Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጥ እያስመዘገበም ከዝቅተኛው ርከን ያልወጣው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት ደረጃ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ይፋ የሚያደርገው የሰብዓዊ ልማት መመዘኛ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ በየጊዜው ያሳየቻቸውን ለውጦች ይጠቅሳል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት፣ በብሔራዊ ገቢ ልኬት፣ በዕድሜ ጣሪያ፣ በእናቶችና ሕፃናት ሞት፣ በምግብ ድህነትና በመሳሰሉት መለኪያዎች ረገድ ያስመዘገበቻቸውን ለውጦች የሚጠቅሰው የዚህ ዓመት ሪፖርት፣ ይህም ይባል እንጂ አገሪቱ አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ከሚፈረጀው የሰብዓዊ ልማት ርከን ልትላቀቅ አልቻለችም፡፡

በዩኤንዲፒ መለኪያ መሥፈርቶች መሠረት በሰብዓዊ ልማት በኩል አገሮች የሚያስመዘግቡት ውጤት ከዜሮ እስከ አንድ ባለው ደረጃ መመዘኛ ተቀምጦላቸው ይመደባሉ፡፡ በዚህ አግባብ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት ጠቋሚ መመዘኛ ውጤት የሚያሳየው ከ0.463 በታች ነው፡፡ ይህ ውጤት ዝቅተኛ የመመዘኛ ውጤት ያገኙ አገሮች ከሚለኩበት የ0.504 በመቶ በታች ከመሆኑም ባሻገር፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ዘንድ በአማካይ ከሚመዘገበው የ0.537 በመቶ በታች ሆኖ የሚገኝ ውጤት ነው፡፡ 

ምንም እንኳ የአገሪቱ የሰብዓዊ ልማት ደረጃ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ቢጠቅስም፣ በሌላ አግባብ ግን ባለፉት ሁለት አሥርታት ውስጥ ለውጦች መመዝገባቸውንም ያትታል፡፡ ዓምና የተዘመገበው የ0.463 በመቶ የሰብዓዊ ልማት ጠቋሚ መመዘኛ ውጤት፣ እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረው መመዘኛ አኳያ ከግማሽ በላይ ውጤት በማሳየት መሻሻሉ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ0.283 ተነስቶ አሁን ወደሚገኝበት ደረጃ ማደጉ ቢገለጽም፣ የሰብዓዊ ልማት ደረጃዎች ከሚመዘኑባቸው 189 አገሮች ውስጥ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ ልማት ደረጃ በ173ኛነት እንድትመደብ አስገድዷታል፡፡

ይህ ውጤት ሲተነተን፣ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ ዓምና ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያውያን መካከል የታው በሕይወት የመኖር ወይም የዕድሜ ጣሪያ የ18.8 ዓመታት ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ማለት እ.ኤ.አ. በ1990 የአንድ ኢትዮጵያ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ 47 ዓመታት የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን 66 ዓመታት ከፍ ብሏል፡፡ በመሆኑም አንድ ኢትዮጵያ በሕይወት የሚቆይበት አማካይ ዕድሜ 66 ዓመታት ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሕፃናት በትምህርት የሚያሳልፉት ጊዜ ከ3.1 ዓመት ወደ 8.5 ዓመታት ከፍ ሲል፣ በየዓመቱ የታየው አማካይ የትምህርት ላይ ቆይታ ጊዜያቸውም ወደ 2.7 በመቶ ተሻሽሏል፡፡

በትምህርትና በዕድሜ ቆይታ ረገድ የታየው መሻሻል በሌሎች እንደ ፆታና የገቢ እኩልነት ባሉ መለኪያዎች ሲታይ፣ አገሪቱ ካገኘችው ውጤትም ያነሰ ውጤት የተመዘገበበት መመዘኛ ላይ ወድቃለች፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በፆታ እኩልነት አግባብ ከሌሎች እንደ ሩዋንዳ፣ ቡርኪና ፋሶና ሴራሊዮን ካሉ አገሮች የተሻለችባቸው መለኪያዎች ቢታዩም ሴቶች ካላቸው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስኮች ተጠቃሚነት አኳያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የተመድ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በጥቂቱም ቢሆን የኢትዮጵያ ሴቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያላቸው ተሳትፎና የፖለቲካ መድረኮች ላይ ያላቸው ውክልና ላይ የተሻለ ውጤት እንደሚታይ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች