Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመስከን ያቃታው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ በሕገ መንግሥታዊነት መነጽር

መስከን ያቃታው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ በሕገ መንግሥታዊነት መነጽር

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውንና ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በአገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በውጭ አገር የነበሩና በአገር ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች አዲስ የሚመሠረቱትንም ጨምሮ የተለያዩ አንድምታ ያላቸው ሁነቶች በመከሰት ላይ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል በራሱ በገዥው ፓርቲ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና በግንባሩ የሚስተዋሉ ለውጦች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩትና አሁን ላይ ፍረጃው የቀረላቸውን ጨምሮ በሌሎች ፓርቲዎች የሚታዩ ለውጦች አሉ፡፡

በዚህ ጽሑፍ በተወሰነ መልኩ ስለፓርቲዎቹና የተወሰኑ ነጥቦችን ከሕግ አንፃር ፍተሻ የሚደረግ ሲሆን፣ በዋናነት ግን የፖለቲካ መብቶችና የፓርቲ ተግባራትን መቃኘትና መጠነኛ ግምገማ ማድረግ ነው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ፓርቲዎች የሚወያዩት ስለዜጎች ፖለቲካዊ መብቶች አከባበርና አተገባበር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዝርዝር ሲተነተኑ በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዋና ግባቸው የዜጎችን ፖለቲካዊ መብቶች በተገቢው ሁኔታ እንዲተገበሩ ማድረግ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ይሁን በሌሎች ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ ዕውቅና ያገኙ በርካታ የፖለቲካ መብቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካዊ መብቶች ደግሞ ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ብቻ ያገኛቸው ስለሆኑ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በመንግሥት ወይም በሌላ አካል ችሮታ የተገኙ አይደለም ማለት ነው፡፡

ከሕገ መንግሥቱ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት የመያዝ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ አባል የመሆን፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ መብቶች ፖለቲካዊ አመለካከትን ወይም ሐሳብንም ጭምር የሚያካትቱ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡ በመያዝ ብቻ ሳይገደብ በነፃነት በመግለጽ ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ከሌላም መቀበል ይችላል፡፡ የያዛቸውን ሐሳቦች ሥራ ላይ ለማዋልም የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ለሐሳቡ ድጋፍ ለማግኘትም ወደ ሕዝብ ለማስረጽም በተለያዩ ሚዲያዎች ማስተላለፍን ጭምሮ ሠልፍና ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እነዚህን ተግባራት በቀላሉ ዕውን ማድረግ ከሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዋነኛው ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ መብቶች ከሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫና ዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነትን ጨምሮ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ጭምር ዋስትና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፖለቲካዊ መብቶች ከፖለቲካዊ ነፃነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ሲሆኑ ሁለተኛው በበኩሉ ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ጋር የተዛመደ ጉዳይ ነው፡፡ ተሳትፎ በበኩሉ ምርኩዙ ወይም መቆሚያው ሥልጣኑ የተገደበ ኃላፊነቱ የታወቀ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነት ያለው መንግሥት መኖርን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት መኖርን ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው መሆንና የሌላን ሰው መብት ማክበር፣ ፍትሐዊነትና ተሳታፊው አካል ለሚያደርጋቸው ተግባራት አንፃራዊ ነፃነት መኖርንም ጭምር ይፈልጋል፡፡ ተሳትፎ፣ እንደ መብት ለሌላ መብት ግብ ማስፈጸሚያነት ብቻ የሚውል ሳይሆን በራሱም ዋጋ ያለው በራሱ ግብ የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ ለተሳትፎ ዋጋ የሚሰጥ መንግሥት ለግለሰብና ለቡድን መብት ጥበቃ ያደርጋል፣ ያከብራል፣ እንዲተገበሩም ያደርጋል፡፡ ፖለቲካዊ መብቶች ሕዝባዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ መሳተፍ የሚያስችሉ መብቶችንም ይመለከታል፡፡ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ዜጎች የማይሳተፉ፣ የሚከለከሉ፣ ከሆነ ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም፡፡  የፖለቲካ መብት ከሚተገበርባቸውም መንገዶች አንዱ በሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ የዜጎች ተሳትፎ መኖር ነው፡፡ ተሳትፎ ከማስፈጸሚያነት ባለፈም በራሱም መብት ስለሆነ ማለት ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ መብቶች ይዞታን በተመለከተ ሁለት ተቋማት አውጥተዋቸው የነበሩትን  ሪፖርት እንመልከት፡፡

