የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2010 ዓ.ም. ውድድር ከፍተኛ ስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የነበረበትና በክልሎች ጨዋታ ማድረግ ለክለብም፣ ለተጫዋችም፣ እንዲሁም ለውድድር አዘጋጅ ምጥ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ችግሮቹ ብሔር ተኮር እየሆኑ መምጣታቸውን ተከትሎ እግር ኳሱን ከመዝናኛ ሥፍራ ወደ ‹‹ጦርነት ዓውድማነት›› ለመቀየር ከጫፍ የደረሰበት ጊዜም ሆኖ ነበር፡፡
በሳምንታዊ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በተመልካቾች መካከል ሲደርስ በነበረው ግጭት የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ ንብረት ጠፍቷል፡፡ ዳኞች በአደባባይ የተደበደቡበትና ለሕይወታቸው ዋስትና እስካላገኙ ድረስ በክልሎች ጨዋታን ወደ አለመዳኘት ደረጃ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ የ2011 ዓ.ም. የውድድር መርሐ ግብርን በይፋ ያስታወቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ጥቅምት 17 ቀን እንደሚጀምር መነገሩ ይታወሳል፡፡
ይኼን ተከትሎ ክለቦች የዕረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው በተለያዩ ክልላዊ ውድድሮችና ጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ጀምረዋል፡፡ በደቡብ የደቡብ ካስትል ሻምፒዮና፣ በትግራይ የትግራይ ዋንጫ፣ በአማራ የአማራ ዋንጫና ኢትዮጵያ ዋንጫ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውድድሮች ጎን ለጎን ደግሞ በተለይ በአማራና በትግራይ ክለቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ክለቦቹ ውድድራቸውን በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ መገደዳቸው አይዘነጋም፡፡
ባለፉት ውድድሮች ከምርጫው በተጨማሪ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር የተያያዙ ሁከቶችንና ብጥብጦች የበዙበት መሆኑን ተከትሎ የዘንድሮ መርሐ ግብርን በተለይ በሁለቱ ክልሎች ክለቦች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታትና የዲሲፕሊን ደንቦች እንዳይጓደሉ በሽምግልና ደረጃ እየታየ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያነት መስከረም 19 ቀን ይጀምራል በተባለው የትግራይ ዋንጫ ላይ ለፋሲል ከነማ የግብዣ ጥሪ መቅረቡ በክልል ክለቦቹ መካከል ያለውን አለመግባባት ከወዲሁ ለመፍታት ትልቅ ማሳያ ነው ተብሎለታል፡፡
በትግራይ ክልል ዋንጫ ውድድር ሁሉም ክለቦች ግብዣ የቀረበላቸው ቢሆንም፣ እስካሁን ግን መቐለ ከተማ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት፣ ሥሁል ሽረ፣ ደደቢትና አክሱም (ከከፍተኛ ሊግ) ቀዳሚ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ድሬዳዋ ከተማና መከላከያ ግብዣውን ተቀብለው እንደሚካፈሉ አረጋግጠዋል፡፡ ቀሪዎቹ ተጋባዦች እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ ያልሰጡ ቢሆንም፣ በክልላቸው የሚያሰናዱት ውድድሮች ምክንያት መሳተፍ እንዳልቻሉ እንደ ምክንያትነት ተነግረዋል፡፡
ከውድድሩ ቀደም ብሎ ዓምና በመቐለ ከተማ እግር ኳስ ክለብና በወልዋሎ ዓዲግራት ተመልካቾች መካከል ሲፈጠር የነበረውን አለመግባባት ዳግም እንዳይፈጠር በሚል የመወያያ መድረክ ተዘጋጅቶ፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በተገኙበት ውይይት መደረጉና ዳግም ችግሮች እንዳይፈጠሩ ስምምነት መድረሳቸው ተልጿል፡፡
የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ጥቅምት 17 ቀን እንደሚጀመር ይፋ ቢደረግም አሁንም ቢሆን የክልል ደጋፊዎች በተለያዩ ክልል ከተሞች ተዘዋውረው ክለባቸውን ለመደገፍ ምንም ዓይነት በራስ መተማመን እንደሌላቸውና ያለ ምንም ሥጋት ክለባቸውን መደገፍ እንዲችሉ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረግ እንዳለበት የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም መስከረም 25 ቀን በሚያደርገው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ በቅድሚያ ከሚወያይባቸው ጉዳዮች መካከል የዲሲፕሊን መመርያ በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን፣ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