Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር መጠን 40 በመቶ ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኩ በብድር አሰጣጡ ላይ ማሻሻያዎች አድርጓል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበሻለ የብድር መጠኑ ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣት፣ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 40 በመቶ መድረሱ ታወቀ፡፡ ባንኩ በብድር ፖሊሲው ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ልማት ባንክ የአምስት ዓመታት የሥራ እንቅስቃሴውንና አሁን በማድረግ ላይ ያለውን ለውጥ አስመልክቶ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች  ዓርብ መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን አሁንም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የባንኩን የተበላሸ የብድር መጠን ከሚያሳየው የአምስት ዓመታት አኃዛዊ  መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው፣ በ2006 ዓ.ም. የተበላሸ የብድር መጠኑ አሥር በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም ከሚለው አንፃር ሲታይ በእጥፍ የጨመረ ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም. 12.5 በመቶ የነበረው የተበላሸ የብድር መጠን በ2008 ዓ.ም. ወደ 17.7 በመቶ አድጓል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተበላሸ የብድር መጠኑ ወደ 25 በመቶ በማሻቀብ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ያመላክታል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ባንኩ ያስመዘገበው የተበላሸ የብድር መጠን በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያልታየ ከፍተኛው መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የተበላሸ ብድር መጠኑ ጨምሮ 39.4 በመቶ ደርሷል፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት ከአገሪቱ ባንኮች የተበላሸ ብድር አኳያ ሲታይ እጅግ የሰፋ ልዩነት አለው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2010 ዓ.ም. አሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች አማካይ የተበላሸ የብድር መጠናቸው ከአምስት በመቶ በታች ነው፡፡ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር 40 በመቶ መድረሱ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ያሳያል፡፡ ይህ መጠን ባንኩ ያበደረውን ገንዘብ ለማስመለስ የገጠመውን ችግር የሚያመላክት ሲሆን፣ አብዛኛው ብድርም ስለመመለሱ አጠራጣሪ መሆኑን ያመላክታል፡፡ የባንኩ ከፍተኛ የተበላሸ የብድር መጠን በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት እያደገ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን፣ ክፍተቱ ከመጥበብ ይልቅ እየጨመረ ለመምጣቱ የባንኩ ሥራ ኃላፊዎች የሚጠቅሷቸው ምክንያቶች አሉ፡፡  

የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እየጨመረ ስለመጣው የተበላሸ የብድር መጠን ዕድገት ካቀረቧቸው ምክንያቶች ውስጥ፣ በዝናብ የሚለሙ ሰፋፊ የግብርና ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ሁኔታ ውጤት አለማሳየታቸው አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ተጨማሪ በአገሪቱ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ጠቁመዋል፡፡ በባንኩ የፋይናንስ ድጋፍ የተደረገላቸው የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ባለመሆናቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻላቸው፣ በወቅቱ ብድራቸውን ለመመለስ አቅቷቸው ለተበላሸ የብድር መጠን የየራሳቸው አስተዋጽኦ ነበራቸው ብለዋል፡፡  

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በሰጡት ማብራሪያ፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በባንኩ ብድር የተቋቋሙ ኩባንያዎች ላይ በፈጠረው ጫና ምክንያት በወቅቱ ብድሩን ለመክፈል እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተሟላ አለመሆን በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳሳደረ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የሠራተኛ ደመወዝ እየከፈሉ ምርት ማምረት አልቻሉም ብለዋል፡፡ አምርተው ለማቅረብ የገቧቸውን ኮንትራቶች በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ማሟላት እንዳልቻሉ፣ በዚህ ምክንያት ፋብሪካዎች ማምረት ከሚጠበቅባቸው አቅም እጅግ በጣም ትንሽ ብቻ የሚጠቀሙ በመሆናቸው ብድር ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ አመልክዋል፡፡

በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር በባንኩ የብድር ድጋፍ የተቋቋሙ በርካታ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ጉዳት ደርሶባቸው ስለነበር፣ የተበላሸ ብድር መጠኑን ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ በየአካባቢው በነበሩ አለመረጋጋቶች የተነሳ ፋብሪካዎች ለረዥም ጊዜ ማምረት የሚያቆሙበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ስለነበር፣  ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከብድር አመላለስ ጋር ክፍተት መፈጠሩን ያመለከቱት አቶ ኃይለየሱስ፣ በነበሩት የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ጥሬ ዕቃና ምርትን ከቦታ ቦታ በሚፈለገው ሁኔታ ለማንቀሳቀስ ችግሮች ነበሩ ብለዋል፡፡ ከባንክ ብድር በወሰዱ አካላት ዘንድ አለመረጋጋቱን እንደ ምክንያት የመጠቀምና ብድር ያለመክፈል አዝማሚያዎች በስፋት ስለመታየታቸውም የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸው፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ጫና አሳድረዋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ብለው ከተሰጡ አብዛኞቹ ብድሮች ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የኢንቨስትመንት ግብዓቶች ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ትልቅ ችግር እንደነበር ያወሱት ኃላፊዎቹ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግር በብድር አመላለሱ ላይ ጫና ፈጥሯል ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ደንበኞች በታሰበው አቅም መሠረት እናመርታለን ብለው ባንኩ ጋር ቀርበው ብድር ባስፈቀዱበት አቅም እያመረቱ አለመሆኑን፣ ይህንንም አብዛኞቹ ደንበኞች የሚያነሱት መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረ ነው፡፡ በእርግጥ በተበዳሪዎቻችን ዘንድም በተወሰነ ደረጃ በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ደረጃውን የጠበቀ የማኔጅመንት ሥርዓት ባለመኖሩ  የምርት የጥራት ደረጃቸው አነስተኛ ነው፡፡ በተለይ ብዙዎቹ የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ሲገቡ በዋናነት ታሳቢ የተደረገው አገር ውስጥ አምርተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢሆንም ይህንን አለመፈጸም እንደ ችግር ተነስቷል፤›› ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድ በታሰበው መጠን መከናወን ላለመቻሉ እንደ ምክንያት እየቀረበ ያለው በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለማግኘትና በጥራት አምርተው ተወዳዳሪ መሆን አለመቻላቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በላይ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ውስጥ ያሉት አምራቾች የአቅርቦት እጥረት በመኖሩ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ አለመሆናቸው ተገልጿል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ተፈትሸውና ምክንያቶቹ ተቀርፈው ወደ ሥራ ሲገቡ ችግሩ ይቀላል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ኃይለየሱስ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ጉዳዩን እንዲህ ቢያቀርቡትም፣ በተለይ ለግብርና የተሰጠው ብድር በአብዛኛው መመለሱ ላይ አጠራጣሪ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለግብርና የተሰጠውን ብድር በተመለከተ በዕለቱ የተሰጠውም ማብራሪያ ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ከተበላሸ ብድር ጋር በተያያዘ እንደ ምክንያት ከቀረቡት ውስጥ በዝናብ የሚለማ ግብርና ፕሮጀክት ላይ የታየው ችግር ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ 471 ለሚሆኑ በዝናብ ለሚለሙ የግብርና ፕሮጀክቶች ብድር ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 177 ወይም 25 በመቶ የሚሆኑት ከባንክ የወሰዱትን ብድር ሙሉ ለሙሉ ለመሬት ማልሚያ መሣሪያዎች፣ ለዘር፣ ለአረምና ለመሳሰሉት ግዥ አውለውታል፡፡ ብድሩ ሥራ ላይ መዋሉ ቢረጋገጥም በቂ የሆነ ምርት ባለማግኘታቸው ወይም አምርተው ገበያ እንዳላገኙ ተጠቁሟል፡፡ ስለዚህ ብድሩን ለመመለስ አልቻሉም ተብሏል፡፡ ነገር ግን የዝናብ ሁኔታም አስተጓጉሎዋቸዋል በሚል ብድሩን ላለመክፈላቸው አሳማኝ ምክንያት አላቸው ለተባሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

ወደ 60 በመቶ የሚሆኑት ተበዳሪዎች ለግብርና ልማት የተሰጣቸውን ብድር በከፊል ሥራ ላይ ማዋላቸውን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሥራ ላይ ያለማዋላቸውን የሚያሳይ ምልከታ የተገኘባቸው ናቸው ብለው፣ እነዚህ በተወሰነ ደረጃ ቢያመርቱም 60 በመቶ ተበዳሪዎች የእርሻ ልማት ችግር አለባቸው በማለት ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ በአጠቃላይ ችግር የታየባቸው የእነዚህ ፕሮጀክቶች 298 መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡  

ሃምሳ ስድስት ፕሮጀክቶች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ለእርሻ የተሰጣቸውን ብድር ሥራ ላይ አለመሆናቸው ሲገልጹም፣ ‹‹እርሻው የለም፣ እንዲገዙ የተፈቀዱላቸው የእርሻ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ የሉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከፊል መሣሪያዎች እርሻው ላይ ተጥለው የተገኙ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍ የተሰጠው ብድር በአንድም በሌላም ምክንያት ለመመለስ አጠራጣሪ መሆኑን ጠቋሚ መሆኑ ይነገራል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ውስጥ ከዚህ ቀደም የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ለሚያካሂዱት ኢንቨስትመንት ከሚያስፈልገው ገንዘብ 30 በመቶውን እንዲያቀርቡ ሲደረግ፣ 70 በመቶው ደግሞ በባንኩ ይሸፈን ነበር፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ መሠረት የእነሱ መዋጮ 50 በመቶ፣ ብድሩ ደግሞ 50 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት የባንኩ ፖሊሲ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የታሰበበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች 25 በመቶ መዋጮ አድርገው 75 በመቶውን በብድር እንዲሸፍኑ ያደርግ የነበረው አሠራር፣ በአዲሱ ማሻሻያ የ15 በመቶ መዋጮ ካደረጉ፣ ቀሪው 85 በመቶ በባንኩ እንዲሸፈን መመቻቸቱ ነው፡፡

በዋስትና ሽፋን ላይ የተደረገ ለውጥ ስለመኖሩም የጠቀሱት አቶ ኃይለየሱስ፣ ከዚህ በኋላ የሚሰጠውን ብድር የሚመጥን ዋስትና ካልቀረበ ብድሩ አይፈቀድም፡፡ ከዚህ ቀደም አብዛኛዎቹ ብድሮች በቂ ዋስትና የማይቀርብባቸው እንደነበሩ ታውቆ የተወሰነ ዕርምጃ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ሲገቡ በውጭ ያሉዋቸውን ማሽነሪዎቻቸውን ነቅለው እንዲያስገቡ ይደረግ የነበረው አሠራርም መሻሻል ተደርጎበታል፡፡ በአዲሱ ማሻሻያ አሮጌ ፋብሪካ ነቅሎ ማስመጣት ስለማይፈቀድ አዲስ ማሽነሪ ይዘው እንዲገቡ ተደንግጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች