Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንድ ሐኪም የሕክምና ስህተት ሠራ ተብሎ እጁ ላይ ካቴና ማስገባት ተገቢ አይመስለኝም››

ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ፣ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ማኅበር ከተመሠረተ 11 ዓመት ሆኖታል፡፡ በግሉ ዘርፍ ያሉ ሐኪሞችና ተቋሞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለሚመለከታቸው አካሎች በማሳወቅ እንዲሁም ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ያደርጋል፡፡ ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት ስላከናወናቸው ተግባሮችና በአጠቃላይ በዘርፉ ስላለው እንቅስቃሴ ምሕረተሥላሴ መኰንን የማኅበሩን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ የተቋቋመው ምን ዓላማ አንግቦ ነው?

ዶ/ር ወንደሰን፡- የተቋቋመበት ወቅት የግሉ ጤና ዘርፍ አገሪቱ ላይ እየሰፋ የመጣበት ጊዜ ስለነበረ የዘርፉ ሐኪሞችና ድርጅቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸትና ቅስቀሳ ማድረግ ከአዓላማዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ካከናወናቸው ተግባሮች መካከል ዋና ዋና የሚሏቸውን ቢነግሩን?

ዶ/ር ወንደሰን፡- በዋናነት የምናተኩረው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ላይ ነው፡፡ የግሉ የጤና ዘርፍ ባለፉት 24 ዓመታት በጣም ተስፋፍቷል፡፡ ብዙ የአገራችንን ክፍል እያዳረሰ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 12,400 ያህል የግሉ ዘርፍ ጤና ተቋሞች የመድሐኒትና የሕክምና አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ተቀጥረው የሚሠሩ ባለሙያዎች ደግሞ ከ34,000 በላይ ናቸው፡፡ ተጨማሪ ጥናት ቢጠይቅም የባለሙያው ቁጥር እኛ በከተማ 59 በመቶ፣ በገጠር 34 በመቶ፣ ነው እንላለን፡፡ ስለዚህ የግሉ ዘርፍ እንደ ዋነኛ ባለድርሻ አካል ታይቶ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ዘርፉ ለአገሪቱ የጤና አገልግሎት ያለው አስተዋፅኦ ትኩረት እንዲሰጠውና እንደ ዋነኛ ባለድርሻ አካል እንዲታይ እንሠራለን፡፡ የጤና ቁጥጥር አካላት፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የአስተዳደር አካላት፣ ማኅበረሰቡና ሚዲያ ለግሉ የጤና ዘርፍ ያላቸው አመለካከት እንዲስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ የግል የጤና ተቋሞች ሲባል ለትርፍ ብቻ የቆሙ አድርጎ የመመልከት ነገር አለ፡፡ ይኼ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ አትራፊ መሆን እንዳለባቸው ባያጠያይቅም የሚሠሩት ግን ንግድ ሳይሆን ሙያዊ ሥራ ነው፡፡ የሚጠይቁትም ሙያዊ ክፍያ ነው፡፡ ይኼንን ማኅበረሰቡ፣ የመንግሥት ተቋማትና ሚዲያውም ሊረዳው ያስፈልጋል፡፡ ሌላው የምንሠራበት ጉዳይ የአገልግሎት አሰጣጥ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአብዛኛው የምናየው የሚገጥሙንን ማነቆዎች ነው፡፡ በቅርቡ ወጥቶ የነበረው የጤና ተቋማት ስታንዳርድ ሐልዝ ሬጉላቶሪ ፋሲሊቲ ከሞላ ጎደል የግሉን ዘርፍ ዕድገት አቁሞታል ብለን ነው የምናየው፡፡ ሐሳቡ በጥናት መደገፍ ግን አለበት፡፡ የታካሚውን ደህንነትና የሥራውን ጥራት በማይነካ መልኩ ሊሻሻል ይችላል ብለን ሰፊ ጥናት ሠርተን ለተቆጣጣሪው አካልና ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም አቅርበን መግባባት ላይ እየደረስን ነው፡፡ ሌላው ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ (የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት አጋርነት) ነው፡፡ የግልና የመንግሥት ተቋማት በጋራ ሊሠሯቸው የሚገቡ ነገሮች የሚያሳይ አዲስ አሠራር አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ የመንግሥት ሆስፒታል ኖሮ ላብራቶሪው የግል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እንሠራለን፡፡ ሌላው ሥራችን የሰው ኃይልን የተመለከተ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ ሐኪሞቹ ግን የድኅረ ምረቃ ትምህርት እንዳይማሩ ተከልክሏል፡፡ ይህ ከተከለከለ ከአሥር ዓመት በላይ ሲሆን፣ ዘርፉን በጣም እየጎዳብን ነው፡፡ ወጣቶቹ ሐኪሞች ወደ ግል ከመጡ የመማር ዕድል ስለሚያጡ አይመጡም፡፡ የሰውን ሕገ መንግሥታዊ መብት መጣስ ነው ብለን ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ እስካሁን መልስ አላገኘንም፡፡ ባሉት ትልልቅ የግል ሆስፒታሎች የድኅረ ምረቃ ትምህርት የሚጀመርበትን አማራጭ እያየን ነው፡፡ ከውጪ ባለሙያዎች መጥተው በቅጥር የሚሠሩበትን መንገድም እያጠናን ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ገበያ ዓለም አቀፍ ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ መክፈል ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል አውሮፓ ብቻ ሳይሆን እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ባሉ ጎረቤት አገሮች ባለሙያዎቻችንን በብዛት ይወስዱብናል፡፡ አገር ውስጥ ያሉ የተራድኦ ድርጅቶች ምክንያትም ውድድሩ ከፍተኛ ስለሆነ ልምድ ያላቸውን ሐኪሞቻችንን ማቆየት ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ለግሉም የጤና ዘርፍ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ እዚህ ላይም ሌላ የምንሠራበት አቅጣጫ የፋርማሱቲካልስ የመድሐኒትና የሕክምና ግብአቶች አቅርቦት ነው፡፡ በጣም ሰፊ ችግር አለ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ምዝገባ፣ ማስመጣትና ማከፋፈል ላይ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ አገልግሎቱን ይጎዳሉ ሌላው የሔልዝ ኬር ፋይናንሲንግ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ በዋነኛነት ኢንሹራንስን ይይዛል፡፡ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሳል ሔልዝ ከቨሬጅ ወይም ብሔራዊ የጤና መድሕን ድርጅት መቋቋሙ በደስታ የምንቀበለውና የምንፈልግው ነገር ነው፡፡ በዚህ ላይ ግን የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ የግድ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ካልሆነ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ማንም ኢንሹራንስ የሚገባ ሰው የሚጠቀምበትን ተቋም የመምረጥ መብት ሊሰጠው ይገባል፡፡  ከኢንሹራንስ ድርጅቱ ጋር ድርድር ላይ ነን፡፡ በምን ዋጋ፣ በምን ሁኔታ መሥራት እንደምንችል የግሉን የጤና ዘርፍ ከሚወክሉ እህት ማኅራት ጋር እንሠራለን፡፡ የአዲስ አበባ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የድሬዳዋና