ከፈረንሣይዋ ዋና ከተማ ፓሪስ ተነስቶ ወደ ግብፅ ካይሮ በመብረር ላይ የነበረው የግብፅ አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ከተከሰከሰ በኋላ፣ ስለአደጋው መንስዔ የተለያዩ መላምቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡
‹‹ኢጅፕትኤር›› በረራ ቁጥር ኤምኤስ 804 ከራዳር ዕይታ ውጪ የሆነው ከፓሪስ በመነሳት፣ የምሥራቅ ሜድትራኒያንን አቅጣጫ ይዞ ወደ ካይሮ በመብረር ላይ ሳለ ነበር፡፡
ኤርባስ ኤ320 አውሮፕላን 56 ተሳፋሪዎችንና አሥር የበረራ ሠራተኞች ይዞ ድንገት የተሰወረው፣ የግሪክ የአየር ክልልን አልፎ ግብፅ የአየር ክልል በሚገባበት ቅፅበት ነው፡፡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የግሪክ አቪዬሽን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አደጋው ከመከሰቱ በፊት ከአብራሪው ምንም ዓይነት የበረራ እክል ምልክት ለአቪዬሽኑ አልደረሰም፡፡
ግሪክና ግብፅ በጋራ ባደረጉት አሰሳም የግብፅ የጦር ኃይል የአውሮፕላኑን ስብርባሪ፣ ቦርሳዎችና የሰውነት ክፍሎች ከአሌክሳንድሪያ በሰሜን አቅጣጫ 290 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚኘው የሜዲትራኒያን ባህር ላይ አግኝቷል፡፡
ቢቢሲ በማክሰኞ ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ዘገባው፣ አውሮፕላኑ በፍንዳታ ምክንያት ተከስክሷል በማለት ስሙን ያልጠቀሰ የፎረንሲክ መርማሪ ለአሶሼትድ ፕሬስ ማስፈሩን ገልጿል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት ግን ‹‹ፍንዳታ ስለመከሰቱ ፍንጭ አልተገኘም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ መርማሪው ከሆነ የተቆራረጡት የሰውነት ክፍሎች ማነስ፣ አውሮፕላኑ በፍንዳታ ምክንያት መከስከሱን ያመላክታሉ፡፡ የግብፅ ፍትሕ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን ፍንዳታ ለመሆኑ ፍንጭ አልተገኘም ብለዋል፡፡
አደጋው እንዴት ተፈጠረ?
የአውሮፕላኑ አብራሪ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ ከ20 ደቂቃዎች በፊት ከግሪክ የበረራ ተቆጣጣሪ ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ በወቅቱም በጥሩ መንፈስ ንግግር የተለዋወጡ ሲሆን፣ ስለእክል የተነሳ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከ20 ደቂቃዎች በኋላ አውሮፕላኑ ወዲህና ወዲያ መዋዠቅ ጀመረ፡፡ የግሪክ መከላከያ ሚኒስትር ፖኖስ ካሜኖስ እንደሚሉት፣ አውሮፕላኑ አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደ ቀኝ ከዋዠቀ በኋላ ከራዳር ዕይታ ጠፍቷል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ግን ከአብራሪው የአደጋ ምልክት ለአቪዬሽኑ አለመድረሱ እስካሁንም ግልጽ አይደለም፡፡ እስካሁን ያሉ መረጃዎችም አውሮፕላኑ ለምን እንደዋዠቀ ምክንያቱን አላወቁም፡፡ አደጋው በምን ምክንያት ተከሰተ የሚለውም አልታወቀም፡፡
ከአውሮፕላኑ መከስከስ ጀርባ ማን አለ?
የግብፅ አቪዬሽን ሚኒስቴር ለአውሮፕላኑ መከስከስ ከቴክኒክ ብልሽት ይልቅ የሽብር ጥቃት ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ያስኬዳል የሚል ግምት ሰንዝሯል፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ. በ2015 ጥቅምት 224 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው የሩሲያ የመንገደኞች አውሮፕላን ሲናይ ውስጥ የተከሰከሰው በሽብር ጥቃት ምክንያት በመሆኑ ነው፡፡
እንደ አቪዬሽን ሚኒስቴር ኤክስፐርቶች ባለፈው ሳምንት የተከሰከሰው የግብፅ አውሮፕላን በመሣሪያ ተመትቶ የመውደቅ ዕድሉም አናሳ ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም አውሮፕላኑ የሽብር ሰለባ ሊሆን ይችላል ከሚል መላምት ባለፈ የተገኘ ነገር የለም፡፡ ለአውሮፕላኑ መከስከስም ኃላፊነት የወሰደ አካል አልተሰማም፡፡ የአውሮፕላኑ የመረጃ ቋት ጥቁሩ ሳጥን ባለመገኘቱም ችግሩ ይህ ነበር ብሎ ለመናገር አልተቻለም፡፡
አውሮፕላኑ በዕለቱ ያረፈባቸው አገሮች
አውሮፕላኑ ረቡዕ ምሽት ከፓሪስ ከመነሳቱ አስቀድሞ በረራውን የጀመረው ከኤርትራ አስመራ ነበር፡፡ ከዚያም ከአስመራ ካይሮ ተመልሶ ከካይሮ ቱኒዚያ በሯል፡፡ ከቱኒዚያ ካይሮ ተመልሶ የሁለት ሰዓት ዕረፍት ካደረገ በኋላ ወደ ፓሪስ የበረረ ሲሆን፣ አደጋው የደረሰበት ከፓሪስ ሻርል ደጎል አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ካይሮ በመብረር ላይ ሳለ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ባረፈባቸው ቦታዎች ሁሉ ፍተሻ ተደርጎለት ነበር ወይ? የሚለው እስካሁን በወጡ መረጃዎች ምላሽ አላገኘም፡፡
ግብፅና ግሪክ የተለያዩበት መረጃ
የግሪክ መከላከያ ሚኒስትር አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት 90 ዲግሪ ወደ ግራ እንዲሁም 360 ዲግሪ ወደቀኝ ተጠምዝዞ ነበር ቢሉም፣ የግብፅ አቪዬሽን ከፍተኛ ባለሥልጣን አውሮፕላኑ ከራዳር ዕይታ ከመጥፋቱ በፊት ምንም ዓይነት የአቅጣጫ ለውጥ አላደረገም፣ አልዋዠቀም ብለዋል፡፡ አውሮፕላኑ በመደበኛ የከፍታ መጠኑ 37,000 ጫማ ላይ እየበረረ እንደነበር የራዳር ንባቡ እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡
የግብፅ አውሮፕላን መከስከስና የዶናልድ ትራምፕ ምላሽ
የአሜሪካ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሙስሊሞች የሚሰጡት ግምት ከሽብርተኝነት የዘለለ አይደለም፡፡ ለአሜሪካ በፕሬዚዳንትነት ቢመረጡም የመጀመርያ ዕርምጃቸው ሙስሊሞች አሜሪካ እንዳይገቡ ማገድ መሆኑን በይፋ መናገራቸው መነጋገሪያ አድርጓቸዋል፡፡
የግብፅ አውሮፕላን በሜዲትራኒያን ባህር ላይ እንደተከሰከሰ ‹‹ችኩልና ግዴለሽ›› ያስባላቸውን መላምት ሰንዝረዋል፡፡ ትራምፕ ከኤምኤስኤንቢሲ ጋር ባለፈው ዓርብ በነበራቸው ቆይታ፣ ‹‹የግብፅን አውሮፕላንን ማን እንዳፈነዳው የተረጋገጠ ነው፤›› ሲሉ ማንንም ሳይጠቅሱ ድፍን ያለ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ትራምፕ ‹‹ማን እንዳፈነዳው ይታወቃል፤›› ከማለታቸው አስቀድሞ፣ ‹‹አውሮፕላኑ የሽብር ሰለባ ሆኗል፤›› ብለው እንደሚያምኑ መናራቸውንም ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡
በአውሮፕላኑ መከስከስ ላይ የተጀመሩ የምርመራ ሥራዎች ምንም ዓይነት መረጃ ባልሰጡበት፣ የሽብር ቡድን ናቸው ተብለው የተፈረጁ አካላትም ኃላፊነት ባልወሰዱበት ጉዳይ የትራምፕ ጉዳዩን ከሽብር ጋር ማያያዝም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ለሙስሊሞች ባላቸው አሉታዊ አመለካከት የሚተቹት ትራምፕ፣ የግብፅ አውሮፕላን በርካታ ሙስሊሞችን ይዞ ሊሆን ይችላል ከሚል መላምት ተነስተው ኃላፊነት የጎደለው ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውንም አል ዓረቢያ ተችቷል፡፡
ትራምፕ ግን የአውሮፕላኑን መከስከስ ለፖለቲካ ቅስቀሳ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ‹‹ሌላ አውሮፕላንም እንደሚከሰከስ ልንገራችሁ፡፡ የሒላሪ ክሊንተን ኋላቀር አመለካከት ለአገራችን ምንም አይፈይድም፤›› ሲሉ ተቀናቃኛቸውን ሒላሪ ክሊንተን እንደተለመደው ዘልፈዋል፡፡
ትራምፕ በሙስሊሞች ላይ ያላቸው ጭፍን ጥላቻ አሜሪካን ለሽብር ጥቃት ሊዳርጋት ይችላል የሚል ሥጋትም አጭሯል፡፡
በአውሮፕላኑ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች
በበረራ ቁጥር ኤምኤስ 804 ኤርባስ ኤ320 አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩ 60 መንገደኞች 15 የፈረንሣይ፣ 30 የግብፅ፣ ሁለት የኢራቅ፣ የእንግሊዝ፣ የቤልጂየም፣ የኩዌት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የሱዳን፣ የቻድ፣ የፖርቹጋል፣ የአልጄሪያና የካናዳ ዜግነት ያላቸው ከየአገሩ አንድ አንድ ተሳፋሪዎች ነበሩ፡፡