Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አይነኬ የተባሉ ቦታዎች የሊዝ ውል እንዲቋረጥ ወሰነ

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አይነኬ የተባሉ ቦታዎች የሊዝ ውል እንዲቋረጥ ወሰነ

ቀን:

ሚድሮክ የአስተዳደሩን ውሳኔ ተቃወመ

ባለቤት አልባ ሕንፃዎች ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል

በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ሚድሮክን ጨምሮ በግል፣ በመንግሥትና በዲፕሎማቲክ ተቋማት ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን የሊዝ ውል በማቋረጥ ላለፉት አሥር ዓመታት ያልተደፈረ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ በሚድሮክ የተያዙ 250,413.89 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 11 ቦታዎች፣ በግል ኩባንያዎች የተያዙ 456,428 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 95 ቦታዎች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተያዙ 127,140.93 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 19 ቦታዎች፣ የፌዴራል ተቋማት፣ መከላከያና የኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ የተያዙ 2,743,200 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 11 ቦታዎች፣ በዲፕሎማቲክ ተቋማት የተያዙ 250,413.89 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው 18 ቦታዎች የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በአጠቃላይ 412.68 ሔክታር (4,126.82 ካሬ ሜትር ቦታ) ስፋት ያላቸው 154 ቦታዎች ውል እንዲቋረጥና ለተሻለ ልማት እንዲውል ያልተጠበቀ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከካቢኔው ውሳኔ በኋላ ምክትል ከንቲባ ታከለ (ኢንጂነር) ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህ ሥራ የአንድ ጊዜ ዘመቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በኋላ ከአስተዳደሩ ቦታ ወስደው ወደ ልማት የማይገቡ ማናቸውም የመንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች ላይ ጥብቅ ክትትል አድርጎ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ሚድሮክን ጨምሮ የግል፣ የመንግሥትና የዲፕሎማቲክ ተቋማት ያልገነቡበትን ቦታ የወሰዱት በአርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) በሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን በፊት፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. ከወጣበት ቀደም ባሉት ዓመታት ነው፡፡

በእነዚህ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ነዋሪዎች አስተዳደሩ በተወሰኑት ላይ ዕርምጃ ሲወስድ፣ በተወሰኑት ላይ ደግሞ ባለመውሰዱ አድሏዊነት ነው በማለት ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

ይህም ቅሬታ በሰፊው ቢነሳም በአቶ ኩማ ደመቅሳ ይመራ በነበረው የከተማው አስተዳደርም ሆነ፣ በአቶ ድሪባ ኩማ በተመራው አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ቦታዎቹ እንዲነጠቁ የውሳኔ ሐሳብ ቢቀርብም ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡

ነገር ግን የምክትል ከንቲባ ታከለ ካቢኔ ሥልጣን በተረከበ ማግሥት የመሬት ኦዲት እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ የኦዲት ጥናቱ ተካሂዶ ካቢኔው በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ያለምንም ማንገራገር ከአሥር ዓመታት በኋላ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን በመሀል አዲስ አበባ ግንባር የሆኑ ቦታዎችን ለዓመታት አጥሮ የያዘው ሚድሮክ የካቢኔውን ውሳኔ አልተቀበለም፡፡ ሚድሮክ ከተወሰዱበት ቦታዎች መካከል በመሀል ፒያሳ ላለፉት 20 ዓመታት ታጥሮ የሚገኘው የመንትያ የገበያ ማዕከል ፕሮጀክትና ከቤተ መንግሥት አጠገብ የሚገኘው 42 ሔክታር የሸራተን ማስፋፊያ ቦታ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ ሚድሮክ በአዲስ አበባ የሚያካሂዳቸውን ፕሮጀክቶች የሚመሩት የሼክ መሐመድ አል አሙዲ የቅርብ ሰው አቶ አብነት ገብረ መስቀል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአስተዳደሩ ውሳኔ እውነታውን ከግምት ያስገባ አይደለም፡፡

‹‹አስተዳደሩ የሊዝ ውል እንዲቋረጥ በወሰነባቸው ቦታዎች ላይ ሚድሮክ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሷል፡፡ በተለይ በሸራተን ማስፋፊያ ከሊዝ ክፍያ በተጨማሪ ነዋሪዎችን ለማንሳት ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ በፒያሳ ፕሮጀክትም ቢሆን የዲዛይን ክለሳ አድርገን የአስተዳደሩን ውሳኔ እየጠበቅን ባለበት ጊዜ ይህ ውሳኔ ሊሰጥ አይገባም ነበር፤›› ሲሉ አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡

በአሥራ አንዱም ቦታዎች ላይ በእኩል መጠን ባይሆንም ሚድሮክ ቅሬታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ሚድሮክ ቅሬታውን በቅርቡ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንደሚያስገባ አቶ አብነት አስታውቀዋል፡፡

‹‹ባለቤቱ ሼክ አል አሙዲ ሐሳባቸውን መግለጽ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እያሉ፣ አስተዳደሩ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ሊወስን አይገባውም ነበር፤›› በማለት  ገልጸው፣ ‹‹የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባሉበት በተካሄደው ውይይት ሼክ አል አሙዲ በሌሉበት ይህ ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ተወስኖ ነበር፤›› ሲሉም አስታውሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ይህ ዕርምጃ የተወሰደው በጣም ጥንቃቄ ተደርጎ በባለሙያዎች ከተጠና በኋላ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ባለቤት በሌላቸው ሕንፃዎች ላይም እንዲሁ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

‹‹በባለቤት አልባ ሕንፃዎች ላይ ኦዲት እየተደረገ ነው፡፡ የኦዲት ሥራው ግን ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ምክንያቱም የባለቤት አልባ ሕንፃዎች ጉዳይ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን እንደ ማጣራት ቀላል አይደለም፤›› በማለት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ በቅርቡ ኦዲቱ ተጠናቆ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ግን አስታውቀዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...