ሌሎችም የግሉ ዘርፍ ማኅበራት አሉ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ባህርዳር ከተማ ለሁለት ቀን ተመካክረን አጠቃላይ የግሉን የጤና ዘርፍ ችግሮች አውጥተን፣ በየሦስት ወሩ ምክክር የሚደረግበት መድረክ ፈጥረን፣ ኮሚቴ አቋቁመን ነው የተለያየነው፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዳያችንን በአንድ ቋት እናያለን፡፡ በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዱ የዋጋ ጉዳይ ነው፡፡ ከሌሎች አገሮች ዋጋ አንፃር የኛ ያነሰ ቢሆንም፣ ግልጽ የዋጋ አተማመን እንዲኖር እንሠራለን፡፡ ሥልጠናዎችም እየሰጠን ነው፡፡ ሌላው ማኅበረሰባዊ ኃላፊነትን የመወጣት ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ክሊኒኮች፣ ሆስፒታሎችና ሐኪሞች በቀን የተወሰነ ሰዓት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቢሰጡ ይመርጣሉ፡፡ ችግሩ የሚሰጡትን አገልግሉት እንደ በጎ አድራጎት ቆጥሮ ታክስ የመቀነሱ ጉዳይ ነው፡፡ በግሉ ጤና ዘርፍ ሐኪሞች ፍቃደኝነት የአብዛኛውን ኅብረተሰብ ችግር ሊቀርፍ የሚችል አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ ሌላው ሜዲኰሌጋል ወይም የሕክምናና ሕግ ጉዳይ በግልም በመንግሥትም ያሉ የጤና ባለሙያዎችን የሚያስጨንቅ ነገር ነው፡፡ አስጨናቂ የሆነው ብዙ ያልተዘረዘሩ ነገሮች በመኖራቸው ነው፡፡ በመጀመሪያ የታካሚና ሐኪሙ ግንኙነት ምንድነው? ስንል በኛ አቋም መሠረት፣ ሐኪሙ የሚሠራው የሕመምተኛውን ፍላጎት ባጠቃላይ ከግምት በማስገባት ነው፡፡ ባለው አቅም፣ እውቀትና ችሎታ ሕመምተኛውን ለማገዝ ይሠራል፡፡ ሕክምና አራት የታወቁ ውጤቶች አሉት፡፡ አንድ ሰው ታክሞ ሊድን፣ ትንሽ ሊሻለው፣ ሊብስበት ሊሞትም ይችላል፡፡ አንድ ሰው ሐኪም ጋር ሲሄድ መቶ በመቶ ለመዳን አይደለም፡፡ ያለበለዚያ በምናክምባቸው ካርዶች ጀርባ ኰንትራት ጽፈን ማስፈረም ሊኖርብን ነው፡፡ እንዲህ የማይደረገው የታወቀ ነው በሚል ነው፡፡ የሕክምና ስህተት የትም አገር ያጋጥማል፡፡ ትክክል ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የሕክምና ስህተትን ለመቀነስ ወይም ለማጥፋት መሠራት አለበት፡፡ አንድ ሐኪም የሕክምና ስህተት ሠራ ተብሎ እጁ ላይ ካቴና ማስገባት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሐኪሙ የሚሠራው ሰውየውን ለማዳን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የሕክምና ስህተት ፈጽሞ ከተገኘ በወንጀል ሕግ ሳይሆን በፍትሐ ብሔር መታየት አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት አንገብጋቢ ጉዳዮችን መንግሥት እንዲያይልን እንፈልጋለን፡፡ ለፖሊሶች፣ ለዓቃቤ ሕግ፣ ለዳኞች፣ ለሚዲያ፣ ለጤና ባለሙያውና ለኅብረተሰቡም ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ችግር ይፈጠራል፡፡ ምክንያቱም ሐኪሙ መጀመሪያ የሚሠራው ራሱን ለማዳን ስለሆነ ኃላፊነት አይወስድም፡፡ ይኼ እንደኛ ባለ ድሀ አገር ትልቅ ጫና ይፈጥራል፡፡ ስደትም ያመጣል፡፡ ለምን እሠራለሁ ብለው ብዙ ሐኪሞች አገር ለቀው ይሄዳሉ፡፡ እዚሁ እያሉ ደግሞ ሥራ ይቀይራሉ፡፡ ስለዚህ በሜዲኰሌጋል ዙሪያ ጠበቅ ያለ ሥራ ለመሥራት አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና ስህተቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ኅብረተሰቡ፣ ሚዲያውና የሕግ ባለሙያዎች ጉዳዩን በሚዛናዊነት የሚመለከቱበትን መንገድ ለማረጋገጥ ምን ሠርታችኋል?

