Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በዓለም የንግድ ጦርነት ሳቢያ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ልትወድቅ የምትችልባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ናቸው››

ሚስ ራሺሚ ባንጋ፣ በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ

ሚስ ራሺሚ ባንጋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና የልማት ጉባዔ ሥር፣ በታዳጊ አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትብብርና ትስስር በተሰኘው የተቋሙ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው፡፡ በመደበኛነት በየዓመቱ በዓለም የልማትና የንግድ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚወጣውን ሪፖርት በአዲስ አበባ ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት ሚስ ባንጋ፣ በዓለም የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን ስለዳደሰሰው ሪፖርት በአፍሪካ ኅብረት ነባሩ አዳራሽ ለጋዜጠኞች ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ በገለጻቸውም ‹‹ፓወር፣ ፕላትፎርምስ ኤንድ ዘ ፍሪ ትሬድ ዲሉዥን›› በሚል ርዕስ የታተመውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ በውስጡ ስለተካቱት ስለአራተኛው የዲጂታል ኢንዱትሪ አብዮት፣ ስለዓለም የንግድ ጦርነት፣ ስለተዛባው የዓለም የንግድ ሚዛንና ስሌሎች በርካታ ጉዳዮች ትንታኔ በማቅረብ ወደፊት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች አብራርተዋል፡፡ ሚስ ባንጋ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታም፣ ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ጦርነት ምክንያት ሊያጋጥማት ስለሚችለው አደጋ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች በዲጂታል አብዮት ዘመን ስለሚጋረጥባቸው ፈተና፣ ስለመረጃ ሀብት አያያዝና መረጃን የሚመራ ብሔራዊ የዲጂታል ፖሊሲ አስፈላጊነት ያጠነጠኑ ሐሳቦች ላይ የሰጡትን ትንታኔ ብርሃኑ ፈቃደ አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው የተመድ የንግድና የልማት ሪፖርት፣ ዘንድሮ ትኩረቱን ካደረገባቸው ነጥቦች መካከል፣ በንግድ ጦርነት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት የሚያሳየው ይገኝበታል፡፡ የንግድ ታሪፍ፣ የንግድ ውድድርን የሚገድብ ፖሊሲ መከተልና የእነዚህ ዕርምጃዎች መጠናከር ደግሞ የንግድ ጦርነት ያስነሳል የሚለው ሙግት የሰሞኑ ትኩሳት ቢሆንም፣ የኃያላኑ ፍጥጫ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ ብዙም ሲነገር አንሰማም፡፡ ከዚህ አኳያ በንግድ ታሪፍና በሚያሠጋው ጦርነት ሳቢያ ምን እየተፈጠረ ነው? ሊያጋጥም የሚችለውስ ምንድነው? ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ዋጋቸው ይቀንሳል? ወይስ ከዚህም ሊብስ የሚችል ነገር አለ?

ሚስ ባንጋ፡- የንግድ ጦርነቱም ሆነ የታሪፍ ፍጥጫው ኢትዮጵያን በብዙ መንገዶች ያሠጋታል፣ ተፅዕኖም ያሳድርባታል፡፡ ተፅዕኖው የሚገለጽባቸው በርካታ መንገዶችም አሉ፡፡ በቀጥታ ሊያጋጥማት ከሚችለው ተፅዕኖ ውስጥ አንደኛው በሪፖርቱ ከተቀመጡት የይሆናሉ መነሻዎች መካከል፣ የንግድ ጦርነቱ ከቀጠለና ሌሎች አገሮችም በዚህ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ከጀመሩ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አጠቃላይ የምርትና የሸቀጥ ፍላጎት እንዲቀንስ የሚያስገድድ ሁኔታ ስለሚፈጠር፣ ፍጆታና ኢንቨስትመንትም እንዲቀንስ የሚያስገድድ ክስተት ይፈጠራል፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ እንደ አሜሪካና ቻይና ባሉ አገሮች ከውጭ ለሚገባ ምርትና ሸቀጥ የሚኖረው ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ በአጭሩ አገሮች ከውጭ የሚገባ ዕቃ የመግዛት ፍላጎታቸውን መግታት ይጀምራሉ፡፡ ኢትዮጵያም ለሸቀጦቿ ገዥ ታጣለች ማለት ነው፡፡ ይህ የመጀመርያው ትልቅ ተፅዕኖ ነው፡፡ ሁለተኛው ፈተና በኢንቨስተሮች መተማመን ላይ የሚፈጠረው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ነው፡፡ ዓለም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መናጥ ስትጀምር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ሀብታቸውን ወደ ሌላ አካባቢ መውሰድ ይጀምራሉ፡፡ ካፒታል ማሸሽ የሚጀመረው በዓለም የንግድ ጦርነት ሳቢያ በዶላር ላይ የሚታየው የዋጋ ሁኔታ እየጠነከረ፣ በሚካሄዱ ግብይቶች ላይም የወለድ ተመን እንዲጨምር ስለሚያስገድድ ለውጭ ኢንቨስተሮች ተስማሚ ሁኔታ አይፈጠረም፡፡ ሥጋትን የሚያባብስ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገቡ ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ወደሚታይባቸው አካባቢዎች መሸሽን ይመርጣሉ፡፡ የነበሩት ብቻም ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውም ኢንቨስትመንት ይገታል፣ አሊያም ይቀንሳል፡፡

