የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከፍተኛ የአመራር አካል የግንባሩ ጉባዔ ነው፡፡
ጉባዔው የግንባሩ አራት የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩል ድምፅ በሚወከሉ ጉባዔተኞች የሚዋቀር ሲሆን፣ የጉባዔ አባላት ከተወከሉበት ጉባዔ እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በቋሚ ጉባዔተኝነት እንደሚቆዩ የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ይደነግጋል፡፡
ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሐዋሳ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ፣ እያንዳንዱ የግንባሩ አባላት 250 ጉባዔተኞችን በድምሩ አንድ ሺሕ ጉባዔተኞች በድምፅ ሰጪነት እንዲሳተፉ ተወስኗል፡፡
የኢሕአዴግ የመጨረሻ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው ይህ ጉባዔ በመተዳደሪያ ደንቡ ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል የግንባሩን መተዳደሪያ ደንብ ማፅደቅ፣ ማሻሻልና መቀየር አንዱ ነው፡፡ ግንባሩን የሚመራባቸውን አገር አቀፍ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መንደፍ፣ የግንባሩን ምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ቁጥር መወሰን፣ የግንባሩን ምክር ቤትና የቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርቶች ማዳመጥ መገምገና ውሳኔ ማሳለፍ፣ ከምክር ቤቱ በሚቀርብለት ሪፖርት መሠረት የግንባሩ ሙሉ አባል እንዲሆን የታጨ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት አባልነትን ማፅደቅ ወይም ከአባልነት የመሰረዝ ውሳኔ መስጠት ሌሎቹ የጉባዔው ሥልጣንና ኃላፊነቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ግንባሩ እስከ ቀጣይ ጉባዔ ድረስ የሚያከናውናቸውን አጠቃላይ ተግባራትና ግቦችንም ጉባዔው የመወሰን ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የግንባሩ ጉባዔ ከሁለት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ፣ ሆኖም የኢሕአዴግ ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጉባዔውን ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ሊያራዝመው እንደሚችል በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተደንግጓል፡፡
በሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ የኢሕአዴግ ጉባዔ በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ፣ አንድ ጊዜ ብቻ በሁለት ዓመት ተኩል ተካሂዷል፡፡ በመጪው መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚጀመረው የኢሕአዴግ ጉባዔ ለመጀመርያ ጊዜ በሦስተኛ ዓመቱ ይካሄዳል፡፡
ከመጪው የኢሕአዴግ ጉባዔ የውይይት አጀንዳዎች መካከል አንደኛው፣ በአሥረኛው ጉባዔ እስከ ቀጣይ ጉባዔ ግንባሩ ሊተገብራቸው ይገባል ተብለው የተቀመጡ ግቦችና ተግባራት አፈጻጸም ግምገማና እስከ ቀጣዩ ጉባዔ መከናወን የሚገባቸውን ተግባራት በመንደፍ ውሳኔ ማስተላለፍ ነው፡፡ ሁለተኛው አጀንዳ በመጋቢት 2010 ዓ.ም. በኢሕአዴግ ውስጥ ከመጣው የአመራር ለውጥ በኋላ የተፈጸሙ ተግባራትን በመገምገም፣ በተመሳሳይ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ዋነኛ መሆናቸውን፣ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የግንባሩን ምክር ቤት መመሥረት፣ አዲስ የሚመሠረተው የኢሕአዴግ ምክር ቤትም በተለመደው አሠራር መሠረት የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡
ከውሳኔ በመለስ ውይይት ተደርጎባቸው ለቀጣይ ጊዜ የሚተላለፉ ሁለት ጉዳዮችም በ11ኛው የግንባሩ ጉባዔ የሚጠበቁ ሁነቶች ናቸው፡፡ እነዚህም በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች የተመሠረተውን ኢሕአዴግ ለማዋሀድ በሚቻልበት መነሻ ሁኔታ ላይ የሚቀርብ ጥናታዊ ሰነድና ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት የግንባሩ አጋር ሆነው የቆዩ ሌሎች ፓርቲዎችን በሙሉ አባልነት መቀበል የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከትና ጥናታዊ ሰነድ ናቸው፡፡
11ኛው ጉባዔ ከቀደሙት በምን ይለያይ?
ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ የተካሄዱት አሥር የኢሕአዴግ ጉባዔዎች ከሞላ ጎደል በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ፣ ከላይ ተወስነው እስከ ታች ድረስ የሐሳብና የተግባር አንድነትን በጠበቀ መንገድ የተከናወኑ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ጉልህ በሆነ ሐሳብ አፍላቂነት ተፅዕኖ በነበራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ዘዋሪነት ጉባዔው የሚካሄድበት ጊዜ ገደብ ቢበጅለትም፣ ከሦስት ዓመታት በላይ የተለጠጠበት ምክንያት ወደ አመራር የመጣው የለውጥ ኃይል የግንባሩን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ጨርሶ ባለመያዙ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ለግንባሩ ጉባዔ አጀንዳዎችን ለውሳኔ በማቅረብ ረገድ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ወሳኝ ድርሻ የነበረው ቢሆንም፣ በመጪው ጉባዔ እንደከዚህ ቀደሙ ያለቀለት አጀንዳ ለውይይት ይቀርባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የግንባሩ የወቅቱ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በነበሩት አምስት ወራት የተተገበሩ የፖለቲካ ሪፎርሞች የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተፈጸሙ መሆናቸው ቢነገርም፣ በዚህ ምክር ቤትም ሆነ በግንባሩ ፓርቲዎች መካከል የሪፎርሞቹን ይዘት መጠንና ስፋት በተመለከተ ስምምነት አለመኖሩ በግልጽ እንደሚታይ የሚገልጹ አሉ፡፡ እየተተገበሩ ያሉትን የለውጥ ተግባራት አስመልክቶ እንኳን ስምምነት ወይም የሐሳብ አንድነት ሊታይ ቀርቶ፣ አንዱ አንዱን በይፋ የለውጥ ሒደቱ ጠላት ነው እስከ መባባል ደርሰዋል›› ሲሉም በግንባሩ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዳሉ፡፡
ከሳምንት በፊት መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የኢሕአዴግ ምክርቤት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይዘው የመጡትና ልዩ መታወቂያቸው የሆነውን ‹‹መደመር›› የፖለቲካ ፍልስፍና፣ ግንባሩ ከዚህ በኋላ የሚመራበት ፍልስፍና እንዲሆን መወሰኑ ይገኝበታል፡፡
በዚህ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዘቶች ባህሪያት ላይ ጥርት ያለና ማኅበረሰቡ በቀላሉ የሚገነዘበው ትንታኔ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች መዋቅሮችም ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍናቸውን በአንድ ወቅት ሲገልጹ፣ ‹‹የእኛ መደመር ሁሉንም የሥሌት መደቦች የያዘ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ይኼንንም ሲያብራሩ የመደመር ፍልስፍናው መደመርን ብቻ ሳይሆን ማባዛትንም፣ ማካፈልንም፣ መቀነስንም የያዝ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
ይህ የመደመር ፍልስፍና ቀጣዩ የኢሕአዴግ የፖለቲካ መርህ እንደሆነ ምክር ቤቱ ሲወስን ወደ መግባባት የተደረሰበት ይመስላል፡፡
ነገር ግን መጪውን የኢሕአዴግ ጉባዔ አስመልክቶ ከሰሞኑ መግለጫ የሰጡት የመደመርን ፍልስፍና የወሰነው ምክር ቤት አባልና የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ መደመር ማለት መጨፍለቅ አለመሆኑን፣ መደመር ማለት የሚያስማሙ ጉዳዮችን በማጉላት የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ታሪክና ቋንቋ አክብሮ በኅብረት አንድ ላይ መጓዝ ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀጣዩ ጉባዔ በዚህ ፍልስፍና ላይ መክሮ የጠራ መልክ እንዲይዝ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት የተካሄዱት የለውጥ ተግባራት ኢሕአዴግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የተፈጸሙ እንጂ፣ በተለያዩ መንገዶች እንደሚገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በግላቸው ያበረከቱት አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠው ኢሕአዴግ መሆኑን በመግለጽም፣ የተከናወኑት የለውጥ ተግባራት የኢሕአዴግ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የተተገበሩ የፖለቲካ ለውጦች በማኅበረሰቡ ውስጥ ተስፋን የጫሩ የመሆናቸውን ያህል፣ ባለፉት ወራት ሥርዓት አልበኝነት በአገሪቱ መፈጠሩን የተናገሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ፣ መጪው የኢሕአዴግ ጉባዔ በዚህ ጉዳይ ላይም በጥልቅ በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የውጭ ተቋም ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑ ስማቸውን ያልገለጹ ተንታኝ በበኩላቸው፣ ቀጣይ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አቅጣጫዎች እንደከዚህ ቀደሙ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ኢሕአዴግ ውስጥ ባለ አንድ የሥልጣን ማዕከል የሚወሰኑበት ጊዜ ማክተሙን ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢሕአዴግ ውስጥ (በርከት ያሉ የፖለቲካ ኃይል ማዕከሎች) Multiple Center of Power እንደተፈጠሩ የሚያስረዱት እኚህ የፖለቲካ አማካሪ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶችን በሚያራምዱ ተገዳዳሪ ኃይሎች መካከል እንደከዚህ ቀደሙ ውሳኔዎች ላይ በቀላሉ ይደረሳል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ ብአዴን የኢሕአዴግ ፕሮግራም የሆነውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወቅቱ ከሚጠይቀው የፖለቲካ ፍላጎት አንፃር ያረጃ ነው፣ አልከተለውም ብሎ ወደ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራም ለመሸጋገር ወስኗል፤›› ሲሉ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራሙን በሥራ ላይ ለማዋል በሚያስችል ደረጃ ምልዓተ ሕዝቡን የማንቀሳቀስ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወት የሚችለው፣ በኢሕአዴግና በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ከላይ እስከ ታች አስተማማኝ የሐሳብና የተግባር አንድነት ሲኖር ነው ይላል፡፡ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በመሠረታዊ መርህነት ያስቀምጠዋል በማለት በማከልም፣ ‹‹ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማ ተግባራዊነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለሆነ፣ በአባልነት ሊቀበልና ሊያሰባስብ የሚችለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዓላማን በግልጽ በፕሮግራማቸው ላይ የቀረፁ ድርጅቶችን ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራምን መቀበል ብቻ በኢሕአዴግ ሥር ለመሰባሰብ አያበቃም፡፡ በተግባርም ለፕሮግራሙ ተፈጻሚነት መታገል ይጠይቃል፤›› ሲል የማይገሰስና የማይሸራረፍ መርህ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
ብአዴን በቀጣይ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ በመጪው ሳምንት እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡ የኢሕአዴግ ጉባዔ ግን የግንባሩን የፖለቲካ ፕሮግራም ለመቀየርም ሆነ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አጀንዳ እንደሌለው ወ/ሮ ፈትለወርቅ ይገልጻሉ፡፡
ታዲያ እንዲህ ዓይነት በርካታ ልዩነቶች ውስጥ የሚዋልለው ኢሕአዴግ በመጪው 11ኛ ጉባዔው በአንድ ጉዳይ ላይ እንኳን በመግባባት ውሳኔ ያሳልፍ ይሆን? የግንባሩ ጉባዔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ሊፈጥር ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎችን ከወዲሁ አጭሯል፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ፣ በመጪው ጉባዔ ስምምነት የሚደርስባቸው ጉዳዮች መኖቸውን ይጠራጠራሉ፡፡ ‹‹ቢሆንም ልዩነቱ ከፍቶ ሌላ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይፈጠር መግባባት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጉባዔው ሊወስን ይችላል፡፡ አልያም ጉባዔው ሥልጣኑን በውክልና በመስጠት መግባባት በማይቻልባቸው ጉዳዮች መፍትሔ አመንጭቶ እንዲያስተገብር በጉባዔው ለሚደራጅ አካል ሥልጣኑን በውክልና ሊሰጥ የሚችልበት አማራጭ ሊፈጠር ይችላል፤›› ሲሉም ግምታቸውን አስረድተዋል፡፡
መጪው ጉባዔ የሞት ሽረት ትግል የሚካሄድበት ሊሆን እንደሚችል፣ ውጤቱም ኢሕአዴግን ሊበትነው ወይም ተጠናክሮ እንዲወጣ ሊያደርገው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
በሚፈጠረው የሐሳብ ትግል መሸናነፍ ሳይቻል ቀርቶ ኢሕአዴግ እንዲበተን የትግሉ ተዋናዮች ምርጫ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ፣ ከዚህ ይልቅ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ኃይል ኢሕአዴግን እንደገና አጠናክሮ ሊፈጥረው እንደሚችል ይገምታሉ፡፡