በሳሙኤል ረጋሳ
በለውጥ ሒደት ውስጥ አስቸጋሪ ወቅት የሽግግር ጊዜ ነው፡፡ የሽግግር ጊዜ ለዘመናት የተሰባሰቡ ብሶቶች ፈጠው የሚወጡበትና ሁሉም ደርሶብኛል ብሎ የሚገምተውን በደል በስሜት የሚያቀርብበት ሁኔታ በመኖሩ በርካታ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ሕግ ይጣሳል፡፡ ንብረት ይወድማል፡፡ ሰው ይሞታል፡፡ ሌሎችም በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ይፈጠራሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የተፈጸሙ ጥፋቶች ጊዜ ሲያልፍ ያስቆጫሉ፡፡ ያስተዛዝባሉ፡፡ ያስገምታሉ፡፡ ያስጠይቃሉም፡፡
በሽግግር ሒደት ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች የማብረድና የማስቀረት ዋናው ኃላፊነት የመንግሥት ሳይሆን የሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ጊዜ ኃይልን በመጠቀምና ሕጋዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ለማስተካከል፣ ከችግሩ ስፋትና ካለው አቅም ጋር የማይሞከር ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ ሁኔታዎችን አቻችሎ ሕይወትን ጠብቆ ለማለፍ የሚጥርበት ጊዜ ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ ቤተ እምነቶች፣ ባህላዊ አደረጃጀቶች ሁሉ የሚፈተኑት በዚህ ወቅት ነው፡፡ የሽግግሩን ሒደት የሚያመሰቃቅሉት ደግሞ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ሁኔታዎች የሚረጋጉትና የሽግግር ወቅት አበቃ የሚባለው ፖለቲከኞች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሰክነው ወደ ሕጋዊ መስመር ሊመለሱና ሕግና መንግሥት የሚፈቅደውን መደበኛ ሥራቸውን መሥራት ሲጀምሩ ነው፡፡ ከሰላማዊ ሽግግር ይልቅ አስቸጋሪ ሽግግር ናቸው በአፍሪካ ውስጥ የሚታዩት፡፡ አስቸጋሪውን የሽግግር ጊዜ የምንፈጥረው ሁሉም ሥልጣን ፈላጊ ሲሆንና በሰላማዊ መንገድ ብንፈጽመው የተሸነፍን ስለሚመስለን ነው፡፡
የአሁኑ የእኛ አገር የሽግግር ወቅት ገና ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ይመስላል፡፡ በ1950ዎችና በ1960ዎቹ አካባቢ የብሔር ጭቆና በአገሪቱ አለ በማለት ማንነትን ማዕከል አድርገው ትግል የጀመሩት ኦነግ፣ ሻዕቢያና ሕወሓት ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስቱም የፖለቲካ ድርጅቶች የነፃ አውጭ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በወቅቱ የተፈጠረ አገራዊ ወይም ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ዘመናዊው የፖለቲካ እንቅስቃሴያችን የተሟሸው በብሔረተኝነት፣ በዘውገኝነትና በክልላዊነት ላይ ተመሥርቶ የየራሱን ክልል ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ በተፃራሪው የእነዚህ ድርጅቶች የወቅቱ ተልዕኮ ኢትዮጵያዊነት ከአድህሮት ጋር የተያያዘና የሕዝቦችን መብት ጨፍልቆ በኃይል የተመሠረተ ነው በሚል መረጃ፣ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬን የማስረፅ ሥራ ተሠራ፡፡ ይኼ ቀደም ሲል በረዥም ሒደት ውስጥ የተፈጠረው የኢትዮጵያዊነት ስሜትም በብሔር ፖለቲካ እየተሸረሸረ በሕዝቡ ስሜት ውስጥ በከፊልም ቢሆን ነባሩን ስሜት እያላላ መጥቶ ለዛሬው ሁኔታችን የበቃ ነው፡፡
በወቅቱም ሆነ ዛሬ ድረስ ዘልቀው የምናያቸው እነዚህ የ1960ዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦችና ምሁራን የተቃኙት ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ሥልጣን ለመቀባበል ያለው መንገድ አብዮት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች በባህሪያቸው አምባገነን ስለሆኑ፣ ወጣቶችን ከተቻለ በማሳመን ካልሆነም በኃይል እያስገደዱ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠት የኃይለ ሥላሴን መንግሥት አንገዳግደው የደርግን መንግሥት ከእነ ጭራሹ አፈረሱት፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶችና ምሁራን ዘላቂ መፍትሔ ያመጣልናል ብለው ያሰቡት አብዮት የኮሙዩኒስቶች የመፍትሔ አቅጣጫ በመሆኑ በዋናነት አመፅን፣ እምቢተኝነትን፣ ሁከትንና መገንጠልን የመሳሰሉ በእልህና በጉልበት ብቻ የሚኬድባቸው አፈጻጸሞች ናቸው፡፡ የተማሩትም፣ ያስተማሩትም፣ የተገበሩትም ይኼንን ነው፡፡ ይኼ አካሄድ በምሥራቅ አውሮፓና በእስያ በተግባር ተፈትኖ በመውደቅ ላይ እያለ ነው፡፡
እኛ አገር ደግሞ እንደ አዲስ ተወልዶ ማደግ የጀመረው እንግዲህ፣ የአገሪቱ ቀዳሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሲፈጠሩ በዚህ ሒደት ውስጥ ስለነበረና አንድም ብሔር ብሔረሰብን አመሳጥሮ የተፈጠረ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከእነዚህ የነፃ አውጭ ግንባሮች ጋር ጎን ለጎን የመጣ አልነረም፡፡ ስለዚህ ነው ዛሬ ድረስ በሁላችን አዕምሮ የተጎዘጎዘው ዓላማን በጉልህ የማስፈጸም፣ አመለካከትን በኃይል፣ በዱላና በእስር የማስረፅ አባዜ የተጠናወተን፡፡ በአብዮት የተሟሸ አዕምሮን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለመቀየር እስከ ዛሬ አልቻልንም፡፡ በመሆኑም መክረን ለመመለስ፣ አስተምረን ለማስረፅ፣ ተወያይተን ለመተማመንና ተደራድረን ለመግባባት አልታደልንም፡፡
አሁንም ቢሆን በአገራችን ህልውና ላይ ትልቅ አደጋ ሊያስከትል የሚችለው ዋናው ጉዳይ፣ የእነዚህ ቀደም ሲሉ የተፈጠሩ ነፃ አውጭ ግንባሮች አስተምህሮና ተግባር መሆኑ ሊታሰብ ይገባዋል፡፡ በወቅቱ ሲታገሉለት የነበረው ዓላማ ኤርትራን ነፃ የማውጣት፣ ትግራይን ነፃ የማውጣትና ኦሮሚያን ነፃ የማውጣት አቋም ተይዞ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ኤርትራ ነፃ ወጥታለች፡፡
ኤርትራ ነፃ የወጣችው ሕወሓትና ሻዕቢያ ቀደም ሲል በፈጠሩት የጋራ ግንባርና ሕዝቡ ከደርግ ለመላቀቅ ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኤርትራ በጂኦግራፊ አቀማመጧ ዳር ላይ ያለች አገር በመሆኗና አብዛኛው ግዛቷን የሚያካልለው የባህር ጠረፍ መሆኑ ነው ለመገንጠል የረዳት፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ነፃ አውጭዎች የመገንጠል ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሕወሓት የመገንጠል