ዶ/ር ወንደሰን፡- አንድ አደጋ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ውስጥ ባለው የሕክምና አገልግሎት እምነት እንዲያጣ የሚሠሩ ኃይሎች ያሉ ይመስላል፡፡ በተጨባጭ ይኼ ነው ባይባልም ጥርጣሬ አለን፡፡ አንድ ሕዝብ በአገሩ ላይ ባለው የሕክምና አገልግሎት ተስፋ የሚቆርጥ ከሆነ አስፈሪ ነው፡፡ ዛሬ ለሜዲካል ቼካፕ 3,000 ዶላር ክፍሎ የሚታከም ሰው ለምን እናያለን? 1,000 ብር ለማያወጣ ምርመራ 25,000 ብር ከፍሎ የሚታከም አለ፡፡ በአገራችን ብቃት ያላቸው ሐኪሞችና ጥሩ ተቋሞች አሉ፡፡ የሌለን የተዘረጋ ሥርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ አንድ ነገር አጠፋህ ተብዬ ብከሰስ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥታዊ መብቴ እስካልተፈረደብኝ ድረስ ነፃ ነው ተብሎ መቆጠር ነው፡፡ ይኼ ግን አይስተዋልም፡፡ ገና አንድ ፍንጭ ሲገኝ ሚዲያው ያንን ሰው ፈርዶ በአደባባይ ይሰቅለዋል፡፡ ወደ 30 ዓመት በቅንነት የሠራ ባለሙያ ሁለተኛ እዚህ አገር እንዳይሠራ ተደርጎ ይፈረጃል፡፡ ለዛ ሰው በአደባባይ ወጥቶ መመስከር አንገት እስከሚያስደፋ ድረስ በሚያሳዝን ሁኔታ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሚባል ደረጃ ይደረጋል፡፡ ይኼ ለማንም አይበጅም፡፡ ልምድ ያላቸው ጥሩ ሐኪሞቻችንን አንዴ ካጣን በፍጹም መልሰን አናገኛቸውም፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅርቡ አንድ የሜዲኰሌጋል ስብሰባ ይኖረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና ባለሙያዎች የሥነ ምግባር ጉዳይ ላይ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሠራችሁት ነገር አለ?

ዶ/ር ወንደሰን፡- ሥነ ምግባርን በተመለከተ ብዙ ነገር ሲባል እንሰማለን፡፡ ማድረግ የሚቻለው ሥነ ምግባር ማስተማር ወይም የጥራት ምዘና መሥራት ነው፡፡ ሁልጊዜ ስለ ሥነምግባር እናስተምራለን፡፡ የጥራት ምዘና በማድረግ ደግሞ የሐኪሞቹ ሥነምግባር ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ነው፡፡ ችግሩ ተወሳሰበ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል ብለን ግን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- የግል የጤና ተቋሞች ታካሚዎችን ከሚገባው በላይ በማስከፈል ጥቅም ማግኘትን ተቀዳሚ ተልዕኳቸው እያደረጉ ነው የሚል ትችት በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ወንደሰን፡- በዚህ ዙሪያ እየሠራን ነው ያለነው፡፡ ይኼ ሁሉም ጋር ያለ ችግር ነው፡፡ ፕሮቫይደር ፔይመንት ሞዴል የአገልግሎት ሰጪዎችን ወይም የባለሙያዎችን ባህሪ ይወስናል፡፡ ኢንሹራንስ፣ ድርጅት ወይም ሰውየው ከኪሱ የሚከፍል ሲሆን የሚኖር የየራሱ ተፅዕኖ አለ፡፡ ችግሩ የሚፈታው በመምከር ወይም በማስተማር ሳይሆን ሥርዓት በመዘርጋት ነው፡፡ በጣም ስላሳሰበን ኅብረተሰቡ የግል የጤና ተቋማትን እንዴት ያያቸዋል ብለን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ 40 ተቋሞችን አጠናን፡፡ ብዙ ሕዝብ የሚገለገልባቸውና ታዋቂ ሐኪሞች የሚሠሩባቸው መካከለኛ ክሊኒኮች አይተን ያገኘነው የሚገርም ነው፡፡ የሚከፈለው ገንዘብ ብዙ አይደለም፡፡ ምክንያታዊ ነው፡፡ በጣም የተጋገነነ ዋጋ ያለበት አካባቢ የቱ እንደሆነም ለይተን አውቀነዋል፡፡ መፍትሄው ሥርዓት መዘርጋት ስለሆነ የተቀናጀ አገልግሎት ሥርዓት ወይም ኢንተግሬትድ ደሊቨሪ ሲስተም ለመፍጥር አስበናል፡፡ በዚህ ዓመት በጥራት በአግባቡ በተተመነ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ 40 ክሊኒኰች ይፋ እናደርጋለን፡፡ ይኼ የሙከራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ወደ 1,070 ተቋሞች ይሆናሉ ብለን አቅደናል፡፡ ለእነዚህ የጥራት ደረጃቸውንና የዋጋ ግልጽነታቸውን እንመሰክራለን፡፡ ይኼ ጠቅላላ የሕክምና አገልግሎትን በተመለከተ ሲሆን፣ ስፔሻሊቲ ሰርቪስ (ልዩ የሕክምና አገልግሎትን) በተመለከተ ከመንግሥት ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ የሕንፃዎችና የመሬት ዋጋ ውድ ነው፡፡ ለሕክምና አገልግሎት ማሻሻያ ወይም ድጎማ የለም፡፡ ይኼ የዋጋ መናር ነው በስተመጨረሻ ወደ ተጠቃሚዎች የሚወርደው፡፡ እኛ ሜዲካል ፕላዛ ለመሥራት እናስባለን፡፡ ሰው የስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን በአንድ ሕንፃ ውስጥ እንዲያገኝ ለማድረግ አቅደናል፡፡ ከመንግሥት ግን እገዛ እንፈልጋለን፡፡ እንደዚህ ባሉ መንገዶች ዋጋን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ አንድ የጠቅላላ ምርመራ ሐኪም ስፔሻሊስት ወይም ሰብ ስፔሻሊስት ማስከፈል የሚችለው ይኼን ያህል ነው ብሎ ቁርጥ ያለ ዋጋ ባይሆንም አካባቢውን መተመን ይቻላል፡፡ በዋነኛነት ኅብረተሰቡ በደንብ እንዲጠቀም ማድረግ የሚቻለው ግን ኢንሹራንስ ውስጥ በማጠቃለል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባለሙያዎች ፍልሰትን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ወንደሰን፡- የሕክምና ገበያ ዓለም አቀፍ ነው፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ቀርቶ የሚያገለግለው አገሩን የሚወድ ነው፡፡ በዘረዘርኳቸው ብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ነው የሚሠራው፡፡ እዚህ ሲሠራ ጥቅም የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሐኪሙ ወገኑን ያገለግላል፣ ራሱንም ይጠቅማል፡፡ እኛ ማበረታታት የምንፈልገው ይኼንን ነው፡፡ ይኼን ማድረግ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ሥራ ሊሰጠን ይችላል፡፡ በመሬት  አቅርቦት፣ በታክስና በሌሎችም ነገሮች በማገዝ ነገሮችን ማቅለል ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት የግሉን የጤና ዘርፍ ተቋማት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚያስብል ሁኔታ አለ?

ዶ/ር ወንደሰን፡- በተለይ አሁን ላይ አዎ፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጥሪ መደራደር ከጀመርን ወደ አራተኛ ወራችን ነው፡፡ ከመንግሥት የምትፈልጉትን ነገር አቅርቡ ተብለን አቅርበናል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመናል፡፡ በተግባር ተተርጉሞ ውጤት ያፈራል ወይ የሚለውን አብረን እናያለን፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አሁንም በግሉ ዘርፍ ነው የሚገለገለው፡፡ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ የሚፈልጋቸውን ነገሮችም አሳውቀውናል፡፡ ለምሳሌ ድንገተኛ ሕመም ለገጠመው ሁሉ ምንም ገንዘብ ሳይጠይቁ አገልግሎት መሰጠት አለበት በሚለው እንስማማለን፡፡ አገልግሎት ሲጠጥ ግን  ከፋዩም አብሮ መምጣት አለበት፡፡ መንግሥት ዝም ብሎ ድንገተኛ አገልግሎት በነፃ ስጡ ሳይሆን ስጡና እኔ እከፍላለሁ እንዲል እንጠብቃለን፡፡ ሌላው ርሕራሄ የተላበሰ የጤና አገልግሎት መስጠት ሲሆን፣ እንዲያውም የግሉ ዘርፍ የሚታወቀው በጥሩ አቀባበል ነው፡፡ በሌላ በኩል ከመንግሥት የጤና ተቋማት እንደ ክትባትና ደምን የመሰሉ በነፃ የሚመጡ መድሐኒቶች አሉ፡፡ ለግሉ የጤና ዘርፍ እንዴት መሰጠት አለባቸው በሚለው ላይ እየተነጋገርን ነው፡፡ እንደ ኤችአይቪና ቲቢ፣ ያሉ በሽታዎች ላይ በተመሳሳይ መመሪያ ለመሥራት የምናደርገው እንቅስቃሴም ጥሩ ነው፡፡ ለዚህ አጋጣሚ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ማመስገን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎች የግል ጤናቸውን በመከታተል ረገድ እምብዛም እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የግል ጤና ሁኔታን አለማወቅ በየጊዜው አለመታየትን የመሰሉ ችግሮች ይስተዋላሉና?

