Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርዕውቀት ወደ ሥልጣን ወይስ ሥልጣን ወደ ዕውቀት?

ዕውቀት ወደ ሥልጣን ወይስ ሥልጣን ወደ ዕውቀት?

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም

አባ ጨጓሬ ሃምሳ እግር አለው፡፡ አንዱ መጥቶአባ ጨጓሬ  በጣም ታድለሃል፡፡ ሃምሳ እግር አለህአለው፡፡ይመሥገነው፣ አዎን የሃምሳ እግር ጌታ ነኝብሎ መለሰ፡፡በጣም ጎታታ ስለሆንክ አካሄድ ላስተምርህአለውና ሥልጠና ጀመረ፡፡ ሥልጠናው አለቀና በሥልጠናው መሠረት ሂድ ሲለው አባ ጨጓሬ ተደነቃቅፎ ወደቀ፡፡

በአገራችን እስከ ዛሬ ባለው ልማድ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ ሳይሆን፣ በሕዝብ መገልገያ ሆኖ ዘመናትን አሳልፏል፡፡ ሥልጣን ጠመንጃና ፈላጭ ቆራጭ የሆነበት፣ ሰድቦ፣ ደብድቦ፣ ገድሎና እስከ ቢሊዮኖች ዘርፎ የማይጠየቁበት ሆኖ ቆይቷል፡፡

የአገራችን ነገር ‹‹ግርምቢጥ›› (ተፃራሪ፣ የተገላቢጦሽ የሆነ፣ ለነገርም ለዘመንም ቁልቁል ሲሉት ሽቅብ) በመሆኑ ቤተ ሃይማኖቶችን ጨምሮ ሥልጣን የሚያርድ፣ ወደ ዕውቀት የሚወስድ፣ የዕውቀት ምንጭ፣ ደፋሮች የሚፈነጩበት፣ ንፅህናና ቅድስና የሌለው ሆኖ እስከ ዛሬ አለን፡፡

በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የተደረሰው ‹‹የደም እንባ›› መጽሐፍ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የእንስሳት ሕክምና ስለተማሩትና የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለነበሩት  ዓለሙ አበበ (ዶ/ር) አንድ ምፀት አቅርቦ ነበር፡፡ ዶ/ሩ መጀመርያ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ሲያስተምሩ ቆዩ፡፡

በኋላ ኮሎኔል መንግሥቱ ዶ/ር ዓለሙን ማርክሲዝም ሌኒንዝምን ብቻ ሳይሆን፣ የእንስሳት ሕክምናንም ያስተምሩ እንደነበር በመጽሐፉ ተገልጿል፡፡ 

አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ የፖለቲካ አመለካከታችንን ከተቀበለ ዘበኛም ቢሆን ሚኒስትር መሆን ይችላል ማለታቸውን በትካዜ አስታውሳለሁ፡፡ የሹመታቸው መሥፈርትም ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ (Meritocracy) ሳይሆን የፖለቲካ ታማኝነት ነበር፡፡ ለጉዳይ በየመሥሪያ ቤቱ የሄዳችሁ እንደምትገነዘቡት በዕውቀትና በችሎታቸው የተከበሩ ጎምቱዎቹን የተኩት አልፎ አልፎ በልምድና በዕውቀት ያልበሰሉ ካድሬዎች ናቸው፡፡ ብቃት ያላቸው ለሕዝብና ለብሔራዊ ክብር የሚቆረቆሩ በጎውን በተግባር ለመግለጥ የሚጥሩ አመራሮች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑና አመራሩን እንዳይዙ በመገፋታቸው ባክነዋል፡፡ 

‹‹መብላት፣ መጠጣት፣ መሰሰንና መሰይጠን›› የሕይወት ግባቸው ያደረጉ፣ ግፍንና መርገምትን በመፈጸም የሚረኩ ለጓደኝነት፣ ለውለታ፣ ሕዝቡ ዋጋ ለሚሰጣቸው ማኅበራዊ እሴቶች ዋጋ የማይሰጡና ለትርፍራፊ ሲሉ ቤተሰባቸውን አሳልፈው ለመስጠት የማያመነቱ የሥልጣን ረሃብ ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች ያጋጥሙኛል፡፡ ዛሬ ‹‹ክቡር እከሌ›› የሚባሉ የአንዳንድ ሰዎች ታሪክ ‹‹ነውር ልብሱ›› ነው፡፡ 

የአገሪቱ ጌታ የሆኑ አንዳንድ ባለሥልጣናት አገራችንን የነውራቸው መጫወቻ ሜዳ አድርገው ቆይተዋል፡፡ ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድ ጎጠኝነት፣ ዝምድና፣ ኔትወርክና ቆሻሻ ድርጊት ናቸው፡፡ የሥልጣን ቆጥ ላይ የወጡትም አገራቸውን ሳያውቁ፣ የዕውቀትና የልምድ ዝግጅት ሳይኖራቸው በቃላት ጉቦና በነውር እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የአንዳንዶቹ ‹‹ክቡር እከሌነት››  ከበስተጀርባው ለፈቺ የሚያስቸግር የወንጀል ትብትብ አለው፡፡ ለራስ ክብር ከመስጠት በበታችነት መንፈስ መሰቃየት፣ ቁም ነገርን በነሁላላነት፣ ጨዋነትን በነውር የለወጡ ሲሆን፣ መርህ አልባ ደፋሮችና ‹‹ሞሰብ ሃይማኖቱ››ዎች መሆናቸውን ተግባራቸው ይመሰክራል፡፡ 
ከተራራ የበለጠ ግዝፈት ያላቸው አርዓያዎች ያሉንን ያህል የአገር ቁጭት፣ ክብርና ኩራት የማያውቁ ማፈሪያ የፖለቲካ ድንክዬዎችን አፍርተናል፡፡ ትንሽ መጥፎ ድርጊት እንደ ጎርፍ በጎውን ጠራርጎ ያጠፋል፡፡

በሻምበል ለገሰ አስፋውና በአብዲ ኢሌ ብናፍርም በጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድና በኮሎኔል ጎሹ ወልዴ እንኮራለን፡፡ በወል ስም መጥራት ስለሚሻል ሌሎች የታሪክና የትውልድ ኩራት የሆኑ አርዓያዎቻችንንና የአገር ማፈሪያ የሆኑትን ዘርዝረን አንጨርስም፡፡

 ምክንያታዊና ‹‹ልከኛ›› አለመሆናችን ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ባለሥልጣኖቻችን ‹‹ምሉዕ በኩለኤ›› እንዲሆኑ እንሻለን፡፡ በዚህም የተነሳ ስናወግዝ ‹‹ሰይጣን›› ስናወድስ ‹‹መልዓክ›› አድርገን ነው፡፡ ሥጋ ለባሽ ሰው በባህርይም በግብርም ሰናዩና ዕኩይን አደባልቆ መያዙን እንዘነጋለን፡፡ በጣም ደግ ከሚባለው ትንሽ ንፍገት፣ በጣም ንፉግ ከሚባለው ጥቂት ቸርነት፣ በጣም ዕኩይ ከሚባለው ደግሞ ትንሽ ሰናይነት፣ የዋህ ከሚባለው ትንሽ ተንኮል፣ ከጀግናው ትንሽ ፍርኃት እንደማይጠፋና የበጎ ወይም የእኩይ ባህርይ ባለቤት ብቻ የሆነ ሰው እንደሌለ አንገነዘብም፡፡

 ‹‹ኃይለ ሥላሴ ይሙት›› በማለት ሲምሉ የነበሩ ወታደሮች ንጉሠ ነገሥቱ እንደ ወደቁ ‹‹ጭራቅ›› ያደረጓቸው በአንድ ጀምበር ነው፡፡ ከአገራችን አልፎ ለአፍሪካ የደከሙ ጎምቱ ባለሥልጣናት በአዳራሽ ስብሰባ እጅ በማውጣት በተሰጠ የደቦ ፍርድ ተረሽነዋል፡፡ በዚህ ዘመንም ያለ ፍርድ በግፍ የተገደሉ ዜጎቻችንን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በዘመነ ደርግ ለፍፁም አንድነት ሲያቀነቅኑ የነበሩ በዘመነ ኢሕአዴግ ወዲያው ተገልብጠው አክራሪ የዘውግ ፖለቲከኛ ሲሆኑም ታዝበናል፡፡ አስተውለው፣ አላምጠውና አስተንክረው የተቀበሉት እምነት በአየር ለውጥና በሞገድ አይናወፅም፣ አይለወጥም፡፡ 

ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በላከው መልዕክቱ (ወደ ጢሞቲዎስ ምዕ ፬፡፭) ‹‹አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፣…›› ይላል፡፡ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ አሳፋሪ ጉዶችን ያየነው በዚህ ዘመን ነው፡፡ ነገሮችን በልክ አለማድረግ ችግራችን ይመስለኛል፡፡ በህሊናና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያለን ምስክሮች አይደለንም፡፡ ይህ ጥቂት ንፅህናና ብፅህና ያላቸውን አይመለከትም፡፡

