Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለ25 ተጨዋቾች ጥሪ አደረጉ

አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለ25 ተጨዋቾች ጥሪ አደረጉ

ቀን:

በጋቦን አስተናጋጅነት በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያውን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዝግጅት ጀመረ፡፡ አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለ25 ተጨዋቾች ጥሪ አድርገዋል፡፡

ቡድኑ ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሌሴቶ አቻው ጋር ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡ ዋሊያዎቹን በጊዜያዊነት ለማሠልጠን ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአምስት ወር ኮንትራት የተቀበሉት አሠልጣኙ፣ ማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. መደበኛ ዝግጅት ጀምረዋል፡፡ ከፊት ለፊታቸው ለሚጠብቃቸው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ 20 ተጨዋቾችን ይዘው ወደ ሌሴቶ ለማምራት ማቀዳቸውም ተሰምቷል፡፡

ከአልጄሪያ፣ ሌሴቶና ሲሸልስ ከሚገኙበት ምድብ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ እስካሁን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ ይዞ ከምድቡ ሁለተኛ ነው፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ከኃላፊነታቸው እንዲሰናበቱ በተደረጉት በቀድሞ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የተተኩት ገብረመድኅን ኃይሌ፣ ከሌሴቶ ጋር በቀጣይ የሚያደርጉት ጨዋታ ዋሊያዎቹ ጥሩ ሁለተኛ ሆነው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዕድሉን እንደሚፈጥርላቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

አሠልጣኝ ገብረመድኅን ከሜዳቸው ውጪ ለሚጠብቃቸው ለዚሁ ጨዋታ  በግብ ጠባቂነት ጀማል ጣሰው ከመከላከያ፣ አቤል ማሞ ከሙገር ሲሚንቶ፣ ሳምሶን አሰፋ ከድሬዳዋ ከተማ መርጠዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ አዲሱ ተሰፋዬ ከመከላከያ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሳላዲን ሰይድ፣ በኃይሉ አሰፋና ምንተስኖት አዳነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አብዱርከሪም መሐመድ፣ አህመድ ረሽድ፣ ጋቶች ፓኖምና ኤልያስ ማሞ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ደስታ ዮሐንስ ከሐዋሳ ከነማ፣ ታፈሰ ተስፋዬ ከአዳማ ከነማ፣ ዳዊት ፈቃዱና ሥዩም ተስፋዩ ከደደቢት፣ ኤፍሬም አሻሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አንተነህ ተስፋዬና ሙሉዓለም መስፍን ከሲዳማ ቡና፣ ያሬድ ባዬና አሥራት መገርሳ ከዳሽን ቢራ፣ ታደለ መንገሻ ከአርባ ምንጭ ከነማ፣ ኤፍሬም ወንደሰን ከኢትዮጵያ ቡና ሲሆኑ ሽመልስ በቀለ ከግብፁ ፔትሮጀት፣ ጌታነህ ከበደ ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በዛምቢያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያውን እያከናወነው የሚገኘው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ባለፈው እሑድ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የጋና አቻውን አስተናግዶ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከሜዳው ውጪ እንደሚያከናውን ይጠበቃል፡፡ ቡድኑ የጋና አቻውን ማሸነፍ ከቻለ ቀጣይ ተጋጣሚው ከቱኒዚያና ሴኔጋል አሸናፊ ጋር ይሆናል፡፡

****

የቀጠለው የኢትዮጵያውያኑ ድል

በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ራባት በተካሄው የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር፣ በሴቶች 5,000 ሜትር የተወዳደረችው አልማዝ አያና የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሽናፊ ሆናለች፡፡ ታዋቂዎቹ ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ በበኩላቸው በእንግሊዝ ማንችስተር ከተማ በተዘጋጀው የማንችስተር 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሽንፈዋል፡፡

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ዘገባ እንዳመለከተው ከሆነ፣ ባለፈው እሑድ ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞሮኮ ራባት በተካሄደው የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ ውድድር፣ በሴቶች 5,000 ሜትር የወቅቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ያሸነፈችው አልማዝ አያና ርቀቱን 14፡16፡31 በሆነ ጊዜ ማጠናቀቅ መቻሏን ገልጿል፡፡ አትሌቷ ያስመዘገበችው ሰዓት በውድድር በዓመቱ ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች አምስተኛው ሲሆን፣ በርቀቱ ከሚታወቁት ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ቀጥላ እንድትጠቀስ ያስቻላት ስለመሆኑም ዘገባው አትቷል፡፡

በሌላ በኩል በእንግሊዝ በየዓመቱ በሚካሄደው የማንችስተር 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፉት ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ በ2005 እና በ2007 ዓ.ም. የርቀቱ አሸናፊ የነበረችው ጥሩነሽ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ያሸነፈችበት ውጤት ያስመዘገበችው 31፡16 መሆኑም ታውቋል፡፡ በወንዶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ፊቱን ወደ ማራቶን ያዞረው ቀነኒሳ በቀለ ርቀቱን 28፡08 በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል፡፡

*****

 

የሚድሮክ ሠራተኞች የስፖርት ውድድር ጥሩ ግንኙነት መፍጠሩ

ተነገረ

በዳዊት ቶሎሳ

በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እህትማማች ኩባንያዎችና 11 ተጋባዥ ተቋማት መካከል ከጥር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሲካሄድ የቆየው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር እሑድ ግንቦት 14 ቀን በመቻሬ ሜዳ ተጠናቋል፡፡

ለአምስት ወራት ሲካሄድ የቆየው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር የኩባንያዎች ሠራተኞችን የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠናከረ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ለ13ኛ ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የሠራተኞች ስፖርታዊ ውድድር በዋነኝነት የእግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ሩጫ፣ ዱላ ቅብብል፣ የጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቼዝ፣ ዳማና ሌሎችም የባህል ስፖርቶችን ያካተተ ነበር፡፡

በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኢግዚኩዩቲቭ ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው እንደገለጹት፣ ‹‹በየዓመቱ የሚደረገው ስፖርታዊ ውድድር በኩባንያዎችና ተቋማት ቤተሰቦች፣ ለማቀራረብና ሠራተኛዎቹ በሥራቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመታዊ ውድድር ላይ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ቴክ ሳርቤት፣ ቴክ አቃቂ፣ ቴክ መገናኛና ቴክ ሰሚት እንዲሁም አዲስ ኢንተርናሽናል ከፍተኛ ፉክክር ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

በእግር ኳስ ጨዋታ ፍጻሜ አዲስ ኢንተርናሽናልና ቴክ አቃቂ ባደረጉት ጨዋታ ቴክ አቃቂ 1 ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ሼሕ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ፣ በባለቤትነት የሚመሯቸውን ኩባንያዎች ሠራተኞች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር፣ ጤንነታቸውን ጠብቀው በጥሩ መንፈስ እንዲሠሩ ስፖርታዊ ውድድሩ እንደሚያስችልና በምርቱም ለውጡም እየታየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአምስት ወራት የውድድር ቆይታ በአጠቃላይ 551 ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ 411 ወንዶች፣ 140 ደግሞ ሴት ተወዳዳሪዎች እንደነበሩም ተነግሯል፡፡

በዚህ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ወቅት የመቻሬ ቴኒስ  ሜዳ መመረቁ ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...