በመጀመርያ ‘ፍሪደም ሐውስ’ የተባለው ተቋም ኢትዮጵያን በተመለከተ ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት ወይም ደረጃ  እንውሰድ፡፡ ተቋሙ ፖለቲካዊ መብቶችና ዴሞክራሲ ስላሉበት ሁኔታ በየዓመቱ ለአገሮች ደረጃ ያወጣል፡፡ የሚሰጣቸውም ደረጃዎች በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ነፃ፣ ከፊል ነፃና ነፃ ያልሆኑ አገሮች በማለት ይመድባቸዋል፡፡

ለአገሮቹ ከአንድ እስከ ሰባት ነጥብ በመስጠት አንድ ካገኘ በጣም ነፃ የሆነ ማለት ሲሆን፣ ሰባት ካገኘ ደግሞ ነፃ ባለመሆን ዝቅተኛ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ተቋሙ ለኢትዮጵያ  እ.ኤ.አ. ለ2010 ለፖለቲካዊም ይሁን ለሲቪል መብቶች ይዞታዋ አምስት ነጥብ ሰጥቷታል፡፡ ደረጃዋም “በከፊል ነፃ” የሆነች ብሏታል፡፡ ከ2011 ጀምሮ ግን ሰባት ወይም ስድስት በማግኘት “ነፃ ያልሆነች” አገር አድርጓታል፡፡ ለ2016ም ሰባት ነጥብ ሰጥቷታል ወይም አግኝታለች፡፡ መለኪያ ያደረጋቸው ነጥቦች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ርዕሰ መንግሥቱና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲመረጡ የሕዝብ ተሳትፎ፣ የምርጫ ነፃነት፣ የፓርቲዎች  ለምርጫ ቅስቀሳ እኩል ዕድል መኖርና ምርጫ ማድረግ ብሎም ነፃ ቆጠራ ማከናወን፣ የሕዝብ እንደራሴዎች የእውነት ሥልጣን መሆን፣ ሕዝብ በፓርቲ የመደራጀት መብት መረጋገጥ፣ ጠንካራና ተገዳዳሪ ፓርቲዎች መኖር (ሕዝብን ማሳተፍና ማንቀሳቀስ የቻሉ)፣ የሕዝቡ ከመከላከያ፣ ከፖሊስ፣ ከፀጥታና ደኅንነት ሠራተኞች፣ ከውጭ ኃይል፣ ከጠቅላይ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማትና በጥቂቶች እጅ ሥር ከሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማት ተፅዕኖ ሥር አለመሆን፣ ወይም በሌላ ጉልበተኛ አካላት መዳፍ አለመውደቅ የተለያዩ አናሳ ቡድኖች ያላቸው በራስ ጉዳይ የመወሰን ነፃነት ናቸው፡፡ ተቋሙ ለእነዚህ መለኪያዎች ለኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ነጥብ ከሰጣት በኋላ ያከናወነችውን ምርጫ የይስሙላ እንደሆነ በመውሰድ ምርጫ እንደሌለ ወስዶታል፡፡ የፖለቲካ መብቶችን ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ኢሕአዴግ ለማስተካከል ቃል ከገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ከላይ የጠቀስነው ተቋም በመለኪያነት የወሰዳቸውንም ያካትታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በይፋ ያወጇቸው ናቸው፡፡

ኢኮኖሚክ ኢንተሊጀንስ ዩኒት’ የተባለ መቀመጫውን እንግሊዝ ወዳደረገውና ወደ ሁለተኛው ተቋም ሪፖርት ስንመጣ ደግሞ፣  ተቋሙ የዛሬ ሁለት ዓመት ስለአገሮች የዴሞክራሲ ሁኔታ የሰጠው ደረጃ ከላይ ከተመለከትነው ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ ጥናቱ ካካተታቸው 167 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 125ኛ ደረጃን አግታለች፡፡ ከአሥሩ በተያዘ ነጥብ ለምርጫ ሁኔታና መድበለ ፓርቲነት ዜሮ፣ መንግሥታዊ አሠራር 3.57፣ የፖለቲካ ተሳትፎ 5.56፣ ለፖለቲካ ባህል መዳበር 5.63፣ በአገሪቱ ላለው ነፃነት 3.24 በመስጠት አፋኝ (Authoritarian) የሆነ መንግሥት ያለባት አገር አድርጓታል፡፡ አፋኝ ያላቸው፣ የፖለቲካ ብዙኃነት የሌለበት ወይም የነጠፈበት፣ መንግሥታቱም አምባገነን፣ ለስም ብቻ የዴሞክራሲ ተቋማት ያሉባቸው፣ የሲቪልና የፖለቲካ ነፃነት የሚጣስባቸው፣ ምርጫ ቢኖርም ነፃና ፍትሐዊ ያልሆኑባቸው ሚዲያው በመንግሥት (በገዥ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር) የሆኑባቸው ወይም በጫና ውስጥ የሆኑባቸው፣ ነፃ ዳኝነት የሌለባቸው በማለት ተርጉሟቸዋል፡፡

ከላይ መሥፈርትነት የተወሰዱትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው የፖለቲካ መብቶች ተከበሩ፣ በነፃነት ተተገበሩ ሊባል የሚቻለው፡፡ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ገዥ ፓርቲ በመሆን አገርን የሚያስተዳድረው፡፡ በመቀጠል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዓበይት ተግባራት እናንሳ፡፡

ፓርቲዎች በመርህ ደረጃ መራጮችን ከመንግሥት ጋር ለማገናኘት የሚፈጠሩ ድልድይ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ዕድል ይንቀሳቀሱና ይጠቀሙ ዘንድ የሕግ ከለላና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕጎቹም ሊያሟሏቸው የሚገቧቸው ዝቅተኛ መሥፈርቶችን ወይም የሕጎቹ ግቦች ምን መሆን እንዳለባቸው የተለያዩ መለኪያዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ በዋናነት የሕጎቹን ግቦች በሦስት ማጠቃለል እንደሚቻል የዘርፉ ተመራማሪዎች ይስማማሉ፡፡ እነዚህም ፍትሐዊነት (Equitable)፣ ነፃነት (Free) እና ሚዛናዊነት (Fair) የሚሉ መለኪያዎች ናቸው፡፡ ሕጎቹ እነዚህን መሥፈርት ሲያሟሉ ፓርቲዎቹን ተወዳዳሪዎች ሊያደርጓቸው ይችላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ዓመት የአካባቢ ምርጫዎች ይደረጋል፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ አገር አቀፍና ለክልል ምክር ቤቶች ስለሚደረግ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ የሚሆነው ታይቶ ነው ከምርጫ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ መብቶች ከወትሮው መሻሻላቸውን መመስከር የሚቻለው፡፡

