የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛነት አያጠያይቅም፡፡ በየትኛውም አገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ለብሔራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ወሳኙን ድርሻ ይይዛል፡፡ በአጭሩ ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የትኛውም ኢኮኖሚ ሊበለጽግ አይችልም፡፡ እንደ ምሶሶ የሚታየው ይህ ዘርፍ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳይወጣ ሰንገው የያዙት ማነቆዎች በርካታዎች ቢሆኑም፣ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል እንደማይሆን ይታመናል፡፡ ይህም ይባል እንጂ፣ በንግዱ ማኅብረሰብ ዘንድ የሚታየው ጉድለትና የአቅም ውሱንነት ለደካማ አስተዋጽኦው ድርሻ እንዳለው አይታበይም፡፡
የግሉ ዘርፍ በሚገኝበት ደረጃ በተለይም በአሁኑ ወቅት እየታየ ካለው አገራዊ ለውጥ አንፃር ብዙ እንዲሠራ የሚጠበቅበት፣ አቅሙና ጉልበቱ እንዲዳብር መንግሥት ሊደግፈው የሚገባ ዘርፍ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ረገድ አንደኛው የድጋፍና የማገዝ ዕርምጃ ሊሆን የሚችለው፣ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ማነቆ የሆኑበትን ሕጎችና አሠራሮች ማስተካከል መቻሉ ነው፡፡
የግሉ ዘርፍም የሚጠበቁበትን ትልልቅ ተግባራት ለማከናወን እንዲችል የንግድ ማኅበረሰቡን ጥቅምና መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትም ኃላፊነትና ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የሚጠበቅባቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ ፍላጎቶች እንደመወከላቸውና ድምፁን ለማስተጋባት እንደመቋቋማቸው፣ ከአገር አልፈው የንግዱን ማኅበረሰብ የወደፊት ህልውና በሚመለከቱ አኅጉርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንቅስቃሴ የማድረግ፣ የግሉን ዘርፍ ተዋንያን እንዲጠነቀቁ፣ እንዲዘጋጁና እንዲወዳደሩ የማገዝ ሥራዎች ላይ የፊት ደጀንነት ሚናቸው እንደሚጎላ ቢታመንም፣ በዚህ የአሠላለፍ መስመር ላይ የእኛዎቹ ምክር ቤቶች ብዙም አይታዩም፡፡ ወቅታዊ የአገር፣ የአኅጉርና ዓለም አቀፍ ክስተቶችንና ሥጋቶችን መነሻ በማድረግ ግንዛቤ ብቻም ሳይሆን፣ ውይይትና ክርክር እንዲካሄድባቸው የማድረግ እንቅስቃሴያቸው ከጋን ውስጥ መብራት የዘለለ ሆኖ አይታይም፡፡
በአገራችን ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው የንግድ ምክር ቤቶቻችን የዘመናት ጉዟቸው ሲታይ፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ አንፃር ሲፈተሹም መሥራት የሚገባቸውን ያህል ሠርተዋል፣ ተንቀሳቅሰዋል ለማለት ይቸግራል፡፡ ነጋዴው የሚገኘው ሌላ ዓለም ውስጥ እነሱ የሚገኙት ሌላ ዓለም ውስጥ በመሆኑ ውክልናቸው በራሱ ግራ ያጋባል፡፡ በአባልነት ያቀፉት የነጋዴ ብዛት ሲታይ፣ ሚናቸው የት ላይ እንደተወሰነ ያመላክታል፡፡ በብዙ መንገድ ብዙ የሚቀራቸው መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ጠንካራ የንግድ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አግዘዋል፤ ነጋዴውን ደግፈዋል፣ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት እንዲስፋፋ ተግተዋል ብሎ በሙሉ አፍ የሚነገርላቸው አይደሉም፡፡ ነገር ግን የተቋቋሙበት ዓላማ እንዲህ ያለውን የነጋዴውን ጥያቄ የመመለስ፣ አቅሙን የመገንባት፣ መብቱን የማስጠበቅ ተልዕኮ እንደሆና ይህንን ማሳካት ስለመሆኑም፣ የምክር ቤቶቹን መቋቋሚያ ሕግ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የእነዚህ ተቋማት ስም ጎልቶ የሚነሳው በአኩሪ ተግባራቸው ከመሆን ይልቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በምርጫ ሽኩቻ ተተብትበው በሚናቆሩባቸው ጉዳዮች እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ ሽኩቻቸው ምክር ቤቶቹ ጠንክረው እንዳይወጡ የበኩሉን አበርክቷል፡፡ በስንት ውትወታ ያሰባሰቧቸው አባላት እንዲሸሿቸውም ምክንያት ሆኗል፡፡ ንግድ ምክር ቤቶቹ አመራሮች ለንግዱ ማኅበረሰብ ጥብቅና ከመቆም ይልቅ፣ ወደ ውጭ በሚደረጉ ልዩ ልዩ የጉዞ ፕሮግራሞች የተጠመዱ፣ ከነጋዴ ይልቅ ለራሳቸውና ለግል ዕውቅናቸው የቆሙ ናቸው የሚለውን የሰላ ትችት ስናዳምጥ ከርመናል፡፡
በአሁን ወቅት ግን በትንሹም ቢሆን እነዚህ ምክር ቤቶች ለተሻለ ተግባር እየተነሳሱ እንደመጡ የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩባቸው ነው፡፡ የቀደመውን ረብ የለሽ ታሪካቸውን ለመለወጥ እየሠሩ ስለመሆናቸውም እየተናገሩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሊጠቀስ የሚችለውና ከአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች በብዙ መመዘኛዎች የተሻለ የሆነው የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ተቋም፣ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ የምርጫ ዘመናት በውዝግብ እንዳሳለፈ አይነጋም፡፡
ይሁንና ከሦስት ሳምንታት በኋላ ምክር ቤቱን የሚመሩ ኃላፊዎችን ለመሰየም አዲስ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ይህ ምርጫ ግን እንደቀደሙት የንትርክ መንስዔ እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከሽኩቻና ከውዝግብ የራቀ የምርጫ ሒደት እንዲኖር እንመኛለን፡፡ ዋናው ነገር ግን የንግዱን ማኅበረሰብ በአግባቡ ሊያገለግሉ የሚችሉ፣ በዕውቀት የዳበሩ፣ ራሳቸውን በአገሩ የሚያሽከረክሩ ሳይሆኑ፣ መንግሥትን ፋታ በማሳጣት ለነጋዴው ጥያቄዎች፣ ለሸማቹም ምቾት፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም የሚጥሩ፣ ተወካዮችን በአግባቡ ማስመረጥና መመደብ የተቋማቱ ኃላፊነት ነው፡፡ እነሱ የሌላቸውን መልካምነት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላው አካል መጠበቅም የማይመስል ነውና ምሳሌነት ያለው አብነታዊ ተግባር ከንግድ ምክር ቤቶችም እንደሚጠበቅ ማስታወስ እንፈልጋለን፡፡
እንደ ቀድሞው በትውውቅና በቲፎዞ ሳይሆን፣ ለንግድ ምክር ቤቱና ለብዙኃኑ ነጋዴ በቀናኢነት የሚያገለግሉ፣ የለውጥ ሐዋርያትን ወደ አመራርነቱ ቦታ የማምጣት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የንግዱን ማኅብረሰብ በትክክል የሚወክሉ ተመራጮች ወደ ምክር ቤቱ እንዲመጡ በማድረግ ታሪካቸውን የማደሱ ሥራ የንግድ ምክር ቤቱ አባላትም ኃላፊነት ነው፡፡
ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዕጩዎቹን ከወዲሁ በማቅረብና ብቃታቸውንና ተነሳሽነታቸውን የምክር ቤቱ አባላት እንዲገመግሙ የሚያስችላቸውን ዕድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ አዲሶቹ አመራሮች ጊዜው የሚጠይቀውን ዕውቀትና ስብዕና የተጎናፀፉ፣ ነገን አሻግረው የሚመለከቱ ስለመሆናቸው፣ መንግሥት የሚሞግቱ፣ የፖሊሲና የሕግ ክፍተቶችን በማጤን እንዲስተካከሉ ያላሰለሰለ ጥረት እንደሚያደርጉ የሚያምንባቸውን ከወዲሁ ለመለየት ንግድ ምክር ቤቱም ዕጩዎችን ለንግዱ ማኅበረሰቡ በማቅረብ እንዲያውቃቸውና ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆን የማድረግ እንቅስቃሴ ከንግድ ምክር ቤቱ ይጠበቃል፡፡ ከእንዲህ ያለው ጠንካራ ተቋም በመውጣት አገር የሚመሩ ኃላፊዎችንም ማውጣት እንደሚቻል ማሳየት የምክር ቤቱ የወደፊት የትኩረት መስክ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ አገር አለች፡፡ ሕዝብ አለ፡፡ መንግሥት አለ፡፡ ሥርዓትና ሕግ አለ፡፡ በሞራል፣ በስብዕና፣ በዕውቀትና በሌሎችም የልቀት መለኪያዎች የጎለበቱ የንግድ ምክር ቤት አባላትና ኃላፊዎች አገርን እንደ መምራት ያለ ኃላፊነት ላይ እንደሚቀመጡ እያሰቡ ለቦታው ቢዘጋጁ፣ አገር ስንት ባተረፈች ነበር፡፡ አሁንም የዚህ ዓይነቱን ስብዕና የተባለበሰ ጉምቱ መሪ ለማግኘት ጊዜው አልረፈደም፡፡