ለአብነት ከቻይና የሚመጣው ኢንቨስትመንት እንደ ቀድሞው ላይሆን ይችላል፡፡ ቻይና በምትሰጣቸው ብድሮችና ኢንቨስትመንቶች ላይ በድጋሚ ለማሰብ የሚያስገድዳት ሁኔታ ስለሚኖር፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገሮች ከምትሰጠው ገንዘብ ይልቅ በራሷ የኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ላይ መጠመድ ትጀምራለች፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ሥጋት ነው፡፡ ሦስተኛው የንግድ ጦርነት የሚያመጣው ችግር የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ ነው፡፡ ዕድገት እንዲገታ የሚያስድድ ጫና ያሳድራል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ከታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ ለኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይሁንና በብድር ድጋፍ የሚካሄድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በአገሮች ውስጥ በስፋት መኖሩም በንግድ ጦርነት ጊዜ ሥጋት የሚያስከትል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ሳቢያ ችግር ውስጥ ልትወድቅ የምትችልባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛው የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱትሪ እንደ ቻይና ካሉ አገሮች በሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተመሠረተ የምርት ሒደት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በንግድ ጦርነቱ ሳቢያ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋም ሌላው የተፅዕኖ ምንጭ ነው ማለት ነው?

ሚስ ባንጋ፡- አዎን፡፡ ምክንያቱም በዶላር በሚካሄድ ግብይት ከውጭ ዕቃ የምታስገቡ ከሆነና የዶላር የመግዛት አቅም እየተጠናከረ ከሄደ፣ በምርትና በሸቀጦች ዋጋ ላይ የሚታየው ጭማሪ ተፅዕኖ መፍጠሩ በግልጽ የሚታይ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችም አይጠፉም፡፡ አንዳንድ አገሮች ወደ አፍሪካ በመምጣት ወደ አሜሪካ ሸቀጥ አምርተው እንደሚልኩ ይታመናል፡፡ ይህ ተስፋ ነው፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሆነው አሜሪካ ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የንግድ ዕድል ለአፍሪካ የሰጠችበትና ‹‹አፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት (አጎዋ)›› የተሰኘው የሕግ ማዕቀፍ አገሮችን ወደ አፍሪካ እንዲመጡና እንዲያመርቱ፣ ለአሜሪካ ገበያም እንዲያቀርቡ ዕድሉን እንደሚፈጥራቸው ይታመናል፡፡ ይሁንና ይህ ግን ብዙም የሚያወላዳ አይመስልም፡፡ አጎዋ በጨርቃ ጨርቅና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ይህ ዘርፍ በቻይና በከፍተኛ ደረጃ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ የሚመረትበት አቅም ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ አፍሪካ የምትገኝበት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማዳበር ወደ አሜሪካ መላክ የሚችሉና አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንዲመጡ የሚያስችል ብቃት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በየቀኑ የሚታየው የዓለም ሁኔታና ተለዋዋጭ ጉዳዮች ሥጋትን ይበልጥ የሚያባብሱ እየሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታየና እየሆነ ካለው ነገር በመነሳት፣ በመጪዎቹ ሦስት ወይም አምስት ዓመታት ውስጥ ምን ሊያጋጥም ይችላል? ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ብትቀጥል ዕጣ ፈንታዋ ምን ሊሆን ይችላል?

