Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሰንደቅ ዓላማና የሌሎች ምልክቶች አገላለጽና አጠቃቀም

የሰንደቅ ዓላማና የሌሎች ምልክቶች አገላለጽና አጠቃቀም

ቀን:

በአረጋ ይርዳው (ዶ/ር)

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ወይም ሳምንት በመስከረም ወር እንዲኖር መደረጉና ሕዝቡ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ እንዲሰባሰብ፣ ኅብረቱንና አንድነቱን እንዲያጠናክር ማድረግ እጅግ በጣም የሚደገፍ ድርጊት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በሰንደቅ ዓላማም ሆነ በተለያዩ ሌላ ምልክቶች (Symbols) ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥፋት፣ በጉዳዩ ላይ በመመካከርና አዎንታዊና ምክንያታዊ አካሄድን በመጠቀም መግባባትን ወደሚያጠናክር ሒደት ውስጥ መግባት እጅግ አስፈላጊና ወቅታዊም ነው፡፡ ስለሆነም በምልክቶች (Symbols) ዙሪያ የሚከተለውን ሳቀርብ በመጠኑም ቢሆን ስለጉዳዩ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው በትዝታ ወደ ኋላ በመሄድ እንዲያስታውሱ፣ በጉዳዩ ላይ ብዙም ያላሰቡበት የተሻለ ማስረጃ እንዲራኖቸው በማሰብ ነው፡፡ ይህን እንዳደርግ ያነሳሳኝ የኃላፊነት ስሜት ሲሆን፣ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያደናግሩ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው አገላለጾችና አካሄዶችን ስለተመለከትኩ ነው፡፡

ምልክት (Symbol) አንድን ነገር ወክሎ ለተመልካቹ ስለወከለው ነገር ማብራራት፣ መግለጽ የሚያስችል ቁመና ወይም ይዘት ያለው ልዩ ሰው ሠራሽ የሰው ልጆች መገልገያ ነው፡፡ ምልክቶች ለተለያዩ ይዘቶች በመለያነት የሚያገለግሉ እንደ መሆናቸው መጠን የተለያየ ይዘት፣ ስም፣ ቅርፅ፣ ወዘተ. አላቸው፡፡ ስለሆነም ለመለያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ምልክቶችን ለአገር፣ ለመንግሥት፣ ለመከላከያ፣ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለማኅበራት፣ ለኅብረተሰብና ለግለሰቦች ወዘተ. በመላው ዓለም በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጎ ለብዙ ዘመን ለመግባቢያነት ስንጠቀምባቸው ኖረናልና አሁንም እየተጠቀምንባቸው ነው፡፡

ምልክት ነክ ጉዳዮች እጅግ በጣም ሰፊ እንደ መሆናቸው መጠን ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ ብቻ ይመጥናሉ ባልኳቸው ወቅታዊ ምልክቶች ላይ ብቻ ማተኮር እወዳለሁ፡፡ ስለሆነም ምልክቶችን በሚከተሉት ሦስት ክፍሎች (Categories) መድቦ መመልከት ይጠቅማል፡፡

ምድብ አንድ

በብሔራዊ ደረጃ ለጥቅም የሚውል ለአንድ አገር በአገር ደረጃ በምልክትነት የሚያገለግል ሆኖ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ይህም በእያንዳንዱ አገር ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በዲዛይኑ፣ በተለያዩ የታሪክ አመጣጡ፣ የገላጭነት ይዘቱ፣ የዘመናዊት ይዘቱና የወካይነት ይዘቱ፣ ወዘተ. በውስጡ አካቶ በጥንቃቄ የተሠራና ተቀባይነቱ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠለት የአገር መገለጫ ነው፡፡

ለምሳሌ የ‹‹UK›› ሰንደቅ ዓላማ የተለያዩ የእንግሊዝ አገር ክፍሎችን ማለትም ‹‹መስቀል›› ኢንግላንድ፣ ‹‹አግዳሚ መስመሮች›› ስኮትላንድና አየርላንድ ከተባሉት የ‹‹UK›› ልዩ የግዛት ክፍሎች በማጣመር የተቀነባበረ ዲዛይን ያለው ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡

የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ አሁን ባለበት ሁኔታ ስንመለከተው 50 ‹‹ሰማያዊ ክዋክብት›› እና 13 ነጭና ቀይ ‹‹አግዳሚ መስመሮች›› ያሉበት ነው፡፡ ይህም በአጭሩ ሲገለጽ ከዋክብቱ በአሁኑ ጊዜ  ‹‹United States›› የምንላቸው 50 የአሜሪካ የግዛት ክፍሎች (States) የሚገለጽ ሲሆን፣ 13 ቀይና ነጭ አግዳሚ መስመሮች የሚያመለክቱት ለመጀመርያ ጊዜ በአባልነት (USA)ን የፈጠሩትን 13 የግዛት ክፍሎችን የሚገልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የሚደንቀው እ.ኤ.አ. በ1777 የነበረው ሰንደቅ ዓላማቸው 13 ከዋክብትና 13 መስመሮች ብቻ ነበሩት፡፡ በዚህም ለ18 ዓመታት ተጠቅመውበታል፡፡ ቬርሞንትና ኬንተኪ ወደ ኅብረቱ ሲቀላቀሉ የከዋክብቱ ቁጥር ወደ 15 ከፍ እንዲል ተደረገና አግዳሚ መስመሮቹ ግን ባሉበት 13 እንዲሆኑ ተደርጎ፣ ለተጨማሪ 23 ዓመታት ሰንደቅ ዓላማው አገለገለ፡፡

በቀጣይ ይህንኑ ሰንደቅ ዓላማ ሕጋዊ የማሻሻል ዘዴን በመጠቀም እ.ኤ.አ. ከ1777 እስከ 1960 ድረስ የአገሪቱ ክፍሎች ብዛት እየጨመረ ስለመጣ፣ በእነዚህ 83 ዓመታት ሰንደቅ ዓላማው ከነበሩት 13 ከዋክብት 50 ከዋክብት እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ‹‹ሀዋይ›› 50ኛው ኮከብ እንዲጨመር ምክንያት የሆነችው የመጨረሻዋ ግዛት ነች፡፡ ከ1960 ዓ.ም. እስካሁን ድረስ ባሉት 58 ዓመታት ሰንደቅ ዓላማው ይህንኑ ከላይ የተጠቀሰውን ቅርፅ እንደያዘ ይገኛል፡፡ በቀጣይ የሚቀላቀሉ ግዛቶች ሲኖሩ ቁጥሩ እንደሚለወጥ ግልጽ ነው፡፡ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ እ.ኤ.አ ከ1777 እስከ 2018 ድረስ ባሉት 241 ዓመታት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም (ዶ/ር) በቅርብ ጊዜ በሚዲያ እንደገለጹት፣ ለ15 ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ አለዋወጡም ከላይ በተገለጸው መንገድ ኮከብ በመጨመር ሲሆን፣ 13ቱን አካዴሚ ጥንታዊ የመሥራች ግዛቶች መገለጫዎችን ቁጥር ባለበት በመያዝ፣ ይህ ዓይነቱ የአገር መለያ ሰንደቅ ዓላማ ስለስፋቱ፣ ቅርፁ፣ አጠቃቀሙ፣ አሰቃቀሉና አወራረዱ በአጠቃላይ ስለልዩ ልዩ ይዞታው የአሜሪካ ሕጎችና ደንቦች በሚገባ ገልጸውታል፡፡ ሕጉን በሥራ ላይ የማዋልና የመቆጣጠር አስፈላጊው ሒደትም ይደረግበታል፡፡

ምድብ ሁለት

በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ግዛቶች/ክፍሎች ምልክቶች ሰንደቅ ዓላማዎች ናቸው፡፡ እነዚህም አግባብ ባለው ሕግ የታቀፉና ከላይ በምድብ አንድ ከተገለጹት ጋር የሚመሳሰሉ፣ ግን በአገር ደረጃ ሳይሆን በክፍለ አገር (ክልል) ደረጃ በሥራ ላይ የሚውሉ ሕጋዊ ምልክቶች ናቸው፡፡

ለምሳሌ የ‹‹UK››ን ብንመለከት ኢንግላንድ፣ ስኮትላንድና አየርላንድ የተለያየ የክፍላቸው/የግዛታቸው መለያ ሰንደቅ ዓላማዎች አሏቸው፡፡ በአሜሪካ 50ዎቹም ልዩ ግዛቶች/ክፍሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ካሊፎርኒያ (California) ግዛት/ክልል እ.ኤ.አ. ከ1911 ጀምሮ የሚጠቀምበት አንድ የእንስሳ ምልክትና አንድ ኮከብ ያለበትና (California Republic) የሚል ጽሑፍን ያካተተ መለያ አለው፡፡ ቴክሳስን ስንመለከት ባለ አንድ ኮከብና ሦስት የተለያየ ቀለማት ያላቸው መደቦች ያሉት ሰንደቅ ዓላማ እ.ኤ.አ. ከ1839 ጀምሮ ይጠቀማል፡፡

ከ50 ግዛቶች ውስጥ ያልተካተተችውና የአሜሪካ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና ከተማ የሆነችው ዋሽንግተን ዲሲ (DC = District of Columbia) የራሷ መለያ አላት፡፡ ከዚህ ሌላ በአሜሪካ አገዛዝና ኬላ ሥር ያሉት እነ ጉዋም የመሳሰሉትም በ‹‹Territory›› ነት የሚተዳደሩና ከአሜሪካ ልዩ ግንኙነት ያላቸው ስለሆነ ልዩ መለያ አላቸው፡፡ ወደ ‹‹USA›› የሚደባለቁ ቢሆን፣ የ50 ከዋከብት ጉዳይ ለተውጦ ቁጥሩ ተጨምሮ የአገሪቱ አካል ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

ከላይ በምድብ አንድና ሁለት የሚገኙት ሰንደቅ ዓላማዎች ለመንግሥታዊ አሠራር በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ እንደ መሆናቸው መጠን፣ አገላለጻችን ሰንደቅ ዓላማ በሚል መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከሌሎች የድርጅት፣ የፓርቲ፣ ወዘተ. ምልክቶች ጋር መደበላለቅ እንዳይፈጠር በእጅጉ ይረዳል፡፡

ሁለቱም አገራዊና ክልላዊ (ክፍለ አገር) የሰንደቅ ዓላማዎች አያያዝ፣ አሰቃቀልና አጠቃቀምን በሚመለከት በከፍተኛ ሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አገር አቀፋዊ ሰንደቅ ዓላማ (Flag) እና የክፍለ አገር (ክልል) ሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀላቸው ከመሬት ወደ ላይ በእኩል ከፍታ መሆን የለበትም፡፡ ሲሰቀሉና ሲወርዱም የአገር አቀፉ ሰንደቅ ዓላማ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ በአንፃራዊነት የክፍለ አገር ሰንደቅ ዓላማ ከአገራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይሰቀላል፡፡ አንድን አገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በመሳሰሉ ተቋማት አገርን በመወከል የሚሰቀለው፣ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ (National Flag) ብቻ ነው፡፡

ምድብ ሦስት

በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማት (ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ወዘተ.) የሚጠቀሙባቸው ምልክቶች ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆኑ ዓርማዎች ወይም በተለምዶ (Logo) የምንላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም በየአገሩ በወጣ ምልክት የማስፈቀድ ሕግና አሠራር የተፈቀዱ ሕጋዊ ዓርማዎች መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን ከሰንደቅ ዓላማ ጋር አደባልቆ ማየት አስፈላጊ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ስህተትም ነው፡፡

ለምሳሌ በአሜሪካ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የራሱ የሆነ መለያ አለው፡፡ በአገረ አሜሪካ የታወቁት ሁለቱ ታላላቅ ፓርቲዎች ማለትም ‹‹የሪፐብሊካን›› እና ‹‹የዴሞክራት›› ፓርቲዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው የ‹‹ዝሆን›› እና የ‹‹አህያ› ምሥሎችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህን ምልክቶች በመጠቀም የፓርቲ ኮንቬንሽን ያዘጋጃሉ፣ የደጋፊዎቻቸውን ቁጥር ያጠናክራሉ፡፡ ልዩነታቸውን በሚገባ በኅብረተሰቡ እንዲታወቅ ያደርጋሉ፡፡ ወደ ንግድ ዓለም ስንገባም አፕል ኮምፒዩተር፣ ማይክሮ ሶፍት፣  ሳምሰንግ፣ ቦይንግ፣ ወዘተ. ልዩ ልዩ ዓርማዎችን በመጠቀም ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ያስፋፋሉ፣ ያጠናክራሉ፡፡ በስፖርቱ ዓለምም የስፖርት ክለቦች የራሳቸው መለያና ዓርማ አላቸው፡፡ የማልያቸው ቀለምና ዲዛይን ቢለወጥም ዓርማቸው አይለወጥም፡፡ በዚህ ምድብ ሦስት የተገለጹት ዓርማዎች በምንም ዓይነት ሁኔታ በምድብ አንድና ሁለት ከተገለጹት ሰንደቅ ዓላማዎች ጋር የሚቀያየሩበትና የሚደባለቁበት መንገድ ሊኖር አይገባም፡፡ በሕጋዊ አቋማቸውም እንኳ የተለያየ ይዘት ነው ያላቸው፡፡ አጠቃቀማቸውም ለየቅል ነው፡፡

ምድብ አራት

ልዩ ልዩ ምልክቶች፣ እነዚህ ምልክቶች ከላይ ከምድብ ሦስት ጋር የተቀራረቡ ቢሆንም ከብዛታቸው አኳያ ጠቅለል አድርጎ ማየቱ ይጠቅማል፡፡ የመኪና ሕጋዊ መታወቂያዎች፣ የሠራተኛ መለያ (ID/Badges)፣ የመንገድ የትራፊክ ምልክቶች፣ ማኅተሞች፣ ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ሕጋዊ ማዕቀፍ ያላቸው ናቸው፡፡

ወቅታዊ የአገራችን የምልክት ይዘቶች

ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ ስንመለከስ በምድብ አንድ የሚመደበው በሕገ መንግሥቱ/በአዋጅ የተፈቀደ የአገሪቱ መለያ የሆነው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ አግዳሚ መስመሮችና ሰማያዊ ኮከብ በመሀሉ ላይ ያለው ነው፡፡ ይህ ሰንደቅ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ በሕግ እስካልተለወጠ ድረስ ብቸኛው ሕጋዊ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ከላይ በአሜሪካ ምሳሌ እንዳየነው አስፈላጊ ሲሆን ሕዝቦች ሰንደቅ ዓላማቸውን ሕጋዊ ሒደቱን ተከትለው መለወጥና ማሻሻል የተለመደ አሠራር ነው፡፡

በምድብ ሁለት የሚገኙት የክልል ሰንደቅ ዓላማዎችም እንደ ብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ በሕጋዊ መልኩ ተይዘው እየተሻሻሉ የሚቀጥሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በብሔራዊውና በክልል ሰንደቅ ዓላማዎች መካከል ያለውን አሠላለፍና አያያዝ በሚመለከት ግልጽ የሆነ ሕጋዊ መመርያ ሊኖር ይገባል፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና የካሊፎርኒያ ሰንደቅ ዓላማ በአንድ ላይ ጎን ለጎን የሚውለበለቡ ቢሆን ስለአቀማመጣቸው፣ ስለከፍታቸው፣ ወዘተ. ግልጽ የሆነ ሕጋዊ መመርያ አለ፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር አስፈላጊ ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

በምድብ ሦስት የሚገኙት ዓርማዎችን በሚመለከት ለምሳሌ ያህል ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የትምህርት ሚኒስቴርን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ዓርማዎች መመልከት ይቻላል፡፡ ከፓርቲዎችም በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት አባል ድርጅቶች፣ ከዚያም ውጭ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ የየራሳቸው ዓርማ እንዳላቸው እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ዓርማዎች ከምድብ አንድና ሁለት ካሉት ብሔራዊና ክልላዊ ሰንደቅ ዓላማዎች ፍፁም የተለዩ ናቸው፡፡

በፓርቲ ስብሰባና በዓል ጊዜ ከፓርቲ ዓርማ በተጨማሪ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖር ማድረግ በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ፓርቲው በሰንደቅ ዓላማው በተወከለችው አገር ውስጥ መሆኑን ያመላክታልና፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ የሰንደቅ ዓላማ በዓል ሲኖር ከፍተኛ ትኩረት ስለአገር አንድነትና ኅብረት ለመዘከር ስለሆነ፣ የአገርና የክፍለ አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎችን ተጠቅሞ በዓሉን ማክበር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የአንድ ፓርቲ ስብሰባ ሲደረግ የፓርቲ ዓርማዎች ይዞ ማክበር የፓርቲ ተከታዮችን ከማጠናከር አኳያ ጥቅሙ የበለጠ ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ወቅት ከሰንደቅ ዓላማ ውጪ ሌላ ዓርማ ወይም ምልክት ይዘው አያክብሩ ማለት አይደለም፡፡ ሐሳብና ደስታን በተለያየ መንገድ በሰላም መግለጽ ልዩ የሰው ልጅ መብት ሊሆን ይገባልና፡፡

በመጨረሻም ከልዩ ልዩ ምልክቶች ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስና የቡና የእግር ኳስ ክለቦች፣ ወዘተ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች፣ ወዘተ. ሕጋዊ ምልክቶች አሏቸው፡፡ ሠራተኞችም የሠራተኛ መታወቂያ በየመሥሪያ ቤቱ በብዛት እንዳላቸውና በምልክትነት እንደሚጠቀሙባቸው እናውቃለን፡፡

ይህ ጽሑፍ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚጨመሩ ምስሎች (Emblems, Signs) የመሳሰሉትን አለማካተቱን ልብ ይሏል፡፡

ለማጠቃለል ያህል በምልክቶች ዘሪያ ያለውን ልዩነት ከግንዛቤ በማስገባት፣ በመረጃ የተደገፉ አስተሳሰቦችን በማጠናከር፣ አላስፈላጊ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ ማድረግና ግልጽ የሆነ መመርያ አዘጋጅቶ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ዘላቂነት ያለው አካሄድ መከተል ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ ቀላል መሳይ ሁኔታዎች ከባድ የቤት ሥራ እንዳይሆኑ ጥርት ያለ መንገድ ይዘን የሰንደቅ ዓላማችንን በዓል በሰላምና በደስታ እንድናከብር ፈጣሪ ይርዳን፡፡ መልካም የሰንደቅ ዓላማ ቀን ይሁንልን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...