Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልያላባራው የኮፒራይት ጥያቄ

ያላባራው የኮፒራይት ጥያቄ

ቀን:

ዴቪድ ስላተር የተባለ እንግሊዛዊ የተፈጥሮ ፎቶ አንሺ ሰለብ ክረስድ፣ ማክዌ የሚባሉ የዝንጀሮ ዝርያዎች የሚኖሩበት ጫካ ውስጥ ፎቶ ለማንሳት ይገባል፡፡ የሚፈልገውን ዓይነት ፎቶግራፍ ለመውሰድ ካሜራውን አስተካክሎ ያስቀምጣል፡፡ በድንገት ከዝንጀሮዎቹ አንዱ ካሜራውን አነሳና ራሱን ፎቶ አነሳ፡፡ ሌሎቹም ዝንጀሮዎች በካሜራው ሰልፊ ማንሳቱን (ራስን በራስ ፎቶ ማንሳት) ተያያዙት፡፡

ፊታቸውን እንዲሁም መላ ሰውነታቸውንም የሚያሳዩም ፎቶዎች ተነሱ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የዝንጀሮዎቹ ሰልፊ መነሳት ዜና መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ፎቶ አንሺው የዝንጀሮዎቹን ሰልፊ ራሱ ካነሳቸው ፎቶዎች ጋር አደባልቆ ሲያቀርብ ግን ያልጠበቀው የኮፒራይት ጥያቄ ተነሳ፡፡ የፎቶዎቹ ባለቤት ፎቶ አንሺው ወይስ ዝንጀሮዎቹ የሚለው ጉዳይ ማከራከረ ጀመረ፡፡

ፎቶ አንሺው በሚፈልገው መንገድ ካሜራውን አስተካክሎ ቢያስቀምጥም ፎቶውን አለማንሳቱ፣ ዝንጀሮዎች እንስሳ እንደመሆናቸው የኮፒ ራይት መብት የሌላቸው መሆኑና ሌሎችም ጉዳዮች እያከራከሩ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደረሰ፡፡ በስተመጨረሻ ጉዳዩን የያዘው የሳንፍራንሲስኮ ፍርድ ቤት ለዝንጀሮዎቹ የኮፒራይት መብት እንደማይሰጥ ወስኗል፡፡ የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ግን በውሳኔው ደስተኛ አልሆኑም፡፡

ይህ በብዛት ከሚሰሙት የኮፒራይት ጥያቄዎች ወጣ ያለ ቢሆንም፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ የሚነሱ የኮፒራይት መብት ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ የመላው ዓለም ራስ ምታት የሆነው የኮፒራይት መብት ጥሰት የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ችግር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጥረት ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡ ችግር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያየ ገጽታ በመላበስ ባለሙያዎችን መፈታተኑን ቀጥሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ግንቦት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ የኮፒራይት ሕግ አበይት ነጥቦች›› በሚል ርዕስ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሙያ ማኅበራትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካሎች በውይይቱ ተገኝተው የተለያዩ ነጥቦች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ የሕግ ባለሙያና የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ፣ የኢትዮጵያ ኮፒራይት ሕግ ያካተታቸውን ድንጋጌዎች በጥናታቸው አቅርበዋል፡፡

ሕጉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች በድንጋጌዎቹ የተጨመሩ መርሆችን ዳሰዋል፡፡ የኮፒራይት ሕግ የአሥር ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ከቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና የፍትሐ ብሔር ሕግ በኋላ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/2004 ወጥቷል፡፡ ሕጉ መጀመሪያ ከወጣበት ጊዜ በኋላ በየወቅቱ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የተረጋገጡ ችግሮችን ከግምት በማስገባት የታከሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ጥናታቸው ያመለክታል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የባለቤትነት መብት ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የሚተላለፍባቸው መንገዶች እየሰፉ መምጣታቸውን ነው፡፡

‹‹የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለአንድ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላላቸው ለጥበቃቸው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎች፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ጂዲፒ  (ጠቅላላ የአር ውስጥ ምርት) ያላቸው አበርክቶ ከፍ እንዲልም በአግባቡ መጠበቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ ካላት እምቅ ሀብት አንፃር አሁን ካለውም በላይ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሊወጡ እንደሚችሉ ገልጸው፣ እነዚህ ሥራዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተፈለገም የሕግ ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

ሕጉ ከለላ የሚሰጣቸውን ሥራዎች፣ ሥራዎቹን ለከለላ የሚያበቃቸው መመዘኛዎችና የኮፒራይት መብት ባለቤቱ ማንነት የሚወሰንባቸውን ሁኔታዎች በጥናታቸው አቅርበዋል፡፡ የኮፒራይት ባለመብቶችን ኢኮኖሚያዊና የሞራል መብቶችንም አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከተወያዮች ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ፣ የስብስብ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የኮፒራይት መብት ባለቤትነት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የመነሳታቸው ጉዳይ ነው፡፡   

ውይይቱን የተካፈሉ የሕግ ባለሙያዎች ያነሱትን የስብስብ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የባለቤትነት ጥያቄ የመለሱት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የብዙ ባለሙያዎች ስብስብ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ባለቤት ሥራውን ያመነጨውና ሥራውን በመሪነት ያስኬደው ሰው ነው፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ በተለያየ ዓይነት የኪነ ጥበብ ሥራዎች ባለሙያዎችን የቀጠሩ ሰዎች፣ ፕሮዲውሰሮች ወይም የባለቤትነት መብት በሕግ የተላለፈላቸው ሰዎች የሚሆኑበትን ሁኔታም አስረድተዋል፡፡ በተያያዥም አንድ የኪነ ጥበብ ውጤት ከለላ እንዲሰጠው ወጥነት፣ ግዙፍነት (ተቀርጾ መገኘት) እና ሌሎችም መመዘኛዎች ቢኖሩም የሥራው ጥራትና ዓላማ መመዘኛ እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡

በኮፒራይት ሕጉ ላይ ለንግድ ሳይሆን ለግል ጥቅም የሚውሉ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በተመለከተ (ከአንቀጽ 9 እስከ 20) ያለው ድንጋጌ ላይ ጥያቄ ያነሱም ነበሩ፡፡ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለንግድ ሳይሆን ለግል ጥቅም ለማዋል አንድ ኮፒ የመያዝ መብት መኖሩን፣ በርካታ የኮፒራይት መብትን የሚጥሱ ነጋዴዎች ያለአግባብ እንደተጠቀሙበት ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይላይ ታደሰ፣ የሙዚቃ አልበሞችን ኮፒ በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸጡ የተያዙ አዟሪዎች ሲከስሱ ለግል ጥቅማቸው እንደያዙ በማስመሰል ሳይቀጡ የታለፉበትን አጋጣሚ ተናግሯል፡፡ የኮፒራይት ሕጉን በመጠቀም ክሶች ውድቅ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች መፈጠራቸውንም አስረድቷል፡፡

አቶ ጌታቸው ከኮፒራይት መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ጉዳዮች ብዛት አንፃር ወደ ፍርድ ቤት የሚያመሩት ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም እንደ አእምሮአዊ ንብረት ጥበቃና የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎችን ማኅበር ያሉ ድርጅቶች ችግሮቹን የፈቱባቸውም ጊዜዎች አሉ፡፡

በውይይቱ ላይ አስተያየት ሰጪዎች ሕጉን ተመርኩዘው ለመተግበር አስቸጋሪ የሆኑ ደንቦችንና ሌሎችም ከኮፒራይት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ አቶ እቁባይ በርኸ የኮፒራይት አስተዳደር መዋቅር መዘርጋት አለበት ብለዋል፡፡ የኮፒራይት አስተዳደር መዋቅሩ ሰዎች ባለው ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የሚያስችልና የባለሙያውንም የባለቤትነት መብት የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አክለዋል፡፡ የኮፒራይት ሕጉ በየዘመኑ ከሚመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር አብሮ መራመድ የሚችል መሆን አለበት የሚል አስተያየትም ሰንዝረዋል፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ደረጀ ወርቁ የኢትዮጵያ የኮፒራይት ሕግ በተቀረው ዓለም ላይ ካሉ ሕጎች ጋር ምን ያህል አብሮ ይራመዳል የሚለው ጥያቄ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ሲገባ የኢትዮጵያን ኮፒራይት ሕግ በዓለም አቀፍ ሁኔታ መመልከት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...