ሚስ ባንጋ፡- አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ መቀጠል ለኢትዮጵያ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ መንግሥት በዚህ ረገድ እየሠራ እንደሚገኝ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ዘለግ ያለ ውይይት አድርገናል፡፡ ችግሩን ይገነዘቡታል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ዙሪያ እየታየ ያለውን ጭጋጋማ ሁኔታና ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከለተ፣ በሚገባ ተዘጋጅተው እንደሚሠሩበት ተረድቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊያጋጥሟት በሚችሉ ተፅዕኖዎች ላይ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ ተነጋግረናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የዓለም የንግድ ጦርነት ስለሚያከትለው ጫና እየተዘጋጁ ነው፣ ግንዛቤውም አላቸው እያሉ ነው?

ሚስ ባንጋ፡- በሚገባ እንጂ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣናት ጨምሮ፣ ከሌሎችም የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በስፋት ተነጋግረናል፡፡ በሚገባ እየተዘጋጁበት እንደሚገኙም በልበ ሙሉነት ነግረውኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ ትኩረቱን በዲጂታል ኢንዱስትሪው ላይ በማድረግ፣ የንግድ ጦርነትና ሌሎችም መሠረታዊ የወቅቱን ጉዳዮች በቃኘው ሪፖርት ውስጥ አፍሪካ በምን ሁኔታ ትገለጻለች? 

ሚስ ባንጋ፡- የዲጂታል ኢንዱስትሪው ለአፍሪካ አገሮች በእጅጉ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሪፖርቱ በአብዛኛው የሚያብራራው ወደፊት በአራተኛው የዲጂታል ኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ወቅት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ፈተናዎች ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዝቅተኛ የኢንተርኔት ስርፀት ያላቸው በመሆኑ፣ የዲጂታል ኢንዱስትሪያቸው ላይ ጫና ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ተስፋ አለ፡፡ በዲጂታል ኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት አፍሪካውያን ብዙም ጫና ላያድርባቸው ከሚችሉባቸው መንገዶች መካከል፣ የዲጂታል ይዘት ያላቸው እንደ የኤሌክሮኒክ ኮሜርስ (ንግድ) ያሉት ለአፍሪካ ተስፋ የሚጣልባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ የኢንተርኔት ስርፀትና ሥርጭት በአራተኛው ዲጂታል ኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ከሚካተቱት አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ የኢንተርኔት ሥርጭቱ ዝቅተኛ ቢሆንና ጥቂት የሕዝብ ቁጥር ተጠቃሚ ቢሆንም፣ በኢኮሜርስ ረገድ አፍሪካ ተስፋ የሚጣልበት እንቅስቃሴ እንደምታደርግበት ይጠበቃል፡፡ ይሁንና የዲጂታል ኢኮኖሚው ወይም የዲጂታል ይዘቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ሳቢያ፣ በርካታ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ያሳድራል፡፡ ለአብነት ያህል ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የዲጂታል ይዘት ያልታከለባቸው ተወዳዳሪና ተቀናቃኝ አገሮች በዚህ በኩል ካላቸው ብልጫና ከፍተኛ የዲጂታል ኢንዲስትሪው ዕድገት በመነሳት፣ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳዳሪነት ያላቸውን ምርቶች ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ከፍተኛ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙት ተወዳዳሪ አገሮች፣ በማምረት ወቅት አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ ትልልቅ ዳታዎችን የሚያጠናቅሩበትና የሚተነትኑበት አቅም ስላላቸው ብሎም የኢኮሜርስ አገልግሎት በስፋት ስለዘረጉ፣ የአፍሪካ አገሮቸን በቀላሉ ጫና ውስጥ ይከቷቸዋል፡፡ በዚህም አፍሪካ ትልቁን የወጪ ንግድ ገበያዋን በቀላሉ የምታጣበት ሥጋት ተደቅኗል፡፡ በአፍሪካ የወጪ ንግድን የሚያቀላጥፈው ዋናው የኢኮኖሚ መስክ የምርት ገዥዎች ፍላጎት ነው፡፡ በአፍሪካ አገሮች የሚታየው ፍላጎት ለምርትና ምርታማነት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከወጪ ፍላጎት አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በሰው ጉልበት ላይ የተመሠረተ የምርት ሥርዓትን የሚከተል በመሆኑ፣ ለአብነት ኢትጵዮጵያ የምታስተዋውቀው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአብዛኛው የሰው ጉልበትን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች የተቀረው አፍሪካ የግብርና ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ ከመሆናቸው አኳያም ሲታይ፣ በዲጂታል ኢንዱስትሪው አብዮት ወቅት ይህ ምን ሊያስከትል ይችላል?

ሚስ ባንጋ፡- ዲጂታል ኢንዱስትሪው ሁሉንም ዘርፎች ይነካካል፡፡ ሪፖርቱ ትኩረት ከሚሰጥባቸው መካከል የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዲጂታል ኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት መንግሥታት ፖሊሲዎቻቸውን እንዲቀይሩ አይገደዱም፡፡ ሆኖም የዲጂታል ይዘት ያላቸውን የፖሊሲ ማዕቀፎች ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዲጂታል ይዘቶች በኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ውስጥ ሲካተቱ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ይጨምሩታል፡፡ ምርቶቹን ለማምረት የሚወጣው ወጪ ስለሚቀንስም፣ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላሉ፡፡ እዚህ ላይ ከግብርና ዘርፍ አኳያ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ አንድ ቡና አምራች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምናልባትም ሮቦቶችንና የምርት ማሸጊያ ማሽነሪዎችን በመጠቀም፣ ትልልቅ ዳታዎች ላይ በመመርኮዝ ምን ያህል የቡና መጠን ማምረት እንደሚችል፣ የትኛው ገበያ ላይ ምን ያህል ቡና ማቅረብ እንደሚችል፣ በኢኮሜርስ ማዕቀፎች ተጠቅሞ ለሌሎች ነጋዴዎችም ሆነ ለሸማቾች መሸጥ የሚችልባቸውን የቴክኖሎጂ ድጋፎች ማግኘት መቻል አለበት፡፡ ይሁንና እንዲህ ያሉ የዲጂታል ይዘት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች የማይጠቀሙ አገሮች ከባድ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በእስያ የሚገኙ ቡና አምራቾች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ይዘቶችን በመጠቀም ቡና ማምረት ጀምረዋል፡፡ ይህም የመወዳደር አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽለዋል፡፡ የእስያ ቡና አምራቾች ኢትዮጵያ ቡናዋን ወደ ምትልክባቸው ገበያዎች ነው የሚልኩት፡፡ በዚህ ሒደት ኢትዮጵያ የቡና ገበያዋን የማጣት ዕድሏ ከፍተኛ መሆኑ ይታያል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅሟን መገንባት ከቻለች ተወዳዳሪነቷ ሊጨምር ቢችልም፣ በራሷ አቅም ብቻ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ትገነባለች ማለት ግን አሁንም ፈታኝ የሚሆንባት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህም ሪፖርቱ ቀጣናዊ የዲጂታል ኢንዱስትሪ ትብብር እንዲፈጠር ሐሳብ ያቀርባል፡፡ የቀጣና ትስስር ሲፈጠር፣ በተለይም የአፍሪካ ኅብረት ይህንን ሥራዬ ብሎ በመያዝ አገሮች የዲጂታል ኢኮኖሚያቸውን እንዲያበለፅጉ ድጋፍ የሚሰጥበት ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ወይም በአገልግሎት ኢኮኖሚው ውስጥ በሚገባ ጥቅም ላይ መዋል ካልቻለ፣ አፍሪካ በዓለም የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚኖራት ተሳትፎ ከባድ ችግር ሊገጥማት ይችላል፡፡ ይህም ሆኖ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁንም ቢሆን ከፍተኛው የዕድገት ሞተርነቱ አያጠያይቅም፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚው ደጋፊ እንጂ ተኪው ሊሆን አይችልም፡፡ ምርታማነት እንዲጨምር፣ የሥራ ዕድል እንዲስፋፋና የምርት ዓይነቶች እንዲጨምሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

