Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ የታሰሩ በርካታ ዜጎች እንዲፈቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ

በወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ የታሰሩ በርካታ ዜጎች እንዲፈቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ

ቀን:

‹‹ታሰሩት ወጣቶች ድርጊት በወንጀል ሲለካ ሙሉ በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው››

ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር  

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከመንገድ ላይና ከተለያዩ ቦታዎች ተይዘው (ታፍሰው) በጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ የታሰሩ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ፣ ወይም የፈጸሙት ወንጀል በሕግ ዕውቅና ያለው ከሆነ ክስ  እንዲመሠረትባቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ፡፡

ሕዝብን ለማደናገር ካልሆነ በስተቀር አንድም የታፈሰ ወጣት እንደሌለ በመግለጽ፣ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ያለምንም ፈቃድ በቡድን ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ወደ ጎዳና የወጡትን መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡  

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ በአዲስ አበባ ከተማ 3,000 የሚጠጉ ወጣቶች መታሰራቸውን፣ ከእነዚህ መካከል 174 ክስ የሚመሠረትባቸው መሆኑን፣ 1,200 የሚሆኑት ግን ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ተወስደው የተሃድሶ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው መናገራቸውን አስታውሷል፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርብ ወራት ውስጥ እስር ቤቶችን ባዶ ለማድረግ ያደረገውን የሚያስመሠግን ሙከራ ያለምንም የፍርድ ቤት መያዣ ጊዜያዊ እስረኞች እንዲሞሉበት ማድረጉን፣ የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ጆአን ንያንዩኪ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎች የታሰሩት በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል መሆናቸው ባልተረጋገጠ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ ሺሻ አጭሰዋል፣ ጫት ቅመዋል በሚል ምክንያት መሆኑን በምሳሌ  ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ታሳሪዎቹ ፈጽመዋል የተባለው ድርጊት ወንጀል መሆኑ በሕግ የተረጋገጠ ከሆነ ክስ ሊመሠረትባቸው፣ ወይም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ እንደሚገባም ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡

በተለይ በቅርቡ በከተማው ከብሔር ጋር በተገናኘ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በመቃወም ሰላማዊ ሠልፍ በመውጣታቸው ታፍሰው የታሰሩት፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በጀመረው የሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነት የማክበር አዲስ ዘመን ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለበት ዳይሬክተሯ አክለዋል፡፡

በተጠረጠሩበት ወንጀል ክስ ይመሠረትባቸዋል ያላቸውን ዜጎችም በሚመለከት ጠበቆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የማግኘት መብታቸው እንዲከበርም፣ ዳይሬክተሯ ሚስተር ንያንዩኪ ጠይቀዋል፡፡ አንድም ታሳሪ ግርፋትም ሆነ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳይደርስበት አሳስበዋል፡፡

የታሰሩት ወጣቶች ድርጊት በወንጀል ሲለካ ‹‹ሙሉ በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው፤›› የሚለው ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡ ኮሚሽነሩ ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ‹‹ፖሊስ ያለ መያዣ ፈቃድ ወጣቶችን እያፈሰ ነው›› የሚባለው ከእውነት የራቀና ሕዝቡን ለማደናገር ነው፡፡ ‹‹በቁጥጥር ሥር የዋሉት በቡድን ሆነው ሰሞኑን በተፈጠረው ሁከት የተሳተፉ ናቸው፡፡ በግል የተደረገ ነገር ሳይሆን በቡድን የተደረገ የጎዳና ላይ ተንቀሳቃሽ ኃይል በመሆኑ፣ ድርጊቱ ከወንጀል አንፃር ሲታይ ሁሉም ሙሉ በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ባልተፈቀደ ሠልፍ የተሳተፉ በመሆናቸው ወንጀል መሆኑን አክለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ የተፈቀደ ሠልፍ የለም ያሉ ቢሆንም፣ ሰላማዊ ሠልፍን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ ግን የእሳቸውን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ፈቃድ ሳይሆን ማሳወቅ መሆኑን የጠቆሙት የሕግ ባለሙያው፣ ፈቃድ ይጠየቅ ቢባል እንኳን ወቅቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ሰላማዊ ሠልፉ ከመደረጉ በፊት በነበሩት ቀናት በቡራዩና አካባቢው የደረሰው የሰዎች ግድያና የንብረት ዘረፋ ምን ሊያስከትል እንደሚችል መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡

ከደረሰው የግድያ፣ የማፈናቀልና የንብረት ዘረፋ አንፃር የከተማው ነዋሪዎች በድምፅ ብቻ ተቃውሞ አሰምተው ወደ ቤታቸው መግባታቸው ሊያስመሠግናቸው ሲገባ፣ በፀጥታ ኃይሎች ከመገደላቸውም በተጨማሪ እንደገና ታፍሰው መታሰራቸው አግባብ እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ወቅቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያልታወጀበት በመሆኑ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወይም ቡድን ቢኖር እንኳን፣ ሕጉን ተከትሎ የመያዣ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት አውጥቶ መያዝ ሲገባ ከኳስ ማሳያ ቤቶች፣ ከመዝናኛ ቦታዎች፣ ከመንገድ ላይ፣ ከሺሻና ከጫት ቤቶች ዝም ብሎ ማፈስ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ የተረሳን የአፈና ሥርዓት በማስታወስ ወጣቱን ተጠራጣሪ፣ በርጋጊና ለሌላ ነገር እንዲነሳሳ ማድረግ ስለሆነ፣ ግብረ መልሱ ሌላ አደጋ ሊሆን እንደሚችል የሕግ ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል ፖሊስ በተቋቋመበት አዋጅ ከተሰጠው ተልዕኮ ባለፈ ባልተሰጠው የማሠልጠን ሥልጣንና በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177፣ 178 እና 179 ተደንግጎ የሚገኝ ‹‹አካልን ነፃ ማውጣትና›› አንድ ተጠርጣሪ በተያዘ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጎ የሚገኘው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 19(3)ን የጣሰ በመሆኑ፣ ፖሊስ የፈጸመው ድርጊት ሊኮነን እንደሚገባም የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ተጠርጣሪ እንዴት እንደሚያዝና እንደሚጣራ እናውቃለን፣ አውቀን ነው ምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡ በቡራዩና አካባቢው የተፈጠረውን ጥቃት አስመልክቶም የ28 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ሰባቱ የተገደሉት በፀጥታ ኃይሎች መሆኑን አክለዋል፡፡ አንድ ግለሰብ በስህተት በመገደሉ፣ የገደለው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና አንደኛው ግን ፍርድ ቤት ሊዘርፍ ሲል ዕርምጃ እንደተወሰደበት አስረድተዋል፡፡

ግድያው የተፈጸመው በአምስት ክፍላተ ከተሞች እንደነበር፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 14 ሰዎች፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አምስት፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ አንድ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አምስትና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሦስት መሆናቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱ ከመስከረም 2 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተፈጸመ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር በባንኮች፣ በተለያዩ ተቋማትና ተሽከርካሪዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ችግሩን ለመቆጣጠር በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ለጊዜው ወደ ሰንዳፋ መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በሰንዳፋ አብዛኛዎቹን በምክር ከተለቀቁ በኋላ 1,204 የሚሆኑትን ‹‹ለህንፀት›› ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ መወሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታንፀው ወደ ኅብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉም አክለዋል፡፡ ‹‹የሚያንፅና የሚገነባ አካል አዘጋጅተናል፡፡ በአጭር ጊዜ አንፀን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ አመቻችተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ከአደንዣዥ ዕፅ፣ ከጫትና ከሺሻ፣ እንዲሁም ከሕገወጥ ንግድ በተጨማሪ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተደራጅተው በሚመጡ አካላት፣ በከተማው የሚፈጸሙ ወንጀሎችም እየተበራከቱ መምጣታቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ተለይተው ለሕግ በመቅረብ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...