ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡30 ሰዓት በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ መሐሙድ ሙዚቃ ቤት በስተጀርባ፣ ከመኖሪያ ቤት የተነሳ እሳት ከፍተኛ አደጋ አስከትሏል፡፡ የአካባቢው ወጣቶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች በመተባበር ለ1፡30 ሰዓት ያህል የቆየውን እሳት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ እሳቱ በመኖሪያ ቤትና በመደብሮች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ አካባቢው የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ እንደመሆኑ፣ በንግድ መደብሮች ውስጥ ችፑድና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች እሳቱን በማባባስ ቃጠሎውን ለመከላከል አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የቦታው ምቹ አለመሆንም የራሱን ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ የአካባቢው ወጣቶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሰባት የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም እሳቱ ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