ሪፖርተር፡- በሰው ጉልበት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ በዲጂታል ኢኮኖሚ መካከል ስላለው ተመጋጋቢነት ይበልጥ ዘርዘር አድርገው እንዲያብራሩልን እንፈልጋለን፡፡ ባለፈው ዓመት ይኸው ሪፖርት ትኩረቱን በሮቦት መስፋፋትና በሚያሳድረው ተፅዕኖ ላይ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሮቦቶች አብዛኛውን የሰው ልጅ ሥራ እንደሚቀራመቱ የሚጠቁሙ መረጃዎች እየተሠራጩ ስለሆነ፣ የአፍሪካውያን የወደፊት ዕጣ ፈንታም ከዚህ አኳያ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ቢገልጹልን?

ሚስ ባንጋ፡- የመጀመርያዎቹ መኪኖች አገልግሎት መስጠት በጀመሩ ጊዜ፣ በጋሪ በማጓጓዝ የሚተዳደሩ ሰዎች ሁሉ ሥጋት ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ ፈተና ሆኖባቸው ነበር፡፡ በርካታ ሰዎች ሥራቸውን ለማጣት ተገደዋል፡፡ በርካቶችም መኪና እንዴት እንደሚነዳ ለማወቅ ተገደው ነበር፡፡ መኪናው መምጣት አልነበረበትም ማለት አንችልም፡፡ መምጣቱ አማራጭ የሥራ ዕድልንም አምጥቷልና ነው፡፡ ጋሪ የሚገፉ ሰዎች መኪና ወደ መንዳት መምጣታቸው አይቀሬ ሆነ፡፡ በተመሳሳይ የዲጂታል አብዮትም ያለውንና የነበረውን ነገር በመገዳደርና በመረበሽ ለውጥ የሚያመጣ  ነው፡፡ አዳዲስ የሥራ ዕድል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ነባር ሥራዎችን ሊያስቀር ይችላል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂን መምጣት ግን ማንም ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ወደ አመቸው አካባቢና አገር ሊያስፋፋ የሚችል የቴክኖሎጂ አብዮት ነው፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች መማርና አቅማችንን ማካበት፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂዎቹ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም በአግባቡ ማግኘት የምንችልባቸውን ዘዴዎች ማስፋት ይኖርብናል፡፡ በተጨባጭ መናገር የምችለው የዲጂታል ቴክኖሎጂው መስፋፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሥራ ዕድል ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ እንደሆነ ነው፡፡ በረዥም ጊዜ ሒደት ውስጥ ግን አማራጭ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥርበትና አዳዲስ መስኮችን የሚያስተዋውቅበት ዕድል አለው፡፡ ዲዛይንና ሶፍትዌር ማበልፀግ ሊጠቀሱ የሚችሉ አዳዲስ መስኮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ በአብዛኛው የዓለም ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ምርትና ሸቀጥ በገፍ የሚገዛ አኅጉር ነው፡፡ ከአፍሪካ ወደ ውጪ የሚላከው ምርት ከሚገባው አኳያ ዝቅተኛ ነው፡፡ የዓለም ሁኔታ በፈጣን አካሄድ ተለዋዋጭ መሆን፣ በርካታ ፈጠራዎችና የሳይንስ ውጤቶች በፍጥነት መውጣታቸው የአፍሪካውያንን ወደ ኋላ መቅረት ይበልጥ እያሰፋው እንደመጣ ይታያልና ከዚህ አኳያ እንዲህ ያለውን ፈተና እንዴት ሊቋቋሙት ይችላሉ?