መብትን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና እንዲያገኝ ያስደረገው ለአንድ ክፉ ቀን ይጠቅመኛል ብሎ በማሰብ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሕወሓት የራሱን ጥግ ይዞ መንግሥትንና እናት ድርጅት ኢሕአዴግን እየተገዳደረ ነው፡፡ በመንግሥት የሚቀመጡ አቅጣጫዎችንና ደንቦችንም እየተቃወመ ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥት የተላኩትን የፀጥታ ኃይሎች አግቶ መቀሌ አቆይቷቸዋል፡፡ አንዳንድ የመንግሥትን ሁኔታ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ትግራይ ውስጥ መሽገዋል ይባላል፡፡ አልፎ አክፎ አንዳንድ የሕወሓትና የክልሉ ባለሥልጣናት የሚሰጡዋቸው መግለጫዎችም ሆኑ ድጋፎች እንደ አንድ የአገሪቱ አካል እንዳልሆኑ ነው፡፡ ሌሎች የሚታዩ ጤናማ ያልሆኑ ምልክቶች በርካታ ናቸው፡፡
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በሚመራበት ጊዜ በሁሉም ነገር ማለት በሚቻል ደረጃ ወሳኙን ሚና የሚጫወተው ሕወሓት ነው ብሎ ነው ሕዝቡ የሚያስበው፡፡ ስለዚህ ለተፈጸመው ጥፋት ሁሉ ሕወሓትን ነው ሕዝቡ የሚኮንነው፡፡ አሁን ያለውን የለውጥ ሒደቱን ባለመቀበል ጎራ ለይተው የሚያሳዩት የእንሞካከር ዓይነት መንፈስ ለሕወሓት፣ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈይደው ምንም ነገር የለውም፡፡ ኤርትራም ብትሆን ከባድመው ጦርነት ወዲህ ሕወሓትን ከሌሎች ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ የከረረ ጥላቻ እንዳላት ስትናገር ቆይታለች፡፡ ስለዚህ ሕወሓት አሁን እየተከተለ ባለው የእልህ መንፈስ ከሁለት ያጣ እንዳይሆን ያሠጋዋል፡፡ ከላይ ያልጨበጡ፣ ከታች ያልረገጡ አዛውንቶቹ የሕወሓት አመራሮች የትግራይን ሕዝብ ይዘው አየር ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡
ስለዚህ አሁን አንድ የአገራችን ክልል ከሌሎች ወንድሞቹ ተለይቶ የመራራቅና ቅራኔዎች የማስፋት አካሄድ ጊዜ ሳይሰጠው፣ በክልሉ መንግሥትና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል መድረክ ተዘጋጅቶ ችግሮችን ሁሉ መፍታትና ሰላምን ማውረድ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ የሕወሓቶችን ሐሳብ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም የቲም ለማ መንግሥት ከተፈጥሮው ስንገምተው ወደ ኋላ የሚል አይመስልም፡፡
ሌላው የአገራችን ትልቁ ጣጣና አስቸጋሪው ጉዳይ የኦነግ ነው፡፡ በእርግጥ ኦነግ ሦስት ቦታ ተከፍሎ በአቶ ሌንጮ የሚመራው ክንፍ የመገንጠል አጀንዳውን ትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ሌሎቹም በተለያየ ሚዲያ ያሉበትን ሁኔታ እየሰማን ነው፡፡ በቅርቡ በእነ አቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ክንፍ ከአንድ የኦሮሚኛ ፕሮግራም ከሚያስተላልፍ ቴሌቪዥን ጋር አቶ ገላሳ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የ1960ዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራም ክልልን ነፃ ማውጣት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ መገንጠልን አስመልክተው በሰጡት መልስ፣ ‹‹የእኛ አቋም ድሮም የታወቀ ነው፡፡ ደብቀንም አናውቅም፡፡ አሁንም ቢሆን የምንታገለው ለኦሮሚያ ነፃነት ነው፡፡ ሕዝቡም የራሱን መብት በራሱ እንዲወስን እንታገላለን፤›› ነበር ያሉት፡፡