የሆነ ሆኖ የምርጫ ዴሞክራሲ ነፃና ግልጽ የሆኑ ውድድሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ውድድሮቹም አማራጮችን ለማግኘት ይረዳሉ፡፡ አማራጮች የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ተቃራኒ ሐሳቦች/ፖሊሲዎች፣ ተመራጮች፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖርንም ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡም፣ ከእነዚህ መካከል ያሰኘውን ሊመርጥ ይችላል፡፡ የፓርቲዎችን አሠራር የሚቀይሩ ሕጎች ሲኖሩ እነዚህ አማራጮች አይኖሩም ማለት ነው፡፡ አማራጮቹ ከሌሉ ደግሞ ዜጎች ፍላጎቶቻቸውን ማንጠርና መጠየቅ አይችሉም፤ ምርጫዎቻቸውንም አይገልጹም፤ ገዥዎቻቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሥርዓት አይኖርም ማለት ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር አሁን ላይ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ከመብዛቱም እንዲሁም አንድ ብሔርን መሠረት ያደረጉ በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው ሕዝቡ ወደማደናገር ደረጃ መሄዱ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ ነገር ግን ማኅበረሰባዊ ድጋፋቸው በውል የማይታወቁ ወይም ያልለዩ በርካታ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በአጭር አገላለጽ ፓርቲ ማለት ተመሳሳይ ወይም የሚጋሩት የፖለቲካ ሐሳብ ያለቸው ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ሐሳቡ ከፓርቲ አባላቱ (መሥራቾቹ) መንጭቶ ወደ ሕዝብ ለማድረስና ሐሳቡን ሕዝብ እንዲሸምተውና ብሎም በምርጫ ወቅት ድምፅ በማግኘት ለመተግበር የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ከሌላ አቅጣጫ ሊመነጭም ይችላል፡፡ ይኸውም ሕዝቡ የሚያነሳቸው ሆነው እነሱን አንጥሮ በማውጣት ለተፈጻሚነታቸው ለመሥራት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ከፓርቲ ወደ ሕዝብ የሚሄድ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሕዝብ ወደ ፓርቲ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በመሆኑም ፓርቲዎች የራሳቸውን ሐሳብ ወደ ሕዝብ በማቅረብ ደጋፊ ማፍራት ካልሆነም ደግሞ የሕዝቡን ብሶትና ችግር ፈርም ፈርጅም አስይዘው አማራጭ ፖሊሲዎችን በማቅረብ ገዥ ፓርቲ ሲሆኑ እንዲተገበሩ ማድረግ ነው፡፡ ተመሳሳይ የሆነ ርዕዮተ ዓለም የያዙ ፓርቲዎች መብዛት ሕዝቡን ምርጫ ከማሳጣት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ስለሆነም ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ወደተወሰነ (ሁለት ወይም ሦስት) ቁጥር አለመጠቃለላቸው ለፓርቲ የሚወጣ ሀብትን ብቻ ሳይሆን የሚያባክነው መብትንም ጭምር ባክኖና ዝርው ሆኖ እንዲቀር ያደርጋል፡፡