ሚስ ባንጋ፡- እዚህ ላይ በተወሰነ ደረጃ የማልስማማበት ነገር አለ፡፡ እንደማስበው የዲጂታል ኢንዱስትሪው ለአፍሪካ አዲስና የተለየ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ አገሮች የየራሳቸውን መረጃዎች ይፈጥራሉ፡፡ መረጃ ወይም ዳታ በማንኛውም ሰው ይፈጠራል፡፡ አፍሪካ የወጣት አኅጉር ነች፡፡ የወጣቶች መብዛት ለአፍሪካ የዲጂታል አብዮት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በየጊዜው የሚመነጨውን መረጃ ወይም ዳታ ማሰባሰብና ማከማችት እስከቻለ ድረስ፣ የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ሀብት አላቸው፡፡ እንዴት መጠቀምና ዳታውን እንዴት ለተጠቃሚው ማቅረብ እንደሚቻል፣ ሶፍትዌር በሚፈለገው መጠንና ደረጃ በጥራት ማምረት እስከቻሉ ድረስ፣ የአፍሪካ አገሮች ትልቅ አቅም እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ተስማሚ የዲጂታል ይዘቶችን በገፍ ማምረት መቻል ለአፍሪካ ተነፃፃሪ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያስገኝላት ዘርፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሮች በዲጂታል ኢንዱስትሪ አማካይነት ከሚያመነጩት መረጃ ተጠቃሚ መሆን ስለሚችሉባቸው ዕድሎች ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ የዲጂታል ፖሊሲ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁንና መረጃዎቻቸው የሚከማቹባቸው ትልልቅ ሰርቨሮችና እንደ ፋይበር ኬብል ያሉት ሰፋፊ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች የሚገኙት በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ እንደመሆኑ፣ የመደራደር አቅማቸውንና የመረጃ ሀብት ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጥ ውጤታማ ፖሊሲ እንዴት ሊተገብሩ ይችላሉ?

ሚስ ባንጋ፡- መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ የዳታ ወይም የመረጃ ምንጭ የሆኑ አገሮች በራሳቸው መረጃ ማዘዝ የሚችሉበት መብት እንዳላቸው ነው፡፡ ሩዋንዳ ብሔራዊ የዲጂታል መረጃ ፖሊሲ አውጥታለች፡፡ ይህ ማለት ማናቸውንም የአገሪቱን መረጃዎች መጠቀም የሚፈልግ አካል የሩዋንዳን ፈቃድ ማግኘት አለበት ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ምዕራባውያን በቴክኖሎጂው መስክ የቱንም ያህል የዳበረ ሀብት ቢኖራቸው፣ መረጃ በሚፈልጉ ጊዜ መረጃው ወዳላቸው አገሮች መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ አፍሪካ ሰፊ የመረጃ ሀብት አላት፡፡ ይህንን ሀብት ለመጠቀም የሚያስችላት አግባብ ያለው ሕግ ሊኖራት ይገባል፡፡ መረጃ እንዴት ወደ ሌሎች መተላለፍ እንደሚገባው፣ የትኞቹ በነፃ፣ የትኞቹ በክፍያ፣ የትኞቹ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረጉ፣ የትኞቹ መረጃዎች ለማንም እንደማይሰጡ በግልጽ የሚደነገግ የዲጂታል ይዘት ፖሊሲ ማውጣት አገሮች የሚጠበቅባቸው ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የራሳቸውን መረጃዎች አሳልፈው በመስጠት ሌሎች አገሮች በነፃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ እየታየ ነውና የአፍሪካ አገሮች ይህንን መለወጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ያላደጉ አገሮች ከበለፀጉት አገሮች የልማት ሥራዎችን የሚያከናውኑበት ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዳለ የሚታወቅ ነው፡፡ ተመድ ያወጣቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ጨምሮ ሌሎችንም ዓላማዎች ለማሳካት ድጋፍ ይሻሉ፡፡ ይሁንና በዓለም ላይ ከሚታየው መመሰቃቀልና ያደጉ አገሮችም ወደ ራሳቸው የማተኮር አዝማሚያ ውስጥ እየገቡ በመሆኑ፣ ያላደጉ አገሮች ተስፋቸው ምንድነው?

ሚስ ባንጋ፡- የወደፊቱ መንገድ የደቡብ ለደቡብ ትብብር ወይም ‹ሳውዝ ሳውዝ› የሚባለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው፡፡ በአፍሪካና በእስያ የሚገኙ የደቡባዊ ንፍቀ ክበብ አገሮች በኢንቨስትመንት መስክ ድጋፍ ማግኘት የሚችሉባቸውና እርስ በርስ መደጋገፍ የሚችሉባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...