የተናገሩት በኦሮሚኛ ስለሆነ ቃል በቃል ላይሆን ይችላል፡፡ ይኼ በአጭር አገላለጽ የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ኤርትራ በሪፈረንደም እንዲገነጠል የማድረግ መብቱን ዕውን እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ኦሮሚያ እንደ ኤርትራ ከዳር ያለች አገር ሳትሆን ሙሉ በሙሉ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ተከባ መሀል ያለች አገር ናት፡፡ ከውስጥ ያለ ነገር ደግሞ ዳር ካለው ላይ ለመገንጠል አይቻልም፡፡ የሚሆነው ዳር ላይ ያለውን መሀል ካለው ላይ መገንጠል ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ አፈጻጸም ከዳር ያሉትን ያለመቀበል ነው የሚሆነው፡፡
እንዲያው ለነገሩ እስቲ ኦሮሚያን ነፃ እናውጣት ብለን እናስብ፡፡ ኦሮሚያ ከ42 ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የምትዋሰን ሰፊዋ ክልል ናት፡፡ ነፃ ስንወጣ ከ42 ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የድንበር ማካለል ጉዳይን እናስብ፡፡ ከ42 ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በግጦሽና በውኃ የሚፈጠር ያለመግባባትን እናስብ፡፡ ወደ ሸኖ ወይም ደብረ ብርሃን ለመሄድ ሰንዳፋን የምናልፈው ፓስፖርት አውጥተን ቪዛ አግኝተን ነው፡፡ ዓባይን ለመሻገር ወይም ሐዋሳ ለመሄድ ተመሳሳይ ተግባራትን መፈጸም አለብን፡፡
ቡናችንን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ ወደ ጂቡቲ ወስዶ ለማስጫን አፋር በሚባለው የጎረቤት አገር ዘልቀን፣ የሱማሌን ክልል ነክተን ጂቡቲ ለመግባት ሦስት የውጭ አገር ድንበርን አቋርጠን ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች የመፈተሽ፣ የመቀረጥና ሰነድ የማስመር ጣጣ አለብን፡፡ ለተለየናቸው የኢትዮጵያ ክልሎች ኤምባሲ ከፍተን ነው የምንሠራው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ በመገንጠል የሚፈጠሩ በርካታ አስተዳደራዊ መፍትሔ የሚፈልጉ፤ ግን ደግሞ ፈጽሞ ለመከወን የሚከከብዱ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ የድሬዳዋ ጉዳይ. . . ወዘተ. ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁሉንም ችግሮች ማንሳቱ አላስፈላጊ ስላልሆነ እነዚህ ማሳያዎች ብቻ በቂ ናቸው፡፡
በዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ የምትፈጠረዋን ኦሮሚያ ለመምራት የሚችልም ሆነ ፈቃደኛ የሚሆን አካል የሚኖር አይመስልም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ በ42 ብሔር ብሔረሰቦች አጥሮ መፈናፈኛ ማሳጣትም አይገባም፡፡ ፈታ ብለን በሰፊ አገርና ከተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር ተዋህደንና ተዋደን በጋራ ዘና ብለን መኖርን እንደ ጭቆና መውሰድ የለብንም፡፡ ዋናው መታገል ያለብን የጭቆና ምንጭ የሆኑት ጨቋኝ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳይገዙን ነው፡፡ እንግዲህ ለመገንጠል እጅግ ከባድ መስዋዕትነትን ከፍሎ ማለቂያ ወደ ሌለው መከራ ከመግባት፣ በትግል ማስተካከል የሚቻለውን የብሔር ብሔረሰብ እኩልነትን አረጋግጦ ከሌሎች ጋር መኖር የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በምንም መመዘኛ ቢሆን ኦሮሚያ ተጠቃሚ የምትሆነው ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በፍቅር ስትኖር እንጂ፣ በመገንጠል የምታገኘው ጥቅም ያለመኖሩንና የሚያስከትለውንም አደጋ አውቆና አሳውቆ አቋምን ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ትልቅ ትቶ ትንሹን፣ ሰፊ አገር ትቶ ጠባብን መምረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ያን ትቶ ይችን ማግኘት ያስቆጫል፡፡ በመገንጠል የሚገኝ መብት የሚከበረው በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ብቻ ነው፡፡ የራሴ ዜጋ ቢያስተዳድረኝ ያልፍልኛል ብሎ ማሰብ፣ ከኤርትራና ከደቡብ ሱዳን ምንም ያለመማራችንን ያሳያል፡፡ እንጠንቀቅ፡፡ በብልኃትና በትዕግሥት እንጂ በስሜት ድል አይገኝም፣ ምኞትም አይሳካም፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ ከሌሎች የመለየት ጥያቄ ጨርሶ አይታወቅም፡፡ ይኼ ዘመን ያመጣው በኦሮሞ ልሂቃን የተፈጠረ አካሄድ ነው፡፡ ይልቅስ የኦሮሞ ሕዝብ በግልባጩ ውጤት ሲያስመዘግብ እንደኖረ ነው ታሪክ የሚነግረን፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በገዳ ሥርዓት በሚተዳደርበት ወቅት በየደረሰበት የሚያገኘውን ወይም ወደ እርሱ የሚመጡትን ሕዝቦች በሙሉ በፍቅርና በክብር ከራሱ ጋር በማዋሀድ፣ ንብረቱን ጭምር በማካፈልና በማውረስ ሌሎችን የራሱ ሳይሆን ራሱን በማድረግ አንድነትን ሳይሆን፣ ሕዝብን የሚፈጥር ታላቅ ሕዝብ ነበር፡፡
ይኼ ማኅበራዊ ደንባቸው ጉዲፈቻ፣ ሞጋሳና ሜድቻ የመሳሰሉት ኦሮሞ ከሌሎች ጋር የሚዋሀድበት፣ በሒደት ከጎኑ ያሉ ጎረቤቶች ከእርሱ ጋር ተዋህደው አገራቸውን አስፍተው በፍቅርና በሰላም የገዳው ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት የሚኖሩና የሚያኖሩ ነበሩ፡፡ ይኼ ማኅበራዊ ደንባቸው ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የመኖሪያ ክልላቸውን እንደ ዋርካ አስፍተው ጠላታቸውን በፍቅር አሸንፈው ሰፊ አገር መሥርተው እንዲኖሩ ያደረጋቸው ነው፡፡ ፍቅር እንዴት ተዓምር መፍጠር እንደሚችልና አሸናፊ እንደሆነ ዓለም በሙሉ ከዚህ እንዲማር ማድረግ የእኛ ተግባር ነው፡፡ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የረዳው እንዲህ ዓይነቶቹ እሴቶቹ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ የገዳ ሥርዓታችንም የዴሞክራሲ አባትና ምንጭ መሆኑንም ለዓለም የሚያሳይ ነው፡፡ አውሮፓውያን ባላቸው ሥልጣኔና ሀብት ልክ የቀኝ ግዛታቸውንና የባሪያ ፍንገላን በግፍና በጭካኔ ለመፈጸም ከመሞከርና በፀብና በቂም ከመለያየት ይልቅ ከላይ በተገለጸው የገዳ ሥርዓት አፍሪካን ቢቀርቡ ኖሮ፣ የእነሱም የመስፋፋት ምኞት ተሳክቶ እኛም በሥልጣኔ እነሱ ከደረሱበት በደረስን ነበር፡፡ እነሱም አፍሪካዊ እኛም አውሮፓዊ በሆንን ነበር፡፡ የገዳ ሥርዓት እንዲቋረጥ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም፣ ይኼንን በመሳሰሉት አወንታዊ ተፅዕኖዎች ሳይታሰብ የሌሎችም ህልውና ይፈታተናል ከሚል እኩይ እሳቤ እንደሆነ ይነገራል፡፡
