Monday, May 29, 2023

ኃላፊነት የጎደለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የሚያስከፍለው ዋጋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የዴሞክራሲ ማዕከላዊ መርህ ነው፡፡ ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ደግሞ በይበልጥ እንዲተገበርና እንዲከበር ካደረጉ የታሪክ ክስተቶች፣ የቅርብ ጊዜውና ትልቁ ተጠቃሽ የማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ በባህርይው በማዕከላዊነት የሚደረግ የይዘት ቁጥጥር ባለመኖሩ፣ ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ጉዳይ ያለማንም ገምጋሚነትና አርታኢነት በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ተጠቃሚ ተከታዮቻቸው በአነስተኛ ወጪ ያስተላልፋሉ፡፡ ይህም ሳንሱር እንዲጠፋ የሚደረገው ትግልና ክርክር እርባን አልባ እንዲሆን በማድረግ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ እሳቤ፣ ይህን ያህል ይሄዳል ተብሎ ያልተጠበቀበት ደረጃ አድርሶታል፡፡

በዚህም ምክንያት የማኅበራዊ ሚዲያው ለዴሞክራሲ ልምምድ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንደሚጫወት ዕሙን ነው፡፡ ዛሬ አንድ ግለሰብ በስልኩ የሚያደርገው ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ሮናልድ ሬገን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሳሉ ያደርጉት ከነበረው እንደሚልቅ፣ ከ20 ዓመታት በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቢል ክሊንተን ያገኙት ከነበረው መረጃ የበለጠ አንድ የ13 ዓመት ታዳጊ በስልኩ እንደሚያገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መረጃ ኃይል ነውና በዚህ ዘመን በቀላሉ የሚገኝ መረጃ ለዴሞክራሲ ልምምድ ብሎም በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ለመስጠት ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ከመሪዎቹ የሚገዳደር መረጃ እጁ ጫፍ ላይ የያዘ ዜጋ የመንግሥትት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ይችላልና፡፡ ከአንድ የዓለም ጫፍ የተከሰተን ጉዳይ  ማግኘትና መተንተን፣ ከዚያም ለውሳኔ መዘጋጀት ከኢንተርኔት ዘመን አስቀድሞ የደኅንነት ተቋማት ተግባር ነበር፡፡ አሁን ግን ከደኅንነት ተቋማት በማይተናነስ ደረጃ ማንኛውም ዜጋ መረጃ አለው፡፡ ይህም መንግሥት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች እየተከታተሉ ለምን? እንዴት? ለማን ተወሰኑ? በሚሉ ጥያቄዎች ማረምና ተጠያቂነትን ማምጣት ይቻላል፡፡

ይሁንና በ1980ዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሬገንና ከ20 ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ሥልጣን ላይ የነበሩት ክሊንተን ያገኟቸው የነበሩ መረጃዎች፣ አሁን ላይ ማንም ከሚያገኛቸው መረጃዎች የሚለዩበት አንድ ነጥብ አለ፣ ተዓማኒነት፡፡ ፕሬዚዳንቶቹ ለሚያስተላልፏዋቸው ውሳኔዎች እንዲረዷቸው መረጃዎቹን ከታማኝ ምንጮች ያገኛሉ፡፡ ለመተንተን ይረዳቸውም ዘንድ ከባለሙያዎች ጋር ይነጋገራሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ከስልኮቻችን፣ በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ የምናገኛቸው መረጃዎች ተዓማኒነታቸው አናሳ በመሆኑ የሚተላለፉ ውሳኔዎች አደገኛ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡

ለዚህ የቅርብ ጊዜ ማሳያ የሚሆነው በማይናማር (በርማ) በሮሂንጂያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ነው፡፡ በዚህች የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር የሚኖሩና እንደ አገሪቱ ዜጎች የማይቆጠሩት የሮሂንጊያ ማኅበረሰብ እ.ኤ.አ. በ2016 በአገሪቱ ወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ሲሞቱባቸው፣ ከ700 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ በቅተዋል፡፡ በዚህች አብዛኛው ማኅበረሰብ ዜናም ሆነ ተያያዥ መረጃዎችን ከማኅበራዊ ገጾች በተለይም ከፌስቡክ እንደሚያገኝ በሚገለጽባት አገር፣ በሮሂንጂያ ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመው በደል ‹በዓለማችን እጅግ በጣም የተጨፈጨፉ ሰዎች› በመባል እንዲታወቅ ያደረገ ጥፋት እንዲፈጸም ያደረገው በፊስቡክ የሚለቀቅ መረጃ ነበር፡፡