አንድ ብሔርን መሠረት ያደረጉ በርካታ ፓርቲዎችም ሲኖሩ እንዲሁ የዚያን ብሔር ሕዝብ መደነጋገር ውስጥ መክተቱ አይቀርም፡፡ አንድን ብሔርን መሠረት የሚያደርጉ ሁለትና ከዚያ በላይ ፓርቲዎች የሚቋቋሙት (በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ) በአብዛኛው  ብሔሩን በትክክልና በእውነት ለመወከል እንጂ በፖሊሲ ልዩነት የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች በትክክልና በእውነት ለቆሙለት ብሔር ጥቅምና መብት መከበር የሚሠሩ ከሆኑ እንዲሁም የብሔሩ ጥያቄዎችን በተመሳሳይ መልኩ የሚጋሯቸው ከሆነ ከሁለት የበለጠ ፓርቲዎች መኖር የብሔሩን አባላት መደናገር ውስጥ ሊከተው የመቻሉ ዕድል ክፍ ያለ ነው፡፡ በእርግጥ ለአንድ ብሔር ሁለት ቢበዛ ሦስት መኖሩ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ ወደተነሳንበት ስንመለስና ፓርቲዎችን በእኩልነት የሚያዩ መሆን ሕግጋትና አተገባበር የመኖር ጉዳይ የፖለቲካ መብትን ለማስከበር ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ሕጎቹ የሚያዳሉና ልዩነት የሚፈጥሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ፓርቲዎች በሚከተሉት ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ፕሮግራምና መርህ ወዘተ. ምክንያት በማድረግ የሚገድቡ ወይም የሚለያዩ መሆን የለባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ አገሮች ሥራ ላይ የሚያውሏቸው ፓርቲዎች የሚተዳደሩበትን ሕግ በሦስት የሚከፍሏቸው አሉ፡፡ የመጀመርያው ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉ፣ ተቃዋሚዎችንና የተለየ ሐሳብ ያላቸውን የሚያገልሉ፣ አንድ ፓርቲ ብቻ እንዲኖር የሚያደርጉ ‘ሞኖፖሊስቲክ’ ሕጎች ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ በጥቅሉ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብሩ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማያንቀሳቅሱ፣ ገዥ ፓርቲን በተለይም በፓርላማ እንዲጠቀም የሚያስችሉ፣ ተቃዋሚዎች ገንዘብ የሚያገኙበትን የሚከለክልና ሥልጣን ላይ የሆነውን የሚጠቅሙ ሕጎች ደግሞ ሌላው ዓይነት ናቸው፡፡ ሦስተኛው፣ አፋኝና ቀያጅ ሕግ እምብዛም የሌለባቸው፣ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ፓርቲ በእኩልነት የሚወዳደሩበት ሕጎች የሚከተሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ፓርቲዎችን የሚመለከቱ ሕጎችን በመገምገም ከላይ ካሉት ውስጥ ወደየትኛው እንደሚያዘነብሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ ለነገሩ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁት ሕጎችም ፓርቲዎችን የሚመለከቱት ይገኝበታል፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩትንም ይሁን አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡  ብሔርን መሠረት ያደረጉ ብሔር ዘለል የሆኑ በማለት፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረጉት የኢሕአዴግ አባልና አጋር የሆኑት ገዥ ፓርቲዎች እንዲሁም የተወሰኑ ተቃዋሚዎችንም ይጨምራል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሠረት ደግሞ የክልልና የአገር አቀፍ በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ ለነገሩ ምንም እንኳን ሕጉ በአገር አቀፍና በክልል ገለጻቸው እንጂ በወረዳ፣ በዞንና በቀበሌ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም መኖራቸውንም ልብ ይሏል፡፡ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ ደግሞ ገዥ፣ አጋርና ተቃዋሚ በማለት ለሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ አጋሮቹና ተቃዋሚ የሆኑ የብሔር ፓርቲዎች ሲኖሩ ተቃዋሚዎች ደግሞ ብሔር ዘለል (ኅብረ ብሔራዊ) የሆኑ አሉ፡፡ ከላይ በተገለጸውና በሌላም መልኩ ቢሆን የአደረጃጀታቸው ሁኔታ በራሱ ፖለቲካዊ መብቶችን ለመተግበር በጎም አሉታዊም ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው፡፡ የምርጫ ሥርዓቱና የአመራረጥ ሁኔታውም ቢሆን እነዚህን መብቶች ለመተግበርና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የራሳቸው ተፅዕኖ ሊኖራቸው መቻሉ አያጠራጥርም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እንደተገለጸው ሥልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው፡፡

የምርጫ መርሆችን በተመለከተ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 38 ላይ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ሁሉን አቀፍና ሚስጥራዊ መሆን በየጊዜው መካሄድ እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ የምርጫ ሥርዓቱን ደግሞ አንደኛ አላፊ የሚባለውን ሥርዓት (First-Past-The-Post) እንድንከተል በሕገ መንግሥት ተወስኗል፡፡  አንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት መራጩ የፈለገውን ሰው ይመርጣል፡፡ በዛ ያለ ድምፅ ያገኘ ያልፋል፡፡ ፓርላማም ላይ አብላጫ ወንበር ያገኘ አስፈጻሚውን በብቸኛነት ስለሚያደራጅ ብዙ ጊዜ ጥምር መንግሥት አያስፈልገውም፡፡  የፓርቲዎች ፕሮግራምና ርዕዮተ ዓለም በጣም ተራርቆ እየተፈራረቁ ሥልጣን የሚይዙ ከሆነ የቀድሞውን ፓርቲ ፓሊሲዎችና ሕጎች፣ እንዲያም ሲል ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልንና መሻርን ያስከትላል፡፡ ቀድሞ የነበረው ፓርቲ ወደ ሥልጣን ሲመለስ ድጋሚ የመሻርና የማፅደቅ ዥዋዥዌ ውስጥ በመግባት ሕዝብን ማደናገርና ሀብትንም እንዲባክን ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ በተመጣጣኝ ውክልና ተወዳደሪዎች የፓርቲ አባላት ብቻ ሆነው (ግለሰብ በግል አይወዳደርም) መራጮች በአብዛኛው ድምፅ የሚሰጡት ለፓርቲው ነው፡፡ ምርጫው ለማዕካለዊው መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሆነ፣ መራጮች የሰጡት ድምፅ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተደመረ በኋላ ፓርቲዎች ባገኙት ምጣኔ/ፐርሰንት ልክ፣ ብዙ የድምፅ ብክነት ሳይኖር፣ ወደ ፓርላማ ይገባሉ፡፡ ሕጎችና ፖሊሲዎች በሚፀድቁበት ጊዜ አብላጫ ድምፅ በቀላሉ ማግኘት ስለሚያስቸግረው ጥልቅ ውይይት እየተካሄደ መተማመንና መግባባት ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡ አለበለዚያ ሕጎች ላይፀድቁ ይችላሉ፡፡ በተመጣጣኝ ውክልና ግን በዚህ ምሳሌ እንዳየነው ኢሕአዴግ መቼም ቢሆን ሁሉንም ወንበር መውሰድ አይችልም፡፡ ጥምር መንግሥት መመሥረት አለበት፡፡ ሚኒስትሮችንም ከየፓርቲዎቹ ማካተት አለበት፡፡

ስለሆነም ፓርላማም ላይ ሕግን ለማፅደቅ ጥልቅ ውይይት ማድረግና ማሳመንን ይጠይቃል፡፡ ውይይትንና ቀናነትን በእጅጉ ያበረታታል፡፡ ተቀራራቢ ርዕዮተ ዓለም እንዲኖርና አገራዊ መግባባት እንዲፈጠርም ይረዳል፡፡ ድምፅም አይባክንም፡፡ የአሸናፊ ፓርቲንም በሕዝብና በተሸናፊ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖር ያበረታታል፡፡ አናሳዎች ከሕዝብ ተወካዮችና ከካቢኔም አይገለሉም፡፡ በተለይ ደግሞ ለዝርው (ተበታትነው ለሚኖሩ) ብሔረሰቦች ድምፃቸው ባክኖ እንዳይቀርና እንዲሰበሰብ ብሎም ዋጋ እንዲኖረው ይረዳል፡፡ የምርጫ ሥርዓቱ ፓርቲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን የዜጎች መብትን ሊያቀጭጭ የሚችልበት ሁኔታ አለ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የዜጎችን የፖለቲካ መብት የሚያሰፋና የሚያስጠብቅ የምርጫ ሥርዓትን ማስፈን ግድ ነው፡፡ ከላይ በጥቅሉ ስለፖለቲካ መብት፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፖለቲካ መብት ይዞታ ምን ይመስል እንደነበር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናና ተግባር ምን እንደሆነ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፉ ምን እንደሚመስል ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪም ኅብረ ብሔራዊ ሆነው ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው አንድ ብሔርንም መሠረት ያደረጉ በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው የፖለቲካ መብትን በአግባቡ ለመጠቀም ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ፍንጮች ቀርበዋል፡፡

ይህ ጽሑፍ በመግቢያው ላይ ለቀረቡት ሁለት ወሳኝ ጥያቄዎች መንደርደሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ቢያንስ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሚያደርጓቸውን ጉባዔዎች ማጠናቀቃቸውንና ውሳኔዎቻቸውን በመንተራስ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንዱ አላባውያን የሆነውን የዴሞክራሲ ማዕከላዊነትና ሕገ መንግሥቱ እንዲሁም በግንባር በአባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ሕጉን ምርኩዝ አድርገን እንመለስበታለን፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...