አሁን በኦሮሞ ወጣቶች ውስጥ አንዳንዶች የሚፈጥሩት የመነጠልና የመገንጠል አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሕዝባችን ባህሉን፣ ቋንቋውንና ማንነቱን በሌሎች ዘንድ አስከብሮና አስፋፍቶ የኖረበትን የማስረፅ ዴሞክራሲያዊ ባህሉን የሚያቀጭጭ ነው፡፡ ከኬንያ እስከ ራያ፣ ከሶማሌ እስከ ወሎና ጎንደር የተስፋፋው የኦሮሚኛ ቋንቋ ከሌሎች በመገንጠልና ወይም በመነጠል ሳይሆን፣ በመዋሀድና በመቀላቀል ነው፡፡ እልህና ጉልበት የትም እንደማያደርሰን እስካሁን አልፈንበት የመጣነው ሒደቶች አሳይተውናል፡፡ ተከታታይ የሆነ ቂምና በቀል፣ ተከታታይ የሆነ ቡድናዊ የሥልጣን ሽሚያ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅ ሁሉ ከምን ጫፍ እንዳደረሰን አንዘንጋ፡፡ ፍቅርን መስበክና አንድነትን መሻት ደግሞ ባለፉት አራት ዓመት ብቻ በአገር ውስጥም በውጭም ለሁሉም ሕዝብ የፈነጠቀለትን ተስፋ እንመርምር፡፡ ጎዶሎና ስህተቶች ካሉም በሒደት እንደምናስተካክላቸው ተስፋ እናድርግ፡፡ የምንጓዝበት መንገድ የት እንደሚያደርሰን ከሩቅ ማየት አለብን፡፡ በችኮላና በሆይ ሆይታ የምናከናውናቸው ስሜታዊ ሥራዎች ሁሉ ድል ቢያስገኙም አይዘልቁም፡፡ ከትርፋቸው ይልቅ በብዙ እጥፍ በበለጠ ኪሳራ ነው የሚደመደሙት፡፡
በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ሕዝብ ዋናው ጥያቄ ለኦሮሞ ሕዝብ ከልብ እንታገላለን የሚሉትን የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ በተናጠል ሳይሆን፣ በጋራ አንድ ጠንካራ ድርጅት ፈጥረው ለሕዝብ ማንነትና መብት እንዲሁም አገራዊ ድርሻ በአግባቡ መወጣት አለባቸው የሚል ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃንና ድርጅቶች ከዚህም የዘለለ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዙሪያ ያሉትን የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ መብቶች ተከብረው የኢትዮጵያ አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆም ማድረግ እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው ለመሀሉ ክፍል ነው፡፡ የኦሮሞ ድርጅቶች ከአሁን በኋላ ማድረግ የሚገባቸው ኢትዮጵያን አንድ አድርገን ማስተባበርና መምራት የሚገባን ነን በማለት ቀዳሚ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡ በትክክል ካሰብን ኢትዮጵያ ያለ ኦሮሞ ኦሮሞም ያለ ኢትዮጵያ ይኖራሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ አንዱ ያለሌላው መኖር ካልቻለ አንዱን ከሌላው አስማምቶና አስተባብሮ ማኖር ግድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አቃፊ የሆነና ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሚከተል ድርጅት ከፈጠርን፣ በነባራዊ ሁኔታውና በዴሞክራሲያዊ አግባቡ የመሪነት ሚና ከኦሮሞ አመራር እንደማይወጣ ማወቅ አለብን፡፡
