Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹ሽበት አያሳጣን››

በቅርቡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች እንዲሁም እንደ አርባ ምንጭ ባሉ የክልል ከተሞች ውስጥ የተመለከትናቸው ዘግናኝ ድርጊቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከማይሽሩ የታሪካችን ጠባሳዎች መካከል ይመደባሉ፡፡ ዳግመኛ ሊፈጸሙ የማይገባቸው አረመኔያዊ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በጉራጌ ዞን አላባ ውስጥ የተፈጠረው ግጭትም እንዲሁ በአሳዛኝነቱና አስከፊነቱ መጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ አገር በለውጥ  ዕርምጃ ላይ ስለመሆኗ በሚነገርበት ወቅት፣ የሰው ሕይወት በጨካኝ አራጆች እንደዘበት ሲጠፋ ማየት ከህመም በላይ ያሳምማል፡፡

አንድነትን የሚያጠነክሩ የተስፋ ዕርምጃዎች በተግባር ሲወሰዱ በሚታይበት ወቅት አንተ እከሌ ነህ፣ እናንተ የእገሌ ዘር ናችሁ የሚል አጸያፊ መናቆር ውስጥ የተገባበት ሰበብ ታውቆ አስቸኳይ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡

ያልተመለሰ የድንበር ወይም የወሰን ጥያቄ አለን በሚሉ ሞገደኞች የተቃጡት የሰሞኑ ግጭቶች፣ መነሻቸው ምንም ይሁን፣ ግጭቶቹን ያፋፋሙ አካላትና ግለሰቦች የሚያናፍሷቸው አሉባልታዎችና ቅስቀሳዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች ሲለቀቁ የቆዩ መረጃዎች ግጭቱን በማባባስ የድርሻቸውን እንደተወጡ ታዝበናል፡፡ እርግጥ እንዲህ ባለው የለውጥ ጊዜ ወቅት፣ በርካታ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙ ቢታመንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት አለመግባባቶች ግን ከቃላት ልውውጥ እንኳ ማለፍ የማገባቸው ተራ ምክንያቶች ሆነው ሳለ፣ ዜጎችን እርስ በርስ እስኪያጫርሱ ሲደርሱ ማየት ግን ሐዘን ከሚገልጸው በላይ ያሳዝናል፡፡ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ሳይታክቱ ላይ ታች የሚደክሙ የእኛው የኢትዮጵያ ልጆች መኖራቸው ህመሙን እጅግ ያከብደዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ ትርምስ ያበቃን ጉድ ምንድነው? ብለን ምክንያቱን በሰከነ መንፈስ ብንመረምረው ምናልባትም ከኃፍረት የሚያሸማቅቀን፣ ከሰውነት ስብዕና በታች የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ በምክንያትና በተጠየቅ ብንመረምረው ነገሩ፣ የጨዋና የኩሩ ሕዝብ ተግባር ሳይሆን፣ የበልቶ አደሮች የረከሰ የፖለቲካ ቁማር ብቻ ነው ውጤቱ ሊሆን የሚችለው፡፡ ይሁንና ከመስመር የወጡ አፈንጋጭ ድርጊቶች መነሻው ምንም ቢሆን፣ ከሰሞኑ የተመለከትናቸው አስነዋሪ ተግባራት እንዳይደገሙ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ሊመለስልን የሚያስችል ዕርምጃ ያስፈልገናል፡፡

መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት በሚገባው ወቅትና ጊዜ አለመውጣቱ ትልቅ ክፍተት እንደሆነ ማመኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በረባ ባልረባው በየቀዬው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ግን፣ የስብዕና ልዕልና ካልዳኛቸው ሕግ ሊዳኛቸው ይገባቸዋል፡፡ መሳት የሌለበት ሌላው ጉዳይ ዜጎች፣ በተለይም ወጣቶች ሕግና ሥርዓት ማክበር፣ የሌሎችን መብትና ማንነት ማክበር የግዴታ ውዴታቸው መሆኑን ነው፡፡ መብት ማለት ግዴታ የሚባል አጥር ያለው ቤት እንደማለት መሆኑን መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመሠልጠን መገለጫው፣ መብቱን የሚጠይቅ ጎበዝ፣ ግዴታውንም አክባሪ እንደሆነ መገንዘቡ ላይ ነው፡፡ አለያማ ሰው የሚነዳ እንስሳ ከመሆን ውጭ ምን ቀረለት?

መንግሥትን እንደ ሥርዓት የሚያኖረው ዋነኛ ተግባሩ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ማድረግ ሲችል ነው፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር ዕድሜ አይኖረውም፡፡ ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ የሚወጣ መብት ጠያቂ፣ የሌሎችን መብት እየረገጠና ንብረት እያወደመ፣ ሕይወት እየጠፋ ማን መብቱን እንዲያከብርለት ይሆን የሚጠይቀው? ለውጥ በልክና በሥርዓት ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሕግና ሥርዓትን ባልተከተለ መንገድ የሚፈጽሙ ድርጊቶች የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍ፣ ከማቁሰልና ከማፈናቀል ባሻገር፣ የሚፈጥሩትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመጠገን የሚጠይቀው ጊዜና ወጪ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ሥብራቱ ከወጌሻ አቅም በላይ ነው፡፡ በመጪው ትውልድ ላይ ከሚያሳርፈው የሞራል ውድቀትና የተስፋ ማጣት ባሻገር፣ አሁን ባለው የአገሪቱ ገጽታም ላይ ትልቅ ጠባሳ የሚጥል በሽታ ነው፡፡

ከዚህ በመለስ ከሰሞኑ የተፈጠሩት ችግሮች በሕዝቡ ላይ ያሳደሩት ሥጋትና የሚነዛው የሐሰት ወሬ የወለደው አለመረጋጋት፣ ሌላው ቢቀር የንግድ እንቅስቃሴውን ከማስተጓጎልም በላይ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን ሲበርዙት ተመልክተናል፡፡

አንዳንዴም አጋጣሚውን በመጠቀም በሩን ከርችሞ በሕዝቡ ዘንድ ‹‹ያልበረደ ችግር እንዳለ የሚያስመስል አይጠፋም፡፡ ከማረጋጋት ይልቅ የሚያራግብ፣ በግርግር ለመጠቀም የሚሽቀዳደም ጥቂት አይደለም፡፡ እዚህም እዚያም የሚነሱት ግጭቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየፈጠሩ ያሉት ጫና ሲደጋገም ድምር ሒሳቡ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ በማረፍ ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ደሃዋ ኢትዮጵያን የበለጠ የደኸየችና የጎስቋላ ሕዝቦች መናኸሪያ ያደርጋታል፡፡

ሱቁና ንብረቱ የተቃጠለበትን ነጋዴ ማቋቋምና በቀድሞ ስሜቱ ተነሳስቶ እንዲሠራ ማድረግ ቀላል ሥራ አይሆንም፡፡ ነገሮች ወደ መረጋጋት መምጣታቸው ባይቀርም ጉዳቱ ለአገር መውደቅ መንስዔ ስለሚሆን፣ ግጭቶችና ግርግሮች የማያዳግም መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጎልማሶች፣ ሕፃናት፣ እናቶች፣ ሌላውም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል መማገዳቸው መቆም አለበት፡፡ ከቀያቸው መፈናቀል የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ከጸብ በፊት መነጋገር፣ መግባትና መደማመጥ ያሻል፡፡ በኃላፊነት ስሜት ሐሳብን ማራመድ እየተቻለ ምነው የአንድ አገር ሰዎች ደመኛ ይሆናሉ?

ከሰሞኑ ግርግር መሐል በአርባ ምንጭ፣ የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ተግባር ብዙ የሚያስተምረን ስለመሆኑ መጥቀሱ ግድ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ ዜጎችን ምክንያት በማድረግ፣ በአርባ ምንጭ ወጣቶች ሊሰነዘር የተቃጣውን የበቀል በትር፣ የአገር ሽማግሌዎቹ በወጣቶቹ ልጆቻቸው ፊት በመንበርከክ፣ ጦር የማይመልሰውን ዘግናኝ አደጋ በእርጥብ ሳር ምልጃ ያስቀሩበት ብልኃት የሚደነቅ ነው፡፡ አበው ሲተርቱ ‹‹ሽበት አያሳጣን፤›› የሚሉት ትክክለኛ ብሒል በተግባር የታየው በጋሞ ምድር ነበር፡፡ ከስሜታዊነት ተቆጥቦ፣ ነገሩ ጣመም መረረም ምራቅ የዋጡ፣ ነገር ያላመጡ አባቶችን በማድመጥ ለአገር የከበደ ችግር እንደዘበት ሲፈታ ያየንበት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ አገር የምንኖር ዜጎች መደማመጥና መከባበራችን ተያይዞ ከመጥፋት ያድነናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት