቸው ሳተላይት ኖሯቸው እንዲሠሩ ጥረት ሲደረግ እንደነበር፣ አሁንም አዲሱ ማኔጅመንት እንዲህ ያለው ነገር መሟላት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ ባንኮች የራሳቸው መስመር እንዲኖራቸው ከተደረገ ሲስተሙን ያስተካክላል፣ ‹‹ይህ ካልተደረገ ግን እንደርስበታለን ብለን የቀረጽናቸው ስትራቴጂዎች ግባቸውን ሊመቱ አይችሉም፤›› በማለት የኔትዎርክ ጉዳይ አሳሳቢነቱን ገልጸዋል፡፡
የባንክ የወደፊት ቢዝነስ ኦላይን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ አሁን ባለው የኔትዎርክ ጥራት መጓደል ኢንዱስትሪውን የትም ማድረስ እንደማይቻል በመጥቀስ፣ ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ዕድገትም ሆነ እንቅስቃሴ የቴሌኮም አገልግሎት ጥራት ማሟላት የግድ ስለመሆኑ በአጽንኦት ጠቅሰዋል፡፡