አንድ ምስክር ችሎት ፊት ቀርቧል አሉ፡፡ በምስክርነት የተጠራበት ምክንያት የግድያ ወንጀልን የሚመለከት ሲሆን፣ ቃሉን እንዲሰጥ የተደረገው በሟች ወገን ነው፡፡ ታድያ ፈሪ ብጤ ነው፡፡ ዳኛው፣ ‹‹ለመሆኑ ሟችና በገዳይነት የተጠረጠረውን ታውቃቸዋለህ?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡

ምስክር፡ ‹‹አዎ ጌታዬ!›› ይላል፡፡

ዳኛው፡ ‹‹እስኪ የሟችን ሁኔታ አስረዳኝ?›› ይለዋል፡፡

ይህኔ ለሥጋው የሳሳው መስካሪ ‹‹ገዳይ የተባለው ሰው በግራዬ በኩል ሟች የተባለው ደግሞ በቀኜ ቆሞ ነበር፡፡ እኔ መሀል ነበርኩ፡፡ በድንገት እንቅልፍ ይዞኝ ሽው አለ፡፡ ብንን ስል ሞቶ አየሁት፤›› ይልና የተወነጃበረ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ‹‹ሲገድለው አይቻለሁ፤›› አላለም፡፡ የገዳይን ወገኖች ፈርቷልና፣ ነገሩ አገም ጠቀም መሆኑ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ነገራችን የተወነጃበረው ከዕውቀት ሥልጣን በመቅደሙ ነው፡፡ ፊደልን የቀሰመ ሁሉ የሕዝብ አገልጋይ አይደለም፡፡ የደርግ አራጆች ከነበሩት ውስጥ ዲግሪ ብርቅ በነበረበት ዘመን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ነበሩበት፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያባሉና የሌብነት መሐንዲስና የመናጢው ጋኔን ግብረ አበሮች የሆኑ አንዳንድ ዕኩይ ባለ ‹‹ማስትሬት››ና ባለ ‹‹ዶክትሬት›› ባለሥልጣናትን ዓይተናል፡፡ 

ለማንኛውም የሕዝብን አደራ ለመሸከም ደንዳና ጫንቃ ያላቸው፣ እውነትን በምጣዳቸው እንጀራ መስፋትና መጥበብ የማይለኩ፣ ኩራትና ስግብግብነት የነፍስ መቅሰፍቶች መሆናቸውን የሚገነዘቡና የሕይወት መርህ ያላቸው፣ ዓለማዊ ዕውቀትን ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊ ሀብታችንም ጠልቀው የተማሩ ሕዝባዊ ባለሥልጣናት ይኖሩን ዘንድ ምኞቴም ጸሎቴም ነው፡፡

 ፈረንጆች ‹‹Nature is Perfect›› ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር በሥራውና በፍጥረቱ አይሳሳትም፡፡ አባ ጨጓሬን በሥልጠና ፈጣን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ከዕውቀት፣ ከልምድና ከማስተዋል በፊት ሥልጣን ሲቀድም አባ ጨጓሬ የደረሰበት ነገር ያጋጥማል፡፡ 

ደሃን እንደ ሙሴ ዘመን ‹‹ለምፃሞች›› የሚያዩ፣ ሕይወትን ከውጭ ቆመው የሚታዘቡ፣ ለብቻቸው ማማ ሠርተው ወደ ላይ የሚንጠራሩና ኅብረተሰቡን ቁልቁል የሚመለከቱ ‹‹ሥልጣን ወደ እውቀት›› የፈጠራቸውን እግዚአብሔር ያርቅልን፡፡ የሕዝቡን ገመና የራሳቸው ገበና የሚያደርጉ፣ ሞታችንን የሚሞቱልንና ሀቃችንን የሚያራምዱልን፣ በእግዚአብሔርና በሕዝብ ፊት ህሊናቸውና ግብራቸው የተመሰከረላቸው ‹‹ዕውቀት ወደ ሥልጣን›› ባለሥልጣናት እግዚአብሔር ያብዛልን፡፡ እግዚአብሔር የባረካቸውን ባለሥልጣናት እንዴት መያዝ እንደሚገባን ለእኛም ማስተዋል ይስጠን፡፡  እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...