Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየፖሊስ ያለህ አንልም ወይ?

የፖሊስ ያለህ አንልም ወይ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የ2010 ዓ.ም. መሰናበቻና የአዲሱ ዓመት መባቻ ሦስት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር ሁከቶችና ብጥብጦች በየመንገዱና በየመንደሩ የተዘረገፉበት፣ በዚህም ምክንያት ሕይወት በሰው እጅ የጠፋበት፣ ፖሊስም እንደ ወትሮውና እንደ ልማዱ ሠልፈኛ የገደለበት፣ እዚሁ መናገሻ ከተማው ውስጥ ሰው በገዛ አገሩ በገፍና በግፍ የተሰደደበት፣ አደጋ መከላከል ቀርቶ መልሶ ማቋቋም እንኳን በአገር የዝግጁነት አቅምና ተቋም ላይ ያፈረበት፣ የተሳለቀበት፣ እንደ ድሬዳዋና ሐዋሳ ባሉ ከተሞች ውስጥ በዘመናት ውስጥ የተገነባ ማኅበራዊ ድርና ማጋችንን የሚያናጋ ሥጋት፣ ፍርኃትና ሽብር የተሰማበት፣ ወዘተ ወቅት ነበር፡፡ ለዓይነትና ለአብነት የተጠቀሰውን የመላው ኢትዮጵያ ‹‹ኑሮ›› የሆነውን ይህን ጉዳትና የአገር ሕመም ልዩ የሚያደርገው አዲስ አበባ መግባቱ፣ አዲስ አበባን መክበቡ አይደለም፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሚመራው መንግሥት ዙሪያ ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ ድጋፍ በተሰባሰበበት፣ ወደ ስደትና ወደ ጫካ የሄዱ ፖለቲከኞችና ‹‹አክቲቪስቶች›› ወደ አገር በገቡበት፣ ከሕገወጡ ይልቅና ይበልጥ ሕጋዊና ሰላማዊው የትግል መንገድ ተመራጭና ቀላል ሆነ ተብሎ በታወጀበትና የሁሉም አዲስ ገቢ ‹‹እንግዳ›› ቢያንስ ቢያንስ የአንደበት ወግ በሆነበት ወቅት ነው፡፡

በጣም የሚያሳዝነው ግን የደም መቀባትና የመፈናቀል፣ የመጋጨት፣ ባይተዋር ተደርጎ የመንጓለል መከራችን በዚሁ በቃችሁ አልል ያለን፣ አሸልበውም ሆነ አድብተው አጋጣሚ የሚጠብቁ ወይም ለመፍጠር የሚሞክሩ፣ የጋራ በሆነ ሕግና ሰላም የማስከበርና ዴሞክራሲን የመገንባት የአገርና የጋራ አደራ ላይ ከመገናኘት ይልቅ፣ ውጥንቅጥ አቋም ያላቸው ከውጭ የገቡ/እየገቡ ያሉ ቡድኖች የተከፋፈለ ብዙ ልብ መፍጠራቸውና የሁሉም ልብ አንድ የሰላማዊ መንገድ ላይ መገናኘት አለመቻላቸው፣ ትግላቸውና ትንቅንቃቸው ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና ውስጥ የገባውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የአዲሱ ዓመት ዋዜማና ማግሥት የዘረገፈውን ሁከትና ብጥብጥ የወለደውም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የተሸፋፈኑ አለመስማማቶች፣ እዚህ አለመስማማታቸው ውስጥ የሚተናነቃቸውን ኢዴሞክራሲያዊነት ማራገፍ አለመቻላቸው ነው፡፡ ፓርቲዎቹ /ድርጅቶቹ የፖለቲካ  መስመሮቻቸውን በግልም ሳያጠሩ፣ በጋራም ሳያቀራርቡና እንደተባለውም ከኢዴሞክራሲያዊነታቸው ሳይገላገሉ፣ ከተጠራጣሪነት፣ ከመሰሪ ሥሌትና ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት ሳይላቀቁ፣ እንዲሁም የአገሪቱ መላ ሕዝቦች የተያያዙበት ጠንካራ ትብብር ሳያበጁ፣ የድሮ ሥርዓት ሊመልሱ፣ የብሔር ብጥብጥ ሊያመጡ ነው የሚል ፍርኃት የሚያስወግድ፣ በድሮ ሥርዓት ናፋቂነት የማያሳማ የፖለቲካ ጥራትና ብልጫ የሚያስመዘግብ አቀራረብ ሳያሳዩ፣ በድሮው በጫካ መንገዳቸው ውረድ እንውረድ መባባላቸውና እንደዚያ በመረማመዳቸው ነው፡፡

የገዥው ፓርቲና የመንግሥትም ከለውጥ ጅምሩ ጋር የሚጣጣም፣ ለውጡን መሸከምና ማራመድ የሚችል የባህሪይና የአሠራር ለውጥ አለማድረግም የአገሪቱን የፖለቲካ ሰላም ፈተናና መከራ ከድጡ ወደ ማጡ እያንሸራተተና እያዳፋ ለውጡን ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ገና እዚያው፣ ‹‹መንታ መንገድ›› ውስጥ (‹‹በመንታ መንገድ ላይ ከመሆናችን ይልቅ ከመንታ መንገድ መውጣት እንደ ጀመርንና እንደምንችል የሚያመላክቱ ነገሮች የሚበዙ እንደሆነ አስተዋልኩ›› የሚለውን የቅርቡን የአቶ በረከት ስምዖንን መጽሐፍ ርዕስ የቃላት አጠቃቀም ይመለከቷል) መቀርቀሩን እየመረቀና እያባባሰው ነው፡፡

በተለይም የመንግሥት ሕገወጥነትን ለመግታት፣ ሕግ ለማስከበር፣ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች የራሱንም የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ ማስገመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምስት፣ ስድስት ወራት ድንገት የተገኘውንና የለውጡም ወሳኝ እርሾ ሆኖ የሚያገለግለውን የሕዝብ ድጋፍና መታመን ለአደጋ አጋልጦታል፡፡ የመንግሥት ተቋማት፣ የሕግ አስፈጻሚ/አስተግባሪ አካላት፣ በተለይም በዚህ ሁኔታዎች በተለዋወጡበት፣ የሕጎችን አፈጻጸም የሚያሰናክሉ፣ የሚከለክሉ፣ የሚያጨናግፉ አፋኝና ጨቋኝ ሁኔታዎች መላላትና መነቃነቅ በጀመሩበት፣ ከሕግ በላይ መሆንን፣ በሕዝብ ላይ መዘባነንና መደንፋትን የአገዛዙ ዋልታና ማገር ያደረጉ ድባቦች እየገፈፉ መሄድ በጀመሩበት፣ የተዘነጉ፣ ኮማ ውስጥ የገቡ፣ ከዚያም ሲብስ በአሳቻ መንገድ የመተርጎም ጥቃት የደረሰባቸው ሕጎች መታወስ በጀመሩበት፣ ወዘተ በዚህ ወቅት መንግሥት ለውጡ በጋበዛቸው ‹‹እንግዶች›› አቀባበል ሒደት ውስጥ ሕገወጥነትን በመታገስ ያሳየውን ጥፋትና ቸልተኝነት፣ በመስከረም ወር ሁለተኛ ሳምንት መጨረሻ ላይ የፖሊስ አፈሳ፣ የጅምላ እስርና የ‹‹ህንፀት›› ዕርምጃ ‹‹አካክሳለሁ›› ማለት አልነበረበትም፡፡ ሁለቱም፣ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው፡፡

ማሳየትና ማስረዳት የምንፈልገውን ነገር በሙሉ መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ፖሊስ በሰጠው የጋዜጣዊ መግለጫ ውስጥና ከእሱም ጋር አዛምዶ መዘርዘርና ማስተንተን ይቻላል፡፡

መጀመርያ የአዲስ አበባ ፖሊስ (በአቋቋመው ሕግ ትክክለኛ ይፋዊ ስሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን) የኮሚሽኑን ሥራ በበላይነት በሚመራው ኃላፊው አማካይነት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው አገር እንደ ወትሮው፣ እንደ ጥንቱ፣ እንደ አባቶቻችንና አያቶቻችን በሹክሹክታና በአሉባልታ የገለማ ‹‹ግንዛቤ››ውንና ‹‹ንቃቱ››ን ይዞ ስለአፈሳ፣ አሰሳ፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ ቅልበሳ፣ ሴራ፣ ወዘተ መወራት መቆሚያ መቀመጫ ካሳጣው በኋላ ነው፡፡ በርካታ በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጉላሉ ጥያቄዎችን ለዘመናዊው የፌስቡክ ሹክሹክታና አሉባልታ መተውና አደራውንም ለእነሱ መስጠት ነጋ ጠባ የሚያሳብቡበትን፣ የሚያላክኩበትን የመከረኛውን የማኅበራዊው ሚዲያ ‹‹እኩይ›› መድረክነት መመረቅ ብቻ አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ የጠራና የነጠረ መረጃ እንዳይሰጡ ማድረግና ማስፈራራት ጭምር ነው፡፡ ዴሞክራሲንም፣ የሕግ መከበርንም፣ የሕዝብ መረጃ የማግኘት መብትም እንደተለመደውና እንደ ወትሮው እየጎዱ፣ እያደሙ መኖሩን ከመቀጠል ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የመንግሥት ግዴታ ውዥንብርን ይጋፋል፡፡ የለውጡን ደጋፊዎች እምነት ከመሸርሸር አደጋ ይጠብቃል፡፡ ውጤታማ ኮሙዩኒኬሽን ማለት ራሱ ውጤታማና መልካም አስተዳደር ማለት ጭምር ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት ዝምታና ዝንጋታ፣ እንዲሁም ቸልተኝነት ያገዘውን ውዥንብር ማጥራት፣ በሕዝብ ውስጥ መታመንን ያገኘ መረጃ መስጠት፣ ለውጡን የማምከን ጥረቶችን ለማርከስ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በተለይም በወሰንም ሆነ በብሔር መብት ስም ወይም በባንዲራ ፍቅርና ሕግ ሰበብ ግጭት የማነሳሳት የማፈናቀል፣ ንብረት የማውደም ተግባርን አስቀድሞ መከላከል፣ መከልከል ሳይቻል ቀርቶ ሲያፈተልክም በቶሎ ማስቆምና ጥፋተኞችን ያለ ማወላወል በሕግ መጠየቅ ተግባርን ሁሉም የተቀበለው፣ ማለትም አፀፋዊ ፕሮፓጋንዳ የማይሠራበት ማድረግ ለውጡ የሚጠይቀው ዋነኛ ተግባርና ግዳጅ ነው፡፡

በስድስቱ የለውጥ ወራት ውስጥ ደጋግመን የምንመሰክራቸው መንግሥታዊ ዝግጁነቶችና ዕርምጃዎች የሚያሳዩን ግን ትልቁ ጉድለት፣ ለውጡን የሚጎዳው ታላቁ መሰናክል ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ቀደም ሲል የተጠቃቀሱ ‹‹ያላዋቂ አስተናናቂ››ነት ጋር ተጋግዞ፣ በመንግሥት ላይ የሚታየው ሕገወጥነትን የመግታት ሕገወጥ ዕርምጃና አረማመድ ነው፡፡ ከሕግ በላይ ሆኖ ሕግ አስከብራለሁ ባይነት ነው፡፡

የዚህ አንደኛው ማሳያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውስጥ ሰማናቸው ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱበትን የገዥዎች ተግባር ዛሬም በፅናት መዋጋት፣ ዛሬም የማይደፈር አስፈሪ ነገር መሆኑን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ዛሬም የአዲስ አበባ ፖሊስን የመሰለ የሕግ አስፈጻሚ አካል የመንግሥት የሕግ አስተግባሪነት (Law Enforcement) ሥራን ነባራዊ አስገዳጅነት መለኪያና የውኃ ልክ የሌለው የቢሻን ውሳኔ አድርጎ ሲያቀርበው ዓይተናል፡፡ በዚያ ላይ የሚገርመው ያን ያህል የጋዜጠኞች ዓይንና ጆሮ ያስተጋባው ይህ ጉዳይ የሚገባውን ያህል ንግግርና ውይይት አቀጣጥሎ አለማየታችን ነው፡፡

በጀመርነው ጉዳይ ለመቀጠል ምላሽ የሚገባው፣ ለጠቅላላ ዕውቀት ተብሎ ሳይሆን ሕግ የማስከበር ሕገወጥነትን የመግታት የፀጥታ አስከባሪዎችን የራሳቸውን በሕግ ውስጥ ሆኖ የመሥራትና ለሕግ የመገዛት ግዴታ ለማረጋገጥ የሚያግዝ ጥያቄ ላንሳ! ጥያቄው በመጀመርያ ዕይታው የአላዋቂ ሳሚ ሊመስል ቢችልም ለመሆኑ ብርጋዴር ጄኔራል፣ ሜጀር ጄኔራል፣ ሌተና ጄኔራል ወይም (ሙሉ) ጄኔራል ብሎ የፖሊስ አዛዥ አለ ወይ? የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልግኝና የሚኖረኝ ሲቪል የፖሊስ ተቋም ነው ብላ በዚህ መንገድ እራመዳለሁ የማለት ምልክት ያሳየችው ከ1992 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በአዋጅ ነው፡፡ የ1995 ዓ.ም. ሕግ ‹‹የተጠናከረ የሲቪል ፖሊስ ተቋም እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ›› በመሆኑ ቀጠለ፡፡ በሁለቱም አዋጆች መሠረት ወታደራዊ ማዕረግ ቀረ፡፡ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ ፖሊስ ወታደራዊ ማዕረግ አይኖረውም ተባለና አሁን በምናውቀው ከኮንስታብል እስከ ኮሚሽነር/ኮሚሽነር ጄኔራል በተዘረጋ የፖሊስ ማዕረግ ተተካ፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው የ2004 ዓ.ም. የፖሊስ አዋጅ ‹‹የሲቪል ፖሊስ ተቋም›› የኢሕአዴግ መንግሥት አዲስ ሐሳብ ከእነ ስሙ እርግፍ አድርጎ ቢተወውም ኮንስታብልን፣ ሳጅንን፣ ኢንስፔክተርን፣ ከማንደርንና ኮሚሽነርን ቀረ ያለና በአሥር አለቃ፣ በሃምሳ አለቃ፣ በመቶ አለቃ፣ በሻምበል፣ በሻለቃ፣ በኮሎኔል፣ በጄኔራል እንደገና የተካ አዲስ አሠራር አልመጣም፡፡ አዎ እንዲህ ያለ ለውጥ የለም፡፡ ነገር ግን አንድን የመከላካያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንን፣ የፖሊስ አዛዥ/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መሾም ምን ‹‹ነውር›› አለበት ከተባለም ይህንን የሚያስረዳ ምላሽ ማግኘት አለብን፡፡

ከሁሉም በላይ የሚከነክነውና እንቅልፍ የሚነሳው ግን ከታላቅ አክብሮት ጋር ጋዜጣዊ መግለጫውን ሲሰጡ፣ ‹‹እንደ ፖሊስ ኮሚሽነር›› ብለው የተናገሩትና ሚዲያው ደግሞ ሜጀር ጄኔራል ብሎ ሙሉ ስማቸውን ደጋግሞ የጠራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ሥራ በበላይነት የሚመሩት ኮሚሽነር የሰጡት ማብራሪያ ይዘት ነው፡፡ አገራችን የትርምስና የመፈናቀል ጣጣዎችን አስቁማ፣ ችግር የደረሰበትን የኢኮኖሚ ልማት መልሳ አነቃንቃ፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ማካሄድ ውስጥ መግባት እንድትችል ለውጡ የሚፈልገውን ሰላምና መረጋጋት ዕውን ማድረግ ቀዳሚ ሥራችን ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ በሕዝብም፣ በመንግሥትም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ውስጥ (ፖሊስን ጨምሮ) በጉልበት ማሰብን፣ እንዳሻ መራመድን ማሟሸሽ፣ ከሕግ በላይ መሆንን መጠየቀና ማሳጣት ዴሞክራሲያዊነትንና ሕጋዊነትን ማስረፅ ሲቻል ነው፡፡

የሕግ አስከባሪዎች ግዳጅና ተግባር ደግሞ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር መሠረታዊ ነፃነቶችን መከላከል የሕዝብና የአገር ፀጥታንና ሥርዓትን፣ እንዲሁም ጠቅላላ ደኅንነትን ሕጋዊ፣ ሰብዓዊና ጨዋነትን ዋና ፖሊሲውና ልማዱ ባደረገ አሠራር መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያገኘ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የታወቀ የሕግ ቃል ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የመስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫም የምናየውና የምናጣጥመው የሁላችንንም ህልውና ከሚወስነው የለውጥ አሸናፊነት አንፃር ጭምር ነው፡፡

