በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ራባት በተካሄው የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር፣ በሴቶች 5,000 ሜትር የተወዳደረችው አልማዝ አያና የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሽናፊ ሆናለች፡፡ ታዋቂዎቹ ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ በበኩላቸው በእንግሊዝ ማንችስተር ከተማ በተዘጋጀው የማንችስተር 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሽንፈዋል፡፡
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ዘገባ እንዳመለከተው ከሆነ፣ ባለፈው እሑድ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ ውድድር፣ በሴቶች 5,000 ሜትር የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ያሸነፈችው አልማዝ አያና ርቀቱን 14፡16፡31 በሆነ ጊዜ ማጠናቀቅ መቻሏን ገልጿል፡፡ አትሌቷ ያስመዘገበችው ሰዓት በውድድር በዓመቱ ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች አምስተኛው ሲሆን፣ በርቀቱ ከሚታወቁት ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ቀጥላ እንድትጠቀስ ያስቻላት ስለመሆኑም ዘገባው አትቷል፡፡
በሌላ በኩል በእንግሊዝ በየዓመቱ በሚካሄደው የማንችስተር 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፉት ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ በ2005 እና በ2007 ዓ.ም. የርቀቱ አሸናፊ የነበረችው ጥሩነሽ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ያሸነፈችበት ውጤት ያስመዘገበችው 31፡16 መሆኑም ታውቋል፡፡ በወንዶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ፊቱን ወደ ማራቶን ያዞረው ቀነኒሳ በቀለ ርቀቱን 28፡08 በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል፡፡