Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየክብረ መስቀል ወጎች ከአዲስ አበባ እስከ ሮም

የክብረ መስቀል ወጎች ከአዲስ አበባ እስከ ሮም

ቀን:

ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ዓመታት በፊት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል የተገኘበት በዓል ከዛሬ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በኮፕቲክ (ግብፅ) ክርስቲኖች እየተከበረ ነው፡፡

የመስቀሉ በዓል የግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠር በሚከተሉት አገሮች ሮምን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅና ምዕራብ ምዕመናን ከ13 ቀናት በፊት ሴብቴምበር 14 ቀን 2018 (መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም.) አክብረዋል፡፡

የጁሊያን ካሌንደር የሚከተሉት በምሥራቅና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያንና ካቶሊካውያን የመስቀሉን በዓል ‹‹ሴብቴምበር 14 ቀን›› ብለው የሚያከብሩት የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ኮፕቲክ ቤተክርስቲያናት በሚያከብሩበት መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም. (ቲቶ 17 ቀን 1735 ዓመተ ሰማዕታት) ነው፡፡ ዕለቱ በግሪጎርያን ሴብቴምበር 27፣ በጁሊያን ሴብቴምበር 14 ይውላል፡፡ ግሪጎሪያን ካሌንደር የጁሊያኑን እስከከለሰበት 16ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሁሉም በአንድነት የመስቀል በዓልን ያከብሩ ነበር፡፡

መስቀሉ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት በቅድስት ዕሌኒ አማካይነት በ326 ዓ.ም. መገኘቱ ይወሳል፡፡ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፣ የዕሌኒ ልጅ ቆስጠንጢኖስ በጌታ ኢየሱስ መካነ መቃብርና በቀራንዮ የመሠረተው ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው ሴብቴምበር 14 ቀን 335 ዓም ነበር፡፡ ቤተክርስቲያኑ ባሁን ጊዜ በነጋድያን (pilgrims/ተሳላሚዎች) እና በቱሪስቶችም ጭምር ይጎበኛል፡፡

ሦስቱ ነገሮች

በዓሉ የሦስት ነገሮች ኅብር አለው፡፡ እነዚህም በቅድስት ዕሌኒ፣ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅዱስ መስቀሉ መገኘት፣ ቆስጠንጢኖስ በቅዱስ መቃብሩና በጎልጎታ የገነባውን ቤተክርስቲያኖች ማበርከቱ በ335 ዓም ሴብቴምበር 13 እና 14 ፣ እና መስቀሉ ዳግም ወደ ኢየሩሳሌም በንጉሥ ሕርቃል አማካይነት በመጋቢት 10 ቀን 629 ዓ.ም. መመለሱ ናቸው፡፡ ክብረ በዓሉ ቀስ በቀስ ከኢየሩሳሌም በተጨማሪ ሌሎች ቤተክርስቲያኖች ቀስ በቀስ ማክበር የጀመሩ ሲሆን በ720 ዓም በዓሉ በሁሉም መከበር ጀምሯል፡፡

በመስቀሉ ዙርያ የተጻፉ መጻሕፍት እንደሚገልጹት፣ በሰባተኛው ምዕት ቀዳሚ ዘመን የፋርስ ንጉሥ ሆስራው ሁለተኛ (Khosrau II) ከኢየሩሳሌም ዘርፎ የወሰደውን ቅዱስ መስቀል ንጉሥ ሕርቃል ሁለተኛ (Heraclius II) በ629 ዓ.ም. በጦርነት ድል አድርጎ ወደቀዳሚው ሥፍራ አምጥቶታል፡፡ በትውፊት እንደሚነገረው ሕርቃል መስቀሉን ራሱ ተሸክሞ በደብረ ቀራንዮ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ለማስገባት ሲጥር የሆነ መንፈስ ያስጨንቀዋል፣ ብሎም ያስቆመዋል፡፡ በዚህን ጊዜ የኢየሩሳሌም ፓትርያርክ የንጉሡን ጭንቀት ተመልክተው የለበሰውን ንጉሣዊ አልባሳትና ዘውድ አውልቆ ለንሥሐ የሚያበቃ አለባበስ እንዲለበስ ይመክሩታል፡፡ ሕርቃልም ምክራቸውን በመተግበሩ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቤተክርስቲያኑ ይገባል፡፡

የቅዱስ መስቀሉ አሻራዎችና ግማደ መስቀል በሮም

መሰንበቻውን በነሐሴ 2010 ዓ.ም. በኛ ክረምት በነሱ በጋ (ሰመር) ለአንድ ወር ንግደት (ጉብኝት) ከፈጸምኩባቸው የሮማ የተቀደሱ ቦታዎች አንዱ መጠርያው -የቅዱስ መስቀል ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም- የሚባለው ነው፡፡ ከሰባቱ የሮም ኮረብታዎች አንዱ ከሆነው ኢስኩሌይን ኮረብታ (Esquiline Hill) አቅራቢያ በሦስት መንገዶች (በካርሎ ፊሊቺ መንገድ፣ በሳንታ ክሮስ ኢን ጄሩሳሌም መንገድና በኤሊያንያ መንገድ) መጋጠሚያ የሚገኘው ቅዱስ መስቀል በኢየሩሳሌም ባሴሊካ ነው፡፡

በጣሊያን ‹‹ሳንታ ክሮስ ኢን ጀሩሳሌም›› (The Basilica di Santa Croce in Gerusalemme /Holy Cross in Jerusalem) በመባል ይታወቃል፡፡ በሮም ከሚገኙት ሰባት ታላላቅ ቤተ ክርስቲያናት ምዕመናን ከሚደርሱበት ቱሪስቶች ከሚጎበኙት አንዱ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅርብ ርቀት በቪያሌ ካርሎ ፌሊቼ በኩል ከቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ላቴርና ባሲሊካ አካባቢ በቀኝ ትገኛለች፡፡ ከሰባቱ የሮም የንግደት (Pilgrim) ቤተ ክርስቲያናት ሳንታ ክሮስ ኢየሩሳሌም፣ ቅዱስ ዮሐንስ ላቴራን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ሮም፣ ከግንቦች ውጪ የሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ሳንታ ማሪዮ ማጆሬ፣ ቅዱስ ላውረስና ቅዱስ ሰባክትያንኮ አንዷ ናት፡፡

ይቺ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በውስጧ ከያዛቸው ንዋያተ ቅዱሳት አንዱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ እንደሚታመነው ግማደ መስቀሉ ከቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የመጣው፣ በአራተኛው ምዕት ክርስትናን ሕጋዊና ምዕመናኑም በነፃነት እንዲያመልኩ ባደረገው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ እናት በቅድስት ዕሌኒ አማካይነት ሲሆን የክርስቶስን መስቀል መስከረም 17 ቀን በጎልጎታ አስቆፍራ አግኝታዋለች፡፡

 በቤተክርስቲያኑ በወርቅና በብር የተነቆጠቆጡ ንዋያት በውስጡ ያሉ ሲሆን፣ በስቅለቱ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለ ችንካር፣ የቅዱስ መስቀሉ ሦስት ጥቃቅን ክፋዮች (ግማድ)፣ የተገነዘበት ከፈን  በቤተመቅደሱ በስተግራ ባለ ልዩ ስፍራ በመስታወት ውስጥ ተቀምጧል፡፡ በሥነ ስቅለቱ ራስጌ – ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ በምሕፃር ‹‹ኢ.ና.ን.አ.›› የሚል በአራማይስጥ፣ በግሪክና በላቲን የተጻፈበትም ሰሌዳም ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ 14ቱ ሕማማተ ኢየሱስን የሚያሳዩ ቅርጾችን በደረጃው ላይ በመቅደሱ ይታያሉ፡፡ ከሁሉም ትኩረት የሚስበውና ዝናው የጎላው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ክፋዮች (ግማዶች) ነው፡፡ አንድ ችንካር፣ ሁለት የሾኽ አክሊል፣ የተጠራጣሪው ቅዱስ ቶማስ ጣት፣ በቀኝ የተሰቀለው ‹‹መልካሙ ወንበዴ›› የመስቀል ክፋይም ይገኛል፡፡ የሐዋርያው ቶማስ አመልካች ጣት ይገኝበታል፡፡ ቶማስ የጌታን ትንሣኤ የተጠራጠረና ጎኑን በጣቱ ነክቶ ያረጋገጠውና ጌታም ‹‹ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው›› ያለበትን ልብ ይሏል፡፡

ቆስጠንጢኖስ ዘውዱን ከደፋና የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ በ313 ዓ.ም. ክርስትና ሕጋዊ ሃይማኖት አደረገው፡፡ ቅድስት ዕሌኒ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቅዱሳን ቦታዎች ለመሳለምና ቅዱስ መስቀሉን ለማግኘት ተጓዘች፡፡ በርካታ ንዋየ ቅዱሳት ይዛ በመመለስ በቤተ መንግሥቷ ቤተ መቅደስ በመገንባት አኖረቻቸው፡፡ ከደብረ ቀራንዮም አፈር በጀልባ ጭና በማምጣት በቤተ መቅደሱ በስሟ በተሰየመው ቤተ ጸሎት (chapel) ወለል ሥር አስቀመጠችው፡፡ ባሰሊካው ‹‹በኢየሩሳሌም›› መሰኘቱ ሕንፃው የኢየሩሳሌም አፈር ስለተቀላቀለበት እንደሆነ ይወሳል፡፡  ቆስጠንጢኖስና እናቱ ዕሌኒ ከዘውዳዊው ቤተ መንግሥት ሰፊውንና ግዙፉን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማድረጋቸው ‹‹ሳንታ ክሮስ ባሴሊካ ዕሌኒ›› ተብሎም ይታወቃል፡፡

ሳንታ ክሮስ ኢን ጀሩሳሌም ኪነ ሕንፃው ፍጽምናን የተላበሰ፣ የባሮክ ስልትን የተከተለ የሮማን ዘመን ልዕልና የሚያሳይ ነው ይባልለታል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሁለት መቅደሶች (Chapels) አሉ፡፡ በስተቀኝ በቅድስት ዕሌኒ ስም የተሰየመና በሞዛይክ የተጌጠ ክርስቶስ ሲባርክ፣ አራቱ ወንጌላውያንና ቅድስት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉ ለማግኘት ያደረገችውን ጥረትና አገኛኘቱን የሚያሳዩ ሥዕሎችም በቤተመቅደሱ በጉልህ ይታያል፡፡ በትውፊቱ መሠረት በወለሉ ሥር ከኢየሩሳሌም የመጣ አፈር ተቀምጦበታል፡፡ ባሴሊካው በኢየሩሳሌም ስም መጠራቱም ለዚህ ነው፡፡ በግራ በኩል የቅዱስ ግሪጎሪዮ መቅደስ ይገኛል፡፡

ዐሥሩ ክፋዮች

በአራተኛው ሴክል (ምዕት ዓመት) ቅዱስ መስቀሉ መስከረም 17 ቀን በቅድስት ዕሌኒ ከተገኘ፣ እንዲሁም በይቀጥላልም በሰባተኛው ሴክል መጋቢት 10 ቀን፣ ከተማረከበት ከፋርስ በንጉሥ ሕርቃል አማካይነት ከተመለሰ በኋላ የክርስቲያኑ ዓለም ቅዱስ መስቀሉን ተከፋፍሎታል፡፡ በዛንታ እንደሚወሳው የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የግሪክ፣ የእስክንድርያ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ከአራት ሲካፈሉት የእስክንድርያ ድርሻ ወደ ኢትዮጵያ በ15ኛው ሴክል መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በቢዛንታይን በኩል የሚወሳው ዛንታ፣ የመስቀሉ ዐሥር ክፋዮች/ አላባዎች (cross particles) በአውሮፓ ቤተክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም በሮም ሳንታ ክሮስ፣ በፓሪስ ኖተርዳም፣ ፒሳ ካቴድራልና ፍሎረንስ ካቴድራል የሚገኙት ክፋዮቹ በማይክሮስኮፕ ተመርምረው ቁራጮቹ የወይራ ዛፍ ዓይነቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ደጀ ሰላሙን የረገጥኩበት ሳንታ ክሮስ በዓለ ንግሡ በዐቢይ ጾም አራተኛ እሑድ ሲሆን በዕለተ ሰንበቱ የተቀደሰው የመስቀሉ ክፋይ በዐውደ ምሕረቱ እየዞረ ምዕመናን ይባረኩበታል፡፡ በዓርብ ስቅለትም እንዲሁ፡፡ ቤተክርስቲያንዋ በጥንት ዘመን ነጋድያን (መንፈሳዊ ተጓዦች) በእግራቸው በመጓዝ ከሚሳለሟቸው ሰባት ዐበይት ቤተክርስቲያናት አንዷ ናት፡፡

ክብረ መስቀል በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያም በኤርትራም ሆነ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ሁለቱ የመስቀል በዓላት መስከረም (ቲቶ) 17 ቀን እና መጋቢት (በርመሃት) 10 ቀን የሚውሉ ናቸው፡፡

መስከረም 17 ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል በቆስጠንጢኖስ እናት በቅድስት ንግሥት ዕሌኒ (ሔለን) በጎልጎታ ተቆፍሮ የተገኘበት ነው፡፡ የመጋቢት 10 መስቀል ደግሞ በሰባተኛው መቶ ዘመን በ629 በሕርቃል ቅዱስ መስቀሉ በፋርሶች (የአሁኗ ኢራን) ከተደበቀበት ቦታ የተመለሰበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቤተክርስቲያን አንዳንድ ቀደምትና የአሁን ዘመን መምህራን ባተሟቸው ጽሑፎቻቸው ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ሰባት ወራት እንደወሰደባት፣ ይሀም ቁፋሮው መስከረም 17 ቀን ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መገኘቱን ያወሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያሳተመችውና አሁንም በማገልገል ላይ ያለው  ጥንታዊው ስንክሳር በመስከረም 17 ንባቡ የአራተኛው ምዕቷ ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ስፍራ ማግኘቷ፣ በመጋቢት 10 ንባቡ የሰባተኛው ምዕት ንጉሥ ሕርቃል መስቀሉን ተዘርፎ ከተወሰደበት የፋርስ ግዛት ማስመለሱን በገሀድ አስቀምጦታል፡፡

 የመስከረም 17 ቀን በዓል በኮፕቲክ ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ነው፡፡ የመጋቢት 10 በዓሉ ግን ለአንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሁለቱ ቀናት በተጨማሪ ግማደ መስቀሉ የገባበት መስከረም 10 ቀን አፄ መስቀል፣ ግማደ መስቀሉ ባለበት ግሸን ማርያም ንግሡ መስከረም 21 ቀን የመስቀሉ ክብር ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደሚተረከው፣ መስቀል ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ተዳፍኖ ቆይቷል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና አስቆፍራ ለማውጣት ጉዞዋን ወደ ኢየሩሳሌም ቀጠለች፡፡ እዚያም ደርሳ ገብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም፡፡ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ኪሪያኮስ የሚባል የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል፡፡ ‹‹አንችም በከንቱ አትድከሚ ሰውም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍስሽበት በእሳትም አያይዥው የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኝዋለሽ›› አላት፡፡ እሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አሳየ ያን ምልክት ይዛ አውጥታዋለች፡፡

የመስቀል በዓል ከአራተኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ  መስከረም 16 ቀን የቤተክርስቲያን መታነፅና የደመራ ሥርዓት እንዲሁም መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡

ግማደ መስቀል በኢትዮጵያ

በዛንታ እንደሚነገረው፣ የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ ይገኛል፡፡ ግማደ መስቀሉ በአፄ ዳዊት ዘመን ከእስክንድርያ (ግብፅ) ሲመጣ ከመጨረሻ ስፍራው መስቀልያ ቅርስ ባለው ግሸን አምባ ከመድረሱ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ተዘዋውሯል፡፡ በዚህ ዘመን በሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ከሚከበርባቸው የዓዲግራቱ ቀንደ ዳዕሮና የመቐለው እንዳ መስቀል (ጮምዓ) አምባዎች እንዲሁም በተጉለት መስቀለ ኢየሱስ ግማደ መስቀሉ ለወራት ተቀምጦባቸው እንደነበር ይወሳል፡፡

የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥቲቱ ቅድስት ዕሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በአይሁዶች ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓቱ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡  በትግራይ፣ በላስታና ላሊበላ፣ በአክሱም፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ፣ በሽናሻ (ንጋት 11 ሰዓት) ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ  አካባቢዎች መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ ነገዶች ከመስከረም 13 ጀምሮ ደመራውና ከበራው ይቀጥላል፡፡

የዘንድሮው አከባበር

የዘንድሮው የመስቀል በዓል እንደወትሮው በመላው ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያኒቱ ባለችበት ቦታ በዓለም ዙሪያ ጭምር  ይከበራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ቅዱሳን ፓትርያርኮች ብፁዓን ወቅዱሳን መርቆሬዎስ ወማትያስ በሚገኙበት ደመራው መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ይለኮሳል፡፡ በተመሳሳይ ዕለትም ሥርዓተ ግዕዝን የምትከተለው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም በበዓቷ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በሚገኙበት ሥርዓተ ደመራውን ትፈጽማለች፡፡

በሮም የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በዓሉን እንደሚከብሩ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...