Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርያዲያቆነ ቀኖናዊነት ሳያቀስ አይለቅም

ያዲያቆነ ቀኖናዊነት ሳያቀስ አይለቅም

ቀን:

በመርሐ ጽድቅ መኰንን ዓባይነህ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ከመስከረም 23 ቀን ጀምሮ እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ያካሂዳል፡፡ የዚህን ጉባዔ ዝግጅት፣ የመወያያ አጀንዳዎችና የሚጠበቁትን ውጤቶች አስመልክቶ የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መስከረም 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ በጥሞና ተከታትያለሁ፡፡ ከሁሉ በፊት ሴትየዋ ምንም ይሁን ምን በቀደመ አቋማቸው የፀኑ፣ እንደ ብዙዎቹ የፖለቲካ አክሮባት ሠሪዎች በቀላሉ ተንሸራታችነትና በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የሚዘወር ተለዋዋጭነት የማይታይባቸው በመሆኑ ላደንቃቸው እወዳለሁ፡፡

መግለጫው በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጉባዔው ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረበት ጊዜ በስድስት ወራት ከተራዘመበት ምክንያት አንስቶ በመድረኩ ይተላለፋሉ ተብለው እስከሚገመቱ ውሳኔዎች የዘለቁ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ ከጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ፈታኝ የሚመስሉ ጥያቄዎች ሳይቀር ከራሳቸው የፖለቲካ እምነት በመነሳት ያለማለባበስ መልሰዋቸዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የለዘብተኛውን ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ተከትለው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየወሰዱት ባለው ፈርጀ ብዙ ዕርምጃና የፖለቲካ አንድምታዎቹ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር በጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ቆፍጣናዋ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከሆነ ሪፎርሙ በመካሄድ ላይ ያለው ኢሕአዴግ ባስቀመጣቸው መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ተመሥርቶ ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር ) ራሳቸው የግንባሩ ሊቀመንበር ባይሆኑ ኖሮ፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በመንግሥት ስም የወሰዷቸውን ዕርምጃዎች የመውሰድ አቅም ባላገኙ ነበር ሲሉ ነገሩን ከተገቢው በላይ ወደ ሰማይ ሰቅለውታል፡፡

ሴትየዋ እንደሚነግሩን ዶ/ር ዓብይ በእርግጥ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ነበሩ፣ አሁንም ናቸው፡፡ ያም ሆኖ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከህቡዕ እስር የለቀቁት በኢሕአዴግ ሙሉ ፈቃድና ውሳኔ ነበር ሊሉን ከቶ አይቻላቸውም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አርበኞች ግንቦት ሰባትን፣ ኦነግንም ሆነ ኦብነግን ከእነ መሪዎቻቸው ከአሸባሪነት መዝገብ አላቀው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና የትጥቅ ትግሉን እርግፍ አድርገው በመተው ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለፖለቲካ ሥልጣን እንዲፎካከሩ እስከ መወሰን የደረሱት፣ በኢሕአዴግ ነፃ ፈቃድና ፍላጎት ነበር ብለው ሊያሞኙን ቢሞክሩ አብዝተን እንታዘባቸዋለን፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ቁልፍ የፖለቲካ ዕርምጃዎች የወሰዱት የለውጡን ደጋፊ ኃይል ከጎናቸው በማሠለፍ፣ ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሐሳቦችን በከፍተኛ ድፍረት በማንቀሳቀስና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ጨምሮ በሥርዓቱ ውስጥ ቢደራጁም፣ ክፉኛ ተዳክመው የቆዩትን መንግሥታዊ ተቋማት በሙሉ አቅም በማሠራት እንደሆነ በውል መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝባዊው የለውጥ ማዕበል ክፉኛ ያወዛወዘው ኢሕአዴግ በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔው የርዕዮተ ዓለም ዕርማት፣ ወይም ማስተካከያ ለማድረግ አስቦ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጧቸው ዘንድ ጋዜጠኞች ወይዘሮዋን ደጋግመው ጎትጉተዋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህኛው ጉባዔውም ቢሆን አንዳንድ ወገኖች እንደሚገምቱት ግንባሩ የርዕዮተ ዓለምም ሆነ የፕሮግራም ለውጥ አያደርግም፡፡ ምናልባት ከአዳጊ ሁኔታዎች ጋር የተገናኙ መጠነኛ ማሻሻያዎችን ሊያደርግ ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ምን ጊዜም ቢሆን በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ የሚከናወንና የተለመደ ተግባር ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ አብዮታዊ፣ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን አይነካካም ሲሉ እቅጩን ነግረዋቸዋል፡፡

ይኸው የሴትየዋ ቁርጥ ያለ አቋም አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ (የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው)፣ 13ኛውን የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ድርጅታዊ ጉባዔ ዝግጅት አስመልክቶ ዓርብ መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓለም ፍሰሐ በተባለው የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው አገልግሎት ጋዜጠኛ በኩል እንዲሁ ተጠይቀው በሰጡትና ከአንድ ወንዝ የተቀዳ መስሎ በተደመጠው ምላሽ የበለጠ ተጠናክሮ ተስተጋብቷል፡፡

ለመሆኑ በኢሕአዴግ ተጠባብያን እሳቤ ወገንተኝነቱ ለጭቁን ሕዝቦች ነው የሚባልለት አብዮታዊ ዴሞክራሲ በቁሙ ሲወሰድ ምን ማለት ይሆን? በግዕዝ ልሳን አበየ ለሚለው ቃል የአማርኛ ቋንቋ ምትኩ እምቢ አለ፣ አወከ፣ አመፀ…ነው፡፡ ከዚህ ሥርወ ቃል ስንነሳ አብዮታዊ የተሰኘው ቅጽል እምቢተኛን፣ ሁከት ፈጣሪን ወይም አመፅ ያረገዘን አሉታዊ ሁኔታ ከወዲሁ ያጠይቃል፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲ በባህሪው ፈቃጅ እንጂ አስገዳጅ፣ እምቢተኛና ሁከት አነሳሽ ወይም አመፀኛ ሊሆን አይችልምና ሳንፈልገው ተጭኖብን ከመቆየቱ የተነሳ፣ ርዕዮቱን ያላንዳች ጥያቄ ተቀብለነውና ተለማምደነው ካልሆነ በስተቀር የዴሞክራሲ አብዮተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀነቀንለት ብቻ ሳይሆን እምብዛም የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡

ታሪክን የኋሊት ስንመረምር በሃያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ እነ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን በላብ አደሩ አምባገነንነት ሥር ተጠልለው ወደ ካፒታሊዝም አቋራጭ መሸጋገሪያ በማድረግ እንደተጠቀሙበት እናስታውሳለን፡፡ ያኔ ታዲያ እነርሱ አወዛጋቢውን ማዕቀፍ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት እያሉ ነበር የሚያንቆለጳጵሱት፡፡ ሶሻሊዝም ከመንኮታኮቱ በፊት በምሥራቅ አውሮፓ ተተክለው የነበሩ የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት አጫፋሪ መንግሥታት ሕዝቦቻቸው እንዳልመረጧቸው ልቦናቸው እያወቀው፣ የሕዝብ ዴሞክራሲዎች ነን እያሉ ያላግጡ እንደነበረው መሆኑ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በመከረኛው ዴሞክራሲ ላይ በዘፈቀደ የማይጫን ቅጽል የለም፡፡ ለዘብተኛ ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ክርስቲያን ዴሞክራሲ፣ እስላማዊ ዴሞክራሲና አሁን ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ወዘተርፈ፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ዴሞክራሲ በተሰኘው ወርቃማ ቃል ላይ እንዲህ ያለውን ብዥታ ፈጣሪ ቅጽል የሚለጥፉት፣ በአንድ በተወሰነ ርዕዮት ወይም እምነት ጥላ ሥር ተሰባስበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ወይም የማኅበረሰብ ቡድኖች ሲሆኑ ምልዓተ ሕዝቡ ለምን ብሎ የመጠየቅ ዕድል እንኳን አግኝቶ አያውቅም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም ብንሆን የምንከተለው ዴሞክራሲ መለያ አብዮታዊ ስለመሆኑ በመሪዎቻችን በኩል ተነገረን እንጂ፣ መደረግ በሚገባው ልክ መክረንበትና እርስ በርስ ተከራክረንበት በብዙኃኑ ውሳኔ ይሁንታ ያገኘ ጉዳይ ነው ማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡

ያም ሆኖ በአንድ አገርና ሕዝብ ውስጥ የታቀፉትን የተለያዩ ማኅበረሰቦች ራሱ ባወጣው መስፈሪያ ጠላትና ወዳጅ ብሎ በመፈረጅ የሚታወቀው አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ለነባር የኢሕአዴግ አባላት የሃይማኖት ያህል ሳይሸራረፍ መመለክ ያለበት ርዕዮት መስሎ ይታያል፡፡ ይልቁንም የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ዓይታው ወደማታውቀው የተወሳሰበ ችግር የገባችው ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ትንሽ ዘነፍ በማለቷ ሲሆን፣ መፍትሔውም ያለ ጥርጥር ወደዚያው መመለስ ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ነግረውናል፡፡

ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ብሔራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣምና ሚዛናቸውን በመጠበቅ ደንግጎልን እያለ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ባለ ዋጋነት ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ሳንሠራ ቆይተናል ሲሉ የተናዘዙበት የመግለጫው ክፍል ነው፡፡ ከማስተዛዘኛነት የማያልፈው ይህ ዓይነቱ አስተያየት በሕገ መንግሥቱ ይዘት ላይ እንዳናተኩርና ጥልቀት ያለው ፍተሻ እንዳናደርግ የማዘናጋት አደጋ ይኖረዋል፡፡

ሕገ መንግሥታችን በመግቢያው ላይ ቀና ቀናውን ሐረግ ጽፎ ቢያስነብበንም ቅሉ፣ በተለበራሱ ቋንቋ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እያለ ለሚጠራቸውና አንደኛውን ከሌላው በውል ለይቶ እንኳ ግልጽ ትርጓሜ ላልሰጣቸው ቡድኖች በአፍ መፍቻ ልሳን የመናገርና የመጻፍ፣ ባህልና ታሪክን የማበልፀግና በራስ ገዝ ተቋማት የመተዳደር መብቶችና ነፃነቶችን በመዘርዘር ብቻ አያቆምም፡፡ ከዚህ በብዙ አልፎ ፌዴሬሽኑን የመሠረቱት ከሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች ያለ ገደብ የተረጋገጠላቸውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተጠቅመው በፈለጉ ጊዜ እስከ መገንጠልና የየራሳቸውን ትንንሽ መንግሥታት እስከ መመሥረት የሚዘልቅ ነፃነት እንዳላቸው በማያሻማ ሁኔታ ያውጅላቸዋል፡፡ ስለሆነም የአገራዊ አንድነታችን መሸርሸር ምክንያቱ ወ/ሮ ፈትለወርቅ እንደሚሉት ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ አንድነት ከብሔራዊ ማንነት ያነሰ ትኩረት ሰጥቶ መቆየቱ ሳይሆን፣ ቀድሞ ነገር ሕገ መንግሥቱ ራሱ ከኢትዮጵያዊ አንድነት ይልቅ ለብሔራዊ ማንነት ክፉኛ አዳልቶ መደንገጉ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በመጨረሻም የዚህን ጸሐፊ የላቀ ትኩረት በእጅጉ የሳበው በጋራ ርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ፕሮግራም ተጣምረው ኢሕአዴግን በፈጠሩት ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ስላለው የርስ በርስ ግንኙነት መስተጋብር ሴትየዋ የሰነዘሩት የአገም ጠቀም አስተያየት ነበር፡፡ በወ/ሮ ፈትለወርቅ አነጋገር የግንባሩ ተጣማሪ አባሎች በሆኑት ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል መለስተኛ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ በውስጥ ትግል መታረም የሚችሉ ከመሆናቸው የተነሳ፣ መሠረታዊ ሊባል የሚችል ቅራኔ ያለ አይመስልም፡፡ ነገር ግን ይህ አባባላቸው ‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›ን ከማስታወስ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

ከዚያ ይልቅ ‹አገር በይፋ ያወቀውንና ፀሐይ አብዝቶ የሞቀው›ን የሕወሓትና የሌሎቹን ተጣማሪ ድርጅቶች የበዛ መንቆራቆስ ገሀድ አውጥቶና በልዩነቶቻቸው ላይ በግልጽ ተከራክሮ አስማሚ መፍትሔ ላይ መድረስና ሌላው ቢቀር እንኳ ለራሳቸው ለብሔራዊ ድርጅቶቹ ህልውና ቀጣይነት አስፈላጊ ሆኖ የሚታየውን አንጋፋውን ግንባር ጨርሶ ከመበተን ማዳኑ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...