ዶ/ር ወንደሰን፡- ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 72 በመቶው ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ወጣት ስለሆነ ብዙም የሚከብደን አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ሰው ዓመታዊ የጤና ምርመራ ቢያደርግ ጥሩ ነው፡፡ የአገልግሎት ሰጪዎች ቅንጅት ላይ ሥንሠራ ዋነኛ ትኩረታችን የሚሆነው ይኼ ነው፡፡ ጤናማነትና አስቀድሞ መከላከል ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚባለው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አብዛኛው ማኅበረሰባችን ወጣት ነው፡፡ ወጣት ደግሞ አይታመም፡፡ እዚህ ላይ መከላከል ሲጨመር ለአገራችንም ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ሴቶች በዓመት አንድ ጊዜ የማሕፀንና የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይኼን ዋጋውን ቀንሰን በ300 ወይም 400 ብር መደረግ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው የዓመት የጤና ምርመራ በ500 ወይም በ600 ብር ማድረግ መቻል አለበት፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሠራሮችን ማስተዋወቅ አለብን፡፡ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን ቀንና ሌሊት ነው የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ካሉት የግል የጤና ተቋሞችና ሐኪሞች ምን ያህሉ የእናንተ አባል ናቸው?

ዶ/ር ወንደሰን፡- 400 ያህል አባላት አሉን፡፡ በቂ አይደለም፡፡ በዓመት አስከ 15 ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት እናደርጋለን፡፡ አዲስ የፈጠርነው አሠራር አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የግሉን ዘርፍ እንደ አንድ ስለሚያሳትፍ የተቀሩትን በዛ እናገኛቸዋለን፡፡ የቆየነውን ዓመት ያህል ብዙ መሥራት ነበረብን፡፡ ሠርተናል ብዬ አላምንም፡፡ ከኔ ከፊት የነበሩትን ወይም ጓደኞቼን ለመውቀስ ሳይሆን አጠቃላይ ሁላችን መሥራት ያለብንን አልሠራንም፡፡ አሁን ግን እየሠራን ነው፡፡ ማኅበሩ አምጥቷል ከሚባለው ነገር የግል የጤና ዘርፍ  በመንግሥት እንደ ባለድርሻ አካል እንዲታይ ማስቻላችን ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎች በእውቀት ከሌላው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ሁልጊዜ አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥልጠና መስጠታችን ጥሩ ስኬት ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የሚያጋጥሟችሁ መሰናክሎች አሉ?

ዶ/ር ወንደወሰን፡- ምላሽ አለማግኘት ይገጥመናል፡፡ ዛሬም ነገም ተናግረን መልስ ስናጣ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል፡፡ እኛ ጉዳያችንን ትክክለኛ በሆነ መንገድ ነው የምናቀርበው፡፡ የሐሳብ ልዩነትም ቢኖረን በመስመሩ ነው የምንሄደው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም የተነጋገርንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ መልስ ካላገኘን ተመሳሳይ ነገር ደጋግሞ ማንሳቱ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል፡፡ እስካሁን ላነሳናቸው ጉዳዮች በቂ መልስ አላገኘንም፡፡ ጥረታችን ግን ይቀጥላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...