ሰላማዊ ተቃውሞን በጥይት እየቀነደቡ፣ የሞቱትን ሰዎች ጥፋተኞች እያደረጉ ከሚኖሩበት ሳይጠየቁ መቅረት ባህልና ሕግ ከሆነበት አሠራር ወጣን እያልን፣ የለመለመው ተስፋችን ግርግርና ሁከት ለመቆጣጠርና ወይም በእሱ ስም ሕግ አስከባሪዎች የነፃ ዕርምጃ ፈቃድ አለን ሊሉ አይችሉም፡፡ በተለይም የፀጥታ አካላት ኃይል የመጠቀም የተለመደ አሠራሮችን ከሥልጣኔ ጋር የማይተዋወቅ፣ ከልካይና ጠያቂ የሌለው የሕዝብ አመፅን ያስከተለ መሆኑን መለስ ብለን አሁንም ገና አልተገነዘብንም፡፡ ፖሊሶችም የዚህ ሀ፣ ሁ፣ . . . ሳይዘልቃቸው ለአገር ዘብ ቆመናል ማለት አይችሉም፡፡

የሰላማዊ ሠልፍ ሕግ ተዋርዶ፣ አፈር ድሜ በልቶ በኖረበት በአገራችን ውስጥ በተለይም ለፖሊስ ከሠልፉ ሰላማዊነት ውጪ ስለሠልፍ ‹ሕጋዊነት›› (‹‹የተፈቀደ›› መሆን) ማውራት ሕግ ማስከበርን እንደ ተለመደው ከፖለቲካ ጋር መለወስና ሕዝብና መንግሥት የተገናኙበትን መተማመን ድራሹን ማጥፋት ነው፡፡ ‹‹በጎዳና ላይ በከፍተኛ ሠልፍ የሚንቀሳቀስ ኃይልን ነው በቁጥጥር ሥር ያዋልነው፡፡ እነዚህ በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው . . . የተፈቀደ ሠልፍ የለም፣ ሕገወጥ ሠልፍ ላይ ነው የተሳተፉት . . ›› ያሉትን ኮሚሽነር የታዘብናቸው ከዚህ አኳያ ነው፡፡

በዓለም የተቋቋመውና ሥልጣኔ መርቆና አፅድቆ የተቀበለው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች በውጭ አገር ሲሰማሩ ግዳቸውን የሚከተሉበት ሕግና አሠራር እንዲህ ያለ ሠልፍ የመቆጣጠር ዋናውና ቀዳሚው ስትራቴጂ ሕግና ሥርዓት፣ እንዲሁም ደኅንነት ማስጠበቅ የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር እንጂ፣ ሕጋዊ ያልሆኑ ሥጋት ያላንዣበበባቸው ይልቁንም የሰላማዊ ሠልፎችን ሕጋዊነት ማረጋገጥ አይደለም፡፡ በተለይም ሰውን/ስብስቡን ራሳቸውን ችለው በነፃ እንደሚያስቡ ግለሰቦች እንጂ፣ እንደ አንድ ተጠፍጥፎ እንደተሠራ ወጥ ነገር አትመልከቱ የሚለው ይህ ፖሊሲና አሠራር ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ሰሚ ጆሮ ያለማግኘቱ ማረጋገጫ የመስከረም 14 ቀን የፕሬስ መግለጫ ነው፡፡ ‹‹ሁከት ነው፡፡ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ . . . ሞብ ነው . . . በጎዳና ላይ በከፍተኛ ሠልፍ የሚንቀሳቀስ ኃይልን ነው በቁጥጥር ሥር ያዋልነው . . . ›› የተባለው በጅምላ አፍሳችኋል የሚለውን ጥያቄ ለማስተባበል ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አዲስ አበባና አዲስ አበቤ ከያለበት ሆኖ ‹‹ሲያደምጥ››ና ‹‹ሲሸበር›› የሰነበተው ሰው ያን ያህል ጊዜ ጆሮውን ቀስሮ ቆይቶ በመጨረሻ ያገኘው መረጃ፣ ‹‹በሕግ መጠየቅ አለባቸው ወንጀሉ በግልጽ የተፈጸመና መረጃም ተገኝቶ ወደ ሕግ ሥርዓት መግባት ያለባቸው የተባሉ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች 174 ተጠርጣሪዎች አሉ፤›› ተብሎ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ 1,459 ሰዎች ከሺሻ ቤት መያዛቸውን፣ 1,828 የሺሻ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር መግባታቸውን፣ 1,204 ዜጎች ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ለ‹‹ህንፀት›› መላካቸውም ተነግሮናል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የግዛት ሥልጣኑ ከሚዘረጋበት መልክዓ ምድራዊ ክልል ውጪ የያዛቸውን፣ ያሠራቸውን ሰዎች ጦላይ ድረስ አርቆ የመስደድ፣ ያሰኘውን ያህል እዚያ የማቆየት ‹‹አድራጊ ፈጣሪነት›› ከየት አመጣ? ጦላይስ ምን አግብቶት አባሪ ተባባሪ ሆነ? ‹‹እዚህ ቦታ ላይ ጥበቃ አለን፣ መርማሪ አለን፤›› የሚለውስ በተለይም መርማሪውን የሚመለከተው ሥራ ያበቃ ነውር አልሆነም ወይ? በሕዝብ ጠያቂነትና ዓይን ሥር መውደቅ የሚገባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ያለ ከልካይና ያለ ጠያቂ የአዲስ አበባ ‹‹ደንብ አስከባሪ›› ያለ ሕግ እንዳሻው አድራጊ ፈጣሪ ሆኖበት የቆየው የሺሻን ጉዳይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደረጃ በዓለምና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ተነስቷል፡፡ ‹‹[በነገራችን ላይ] እነዚህ የሺሻ ዕቃዎች ሕገወጥ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሺሻ ዕቃ ሆነ ሺሻ የሚጨስበት ሕግ የለም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ማለት [ነው]፡፡ ሊኖርም አይችልም ተብለናል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያለ ሕግ አስከባሪ ከሁሉም በፊት መጨበጥ ያለበት ዕውቀት የሕጉ መሠረት፣ ‹‹ያልተከለከለ ሁሉ የተፈቀደ ነው፤›› ነው? ወይስ ‹‹ያልተፈቀደ ሁሉ የተከለከለ ነው፤›› የሚለው ነው፡፡

በዚህ መሠረት መነገርና ለክርክር መቅረብ ያለበት ሺሻንና የሺሻ ዕቃን ሕገወጥ ያደረገ ሕግ አለ ብሎ እሱን መጥቀስ እንጂ፣ እሱን የፈቀደ ሕግ የለም ማለት አይደለም፡፡

ለማንኛውም ግን የተባሉት ምርቶች በኢትዮጵያ የንግድ ፈቃድ መስጫ መደቦች መመርያ መሠረት የአስመጪና የላኪ፣ የጅምላና የችርቻሮ በካርታ አርዕስቶች የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጉምሩክ የዕቃ ቀረጥ ሥርዓትና ተመን ሕግ በምዕራፍ 24 በጠቅላላው የትምባሆና የተፈበረኩ እንደ ትንባሆ የሚያገለግሉ ውጤቶችን በኪሎ ግራም ከ20 እስከ 35 በመቶ፣ በምዕራፍ 96 ደግሞ የትምባሆ ፒፓዎችንና ጋያዎችን በቁጥር 35 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ያስከፍላል፡፡ በሥራ ላይ ያለው የኤክሳይስ ታክስ (አዋጅ ቁጥር 307/95 በአዋጅ ቁጥር 610/2001 የተሻሻለው) የትምባሆና የትምባሆ ውጤቶች ላይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ በአገር ውስጥም ሲመረቱ የ20 እና የ75 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ይጥላል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ሕጎች (አዋጅና ደንብ) የትምባሆ ውጤት ማለት በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጀ በማጤስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ ወይም በማሽተት የሚወሰድ ማናቸውም ንጥረ ነገር መሆኑን ይገልጽና ትምባሆ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ወይም ለማከፋፈል ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ይደነግጋል እንጂ፣ ትምባሆና ተያያዥ ምርቶቹ ሕገወጥ ናቸው አይልም፡፡

ፍትሕ ተጓደለ፣ ደሃ ተበደለ ብላችሁ እሪ በሉ የሚል የዜግነት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅነት ጥሪ በቀረበበት አገር አዲስ አበባን በመሰለ የአስተዳደር ዕርከን ደረጃ ‹‹ህንፀት›› ስለሚባል በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ስለማይታወቅ ነገር ሲነገር፣ የዚህ ዓይነት ዕርምጃ መውሰዱ ሲሰማና የተለመደው ዝምታና ምን አገባኝ ባይነት ተጭኖንና ደንታ የለሽ ሆነን ለውጡ ለአደጋ ቢጋለጥ ያጣነው ያልለፋንበትን ነው፣ ያገኘነውም የፈቀድነውን ነው ከማለት በቀር ሌላ ተጠያቂና ማሳበቢያ የለንም፡፡ የፖሊስ ያለህ ማለት እንኳን አልቻልንም፣ አንችልም፡፡        

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...