ያለፈውን በደል እያስታወስን ትውልዱ በበቀል ስሜት እንዲብሰለሰል አናድርግ፡፡ሐሕ
የምንሠራው ሥራ ሁሉ ለመጪው ትውልድ እንጂ ላለፈው ታሪካችን ማካካሻ አይደለም፡፡ አሁን የምንሠራው ሥራ ሁሉ ለመጪው ትውልድ እንጂ ላለፈው አይደለም፡፡ የምንሠራው ሥራ ሁሉ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችለው በመጪው ትውልድና ትግል ላይ እንጂ ያለፈው ላይ አይደለም፡፡ እኛ ግን አሁን እየተጣላንና እየተወቃቀስን ያለው ባለፈው ትውልድ ታሪክ ነው፡፡ ሙገሳ ምንም ለማይጨምርለት፣ ነቀፌታ ምንም ለማይቀንስለት ላለፈው የታሪክ ሒደት መቃቃርንና መጠፋፋትን ማውገዝ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ወደንና ፈቅደን በራሳችን ጥያቄ በማመልከቻ ላልተወለድንለት ብሔር ልንጠቃም ልንጎዳም አይገባም፡፡ የተፈጠርንበትን ብሔር አባል ለመሆን ትንሽም እንኳን የግለሰቡ አስተዋፅኦ የለበትም፡፡ ክፉዎች የራሳቸውን ብሔር ወይም ቡድን ለመጥቀም ሲባል ብቻ ሌላው በማያውቀውና ባልፈጸመው ጥፋት ሲገፉት ነው የመከራ ዘመን መቁጠር የሚጀመረው፡፡
ሁልጊዜ ግባችን የራሳችንን የፖለቲካ አጀንዳ ሌሎች የግድ እንዲቀበሉት ማድረግ መሆን የለበትም፡፡ በቅድሚያ ሊጤን የሚገባው የእኛ ፍላጎት ለሁሉም ሕዝቦች የጋራ መፍትሔ ያመጣል ወይ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ወደ ጎን ትተን ስለአንድነት ማቀንቀን የትም አያደርስም፡፡ ስለአገራዊ አንድነትና ስለሌሎች ብሔር ብሐረሰብ ያለን አመለካከትም ወደጎን ተገፍቶ፣ ለብቻ ማደግና ሰላም ማግኘት አይቻልም፡፡ በሕወሓት ፊታውራሪነት የሚመራው ኢሕአዴግም ለዚህ የበቃው በዚህ ሚዛናዊነት በጎደለው የፖለቲካ ዘይቤው ነው፡፡ የሕወሓት ዋናው ችግርና ለውድቀት የሚያበቃውም ይኼ እኔ ያልኩት ብቻ የሚለው አቋሙና የሌሎችን ሐሳብ ሁሉ በክፋት መፈረጁ ነው፡፡
እንግዲህ አሁን መንግሥት ለሰላማችንና ለልማታችን ሲል በነፃ አውጭነት መንፈስ አድገው ያረጁትን የሕወሓትና የኦነግ አመራሮችን ጊዜ ሰጥቶ በማወያየት፣ መጪውን ጊዜ ብሩህ ሊያደርገው ይገባል፡፡ ኦነግ ሲባል በአሁኑ ጊዜ ቀድሞ በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው አሁን ሦስት ቦታ ተሰንጥቆ የሚገኝ በመሆኑ፣ የእነ ሌንጮን ቡድን አይመለከትም፡፡ እንግዲህ አሁን ወደ ኦዴፓ የተቀየረው ኦሕዴድ ከጉባዔው በኋላ በኦሮሚያ ውስጥ ላለው አለመረጋጋት የወደፊቱን ተስፋ በተመለከተ ምን እንደሚል እናያለን፡፡ የሕወሓት ጉባዔም እውነት ለአገር የሚያስቡ ዜጎች ከተሰባሰቡት በጎሪጥ እያዩት ያለውን የፌዴራል መንንግሥትንና ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ራስ አካል በመቁጠር፣ ስህተቶች ታርመው ጠንካራ አንድነትን ይፈጥራሉ የሚል እምነት አለ፡፡ የተፈጠርንበትን የነፃ አውጭነት አቅጣጫን አንለቅም በማለት ከዓለም ላይ የተወገደውን ኮሙዩኒስታዊ ባህሪ ማስወድ ካልተቻለ፣ ለአንድነት መቆም በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ብቻ መሆኑን ካልተረዳን በታሪክም ሆነ በሕዝብ የምንጠየቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