ሕወሓት ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የዕድሜ ገደብ ሊጥል ነው
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከሐሙስ መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሚያካሂደው ጉባዔ፣ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለ ለውጥ በማዕከላዊ ኮሚቴው ላይ እንደሚያደርግ ተሰማ፡፡
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከመስከረም 17 እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው የብአዴን ጉባዔ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአዲስና በወጣት አመራሮች ይተካሉ፡፡
በብአዴን ታሪክ ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ድርጅታዊ የኃላፊነት ቅብብሎሽ፣ ብአዴንን ከጎምቱ አመራሮች ተፅዕኖ በማውጣት ሁለተኛ የሥልጣን አካል የሆነው ማዕከላዊ ኮሚቴ ወቅቱ የሚጠይቀውን ብስለት በተላበሱ ወጣት አመራሮች እንደሚደራጅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ በቀጣይ የብአዴን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር የሚሆኑ አመራሮች እንደሚመረጡ ጠቁመዋል፡፡
የድርጅቱን ቀጣይ አመራሮች ለመወሰን በሚደረገው ምርጫም፣ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ወደ አመራርነት ከሚመጡት መካከል ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አምባቸው (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስትርነት በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
የብአዴን ጉባዔ በማዕከላዊ ኮሚቴውና በከፍተኛ አመራሩ ላይ ከሚያደርገው ለውጥ ባሻገር፣ ድርጅቱ የሚመራበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፕሮግራም ለመቀየር የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ይጠበቃል፡፡
የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለመቀየር ለጉባዔው የሚቀርበው የውሳኔ ሐሳብ፣ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥትን በዋና አማራጭ ፕሮግራምነት እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
ሶሻል ዴሞክራሲና ሊበራል ዴሞክራሲ እንደ ቅደም ተከተላቸው በአማራጭነት ለውይይት የሚቀርቡ አማራጭ ፕሮግራምች እንደሚሆኑም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ብአዴን የሚለውን የድርጅቱ ስያሜ ለመለወጥ ሁለት አማራጮች ቀርበው ጉባዔው ውሳኔ የሚያሳልፍ ሲሆን፣ የዓርማ ለውጥም ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጉባዔም በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
ሕወሓት የመተዳደሪያ ደንቡን ለማሻሻል ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መሥፈርቶችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከመሥፈርቶቹ መካከል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በታች እንዲሆን ገደብ የሚጥል ሲሆን፣ አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከአራት ጊዜ በላይ እንዳይቀጥል ማሻሻያ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እነዚህን መሥፈርቶች የሕወሓት ጉባዔ ካፀደቀ ውጤቱ በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ላይ አንፃራዊ ለውጥ ያስከትላል ተብሏል፡፡