በማይናማር የቡድሂስት መነኩሴ የሆኑት አሺን ዊራቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተከታይ ያላቸው ሲሆኑ፣ ይኼንን የተከታዮቻቸውን መብዛት ለበጎ ሳይሆን የውሸት መረጃዎችን በማሠራጨት ለበርካቶች ሞት መንስዔ ሆነዋል፡፡ እኚህ የማይናማር ቢን ላዲን በመባል የተሰየሙት መነኩሴ ለተከታዮቻቸው ሙስሊም የሆነ አንድ ባለድርጅት አሠሪ፣ የቡድሂስት እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ደፍሯል የሚሉ የሐሰት ማስረጃ ቢያስራጩም ተጠያቂ አልሆኑም ነበር፡፡ ፌስቡክም በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢደረግለትም እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ድረስ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ከፍተኛ ጥፋት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል፡፡

በዚህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በተንሰራፉበት ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉና አብዛኛው ኅብረተሰብ ያልተማረ በሆነባቸው አገሮች፣ የማይናማር ዕጣ ፈንታ ሊደገምባቸው እንደማይችል ማረጋገጫ እንደሌለ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ይህ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፈር ካልተበጀለት አጥፊነቱ ሊከፋ ይችላልም ይላሉ፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የኢንተርኔት ተደራሽነትና የስማርት ሞባይል ስልኮች መስፋፋት ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዕድገት እንዲኖር አድርጓል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ እንደሚያሳየው፣ አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 67.5 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 65.7 ሚሊዮን የሚሆኑት የሞባይል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ 17.8 ሚሊዮን ደግሞ የኢንተርኔትና የዳታ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 1.2 ሚሊዮን የመደበኛ ስልክ ደንበኞች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የስማርት ስልኮች ተጠቃሚነት ከዓለማችን የመጨረሻው ቢሆንም (ከአጠቃላይ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች አራት በመቶው ብቻ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው)፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ ነው፡፡ ሆኖም ከዓለም አንፃር አናሳ ነው፡፡

ኩዋርትዝ አፍሪካ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አጠቃላይ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ብዙ ቢሆንም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ግን ከአራት ሚሊዮን አይበልጥም፡፡ ይሁንና እያደገ በመጣው የተጠቃሚዎች ዕድገት በመሳብ ግለሰቦችም ሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማት ማኅበራዊ ሚዲያ ወደ መጠቀም አዘንብለዋል፡፡ በዚህም በአነስተኛ ወጪ መረጃዎችን ለበርካቶች ተደራሽ ያደርጋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከሚውሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በቀዳሚነት የሚነሳው ፌስቡክ ሲሆን፣ 93.7 በመቶ የሚሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው፡፡ በመቀጠል ዩቲዩብ፣ ፒንተረስት፣ ትዊተር፣ ጉግል ፕላስና ሊንክደን ይከተላሉ፡፡

በዓለም እንደሚታየው ሁሉ የማኅበራዊ ሚዲያው በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በኢትዮጵያም ራሱን እየገለጠ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን ሥራቸውን ለማስተዋወቅ፣ ጠቃሚ ማረጃዎችን ለማቀበል፣ ለማዝናናት፣ አገራቸውንና አካባቢያቸውን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙበት እንዳሉ ሁሉ፣ የጥላቻ መልዕክቶችን ለማሠራጨት፣ ዘረኝነትን ለመስበክ፣ ሃይማኖትና ብሔርን ለማንቋሸሽ፣ ለመሳደብና ለፀብ ለማነሳሳት የሚጠቀሙበት ትንሽ አይደሉም፡፡ ፌስቡክና የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡትን ሐሳብን ያለገደብ የመግለጽ መብት በመጠቀም፣ የአንድ ወገን በደሎችን ብቻ የሚያጎሉ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ሳይታክቱ የሚሠሩ በርካቶች ናቸው፡፡

በርካታ ተከታዮች ኖረዋቸው ለእነዚህ ተከታዮቻቸው ለፀብ የሚያነሳሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ እነዚህ መልዕክቶቻቸው የሚያደርሷቸው ጥፋቶች እነርሱ ላይ ጉዳት ስለማያስከትሉ ሰዎች እየሞቱ፣ ንብረቶች እየወደሙና በርካቶች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ በምቾት የጥፋት ሥራዎቻቸውን ያከናውናሉ፡፡

ይኼንን በማድረጋቸውም ለማኅበረሰብ መብት ተቆርቋሪ ተደርገው ይቆጠራሉ፣ የነፃ አውጪነትን ማዕረግን ይሸለማሉ፡፡ ይህ በተለይ የፖለቲካ አክቲቪስት ነን በማለት ጎራ ለይተው የቃላት ጦርነት እያደረጉ፣ በአካል ጦርነቶችን በማነሳሳት የሚሠሩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጠቃሚዎች ላይ በጉልህ ይታያል፡፡ በአንዱ ጎራ የእኔ ብሔር ተጠቃ አጥቂውም የእገሌ ብሔር ነው እያሉ ጣት ሲቀሳሰሩ፣ ለበርካታ ዓመታት ተዋልዶና ተፋቅሮ በኖረ ማኅበረሰብ ዘንድ ጠላትነትን ይዘራሉ፡፡ ይህ ድርጊት የማይናማር ቢን ላዲን የተባለን ግለሰብ በደቡብ ምሥራቅ እስያ እንደፈጠረ ሁሉ፣ ተመሳሳይ አዛሳኝ ታሪክ በኢትዮጵያ ሊደገም እንደማይቻል ምንም ማስተማመኛ እንደሌለ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ከልማታቸው እኩል ለዴሞክራሲና እንደ መናገር ላሉ መርሆች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ዕሙን እንደሆነ ባለሙያዎች ቢስማሙም፣ ከሰላም የሚበልጥ የለምና የሕዝቦችን አብሮ የመኖርና ሰላም የሚያደፈርስ ጉዳይ ከተከሰተ መላ ሊባልና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ ያትታሉ፡፡

የክፋት ዓላማ ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ባገኙት አጋጣሚ ፍርኃትን በመንዛት ከፍተኛ ጥፋት ለመፍጠር የሚችል የጥፋት ሠራዊት እንደሚገነቡ፣ ዴሞክራሲን ፈተና ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ክፉ ሐሳብ ያላቸው ተጠቃሚዎች ደግሞ የሕግ፣ የሥነ ምግባር ወይም የሞራል ተጠያቂነት ስለሌላቸው ያለ ገደብ የበላይነታቸውን ይዘው ሁሉንም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ እንደሚያደርጉም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያም ሊሠራ የሚችል ነው፡፡

ፈተናዎችና መፍትሔዎች

እንዲህ ዓይነት ጥፋቶችን ለመከላከል ሲሉ እንደ ፌስቡክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት የጥላቻ መልዕክቶችን፣ ሰቅጣጭ ምሥሎችንና የሐሰት መረጃዎችን ለመለየትና ለማጥፋት የሚያስችሏቸውን መፍትሔዎች አስቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ (በሮቦት) የታገዘ የልየታና የማስወገድ ሥራ ነው፡፡ ይህ በዋናነት ለእንግሊዝኛና ለአውሮፓ ቋንቋዎች በብቃት የሚሠራ ውጤታማ መፍትሔ ሲሆን፣ ለበርማና አማርኛን ለመሳሰሉ ቋንቋዎች መፍትሔ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፕሮግራም የተደረጉ ሮቦቶች በቋንቋዎቹ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ባህርያትንና ትርጉሞችን የመለየት ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ስለዚህ በሁለተኛ አማራጭነት የተቀመጠው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ተጠቅሞ ማጣራት ነው፡፡ ተጠቃሚዎች የሚያጋጥሟቸውን ያልተገቡ ይዘቶች ለሚመለከታቸው በመጠቆም ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ቁጭ ብለው የሚለዩ ባለሙያዎችን መጠቀም ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተቀጥረው የሚቀመጡ ሰዎች በየቋንቋዎቻቸው እየገቡ የሚያገኟቸውን ያልተገቡ መልዕክቶች ያስወግዳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ በበቂ የሰው ኃይል ስለማይሠራ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው በማይናማር ያ ሁሉ እልቂት እየተፈጸመ ፌስቡክ የነበሩት ስድስት በማይናማር ቋንቋ የሚሠሩ የልየታ ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውና የጥላቻ መልዕክት የሚያስተላልፉትን መነኩሴ ገጽ ለመዝጋት መለሳለስ ማሳያታቸው ነው፡፡

የተጠቃሚዎች ሚና

የፌስቡክም ሆነ የተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጠቃሚዎች፣ እነዚህን ገጾች በሚጠቀሙበት ወቅት በራሳቸው ጽሑፎችም ሆነ ከሌሎች ወስደው በሚያጋሯቸው ጽሑፎች ውስጥ ያሉ የጥላቻ መልዕክትና የተለያዩ የጥፋት ይዘቶችን በመለየት ከጥፋት የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በርካታ ተጠቃሚዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለበጎ ዓላማ ለማዋል ቢያሰጡም፣ ቢጀምሩም፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ባላቸው ተጠቃሚዎች ሊጠለፉ ስለሚችሉም ጥንቃቄ በማድረግና በጎ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ግለሰቦችና ከሚያውቋቸው ጋር ትስስርን እንዲፈጥሩ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ዋጋቸው አነስተኛ በሆኑ ስማርት ስልኮች አማካይነት ይበልጥ ስለሚስፋፋም በጎ ዓላማ ያላቸው ተጠቃሚዎች ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እያጎሉ እንዲመጡ አጥኚዎች ይመክራሉ፡፡

የመንግሥት ኃላፊነት

ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የመንግሥት የመጀመርያው ተግባር የዜጎቹን የደኅንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል የትኛውም ሥጋት ሊወገድ ይገባል ይላሉ፣ ማኅበራዊ ሚዲያም ቢሆን፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚቆሙ አካላት ደግሞ መንግሥት የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከማፈን ይልቅ፣ ኅብረተሰቡን ማስተማር ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፣ ማኅበራዊ ሚዲያውንም ሆነ ኢንተርኔት መዝጋት ከቴክኖሎጂ ጋር የሚደረግ ትግል ስለሆነ በድል የሚወጡት ጦርነት አይደለም ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡበት ሰሞን ከመከላከያ ከፍተኛ መኰንኖች ጋር በነበራቸው ውይይት፣ አንድ አሜሪካ ባለ አንድ ፌስቡክ ያለ ተቋም አማካይነት የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይወድቃል ብለው ነበር፡፡ ስለዚህም የመከላከያ ኃይሉ የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ክስተቶችን የማስቆም አቅሙ ማደግ አለበት፡፡ ይህ ግን እንደ ባለሙያዎች ዕይታ በሕግ መታገዝ ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት መንግሥት በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ጉዳዮችን መቆጣጠር ስለላለበት፣ የሕግ ማዕቀፍ አውጥቶ መድረኮቹ ለበጎ አገልግሎት እንጂ ለጥፋት እንዳይውሉ ማድረግ አለበት፡፡

ከዚህ በዘለለ መንግሥት ቁጥጥሩን ተቋማዊ በማድረግ አገርን ከጥፋት መከላከል አለበት ሲሉም ይመክራሉ፡፡ ለዚህ ተሞክሮ ከግብፅ መውሰድ እንደሚቻልና ግብፅ የፌስቡክ ሚኒስቴር በማቋቋም የቁጥጥር ሥራ እንደምታከናውን ያመለክታሉ፡፡ በዚህም የሐሰት ምሥሎችን በሚለጥፉ፣ የውሸትና የፈጠራ ወሬዎችን በሚያሠራጩና ጥፋትን በሚያነሳሱ ላይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -